Saturday, December 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከማዳበሪያ ግዥ 2.6 ቢሊዮን ብር ማዳን እንደተቻለ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ ፈቀቅ አላለም

ለ2009 ዓ.ም. የሰብል ምርት ዘመን ከተሸመተው የአፈር ማዳበሪያ 119 ሚሊዮን ዶላር (2.6 ቢሊዮን ብር) ማዳን መቻሉን፣ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ከፍያለው ብርሃኑ ሐሙስ ታኅሳስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ኮርፖሬሽኑ ለ2009 ምርት ዘመን 1.2 ሚሊዮን ቶን ማዳበሪያ ለመግዛት 400 ሚሊዮን ዶላር (ዘጠኝ ቢሊዮን ብር) መመደቡን ገልጸው፣ ከዚህ ውስጥ በመጀመሪያ ዙር 936,430 ቶን ማዳበሪያ በ290 ሚሊዮን ዶላር (6.4 ቢሊዮን ብር) መግዛቱን አስታውቀዋል፡፡

ይህም ካለፈው ዓመት ግዥ ጋር ሲነፃፀር 2.6 ቢሊዮን ብር (119 ሚሊዮን ዶላር) ቅናሽ ማሳየቱን አቶ ከፍያው ገልጸዋል፡፡ ይህን ያህል ገንዘብ ማዳን የተቻለው የግዥ ሥርዓቱን በማሻሻል፣ በባንክ አሠራርና በጨረታ ሒደት ቀልጣፋ አሠራር በመዘርጋት መሆኑን የገለጹት አቶ ከፍያለው፣ ዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መቀነስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በማዳበሪያ ግዥ ሥርዓት ውስጥ ረዥም ሰንሰለትና በርካታ ተዋንያን መኖራቸውን የገለጹት አቶ ከፍያለው፣ መንግሥት ማዳበሪያን ባነሰ ዋጋ ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ በሚያደርገው ከፍተኛ ጥረት የግዥ ሰንሰለቱን ለማሳጠር ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል ማዳበሪያ ይገዛ የነበረው በወኪል ኩባንያዎች አማካይነት እንደነበር አስታውሰው፣ ይህን የግዥ ሥርዓት በማሻሻል ማዳበሪያ አምራች ኩባንያዎች በቀጥታ በማዳበሪያ ግዥ ጨረታ እንዲሳተፉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

ዘንድሮ አርሶ አደሩ በሚከፋፈለው የማዳበሪያ ዋጋ ላይ በኩንታል ከ250 እስከ 300 ብር ቅናሽ እንደሚያገኝ ተገልጿል፡፡ ባለፈው ዓመት መንግሥት 852,400 ቶን ማዳበሪያ በ385 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ገዝቷል፡፡ የተጠቀሱት ዋጋዎች ከወደብ ወደ ክልሎች ማጓጓዣ ወጪ፣ የባንክና ኢንሹራንስ ክፍያዎችን አይጨምርም፡፡

ዘንድሮ የተገዛው 350,000 ዩሪያ፣ 193,000 ቶን ኤንፒኤስ፣ 338,000 ቶን ኤንፒኤስ ቦሮንና 54,430 ኤንፒኤስ ዚንክና ቦሮን በድምሩ 936,430 ቶን ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆነውን የሚያቀርበው ኦሲፒ የተሰኘው ግዙፉ የሞሮኮው ማዳበሪያ አምራች ኩባንያ ነው፡፡

የተቀረው ማዳበሪያ ከተለያዩ አገሮች ይቀርባል፡፡ ኦሲፒ ኢትዮጵያ ውስጥ ድሬዳዋ ከተማ አቅራቢያ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በሽርክና የማዳበሪያ ፋብሪካ በ2.5 ቢሊዮን ዶላር ለማቋቋም በቅርቡ ስምምነት መፈረሙ ይታወሳል፡፡

ከተሸመተው ማዳበሪያ ውስጥ ሁለት መርከቦች በአሁኑ ወቅት ጂቡቲ ወደብ አራግፈው በመጨረስ ላይ ናቸው፡፡ ሦስተኛ መርከብ ወደ ጂቡቲ በመጓዝ ላይ ሲሆን፣ ሌላ 50,000 ቶን ማዳበሪያ የጫነ መርከብ በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ፓርት ሱዳን እንደሚደርስ አቶ ከፍያለው ተናግረዋል፡፡ ‹‹ጂቡቲ ወደብ መጨናነቅ አለ፡፡ ይህን በመመልከት መንግሥት የሶማሌላንድ በርበራ ወደብንና ፖርት ሱዳንን ለመጠቀም በመንቀሳቀስ ላይ ነው፡፡ በተለይ ፖርት ሱዳን ለሰሜኑ የአገራችን ክፍል አዋጪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ 85 በመቶ የሚሆነው የሚተዳደረው በእርሻ በመሆኑ ማዳበሪያን ከውጭ በማስገባት መቀጠሉ እንደማያዋጣ የገለጹት አቶ ከፍያለው፣ መንግሥት የውጭ ባለሀብቶች በማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ በሽርክናም ሆነ በራሳቸው አቅም እንዲሰማሩ ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በኬሚካል ኮርፖሬሽን በኩል መንግሥት በራሱ አቅም አምስት የማዳበሪያ ፋብሪካዎችን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ኮንትራክተሩ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ግንባታ ፕሮጀክቱን ሥራ ብዙም ፈቀቅ እንዳላደረገው አቶ ከፍያለው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አምስት የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን በማዋሀድ ከአንድ ዓመት በፊት ነው የተቋቋመው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በዋነኛነት ለአርሶ አደሮች የግብርና ቴክኖሎጂዎች፣ ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና የእርሻ መሣሪያዎች አገልግሎት ያቀርባል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች