Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለሦስት ወራት የተስተጓጎለው የጂፒኤስ አገልግሎት ተለቀቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የተሽከርካሪዎችን ሥምሪት ለመቆጣጠርና ተያያዥ ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችለውንና በአገሪቱ ሲተገበር የቆየው የጂፒኤስ ቴክኖሎጂ ከሦስት ወራት በላይ ሲስተጓጎል ቆይቶ ባለፈው ሳምንት በድጋሚ ሥራ መጀመሩ ተገለጸ፡፡

የተሽከርካሪዎችን ሥምሪት በዘመናዊ መንገድ ለማስተናበር የሚያስችለው ይህ አገልግሎት ተቋርጦ የነበረው በአስቸኳይ ጊዜ  አዋጁ ምክንያት ተሽከርሪካዎቹ ላይ የተገጠሙ ጂፒኤሶች የሚጠቀሙባቸው ሲምካርዶች በመዘጋታቸው ነበር፡፡

ተሽከርካሪዎቹ ላይ የተገጠሙት መሣሪያዎች መረጃዎችን የሚያስተላልፉት ከኢትዮ ቴሌኮም በሚያገኙት ሲም ካርድ ታግዘው ሲሆን፣ የጂፒኤስ ኔትወርክ አገልግሎት በመቋረጡ ሳቢያ ለሦስት ወራት እክል ተፈጥሮ ቆይቷል፡፡ አገልግሎቱ ኪሳራ ውስጥ እንደከተታቸውና ህልውናቸውን እንደተፈታተነው ቴክኖሎጂዎቹን የሚያቀርቡት ኩባንያዎች መግለጻቸውን መዘገባቸውን ይታወሳል፡፡

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ግን ተሽከርካሪዎች ላይ የተገጠሙት መሣሪያዎች ዳታ የሚያስተላልፉበት ሲም ካርድና የጂፒኤስ ኔትወርክ አገልግሎት ማግኘት በመቻላቸው የተስተጓጎለው አገልግሎት እየተስተካከለ መምጣቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህንን ቴክኖሎጂ ከሚያቀርቡ ኩባንያዎች ያገኘነው መረጃ እንደሚያስረዳው፣ በአሁኑ ወቅት ኢትዮ ቴሌኮም አቋርጦት የነበረውን የጂፒኤስ ኔትወርክ በመልቀቁ አገልግሎቱን ገዝተው ይጠቀሙ የነበሩ ኩባንያዎችና ግለሰቦች የተሽከርካሪዎቻቸውን ሥምሪት ዳግመኛ ለመከታተል አስችሏቸዋል፡፡

ከአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች በስተቀር ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ የተገጠሙ መቆጣጠሪያና አቅጣጫ አመላካች መሣሪያዎች ዳታዎችን እያስተላለፉ እንደሚገኙም ተገልጿል፡፡ ከሦስት ወራት በፊት አገልግሎቱን ገዝተው ሲጠቀሙ የቆዩ ኩባንያዎች ተሽከርካሪዎቻቸው የት እንዳሉ ማወቅ ሳያስችላቸው በመቅረቱ፣ በሥራቸው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ከመፍጠሩም በላይ የቴክኖሎጂ አቅራቢ ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮ ነበር፡፡

የካሳ ኢንጅነሪንግ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሳ ሰለሞን እንደሚሉት፣ የአገልግሎቱ መስተጓጎል ቴክኖሎጂውን በሚያቀርቡት ኩባንያዎችና ቴክኖሎጂውን ሲጠቀሙ በነበሩት መካከል አለመግባባትን አስከትሎ ነበር፡፡

ለ28 አዲስ ተገልጋዮች ዘመናዊ አገልግሎት ለማስገባት የተደረጉ ስምምነቶች በእንጥልጥል እንዲቆዩና የአገልግሎት ክፍያዎችም እስከመቋረጥ በመድረሳቸው ችግሩን ለኢትዮ ቴሌኮምና ለመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለማሳወቅና መፍትሔ እንዲሰጣቸው እስከመማጸን ደርሰው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የኩባንያዎቹ ገቢ መቀዛቀዝ እሳቸው የሚያስተዳድሩት ኩባንያ ገቢ ላይ ተፅዕኖ በማሳደሩ፣ ሠራተኞች እስከመቀነስ የደረሰ ዕርምጃ በመውሰድ ድርጅቱን ለመታደግ ተገደው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አሁን ግን ኢትዮ ቴሌኮም የኔትወርክ ስርጭቱን በመልቀቁ ኩባንያቸው ላለፉት ሦስት ወራት የተስተጓጎለበትን ሥራ በመቀጠል የቴክኖሎጂው ተጠቃሚዎች ወደ ሥራ የሚገቡበትን መንገድ አደላድሏል፡፡

አገልግሎቱ የተሽከርካሪዎችን ሥምሪት በቀላሉ ለማቀጣለፍ ከማስቻሉም በላይ ከፍጥነት ወሰን በላይ እንዳያሽከረክሩ፣ ባልተገባና ባልተፈቀደ ቦታ እንዳይቆሙ፣ በነዳጅ አጠቃቀምንና በመሳሰሉ ላይ የቁጥጥር ሥራዎች እንዲካሄዱ የሚያግዝ ቴክኖሎጂ ነው፡፡ የተሽከርካሪዎች ባለቤቶችና ኩባንያዎች በሞባይል ስልኮችና በኮምፒውተር አማካይነት በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስችላቸው ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዚህ ዓይነቱ ቴክኖሎጂ ከ5,000 በላይ ተሽከርካሪዎች ጂፒኤስ ተገጥሞላቸው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች