Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሆላንዱ ሎቨር ግሩፕ ግማሽ ቢሊዮን ብር ኢንቨስት የተደረገበትን ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ሊያስተዳድር ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚታወቁ የሆቴል ብራንዶች መካከል ወደ ኢትዮጵያ  በመምጣት አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ሆቴሎች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የሚሰማሩ ባለሀብቶችም ለአገልግሎት የሚያውሏቸውን ሆቴሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ብራንድ ሆቴሎችን ከሚያስተዳድሩ ኩባንያዎች ጋር በመደራደርና ኩባንያዎቹ በሚጠይቁት መሥፈርት የሕንፃ ግንባታዎችንና ውስጣዊ ዲዛይኖችን አሟልተው እያደራጁ በጋራ መሥራት እየተለመደ መጥቷል፡፡

እንዲህ ያለውን መንገድ በመከተል ወደ ግንባታ የገቡና አገልግሎት እየሰጡ ካሉት ውስጥ ሒልተን፣ ጎልደን ቱሊፕ፣ ራዲሰን ብሉ፣ ራማዳ፣ ቦን፣ ማሪዮት፣ ዊንድሃምና ሌሎችም ሆቴሎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ ባሻገርም ዓለም ላይ የሚታወቁበትን ስያሜ የያዙ ሆቴሎች እየተበራከቱ እንደሚመጡ ይታመናል፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ወቅት በተመሳሳይ መንገድ ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል ድርድር በማድረግ ላይ ያሉና ድርድራቸውን ወደ መገባደድ ላይ የተቃረቡ ከ60 ያላነሱ ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ ስማቸውን በዓለም የተከሉ ሆቴሎች ከአገር በቀል ባለሀብቶች ጋር እንዲሠሩና የማማከር ሥራ በመስጠት ከሚታወቁ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ኦዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት ግሩፕ ብቻ፣ ወደ 17 የሚደርሱ ሆቴሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ጋር በመደራደር ላይ መሆኑ አንድ ማሳያ ይሆናል፡፡  ከዚህ ቀደም በካሊብራ ሆስፒታሊቲ ኮንሰልታንሲና ቢዝነስ ኩባንያ አማካይነት ድርድሮችን አጠናቀውና ሆቴሎችን ገንብተው ሥራ ከጀመሩ መካከል ካፒታል ሆቴልና ስፓና ራማዳ አዲስ ይጠቀሳሉ፡፡ ካሊብራም እንደ ኦዚ ሁሉ በርካታ ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር ለማምጣት በማደራደር ላይ እንደሚገኝና ዱባይ ከሚገኘው አሌፍ የሆቴል አማካሪ ድርጅት ጋር በሽርክና መሥራት መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡

ሰሞኑን በኦዚ አማካሪነት ሎቨር የተባለው የኔዘርላንድስ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለተኛው እንደሚሆን የሚጠበቀውን የሆቴል ፕሮጀክት ለማስተዳደር በጊዜ ቢዝነስ ግሩፕ ከተባለው አገር በቀል ኩባንያ ጋር ስምምነት አድርጓል፡፡ ሎቨር ኩባንያ ከሚያስተዳድራቸው ሆቴሎች መካከል ባለአምስት ኮከብ ደረጃ እንደሚኖረው የሚጠበቀው ‹‹ሮያል ቱሊፕ ፕላዛ አዲስ አበባ ሆቴል ሌግዤሪ ስታይል ኮሌክሽን›› የሚል መጠሪያ የተጠሰው ሆቴል ነው፡፡

የበጊዜ ቢዝነስ ግሩፕ ንብረት የሆነው ይህ ሆቴል፣ ከአውሮፓ ኅብረት ጽሐፈት ቤት ፊት ለፊት ደሳለኝ ሆቴል አካባቢ የሚገነባ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የግንባታ ሥራው ተገባዶ የማጠናቀቂያና የውስጥ ዲዛይንና ዲኮር ሥራዎች እየተከናወኑለት ይገኛል፡፡

ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል የተባለው ይህ ሆቴል ከሎቨር ጋር በተደረገው ስምምነት መሠረት የሎቨርን የአምስት ኮከብ ደረጃ ሊይዝ ከቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ ውስጣዊ የዲዛይን ሥራው ነው ተብሏል፡፡ ይህ የዲዛይን ሥራ ንጎያማ ኦክፓኔምና አጋሮቹ በተባለ ታዋቂ የደቡብ አፍሪካ ኩባንያ እየተካሄደ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

88 መኝታዎች የሚኖሩት ይህ ሆቴል ባለስምንት ወለል ሲሆን፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ ስፓ፣ ሬስቶራንት፣ ባርና የመሳሰሉትን እንደሚያካትት በሁለቱ ተሻራኪዎች መካከል ስምምነት በተደረሰበት ወቅት ተገልጿል፡፡ በመጪው ዓመት ሥራው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገለግሎት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሎቨር ሆቴል ግሩፕ ሮያል ቱሊፕ ሌግዤሪ ኮሌክሽን ወይም ሮያል ቱ ሊፕ በሚል ብራንድ የሚጠሩ ባለአምስት ኮከብ ደረጃ ያላቸውን ሆቴሎች የሚያስተዳድር ነው፡፡ ጎልደን ቱ ሊፕ በሚል ስያሜ የሚጠሩ ሆቴሎች ባለአራትና አምስት ኮከብ ደረጃ ያላቸው ሲሆኑ፣ በሦስተኛ ደረጃ የሚቀመጡት ደግሞ ቱሊፕ ኢን በመባል የሚታወቁት ናቸው፡፡ ቱሊፕ ኢን ሆቴሎች ባለሦስት ኮከብ ያላቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሎቨር ሆቴል ግሩፕ ሦስት ብራንዶችን በመያዝ በ45 አገሮች 240 ሆቴሎችን በማስተዳደር ላይ የሚገኝ ኩባንያ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች