Saturday, June 22, 2024

ሞጋች ትውልድ የሚፈጠረው ጠንካራ የሲቪክ ማኅበራት ሲያብቡ ብቻ ነው!

የአንድ አገር ሕዝብ በአገሩ ጉዳይ ሁለገብ የሆነ ዕውቀትና መረጃ ኖሮት፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ራሱን ማዘጋጀት የሚችለው ጠንካራ የሲቪክ ማኅበራት ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ እነዚህ ሲቪክ ማኅበራት ከፖለቲካ ተፎካካሪዎች ገለልተኛ፣ በበጎ ፈቃደኞች የሚመሩ፣ በገንዘብም ሆነ በቁሳቁስ ከተፅዕኖ ፈጣሪዎች ነፃ በመሆን ራሳቸውን የሚችሉ፣ ከማኅበረሰቡና ከትምህርት ተቋማት ጋር ጠንካራ ግንኙነት የሚመሠርቱና ዜጎችን ስለመብቶቻቸውም ሆነ ስለግዴታዎቻቸው በጥልቀት የሚያስተምሩ መሆን አለባቸው፡፡ የሲቪክ ማኅበራቱ በዚህ ዓይነት መንገድ በጥንካሬ ሲመሠረቱና ሲያብቡ ከሁከትና ከብጥብጥ ይልቅ ውይይት፣ አገርን አደጋ ውስጥ ከሚከቱ አስከፊ ድርጊቶች ይልቅ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ድባብ ይፈጠራል፡፡  በአሳዛኝ ሁኔታ የሰው ሕይወት ከመቀጠፍ ይድናል፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም ሲባል ሞጋች ትውልድ መፈጠር አለበት፡፡

በአገሪቱ ተፈጥሮ በነበረው ሁከት ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያስፈጽም በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት በቁጥጥር ሥር ከዋሉ ዜጎች መካከል 9,800 ያህሉ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ተለቀዋል፡፡ በአምስት የተለያዩ ሥፍራዎች የተሃድሶ ሥልጠና ወስደው ከኅብረተሰቡ ጋር ከተቀላቀሉት እነዚህ ወገኖች መካከል ብዙዎቹ፣ ቀደም ሲል በተሳተፉባቸው ሁከቶች በአገሪቱ ላይ የተጋረጠው ችግር በሰከነ አዕምሮ ሲያስቡት ጥሩ እንዳልነበር ግንዛቤ ማግኘታቸው ተገልጿል፡፡ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችም ሥልጠና መውሰዳቸው ተነግሯል፡፡ ያ ሁሉ አሳዛኝ ጥፋት ደርሶ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎች ለእስር ከተዳረጉ በኋላ፣ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ለደረሰው ነገር ሁሉ ፀፀት ተሰምቷል፡፡ በአገሪቱ ጠንካራ የሲቪክ ማኅበራት የመኖራቸውን አስፈላጊነት ያመላከተ ወቅት ላይ መደረሱን በአንክሮ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ መብት እንዲያስከብር ሲጠየቅ እንቢ የሚል ሹምና መብቱን በድንጋይም ሆነ በሌላ የኃይል ተግባር ለማስከበር የሚነሳ ዜጋ ችግር የሚፈጥሩት፣ ጠንካራ የሲቪክ ማኅበራት ሲጠፉ ነው፡፡

በየትኛውም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ጠንካራ የሲቪክ ማኅበራት መኖራቸው የግድ ነው፡፡ እነዚህ የሲቪክ ማኅበራት የአገሪቱን ሕግ የሚያከብሩ፣ የግለሰብና የቡድን መብቶችን የሚቀበሉ፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ መቻቻል እንዲኖር የሚጥሩ፣ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ የሚያግዙ፣ የዜጎችን ንቃተ ህሊና የሚያጎለብቱ፣ ለራሳቸው በፍፁም የፖለቲካ ሥልጣን የማይፈልጉ፣ ተፅዕኖ በሚፈጥሩ ኃይሎች በገንዘብም ሆነ በሌሎች መደለያዎች የማይሸነገሉ፣ ዜጎች መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ሲፈልጉ ከኃይል ይልቅ ዴሞክራሲያዊ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የሚረዱ፣ ማናቸውንም የኃይል ተግባራት የሚቃወሙ፣ ለአገር ጥቅም ብቻ ጠንክረው የሚሠሩ፣ ወዘተ ሊሆኑ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ጠንካራ የሲቪክ ተቋማት እንዲፈጠሩና በብዛት እንዲኖሩ ለማድረግ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው ወገኖች በብርቱ ሊያስቡበት ይገባል፡፡ ዴሞክራሲ ሕይወት ኖሮት በሰላም መንቀሳቀስ የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ሞጋች ትውልድ የሚፈጠው በዚህ ሁኔታ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጦላይ ማሠልጠኛ ማዕከል ተገኝተው ከእስር ለተፈቱ ዜጎች ባደረጉት ንግግር ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ የማይነጣጠሉ የአንድ አገር የህልውና መሠረት መሆናቸውን ወጣቱ ተገንዝቦ እነዚህን እሴቶች መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡ ወጣቱ ጥያቄ ቢኖረውም እንኳን ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት የማቅረብና መልስ የማግኘት መብት እንዳለው አስረድተው፣ ባለፉት ወራት እንደታየው በአመፅና በግርግር ጥያቄ መቅረቡ አገሪቱን ዋጋ እንዳስከፈለ አውስተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ እንዳይደገም መንግሥትም የራሱን ስህተት ለማረም ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ መሆኑን፣ ወጣቱም የራሱን ስህተት በማረም ከመንግሥት ጋር ሆኖ ሰላሙን መጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡ ይህ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መልዕክት ዋጋ የሚያገኘው፣ በአገሪቱ ጠንካራ የሲቪክ ማኅበራት እንዲፈጠሩ በማድረግ ነው፡፡ በተቻለ መጠን ራሳቸውን ከተለያዩ ተፅዕኖዎች መከላከል የሚችሉና የሕዝቡን አመኔታ የሚያገኙ ማኅበራት እንዲፈጠሩ መንግሥት ከማንም የበለጠ ኃላፊነት አለበት፡፡ የአገሪቱ ሕገ መንግሥትም ይህንን በሚገባ ይደግፋል፡፡ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከዚህ የበለጠ ተመራጭ መንገድ አይኖርም፡፡

የወጣቱም ሆነ የአጠቃላዩ ሕዝብ ንቃተ ህሊና ማደግ የሚችለው መንግሥት በሚሰጠው ሥልጠና ወይም በትምህርት ተቋማት ብቻ አይደለም፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚረዱ ግብዓቶችን የሚያስታጥቁ በዘርፉ በቂ ክህሎት ያላቸውና ፈቃደኛ የሆኑ ዜጎች በሲቪክ ማኅበራት ሲደራጁ፣ እከሌ ከእከሌ ሳይባል ለጥንካሬያቸውና ለተደራሽነታቸው እገዛ ማድረግ ይገባል፡፡ የሲቪክ ማኅበራቱ በገለልተኝነት መንፈስ ሥራቸውን ሲያከናወኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት በአግባቡ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ፡፡ በሥልጣን ያላግባብ መገልገል ይወገዳል፡፡ የመረጃ ፍሰት በነፃነት ይከናወናል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ይከበራል፡፡ ሙስናና ብልሹ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ የሕግ የበላይነት ይረጋገጣል፡፡ ከሕዝብ ለመንግሥት የሚቀርቡ ጥያቄዎች በግልጽና በሰላማዊ መንገድ ይደርሳሉ፡፡ የመንግሥት ምላሽም ፈጣንና አርኪ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚታየው ግን በሁከትና በብጥብጥ የታጀበ የሰዎች ሞት፣ የአካል ጉዳትና የአገር ሀብት ውድመት ነው፡፡ ይህንንም በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ እዚህ አገር ውስጥ ማየት ተችሏል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ነውጠኛ መንገድም ዴሞክራሲ ተገንብቶ አያውቅም፡፡ አገርም አገር አይሆንም፡፡

ዴሞክራሲ እንደ ሥርዓት ዕውን እንዲሆንና ዜጎች በተቻለ መጠን ከአገሪቱ ሀብትና ከመንግሥት ሥልጣን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲቋደሱ መደረግ አለበት ሲባል፣ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ የሚቀነቀን ተራ ፕሮፓጋንዳ መሆን የለበትም፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግም ሆነ የሚመራው መንግሥት ጥልቅ ተሃድሶ ውስጥ ነኝ ሲል፣ ተሃድሶው በአገሪቱ ሥር ነቀል ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ከባቢዎችን መፍጠር አለበት፡፡ ከእነዚህም አንዱ የጠንካራ ሲቪክ ማኅበራት ማበብ ነው፡፡ ጠንካራ የሲቪክ ማኅበራት ሲባል ወትሮ ከምናውቃቸው መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች (NGOs) በጣም በላቀ ደረጃ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የሚወጡ ማለት ነው፡፡ እነዚህ ለአገርና ለሕዝብ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን መርህ ያደረጉ፣ ከአልባሌ ድርጊቶች የራቁ፣ በምንም ዓይነት ሁኔታ ወገንተኝነት የሌላቸው፣ በጥቅም የማይደለሉ፣ ወዘተ ሊሆኑ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ናቸው ለአገር የሚያስፈልጉት፡፡ ንቃተ ህሊናው የጎለበተ ዜጋ ምክንያታዊ በሆነ ሞጋችነት መብቱን የሚያስከብረው ጠንካራ የሲቪክ ማኅበራት ሲኖሩ ነው፡፡ በስመ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ወይም ደጋፊነት ብቻ ንቃተ ህሊናው ሳይጎለብት የሚጓዝ ዜጋም ቢሆን ኮምፓሱ እንደጠፋበት መንገደኛ ነው የሚሆነው፡፡ በምክንያት መተቸትም ሆነ መሞገት የሚቻለው በሲቪክ ማኅበራት አማካይነት ንቃተ ህሊና ሲዳብር ብቻ ነው፡፡ ያለበለዚያ ለሁሉም ጉዳይ ጥያቄና መልሱ ኃይል ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለማንም አይጠቅምም፡፡ ስለዚህ ሞጋች ትውልድ የሚፈጠረው ጠንካራ የሲቪክ ማኅበራት ሲያብቡ ብቻ ነው!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...