Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየወላጅ አለንጋ

የወላጅ አለንጋ

ቀን:

ከተወለደችበት ክልል አዲስ አበባ ከመጣች ሁለት ዓመት ሆኗታል፡፡ እነዚህን ሁለት ዓመታት ‹‹እንደ እናቴ ናቸው›› ከምትላቸው አሠሪዋ ቤት በሠራተኝነት እያገለገለች ነው፡፡ አዲስ አበባ ከመጣች በኋላ ሥራ ስትሠራ ለምትሰብረው ዕቃም ሆነ ለምታቃጥለው ኤሌክትሪክ ምድጃ ከቁጣ የዘለለ ነገር ገጥሟት እንደማያውቅ ትናገራለች፡፡ ሆኖም በትውልድ ቀዬዋ የነበረው የተለየ ነው፡፡

16 ዓመቷ እንደሆነ የነገረችን ታዳጊ፣ አዲስ አበባ ከመምጣቷ በፊት በቤት ውስጥ እናቷን ከማገዝ በተጨማሪም ከሁለት ታላላቅ እህትና ወንድሟ ጋር በመሆን ከብት ማሰማራትና ማገድም ሥራዋ ነበር፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎንም ትምህርቷን ትማራለች፡፡ ‹‹ብዙ ጊዜ ደርሶብኛል›› የምትለውን የእናቷን ግርፊያ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች፡፡

‹‹እናታችን ከአባታችን በተለየ ኃይለኛ ናት፡፡ ለእያንዳንዱ ጥፋታችን ትገርፈን ነበር፡፡ እኔም ብዙ ጊዜ ተገርፊያለሁ፡፡ ከብት ሲጠፋ፣ ከብቶች ሰው ማሳ ውስጥ ሲገቡ፣ ቤት ውስጥ ሥራ ስሠራ ዕቃ ስሰብር ትገርፈኝ ነበር›› ትላለች፡፡

ብዙውን ጊዜ ከብቶች ሰው ማሳ የሚገቡት እሷ ከብቶቹን ለቃ ከሌሎች ልጆች ጋር ስትጫወት ነው፡፡ ለዚህም ታዲያ ብዙ ጊዜ በ‹‹ለመጥ›› (ከእርጥብ ዛፍ የሚቆረጥ ጨፈቃ) ተገርፋለች፡፡ ማማሰያ ከሚመስል  እንጨት ይልቅ ‹‹ለመጥ›› ያቃጥላል የምትለው ታዳጊ፣ ከእናቷ አለንጋ ሁሉ የማትረሳው ግን ክረምት ላይ ትከሻዋ ላይ የምታደርገውን ፎጣ ጥላ የገባች ዕለት የተገረፈችውን ነው፡፡

‹‹በዕለቱ ዝናብ ነበር፡፡  ፎጣዬን ከትከሻዬ አድርጌ ከብት ለማሰማራት ወጣሁ፡፡  ወደ ቤት ስመለስ ግን ፎጣዬ አልነበረም፡፡ የት እንደወደቀም አላስታውስም፡፡ ይህን ያስተዋለችው እናቴ የት እንደጣልኩት ጠይቃኝ መልስ ስታጣ ዱላዋን ይዛ ብድግ አለች፡፡ የዛን ዕለት ሮጬ ከቤት ወጣሁ፡፡ ስትከተለኝ ያዩ ጎረቤታችን እናቴን ‘ተይ’ ብለዋት እኔም ወደ ቤት ገባሁ፡፡ ነገር ግን ቀጋ (ፍሬው የሚበላ ሆኖ ግንዱ እሾህ ያለው ተክል) ቆርጣ ገረፈችኝ›› የምትለው ታዳጊ፣ በለመጥ መገረፍና ማልቀስ ቤት ውስጥ ጥፋት ተፈፀመ በተባለ ቁጥር የሚገጥማት እንደነበር ትናገራለች፡፡

በገጠርም ሆነ በከተማ ወላጆች ልጆቻቸውን በተለያዩ ክስተቶች ሳቢያ ሲቀጡ ይስተዋላል፡፡ አንዳንዶች ልጆቻቸውን በምክር ለመገሰጽ ሲሞክሩ፣ ሌሎች ደግሞ በአለንጋ፣ በቀበቶ ወይም በጨፈቃ መግረፍን ይመረጣሉ፡፡ ጭንና ጭን መሃል ገብተው የሚቆነጥጡ፣ ጥፊና እርግጫ የሚሰነዝሩ ንዴታቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ዕቃ አንስተው የሚወረውሩም አሉ፡፡

የሁለት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ደረጀ የሚያስታውሱት፣ አባታቸው በአለንጋ ይጋረፉ እንደነበር ነው፡፡ ‹‹አባቴ የበግ አለንጋ ነበረው፡፡ በግ በታረደ ቁጥር አለንጋውን በላት ያሽ ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ እኔንም ሆነ ወንድሞቼን የሚገርፈው ስለሚጠላን ነው ብዬ አስቤ አላውቅም፣ አይደለምም፡፡ ጥሩ ሥነምግባር እንዲኖረን ነው›› ይላሉ፡፡

አቶ ደረጀ እንደሚሉት፣ የቤተሰብ ትዕዛዝ ሳይፈጽሙ ሲቀሩ፣ ጨዋታ ሲበዛ ቁማር ሲጫወቱ ወይንም ሰው ቤት መሄድ አንፈልግም ሲሉ ግርፊያ ይከተላቸው ነበር፡፡

ከትምህርት ይልቅ የወላጅን ትዕዛዝ አለማክበር ያስቀጣ እንደነበር፣ ያለፉበት ቅጣት ግን እሳቸውንም ሆነ ሌሎች ወንድሞቻቸውን መስመር እንዳስያዘ፣ ሁሉም ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው፣ ሥራ ይዘውና ቤተሰብ መሥርተው ለመኖር የራሱ አስተዋፅዖ እንደነበረውም ይናገራሉ፡፡

አቶ ደረጀ ዛሬ ላይ ልጆቻቸውን ለመቅጣት እሳቸው እንዳለፉበት የበዛ ግርፊያም ሆነ አለንጋ የማይጠቀሙ ቢሆንም፣ ልጆቻቸው ከመስመር ሲወጡና ለወደፊቱ የማይበጅ ነገር ፈጽመዋል ብለው ሲያምኑ በእጃቸው የልጆቹን እጅ ወይም መቀመጫ እንደሚመቱ፣ ምቱ ለማስደንገጥ ያህል እንጂ ለመጉዳት እንዳልሆነ፣ አንዳንዴ ደግሞ ጥፋት መሆኑን ተናግረው በተደጋጋሚ ከድርጊቱ ሳይታቀቡ ሲቀሩ ‹‹ትንሽ ቆንጠጥ›› እንደሚያደርጉና ይህም፣ ልጆች ዳግም ጥፋቱን እንዳይፈጽሙ ለማስታወስ እንደሚረዳ ይናገራሉ፡፡

‹‹ድሮ አባቴ በምጠላው አለንጋ ይቀጣኝ ነበር፡፡ አሁን ላይ እኔም ሆንኩ ብዙ የማውቃቸው ወዳጆቼ ልጆቻችንን የምንቀጣው በሚወዱት ነው›› ይላሉ፡፡ ፊልም ማየት ሲፈልጉ በመከልከል፣ መጫወቻ ቦታ ባለመውሰድ፣ በአጠቃላይ የሚወዱትን ነገር ለተወሰነ ጊዜ በማሳጣት የሚቀጡ ቢሆንም፣ ይህ ከመጥፎ ድርጊቱ አልመልሰው ያለን ልጅ ትንሽ መቆንጠጡ እንደሚያስፈልግ የራሳቸውን ተሞክሮ በምሳሌ በማንሳት ይናገራሉ፡፡

የአራት ዓመቱ ልጃቸው መኪና ተከፍቶ ባገኘ ቁጥር ዘሎ ይገባል፡፡ ቁልፍ ሲያገኝ ከፍቶ መግባትም አያዳግተውም፡፡ አንድ ቀን ቁልፋቸውን ከመኪና ሳይነቅሉ ከመኪና በወረዱበት ቅጽበት ቁልፍ አስነሳ፡፡ የዛን ዕለት ተቆጥተውታል፡፡ ሁለተኛ እንዳይነካም ኮስተር ብለው ነግረውታል፡፡

በሌላኛው ቀን ልጃቸው የእጅ ፍሬንና ማርሽ ለቆ መኪናዋ ከግቢ በር ጋር ተጋጨች፡፡ የዚህን ቀን ልጃቸውን እጁን በእጃቸው መትተውታል፡፡ ‹‹እንዳይረሳ ብዬም ቆንጥጬዋለሁ›› ይላሉ፡፡ ይህ ከሆነ አራት ወራት ያለፈ ሲሆን፣ ከዛን ቀን ወዲህ የመኪና ቁልፍ እንኳን ቢያገኝ አያነሳም፣ ፍሬንም ሆነ መሪ አይነካም ሲሉም ያክላሉ፡፡

እንደ አቶ ደረጀ፣ ወላጅ ልጆቹን የሚቀጣው ልጆቹን ለመጉዳት ብሎ ሳይሆን ከጉዳትና ከአልባሌ ቦታ ለመከላከል ነው፡፡ ቦታን ያገናዘበና ሥርዓት ያለው ቅጣት ልጆችን የሚገራ እንጂ የሚጎዳ እንዳልሆነ እምነት እንዳላቸውም ይገልጻሉ፡፡

ልጆች እንደፍላጎታቸው ይደጉ የሚሉ አመላካከቶች ቢኖሩም፣ ልጆች ሁሉ የጠየቁትን የሚያደርጉ፣ ጥፋት ሲያጠፉም እያደጉ ሲሄዱ ይተዋሉ ብለው ዝምታን የሚመርጡ ቢኖሩም፣ ይህ ለልጆች ጠቃሚ ይሆናል ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ልጆች ይህ ጥፋት ነው! ተብለው ሊነገራቸው ይገባል፡፡ የጠየቁትን ሁሉ ማድረግም ተገቢ አይደለም›› ይላሉ፡፡

አሁን ላይ ልጆች በጣም ከመስመር ካልወጡ በስተቀር ለመቅጣት የሚመቹ አይደሉም፣ ‹‹እናቴ እወድሻለሁ፣ አባቴ እወድሃለሁ›› እያሉ የወላጅን ልብ የሚረቱበት ሁኔታ እጅን በእነሱ ላይ ለማንሳት አይጋብዝም የሚሉት አቶ ደረጀ፣ በእሳቸው ልጅነት ጊዜ የበዛ ቅጣት ለመኖሩ ወላጅና ልጆች የነበራቸው የቅርርብ ደረጃ ከመራራቁም መነጨ እንደነበር ይናገራሉ፡፡

‹‹አባቴ እኔን ገርፎኝ፣ ወይም ተሳስቶ ቢረግጠኝ ይቅርታ ጠይቆኝ አያውቅም፡፡ እኔም ቀና ብዬ ይህን አደረከኝ ብዬ አላውቅም፡፡ የኔ ልጅ ለእያንዳንዷ ነገር ይቅርታ እንድጠይቀው ይጠብቃል፡፡ እኔም ይቅርታ እላለሁ፡፡ እሱም ይቅርታ ይላል›› ሲሉ አሁን ላይ የሚታየው የልጆችና ወላጆች መቀራረብ ልጆችን ብዙ ጊዜ ከመቅጣት ይልቅ በመነጋገርና በመተማመን ችግሮችን ለመፍታት ዕድል ከፍቷል ይላሉ፡፡

ልጆቻቸው ወደማይፈለግ ባህሪ ማለትም ስርቆት፣ ድብድብ፣ ቁማር፣ ሱስ ሲያዘነብሉ የሚመክሩ ወላጆች እንዳሉ ሁሉ፣ ከልክ በላይ የሚገርፉም አሉ፡፡ ንዴታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው ልጆቻቸው ላይ የአካል ጉዳት የሚያደርሱ፣ በርበሬ የሚያጥኑ፣ ብረት አግለው የሚጠብሱ፣ ጀርባቸው እስኪላጥ የሚደበደቡም ስለመኖራቸው በተለያ ጊዜያት በመገናኛ ብዙኃን ቀርቧል፡፡ ከዚህም አልፎ በንዴት ውስጥ ሆነው በሚሰነዝሩት ምት የልጅን ሕይወት የሚያጠፉ ተስተውለዋል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ልዩ ስሙ ቂሊንጦ በሚባለው አካባቢ የ13 ዓመት ልጃቸውን ‹‹ገንዘብ ወስደሃል›› በሚል ሲቀጡ የነበሩ አባት፣ ልጁ ስለሞተባቸው የራሳቸውን ሕይወት ማጥፋታቸው ሰሞኑን ተዘግቧል፡፡

በጉለሌ ፖሊስ መምሪያ የሕፃናትና ሴቶች ምርመራ ክፍል ኃላፊ ኢንስፔክተር አልጋነሽ ተወልደ ልጆች በአብዛኛው በወላጆች ሳይሆን በሌሎች የቤተሰብ አባላት በኤሌክትሪክ ገመድ ተገርፈው እንዳጋጠማቸው ይናገራሉ፡፡

‹‹ጀበና ሰበርሽ፣ እጅሽን ድስት ውስጥ ከተትሽ›› ብለው የአካል ጉዳት ያደረሰ ግርፊያ የፈጸሙ እንዳሉም ያስታውሳሉ፡፡ ልጆቹ በግርፊያ ምክንያት ጉዳት ቢደርስባቸውን ለመናገር እንደሚፈሩ ጥቆማው የሚደርሳቸው ከአስተማሪ ወይም ጉዳዩን ከሚያውቅ እንደሆነም ያክላሉ፡፡ እንደ መምሪያ ወንጀሉን ከመከላከል ጎን ለጎን የቤተሰብ ፍቅር እንዲኖር የግንዛቤ ማስጨበጫ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡

የሥነልቦና ባለሙያዋ ወይዘሮ ፍቅርተ አዲስ፣ ልጆቻቸውን የሚገርፉም ሆነ አካላዊ ጉዳት የሚያደርሱ ወላጆች፣ ድርጊቱን የሚፈጽሙት ራሳቸውን መቆጣጠር ሲያቅታቸው እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡

ቅጣት የባህሪ ለውጥ እንደማያመጣ፣ መሠረታዊ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት ሕፃናት ከሆኑና በመነጋገር ወዲያው ለውጥ ሊያመጡ የማይችሉ ከሆነ፣ ከሚፈልጉት ነገር በመከልከል፣ ነፍስ ያወቁትን ደግሞ በመመካከር ከጥፋታቸው እንዲቆጠቡ ማድረጉ የተሻለ ውጤት ያስገኛልም ይላሉ፡፡

ልጆች ሲገረፉ ጥፋት ማጥፋታቸው ሊገባቸው እንደሚችል፣ ሆኖም መግረፍ ልጆች ራሳቸውን እንዲጠሉ እንደሚያደርግ፣ ከዚሁ ጎን ለጎንም ‹‹የኔ ናቸው፣ አሉኝ ከጥቃት ይጠብቁኛል›› ብለው በሚመኩባቸው ወላጆች ሲገረፉ የኔ ነው የሚሉትና የሚመኩበት ወላጅ እንደሚያጡና የሥነልቦና ቀውስ ውስጥ እንደሚገቡም ያክላሉ፡፡

እንደ ወይዘሮ ፍቅርተ፣ ልጆች ከመጥፎ ነገር እንዲቆጠቡ የወላጅ ክትትል ወሳኝ ነው፡፡ ልጅን በማሳደግ ወቅትም ወላጆች ልጆቻቸው እንዳያደርጉ የሚፈልጉትን ነገር በሙሉ ራሳቸው እያሳዩ ማሳደግ አለባቸው፡፡ የሚሳደብ ወላጅ ልጄ ተሳደበ ብሎ መግረፍም ተገቢ አይደለም፡፡

ልጆች በቤት ውስጥ ጥፋት ሲያጠፉ ከሚወዱት ነገር ለተወሰነ ጊዜ መከልከል፣ ከመጥፎ ባህሪያቸው እየተሻሻሉ ሲመጡ ደግሞ ማመስገንና መሸለም መልካም እንደሆነም ይመክራሉ፡፡

መግረፍ በልጆች የባህሪ ለውጥ ላይ አስተዋጽኦው አሉታዊ እንደሆነ በመግለጽም፣ ‹‹ወላጆች ልጆቻችንን የምንገርፈው መጥፎ ባህሪ እንዳያዳብሩ፣ መልካም ዜጋ እንዲሆኑ ስለምንፈልግና ስለምንወዳቸው ነው›› የሚሉት ትክክል እንዳልሆነና ለልጆቻቸው ካላቸው ፍቅር የተነሳ ልጆች ከሥነ ምግባር ውጭ እንዳይሆኑ መግረፉ አብሮ እንደማይሄድም ያብራራሉ፡፡

ልጆች ጥፋት ሲያጠፉ በተደጋጋሚ እየተነገራቸው ደጋግመው የሚያጠፉበት ሁኔታ፣ ዕድሜያቸው ጥፋትን ለማገናዘብ ካለመድረሱና የማስታወስ ችሎታቸው ዝቅተኛ ከመሆኑ እንደሚመነጭ በመግለጽም፣ ወላጆች በተቻለ መጠን ትዕግስተኛና በማናቸውም ጊዜ ራሳቸውን የመቆጣጠር ባህሪ አዳብረው ልጆቻቸውን በተከታታይ ጊዜ ለሚፈጽሙት ጥፋት ተከታታይ ምክር በመለገስ ፀባያቸውን ማረቅ እንደሚችሉ ይናገራሉ፡፡

ኪድስ ሄልዝ በድረ ገጹ እንዳሰፈረው፣ ልጆች በሥነ ምግባር የታነጹ ሆነው እንዲያድጉ ወላጆት በቤት ውስጥ የሚያሳዩት ባህሪና በቤት ውስጥ መተግበር ያለበት ሥርዓት ሁሌም ተመሳሳይ መሆን አለበት፡፡ አንድ ልጅ ዛሬ ላጠፋው ጥፋት ከሚፈልገው ነገር እንዲገለል ተደርጎ ነገ ጥፋቱን ሲደግመው ፀጥ የሚባል ከሆነ የወላጆቹን ዕርምጃ ከምንም አይቆጥረውም፡፡ ልጆች አንዴ የተከለከሉትን ነገር ሌላ ጊዜ ሲያደርጉት ፀጥ ማለትም የልጆችን የወላጅን ምክር የመቀበል አቅም ያሳሳዋል፡፡ አንድ ልጅ አታድርግ የተባለውን ነገር አድርጎ ሲገኝ፣ ሊወሰድበት የታሰበን አካልንም ሆነ አዕምሮን የማይጎዳ ቅጣት ሳይፈጽሙ መቅረትም የወላጆችን ልጆችን በሥነ ምግባር የማነጽ ትግል ባዶ ያደርገዋል፡፡ እናትም ሆነ አባት በልጆቻቸው ላይ ያላቸው በሥነ ምግባር የማነጽ አቋምና በቤት ውስጥ ያለ ሥነ ሥርዓትም አንድ መሆን አለበት፡፡ በልጆች መሀል ልዩነት ማድረግም አይመከርም፡፡

ልጆች ማኅበረሰቡ የማይቀበላቸውን ባህሪያት ሲያመጡ አካላዊ ቅጣት በመፈጸም ለማስተካከል መሞከር በተለይ በወላጆች ወይም በአሳዳጊዎች ይከናወናል፡፡ በጫማ፣ በቀበቶ፣ በአለንጋ፣ በእርጥብ እንጨት (ጨፈቃ)፣ በማበጠሪያ እጀታ፣ በጥፊ፣ በቁንጥጫ ወይም ልጆች እንዲንበረከኩ፣ እጅ ወደላይ እንዲያደርጉ፣ ፊታቸውን ወደግድግዳ እንዲያዞሩ በማድረግ ይቀጣሉ፡፡

አካል ላይ ከባድ ጉዳት እስካልደረሰ ድረስ ወላጆች ልጆቻቸውን መስመር ለማስያዝ የሚፈጽሙት ቅጣት በአብዛኛው አገሮች በሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደ መልካም ነገር ይወሰዳል፡፡ ወላጅ ያልተገባ ፀባይ ያለው ልጁን ለማረቅ አካላዊ ቅጣት የማድረግ መብት ያለው ተደርጎም ይወሰዳል፡፡

ጥናቶች ግን ከዚህ በተቃራኒው ወላጆች የልጆችን ባህሪ ለማስተካከል በማለም የሚፈጽሙት አካላዊ ቅጣት የጎንዮሽ ጉዳቱ ያመዝናል ይላሉ፡፡

ልጆችን መግረፍና ላጠፉት ጥፋት መጮህ ኃይለኛና ቁጡ እንዲሆኑ ከማድረግም በላይ የተቀበሉት ቅጣት ከጥፋታቸው ለአጭር ጊዜ ቢታደጋቸው እንጂ ለሁልጊዜ አይጠቅማቸውም፡፡ በልጆቻቸው ያልተገባ ድርጊት በመናደድ በእጃቸው መቀመጫ ላይ የሚገርፉ ወላጆች ቢኖሩም፣ ከዚህ ባለፈ በዱላ፣ በቀበቶ ወይም በአለንጋ ልጆቻቸውን በተደጋጋሚ የሚገርፉ ወላጆች ልጆቹን ለድብርት፣ ለብቸኝነት እንዲሁም ራስን ለመጥላት ይዳርጓቸዋል፡፡ ሲገረፍ ያደገ ልጅም መግረፍን እንደመልካም ይቆጥረውና ይህንኑ ሲያደርግ ይኖራል፡፡

ስዊድን ወላጆች ልጆች ላይ የሚፈጽሙትን ግርፊያ በመቃወም እ.ኤ.አ በ1979 ገደብ ስትጥል፣ ብዙ አገሮችም ሕፃናትን መግፋት የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው በማለት የሕግ ከለላ አስቀምጠዋል፡፡ ሆኖም በተለያዩ አገሮች በተለይም ባላደጉት ወላጆች ልጆቻቸውን ቀላል ከሚባለው እጅን በእጅ መምታት አንስቶ አካላዊ ጉዳት ብሎም እስከሞት የሚያደርስ ግርፊያ ሲፈጽሙ ይስተዋላል፡፡ በሕፃናት ቅጣት ላይ የተሠሩ ጥናቶች ግን ወላጆች ልጆቻቸው ላይ የሚፈጽሙት ግርፊያ ሙሉ ለሙሉ መቆም እንዳለበት ይመክራሉ፡፡     

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...