Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ጃፓን በደቡብ ሱዳን ላይ ማዕቀብ መጣል ዘላቂ ውጤት ያመጣል ብላ አታምንም››

አምባሳደር ኦካሙራ ዮሺፉሚ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ልዩ መልዕክተኛ

አምባሳደር ኦካሙራ ዮሺፉሚ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የጃፓን ቋሚ ልዑክ ናቸው፡፡ በጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ የደቡብ ሱዳን ልዩ መልዕከተኛ በመሆን ለሦስት ቀናት አስቸኳይ የሥራ ጉብኝት በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ቆይታ አድርገው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርን ጨምሮ ምክትላቸውን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸውንና በተዋረድ ሥልጣን እርከን ላይ የሚገኙ ባለሥልጣናትን አነጋግረው በመደምደሚያቸው ወደ አዲስ አበባ መጥተዋል፡፡ ሐሙስ ታኅሳስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ከወቅቱ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት የልማት ድርጅት (ኢጋድ) ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር በደቡብ ሱዳን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ትኩሳት ላይ ተነጋግረዋል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ የመከላከያ ሚኒስትሩን አቶ ሲራጅ ፈጌሳን፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሳሞራ የኑስን ጨምሮ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለጋዜጠኞች በሩን በመዝጋቱና ይህንን ያደረገበትንም ምክንያት በአግባቡ ከማስታወቅ ይልቅ በእንግዶቹ ዘንድ ግራ መጋባት የፈጠረ የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ ሲፈጽም ለመታዘብ ተችሏል፡፡ አምባሳደሩ በሚኒስቴሩ ቅጥር ግቢ ቆይታቸው አጋጣሚ ሊሰጡ ተዘጋጅተውበት የነበረውን ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰዓታት እንግልት በኋላ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር መኖሪያ ቤት ተገኝተው እንዲሰጡ አስገድዷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ስለልዩ መልክዕተኛው ጉብኝት ከመንግሥት ዜና አውታሮች በቀር የግልና የውጭ ጋዜጠኞች እንዲዘግቡ አለመፈለጉም፣ በልዩ መልክዕተኛውና በጋዜጠኞች ላይ ቅሬታ አሳድሯል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን መስተንግዶ እዚሁ በመተው፣ አምባሳደር ዮሺፉሚ በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ ለመነጋገር የመጡት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ ማዕቀብ ለመጣል ድምፅ ማሰባሰብ መጀመሩን ጃፓን እንደምትቃወም ለማሳወቅ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ መንግሥታቸው ከማዕቀብ ይልቅ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ አፍሪካውያን መክረው በራሳቸው መፍትሔ እንዲያመጡ ማገዝ ይገባል የሚል አቋም እንዳለው የተናገሩት አምባሳደር ዮሺፉሚ፣ በደቡብ ሱዳን መንግሥት ሊካሄድ የታሰበው ብሔራዊ ምክክር ስደተኛውን የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሬክ ማቻርን ጨምሮ ሁሉንም ሱዳናውያን ያካተተ እንዲሆን ፍላጎት እንዳላት አብራርተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ከላኳቸው መልዕክቶች መካከል የአካባቢው አገሮች የፀጥታ ኃይሎች በአስቸኳይ ለሰላም ማስከበር ሥራ እንዲሰማሩ የሚለው ይገኝበታል፡፡ አምባሳደር ዮሺፉሚ ሪፖርተርን ጨምሮ ከደይሊ ሞኒተር፣ ከአሶሼትድ ፕሬስ፣ እንዲሁም ከሱዳን ትሪቡን መገናኛ ብዙኃን ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ብርሃኑ ፈቃደ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

ጥያቄ፡- በደቡብ ሱዳን ላይ ሊጣል ስለታሰበው ማዕቀብ ተናግረዋል፡፡ ኢጋድ ያወጣውን መግለጫ ጃፓን እንደምትደግፍም ተገልጿል፡፡ የኢጋድ የድርድርና የመፍትሔ ሙከራዎች አልሠሩም፣ አባል አገሮችም በደቡብ ሱዳን ጉዳይ እየተሰላቹ ነው በማለት ታዛቢዎች እየተቹ ነው፡፡ በደቡብ ሱዳን ላይ ማዕቀብ ባለመጣሉ ምክንያት ግጭቶች ተባብሰው ቀጥለዋል፡፡ በርካቶችም አሁንም ድረስ እንዲገደሉ ምክንያት የሆኑት ግጭቶች ሊቆሙ አልቻሉም እየተባለ ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሳማንታ ፓወርም የዚህን ጉዳይ አሳሳቢነት አስረድተዋል፡፡ ይህ እየተባለ ባለበት ወቅት ማዕቀብ አያስፈልግም በማለት ጃፓን ከኢጋድ አቋም ጋር መተባበርን ለምን መረጠች? 

አምባሳደር ዮሺፉሚ፡- በደቡብ ሱዳን ሊጣል የታሰበውን ማዕቀብ በሚመለከት በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ በከፍተኛ ግለት እየታዩ ካሉ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ የፀጥታው ምክር ቤት በአገሪቱ ያለው ቀውስ መወገድ እንዳለበት በአንድ ድምፅ ተስማምቷል፡፡ በዚህ አቋም ላይ የምክር ቤቱ አባላት አንድነት አላቸው፡፡ የትኛውንም ዓይነት ግድያና ደም መፋሰስ ማስቆም አለብን፡፡ ሰብዓዊ ቀውሱንና ብጥብጡን ማስወገድ ይኖርብናል፡፡ ተገቢውን ጥረት በማድረግ በንፁኃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ማስቆም አለብን፡፡ በዚህ ዓላማ ላይ የፀጥታው ምክር ቤት የጋራ አቋም መያዙን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ማዕቀብን ጨምሮ ምን ዓይነት ዕርምጃዎች ይወሰዱ በሚለው ላይ ግን የልዩነት አቋሞች አሉ፡፡ በጃፓን በኩል ያለው አቋም የደቡብ ሱዳንን ሰላምና መረጋጋት ሊያመጡ የሚችሉ መልካም ዕርምጃዎችን እንደግፋለን፡፡ በዚህ ረገድ ጃፓን ኃላፊነት ያለበት የመፍትሔ መንገድ ሊኖር እንደሚገባ ታምናለች፡፡ አቋሟም ይህንኑ ሊያሳኩ የሚችሉ ዕርጃዎች እንዲኖሩ ነው፡፡ እንደ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሰላምና ፀጥታ በደቡብ ሱዳን እንዲሰፍንና ነገሮች ወደነበሩበት አኳኋን እንዲመለሱ በጥብቅ ትፈልጋለች፡፡ ይህ እንዲሳካም ተገቢውን ግፊት ማድረግ እንፈልጋለን፡፡

ይሁንና ጃፓን ምን ዓይነት ዕርምጃ ትወስዳለች ከተባለ በተለይ ኅዳር 16 ቀን 2009 ዓ.ም.  የደቡብ ሱዳን መንግሥት የቀጣናው ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ወደ አገሪቱ እንዲገቡ ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ብሔራዊ ምክክር ለአንድነት ሲባል መካሄድ እንዳለበት የሚጠይቅ ጠንካራ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህ ዕርምጃ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል በማመን ትልቅ ተስፋ ጥለንበታል፡፡ በቀጣናው ደረጃም ኢጋድ በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ ጠንካራ አቋም በመያዝ አገሪቱ የቀጣናውን ሰላም አስከባሪ ኃይሎች እንድትቀበል እያደረገ ነው፡፡ ኢጋድ ኅዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የጦር መሣሪያ ክልከላ ወይም ማዕቀብ መጣል ለደቡብ ሱዳን ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ አስታውቋል፡፡ እኛም ይህንን የኢጋድን አቋም እናከብራለን፡፡ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች መኖር እንዳለባቸው ጃፓን እምነቷ ነው፡፡ ጃፓን በደቡብ ሱዳን ላይ ማዕቀብ መጣል ዘላቂ ውጤት ያመጣል ብላ አታምንም፡፡

ጥያቄ፡- በኅዳር ወር ወደ ደቡብ ሱዳን ከተላኩት የጃፓን ተጠባባቂ የሰላም አስከባሪ ጦር አባላት በተጨማሪ ለመላክ አስባችኋል? ይህ ታስቦ ከሆነ ምን ያህል ተጨማሪ ጦር ወደ ደቡብ ሱዳን ትልካላችሁ? መቼ ለመላክስ አስባችኋል?

አምባሳደር ዮሺፉሚ፡- 350 ያህል የጃፓን ተጠባባቂ ወታደራዊ ኃይል አባላት ወደ ደቡብ ሱዳን ተልከው በምህንድስና ሥራዎች ላይ ተሰማርተዋል፡፡ የመንገድና ሌሎች ግንባታዎችንም እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡ ወታደሮቻችንን በደቡብ ሱዳን እንዲቆዩ የማድረግ ሒደቱን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ የሠራዊቱ አባላት በደቡብ ሱዳን ጥሩ ሥራ እየሠሩ እንደሆነ እናምናለን፡፡ ይሁንና ለአሁኑ ባሉት ወታደሮች መቀጠሉን እንመርጣለን፡፡ ተጨማሪ ጦር ወደ አገሪቱ የመላክ ዕቅድ ለጊዜው የለንም፡፡

ጥያቄ፡- እነዚህ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ወደፊት የመዋጋት ተልዕኮ ሊኖራቸው ይችላል?

አምባሳደር ዮሺፉሚ፡- ተጠባባቂ ወታደራዊ ኃይሉ የውጊያ ተልዕኮ አለው ብዬ አላስብም፡፡ ተልዕኳቸው ይህ አይደለም፡፡ ሥራቸው በምህንድስና መስክ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የውጊያ ተግባር ውስጥ ይሳተፋሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ቀደም ብሎም ደቡብ ሱዳን ነፃነቷን ከተቀዳጀች ጀምሮ ጃፓን ለደቡብ ሱዳን ድጋፍ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ በደቡብ ሱዳን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ ጠንካራ እምነት ስለነበረን ከነፃነት ማግሥት ጀምሮ በድልድይ ግንባታ፣ በውኃ አቅርቦት፣ እንዲሁም በናይል ወንዝ ላይ የወደብ ግንባታ ሥራዎችን ለማከናወን የሚችሉ የጃፓን ኃይሎችን ወደ አገሪቱ ልከን ነበር፡፡ ይሁንና ፕሮጀክቶቹ ተግባር ላይ መዋል ከመጀመራቸው በፊት ፖለቲካዊ ቀውሱ ተከሰተ፡፡ ጃፓንም በምንም ዓይነት ሁኔታ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ከመግባት ትቆጠባለች፡፡ የቀጣናው ፖለቲካዊ ጉዳይ በቀጣናው አገሮች መፈታት አለበት ብለን ስለምናምን በፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ መግባት አንሻም፡፡

ይሁንና በደቡብ ሱዳን የነበረው ሰለምና መረጋጋት እየተናጋ ነገሮችም እየተባባሱ በመቀጠላቸው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሥጋቱን መግለጽ ጀመረ፡፡ ግድያዎችና ብጥብጦች እያየሉ በመምጣታቸው የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት በአገሪቱ ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድና ማዕቀብም እንዲጣል ግፊት ማድረግ ጀመረ፡፡ ጃፓን ማዕቀብ እንዲጣል የሚጠይቀው ረቂቅ ውሳኔ አትቀበልም፡፡ ሆኖም ሰላም አስከባሪዎች ወደ ደቡብ ሱዳን እንዲላኩ ስለምትደግፍ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡ ተጠባባቂ የጃፓን ወታደራዊ አባላቱ የተሰጣቸውን የምህንድስና ሥራ ከማከናወን ውጪ በውጊያ ተልዕኮ ላይ የሚሳተፉ አይደሉም፡፡

ጥያቄ፡- ጃፓን በቀጣናው አገሮች በተለይም በኢጋድ አባል አገሮች በኩል ሲደረጉ የነበሩ የማደራደርና የማግባባት ሒደቶችን እንዴት ትገመግማቸዋለች? የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች እንዲስማሙ በርካታ ሙከራዎች ቢደረጉም፣ በመጨረሻ ግን ውጤት አልባ ሲሆኑ ታይተዋል፡፡ እንዲህ ያሉትን ሒደቶች እንዴት ትመዝኗቸዋላችሁ? ማዕቀቡ ቢጣል ውጤት ስላለማምጣቱስ ምን ያህል እርግጠኞች ናችሁ?

አምባሳደር ዮሺፉሚ፡- በቀጣናው አገሮች ሲሞከሩ የነበሩ መፍትሔ የማፈላለግ ሒደቶች አልተሳኩም ብሎ ለመደምደም ጊዜው ገና ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉባቸው ድርድሮችና የማስታረቅ ሥራዎች ላይ የቀጣናው አገሮች ፕሬዚዳንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትሮች በጉባዔ ደረጃ የተካሄዱ ምክክሮችን በማድረግ የቀጣናው ሰላም አስከባሪ ኃይሎች ወደ አገሪቱ ገብተው እንዲያረጋጉ ለማስቻል፣ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ፈቃደኛ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበውላቸዋል፡፡ ብሔራዊ የምክክር መድረክ እንዲደረግ የሚለውም ከቀጣናው አገሮች በተደረገ ግፊት የመጣ የመፍትሔ ሐሳብ በመሆኑ፣ የቀጣናው የሰላም መፍትሔዎች ውጤት ማምጣት አልቻሉም በተባለው ግምገማ አልስማማም፡፡ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር የሰላም አስከባሪ ጦር ከቀጣናው አገሮች እንዲላክ በሚለው ሐሳብ ላይ ተስማምተዋል፡፡ ሰላም አስከባሪዎቹን ለመቀበል ፈቃደኛ ሆነዋል፡፡

ይሁንና አገሮቹ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚላኩ ሰላም አስከባሪዎችን ለማዋጣት ቢስማሙም ተግባራዊ ምላሽ መስጠት ግን አልጀመሩም፡፡ ጃፓን የቀጣናው አገሮች አካል አይደለችም፡፡ በዚህም ሳቢያ ማድረግ የምንችለው በጣም የተወሰነ አስተዋጽኦ ነው፡፡ ነገር ግን ጃፓን የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካ መፍትሔዎች መፈታት አለባቸው የሚል ጠንካራ አስተሳሰብ ታራምዳለች፡፡ የቀጣናው አገሮችም በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ መፍትሔ ለማፈላለግ ቁርጠኛ ስለመሆናቸው መናገር እችላለሁ፡፡

ጥያቄ፡- በቀጣናው አገሮች የሚቀርቡ የመፍትሔ ሐሳቦች ሊከበሩ እንደሚገቡ ገልጸዋል፡፡ ከሁለት ጊዜ በላይ የሰላም ስምምነቶች ተፈርመው ነበር፡፡ ነገር ግን ውጤት ማምጣት አልቻሉም፡፡ ይህ በሆነበት ብሔራዊ ምክክር እንዲደረግ የቀረበው ጥሪ ምን ያህል ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ታምናላችሁ? በእናንተ በኩል ምን ዓይነት መፍትሔዎችን እያቀረባችሁ ነው? እስካሁን ሊሳኩ ካልቻሉ የመፍትሔ መንገዶች ባሻገር እናንተ የምታቀርቡት ሐሳብ ምንድን ነው?

አምባሳደር ዮሺፉሚ፡- ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች የሚለውን አቋማችንን አሁንም ደግሜ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ የሰላም ስምምነት አሁንም ቢሆን ተቀባይነት ያለው መፍትሔ እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ እንደማስበው ለአሁኑ ብቸኛው አማራጭ የትኛውም የደቡብ ሱዳን ቡድን የሰላም ስምምነት እንዲያደርግና እንዲያከብረው ማድረጉ ነው፡፡

ጥያቄ፡- ጉብኝትዎ በኢትዮጵያ ላይ ማተኮሩ በምን ምክንያት ነው?

አምባሳደር ዮሺፉሚ፡- ኢትዮጵያ የኢጋድ ወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር በመሆኗ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ መፍትሔ ለማምጣት ጠንካራ አቋም እንዳላቸው አውቃለሁ፡፡ ኢትዮጵያ በቀጣናው ካሉ አገሮች ትልቋና የተከበረች አገር እንደመሆኗ ጃፓን አንዳንድ ሐሳቦችን ለመቀበል እንዲያስችላት፣ ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት ስለሚያስፈልጋትም ጭምር ነው፡፡ በጉብኝቴ ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ፍሬያማ የሐሳብ ልውውጦችን በማድረግ፣ በደቡብ ሱዳን ጉዳይ ላይ የነበረንን መረዳት ይበልጥ ለማዳበር ችለናል፡፡ ከውይይቱ በመነሳት ለመፍትሔው ጃፓን ምን ዓይነት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባትም ለማሰብ አስችሎናል፡፡

ጥያቄ፡- ሬክ ማቻርን በተመለከተ ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር ተነጋግራችሁ ነበር? ፕሬዚዳንቱ ስለ ማቻር ምንድነው የሚያስቡት? እንደሰማነው ከሆነ በደቡብ አፍሪካ፣ ፕሪቶሪያ ከተማ በቁም እስር ላይ እንደሚገኙ ነው፡፡

አምባሳደር ዮሺፉሚ፡- ከፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ በቀጥታ አልተነጋገርንም፡፡ ሆኖም በብሔር ምክንያት ዳግመኛ ግጭት ውስጥ የገቡ ሰዎች ጉዳይ እንደሚያሳስበን ለፕሬዚዳንቱ ነግረናቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለዚህም ነው ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ጀምሮ ብሔራዊ ምክክር እንዲደረግና አንድነት መልሶ እንዲሰፍን ለማስቻል የተነሱት፡፡ የሬክ ማቻር ጉዳይም ተመሳሳይ አጀንዳ እንደሚሆን አምናለሁ፡፡ ብሔራዊ ምክክሩ ሁሉንም የደቡብ ሱዳን ጎሳዎችና ሌሎችንም የሚያካትት እንደሚሆን አስባለሁ፡፡

ጥያቄ፡- የቀጣናው አገሮች ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን በማዋጣት ወደ ደቡብ ሱዳን ለመላክ ከሚያቅማሙባቸው ምክንያቶች አንዱ የፋይናንስ ችግር ነው እየተባለ ነው፡፡ ጃፓን በደቡብ ሱዳን ለሚሠማሩ ኃይሎች የፋይናንስ ድጋፍ የማድረግ ዕቅድ አላት?

አምባሳደር ዮሺፉሚ፡- እኔ እስከማውቀው ድረስና ከደቡብ ሱዳን መሪዎች ጋር ካደረጉት ውይይት አኳያ የፋይናንስ አስተዋጽኦ ጉዳይ ጥያቄ አልነበረም፡፡ በውይይታችን ወቅትም አልተነሳም፡፡

ጥያቄ፡- በጠቅላላው ከተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ፍላጎት አኳያ የጃፓን አቋም ምንድነው?

አምባሳደር ዮሺፉሚ፡- ይህንን ቀደም ሲል ጠቅሼዋለሁ፡፡ የደቡብ ሱዳን መሪዎች ማዕቀብ እንዳይጣልባቸው ከፈለጉ ትርጉም ያለውና ተጨባጭ ዕርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ማዕቀቡ በተለይ በጦር መሣሪያ ክልከላ ላይ ሊጣል ከታሰበው ዕገዳ ይልቅ፣ የቀጣናው አገሮች የደቡብ ሱዳን መንግሥት ተጨባጭ ዕርምጃ እንዲወስድ ለማድረግ እያደረጉት ያለው ጥረት ፍሬያማ ሊሆን እንደሚችል እናምናለን፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋችንን እንቀጥላለን፡፡

ጥያቄ፡- ጃፓን ከማዕቀብ ይልቅ ውጤታማ ተግባራትን እንደምትደግፍ ገልጸዋል፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ተግባራት ምንድን ናቸው?

አምባሳደር ዮሺፉሚ፡- ተግባራት ስል በመሬት ላይ ያሉ ሥራዎችን ለመጥቀስ ነው፡፡ ሰላም አስከባሪዎች ወደ ደቡብ ሱዳን እንዲገቡ መፍቀድ አንዱ ነው፡፡ ንፁኃን ዜጎችን ከጥቃት ለመከላከል የሚያስችል ግልጽ ትዕዛዝ ከደቡብ ሱዳን መንግሥት መሰጠት አለበት፡፡ በንፁኃን ዜጎች ላይ ጥቃት ያደረሱና በርካታ ወንጀሎችን የፈጸሙ የትኞቹም የደቡብ ሱዳን አማፂ ኃይል አባላትና ወታደሮች ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ በደቡብ ሱዳን መንግሥት እንዲወሰዱ የምንጠብቃቸው ዕርምጃዎች ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ እንዲተላለፉ የፈለጓቸው መልክዕቶች ንፁኃን ዜጎች ላይ የሚደርሰው ጉዳትና የሚፈጸመው ግድያ በአስቸኳይ እንዲቆም ነው፡፡ ይህንኑ መልዕክት ለደቡብ ሱዳን መሪዎች አስተላልፈናል፡፡ የሰላም አስከባሪዎች በአስቸኳይ እንዲላኩ ጠይቀናል፡፡

ጥያቄ፡- ከሥልጣናቸው ስለተባበሩት ሬክ ማቻር ጉዳይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምና ከሹማምንቶቻቸው ጋር ተነጋግራችኋል?

አምባሳደር ዮሺፉሚ፡- ማለት የምችለው ነገር ቢኖር ሊካሄድ የታሰበው ብሔራዊ ምክክር ሁሉንም አሳታፊ እንደሚሆን ማድረጉ ላይ ስምምነት መኖሩን ነው፡፡ ሁሉንም የሚያሳትፍ ሲባል ደግሞ ሁሉንም ደቡብ ሱዳናውያንን ያጠቃልላል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምም ተመሳሳይ ሐሳብ አንፀባርቀዋል፡፡ ማድረግ የሚገባን ነገር ቢኖር ምርጥ ሊባል የሚቻለው መፍትሔ ምን እንደሆነ፣ ለደቡብ ሱዳናውያን የሚበጀው አማራጭ ምን እንደሚሆን ማፈላለጉ ላይ ነው፡፡  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...