ኅዳር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በ15 ሲኖትራክ ተሽከርካሪዎች ግምቱ ከ6.4 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ለ40/60 ቤቶች ግንባታ የሚውል የአርማታ ብረት ዘርፈዋል ተብለው የታሰሩ ሰባት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሠረተባቸው፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ታኅሳስ 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበው ክስ እንደሚያስረዳው፣ ተከሳሾቹ የዝርፊያ ወንጀሉን የፈጸሙት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኢንተርፕራይዝ መጋዘን ነው፡፡ መጋዘኑ የሚገኘው በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት ውስጥ ሲሆን፣ ተከሳሾቹ ድርጊቱን የፈጸሙት ኅዳር 10 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀኑ ሰባት ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን ዓቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል፡፡
ተከሳሾቹ የኢንተርፕራይዙ የግብዓት ክምችትና ሥርጭት ኦፊሰር ተስፋለኝ በቀለ፣ ነጋዴ መሆናቸው የተገለጸው ዳርሰማ ጃኦ፣ ስንታየሁ ተስፋዬ፣ አበበ ተስፋዬ፣ ልዑል ፈቃዱ፣ አሸናፊ ረታና ኢዮስያስ ዓለሙ ናቸው፡፡
ኦፊሰሩ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘትና ለሌሎቹም ለማስገኘት በማሰብ ግምቱ 6,407,229 ብር የሆነ ባለ ስድስት ዲያሜትር 55 ጥቅልና ባለ ስምንት ዲያሜትር 73 ጥቅል የመንግሥት ብረት፣ በ15 ሲኖትራኮች በማስጫን እንዲዘረፍ ማድረጉ በክሱ ተገልጿል፡፡
ዳርሰማና ስንታየሁ በ15 ሲኖትራኮች የተጫነውን ብረት ሞጆ ሳይት ፋሪ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘውና ዳርሰማ በተባለው ተከሳሽ መጋዘን ውስጥ እንዲራገፍ ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡ ብረቱን ከመጋዘን በማውጣት ከኢንተርፕራይዙ ያወጡት በፎርጅድ ሰነድ ተጠቅመው መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ተከሳሾቹ የብረቱን ምንጭና የባለቤትነት መብት እንዳይታወቅ ከማድረጋቸውም በተጨማሪ፣ ዳርሰማ ከሕግ ተጠያቂነት እንዲያመልጥ ስንታየሁ ሞጆ ሳይት ከሚገኘው መጋዘን የተራገፈውን ብረት በ11 ሲኖትራኮች በማስጫን ሰበታ በሚገኘው የግሉ ፕላስቲክ ፋብሪካ መጋዘን ውስጥ ማስተላለፉን ክሱ ያብራራል፡፡
አበበ ተስፋዬ የወንጀሉ ድርጊት እንዲፈጸም ሲያመቻች፣ አሸናፊ ደግሞ በሁለት ሲኖትራኮች የቀረበለትን ብረት በመግዛት አዳማ (ናዝሬት) በሚገኘው የግል የንግድ ድርጅቱ ውስጥ ማስቀመጡን ክሱ ይጠቁማል፡፡ ኢዮስያስ ደግሞ የተሸጠለትን 1932 ኩንታል ብረት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ‹‹ጭድ ተራ›› በሚገኘው ንግድ ድርጅቱ ውስጥ ማስቀመጡን ክሱ ያብራራል፡፡
በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1ሀ እና ለ)ን፣ 33 እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 31(2)ን፣ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 እና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 23(2ሀ) ላይ የተደነገገውን ተላልፈው በመገኘታቸው፣ በፈጸሙት ከባድ የእምነት ማጉደል ሙስና ወንጀል፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ (ንብረት) ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ የሙስና ወንጀልና መንግሥታዊ ሰነዶችን አስመስሎ ማዘጋጀትና መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ እንደተመሠረተባቸው፣ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ክስ ያስረዳል፡፡
ተከሳሾቹ ዋስትና እንዲፈቀድላቸው ባቀረቡት የመብት ጥያቄ ላይ ተገቢ ምላሽ ለመስጠትና ከጠበቆቻቸው ጋር ተመካክረው የቅድመ ክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለታኅሳስ 14 ቀን 2009 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡