[ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው ቲቪ እየተመለከቱ አገኙዋቸው]
- ሰላም ውዴ፡፡
- እንዴት ዋልሽ?
- ታንኪው፡፡
- ለምኑ?
- ለቲቪው፡፡
- ከየት ነው የመጣው?
- እንደዚህ ዓይነት ጨዋታ ደስ አይለኝም፡፡
- የምን ጨዋታ ነው?
- የፈረንጆቹ ጨዋታ ነዋ፡፡
- ምንድን ነው የምትቀባጥሪው?
- ሰርፕራይዝ ለማድረግ ፈልገህ ነው?
- የምን ሰርፕራይዝ ነው?
- ቲቪውን ነዋ፡፡
- እኮ ከየት ነው የመጣው?
- እሱንማ አንተ ንገረኝ፡፡
- እ…
- እኔ አልላኩትም ለማለት ፈልገህ ነው?
- ለመሆኑ ቲቪውን አውቀሽዋል?
- ምን እያልክ ነው?
- በየትኛው አቅሜ ነው እንደዚህ ዓይነት ቲቪ ልገዛ የምችለው?
- የሚገዛልህ አይጠፋማ፡፡
- እንደዚህ ዓይነት ነገር ውስጥ እንደማልገባ ታውቂያለሽ፡፡
- ምን እያልከኝ ነው?
- ቲቪው እኮ በጣም ዘመናዊ ነው፡፡
- እኔም በጣም ወድጄዋለሁ፡፡
- ከ500 ሺሕ ብር በላይ ነው፡፡
- በጣም ይገርማል፡፡
- እና ማን ነው ያመጣው?
- እኔ አላውቅም፡፡
- ቤት ማን አመጣው ታዲያ?
- ወዳጆችህ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸው ጋ ደወሉ]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ይቅርታ ከመሸ ደወልኩልሽ፡፡
- ችግር የለውም፡፡
- ዛሬ ቤት ምን ልከሽልኛል?
- ቅድም አስቤዛ ልኬያለሁ፡፡
- እኮ ምንድን ነው የላክሽው?
- ስኳር፡፡
- እሺ፡፡
- ዘይት፡፡
- ሌላስ?
- ሥጋ ያላኩልዎት ፆም ነው ብዬ ነው፡፡
- ቲቪ አላክሽም?
- ኧረ አላኩም፡፡
- ማን ነው የላከው ታዲያ?
- ተጀመረ ማለት ነው፡፡
- ምኑ?
- ስጦታ መሰጣጣቱ፡፡
- የምን ስጦታ ነው?
- በቃ ክቡር ሚኒስትር ሊያስገቡዎት እኮ ነው፡፡
- የት ነው የሚያስገቡኝ?
- መስመሩ ውስጥ፡፡
- የምን መስመር?
- የጥቅሙ ነዋ፡፡
- እ…
- ቲቪ ተልኮልዎት…
- እ…
- መሬት እንዳይቀበሉዎት!
[ክቡር ሚኒስትሩ በጣም ተናደው የቀድሞው ጓደኛቸው ጋ ደወሉ]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሰላም ወዳጄ፡፡
- ከየት ተገኙ ዛሬ ክቡር ሚኒስትር?
- እስቲ ክቡር ሚኒስትር የሚለውን ተወው፡፡
- እሱማ ፕሮቶኮል ነው፡፡
- የት ነው ያለኸው?
- እዛ ድሮ የምናመሽበት ግሮሰሪ ነኝ፡፡
- መጣሁ ጠብቀኝ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- በጣም ብዙ ሰው አለ እኮ?
- መኪና ውስጥ እንሆናለን፡፡
- እሺ እጠብቅዎታለሁ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ከጓደኛቸው ጋር መኪና ውስጥ አንድ ሁለት ማለት ጀመሩ]
- ሥራ እንዴት ነው ክቡር ሚኒስትር?
- በጣም ያስቸግራል፡፡
- ማለት ክቡር ሚኒስትር?
- ሁሉም ሌባ ብቻ ነው፡፡
- ለዚያ አይደል እንዴ የተሾሙት፡፡
- አሁን ግን አልቻልኩም፡፡
- ምን እያሉ ነው?
- በቃ ሁሉም በሙስና ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡
- መቼም አልገቡበትም?
- እ…
- ሙስና ውስጥ አልገቡም አይደል?
- እኔማ መግባት አልፈልግም፡፡ ግን…
- ግን ምን?
- በግድ እየገፋፉኝ ነው፡፡
- በፍፁም እንዳይገቡ፡፡
- ምን ላድርግ?
- ምን ሆነው ነው?
- አንድ ነገር እንድታማክረኝ ነው፡፡
- እኮ ምን?
- የማላውቀው ሰው ስጦታ ላከልኝ፡፡
- ምን ዓይነት ስጦታ?
- ከ500 ሺሕ ብር በላይ የሚያወጣ ቲቪ፡፡
- እ…
- ምን ላድርግ?
- እንዳይቀበሉት፡፡
- ምን ላድርገው?
- ለእኔ ይስጡኝ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ግሮሰሪ ወጥተው ሲያሽከረክሩ ትራፊክ ያዛቸው]
- እስቲ መንጃ ፈቃድ?
- ይኸው፡፡
- ይኼ እኮ መታወቂያ ነው፡፡
- ምን ፈልገህ ነው?
- መንጃ ፈቃድ፡፡
- ዋናው መንዳት መቻሌ ነው፡፡
- ጭራሽ ጠጥተዋል?
- ምነው ቀናህ?
- እ…
- ጋብዘኝ እኮ አላልኩህም፡፡
- ጠጥቶ ማሽከርከር አይቻልም እኮ፡፡
- ማን ነው ያለው?
- ሕጉ፡፡
- የትኛው ሕግ?
- እሺ ጌታዬ እርስዎም መኪናውም ይታሰራሉ፡፡
- ምን?
- ሞተሩን ያጥፉት፡፡
- ሕይወትህን እንዳላጠፋው፡፡
- ሰውዬ ወደ ጣቢያ እንሂድ፡፡
- ማን እንደሆንኩ አውቀሃል?
- ማን ነዎት?
- ክቡር ሚኒስትር!
[ክቡር ሚኒስትሩ አረፋፍደው ቢሮ ሲገቡ አማካሪያቸውን አገኙት]
- ምነው አረፈዱ?
- ትናንት ትንሽ ቀማምሼ ነው፡፡
- ምን ተገኘ?
- አንዳንዴ ጠጣ ጠጣ ይልሃል አይደል?
- ከዚህ ሲሄዱ ሰላም ነበሩ እኮ፡፡
- ቤት ስገባ ተናድጄ ነው፡፡
- ከሚስትዎ ተጣሉ?
- ኧረ አንድ ነገር አጋጥሞኝ ነው፡፡
- ትራፊክ ይዞዎት እንደነበር ሰምቻለሁ፡፡
- ምን?
- ምነው ደነገጡ?
- እንዴት አወቅክ?
- መረጃ ሁሌም ይደርሰናል፡፡
- ሁሉም ሰው ሰምቷል?
- መስማት ያለበት ሰምቷል፡፡
- ተዋርጃለኋ?
- በምን ተናደው ነው የጠጡት?
- አንዱ ቲቪ ልኮልኝ ነዋ፡፡
- ታዲያ ይኼ ምን ያናድዳል?
- እ…
- እንዲያውም በጣም ያስደስታል፡፡
- ምን አልክ?
- ገና ይቀጥላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምኑ?
- ቪ8ቱ…
- እ…
- ፎቅ…
- እ…
- ኧረ ስንቱ?
- ምንድን ነው የሚሻለኝ?
- ቶሎ መግባት ነዋ፡፡
- የት?
- ኔትወርኩ ውስጥ፡፡
- ወይ ጣጣ፡፡
- ሚኒስትር መሆንዎን ትራፊኩ ሲያውቅ እንዴት እንደተሸማቀቀ አይተዋል አይደል?
- ቀላል ተሸማቀቀ፡፡
- ስለዚህ በደንብ ይጠቀሙበት፡፡
- ምኑን?
- ሥልጣንዎትን፡፡
- እ…
- የያዙት ሥልጣን ትርፉ ይኼ ነው፡፡
- ምንድን ነው ትርፉ?
- ስጦታ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሌላ ሙሰኛ ሚኒስትር ጋር እያወሩ ነው]
- ራስ ምታቱ ለቀቀዎት ክቡር ሚኒስትር?
- የምን ራስ ምታት?
- ትናንት ቀማምሰው ተይዘው ነበር አይደል እንዴ?
- እ…
- ምነው ደነገጡ?
- አንተም ሰምተሃል?
- ወሬ መቼ ይደበቃል ብለው ነው?
- ስማ የፈለኩህ ለአንድ ጉዳይ ነው፡፡
- ለምን ጉዳይ ክቡር ሚኒስትር?
- በርካታ ነጋዴዎች በጣም ተማረዋል፡፡
- ምን ሆነው?
- በገበያ ውስጥ መወዳደር አቃተን እያሉ ነው፡፡
- ታዲያ ነፃ ገበያ እኮ ነው፡፡
- የኮንትሮባንድ ንግድ አስቸገረን እያሉ ነው፡፡
- ምን እናድርግላቸው?
- እነሱ እኮ ታክስ እየከፈሉ ነው የሚነግዱት፡፡
- ታዲያ በነፃ ገበያ መርህ መወዳደር ነዋ፡፡
- መወዳደር አቅቷቸው ከገበያ እየወጡ ነው እያልኩህ?
- እኔ እኮ ይኼ አይመለከተኝም፡፡
- እንዴት አይመለከትህም?
- ሌላ የግል ሥራ፣ የመንግሥትም ሥራ አለብኝ፡፡
- በጣም ያሳዝናል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በግሌ እኮ የምሠራው ገበያው ውስጥ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ነው፡፡
- እ…
- ስለዚህ እርስዎም ቢያግዙን ጥሩ ነው፡፡
- አንተም የኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ አለህበት ማለት ነው?
- ክቡር ሚኒስትር…
- እዚህ ንግድ ውስጥ ያሉት በርካቶች የመንግሥት ሰዎች መሆናቸውን ነግረውኛል፡፡
- መሄድ አለብኝ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- በነገራችን ላይ የሚያምር ሰዓት አድርገሃል፡፡
- ዋጋውም ቀላል አይደለም፡፡
- ምን ያህል ነው?
- 20 ሺሕ፡፡
- 20 ሺሕ ብር?
- ዩሮ!