Tuesday, April 16, 2024

ኢትዮጵያ በጆን ማርካኪስ ምልከታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአገሪቷ ታዋቂ የሆኑት ግሪካዊው ጆን ማርካኪስ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ጥልቅ ዕውቀትን ያዳበሩ ምሁር ናቸው፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ከብሩክሊን ኮሌጅ፣ ሁለተኛ ዲግሪንና ፒኤችዲያቸውን በመንግሥትና የአፍሪካ ጥናት ዘርፍ ከታዋቂው ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡ በአፍሪካ አገሮች ኢኮኖሚ በተለይም በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ በሚገኙ አጎራባች አገሮች ከፍተኛ ጥናት አድርገዋል፡ የሕይወታቸውን ረዥም ጊዜ በማስተማር ያሳለፉት ጆን ማርካኪስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ዘ ሲቲ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒውዮርክና ኒውዮርክ በሚገኘው በሴንት ጆንስ ዩኒቨርሲቲ አስተምረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ አፍሪካ አገሮች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በቦትስዋና፣ ሌሴቶ፣ ስዋዚላንድና ዛምቢያ የካበተ ልምዳቸውን በማስተማር አካፍለዋል፡፡ እኚህ ምሁር በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪካዊ የሚባሉ መጻሕፍትን ለአብነትም ‹ኢትዮጵያ አናቶሚ ኦፍ ኤ ትራዲሽናል ፖሊቲ›፣ ‹‹ክላስ ኤንድ ሪቮሉሽን ኢን ኢትዮጵያ››፣ ‹‹ናሽናል ኤንድ ክላስ ኮንፍሊክት ኢን ዘ ሆርን ኦፍ አፍሪካ›› እና ‹‹ፓስቸራሊዝም ኦን ዘ ማርጂን›› የመሳሰሉትን አበርክተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ‹‹ዘ ግሪክ ኢን ብላክ አፍሪካ›› የሚለው መጽሐፋቸው ግሪክ ከአኅጉሪቷ ጋር ያላትን ግንኙነት በጥልቀት የሚያሳይ ነው፡ ከመጻሕፍቶቻቸው በተጨማሪ የተለያዩ የምርምር ወረቀቶችን የብሔር ብሔረሰቦች መብት፣ እምነትና የብሔር ግጭቶች፣ አርብቶ አደር፣ አገራዊ ውህደት፣ ድንበር ዘለል ንግድና የአካባቢያዊ ፀጥታና የመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ በተለያዩ መድረኮች ላይ አቅርበዋል፡፡ በቅርቡ የወጣው ‹‹ኢትዮጵያ ዘ ላስት ቱ ፍሮንትየርስ (Ethiopia The Last Two Frontiers) የሚለው መጽሐፋቸውም ኢትዮጵያን ከኅብረ ብሔር ዘውዳዊ አገዛዝ ሥርዓት ወደ ዘመናዊ ኅብረ ብሔር ውህደት ለማሸጋገር በሚደረገው ሒደት ላይ የሚገጥሙ ውጣ ውረዶችን ለሚስገነዘብ ነው፡፡ አዲሱን መጽሐፋቸውና ኢትዮጵያ ውስጥ ስለነበራቸው ልምድና ቆይታ በተመለከተ ጥበበ ሥላሴ ጥጋቡ ኮጆን ማርካኪስ ጋር ቆይታ አድርጋለች፡፡

ሪፖርተር፡- ወደኋላ አሥርት ዓመታት ልመልስዎትና ወደ ኢትዮጵያ መጀመርያ እንዴት ሊመጡ ቻሉ?

ጆን ማርካኪስት፡- በጊዜው ኢትዮጵያ ለመምጣት ምንም ዓይነት ዕቅድ አልነበረኝም፡፡ በአጋጣሚ ነው የመጣሁት፡፡ አሜሪካ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን በፖለቲካል ሳይንስ የትምህርት ዘርፍ ተመረቅኩኝ፡፡ ከፖለቲካል ሳይንስ በተጨማሪ የአፍሪካ ጥናት (አፍሪካን ስተዲስ) ጠለቅ ያሉ ኮርሶችን ወስጃለሁ፡፡ በዚያን ጊዜ አፍሪካ እንደ አኅጉር ብዙ እንቅስቃሴዎች እንደ ፀረ ቅኝ ግዛት፣ የቅኝ ግዛት ጥሎ ያለፈውን አሻራ ከሥር መሠረቱ ለማጥፋት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች፣ አገራዊ ብሔርተኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳዎች የተሞላበት ወቅት ነበር፡፡ ነፃ በወጣችው አዲሷ አፍሪካ የነፃነት ታጋይ ሰዎች እንደ ጋናዊው ክዋሜ ንክሩማህ መኖራቸው እኔም ፊቴን ወደ አፍሪካ እንዳዞር አድርጎኛል፡፡ በናይጄሪያ ሥራ መኖሩን ሰምቼ ጓዜን ጠቅልዬ መጣሁ፡፡ ነገር ግን በናይጄሪያ ወጥቶ የነበረው ሥራ ክፍት አለመሆኑን ሰማሁ፡፡ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች አማራጭ እንዳለ ብጠይቅም ብቸኛው አማራጭ ብዙዎች ያልፈለጉት ሥራ ኢትዮጵያ መሆኑ ተነገረኝ፡፡ ስለኢትዮጵያ ብዙ አላውቅም ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም እንደ ሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች አገራዊ ብሔርተኛ ፖለቲካ ፓርቲዎች አለመኖሩ ለእኔ ተመራጭ አገር አልነበረችም፡፡ ነገር ግን ምንም ዓይነት አማራጭ ባለመኖር ጉዞዬን ወደ ኢትዮጵያ አቀናሁ፡፡ የመጣሁበት ወቅት አፄ ኃይለ ሥላሴ አገሪቷን በከፍተኛ ጥንካሬ ያስተዳድሩ በነበሩበት እ.ኤ.አ. በ1965 ነው፡፡ አዲስ አበባም ከገባሁ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ፖለቲካል ሳይንስ የትምህርት ክፍል አቀናሁ፡፡ የዲፓርትመንቱ ኃላፊ በዕድሜ ገፋ ያሉ አጥባቂ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የፖላንድ ዜግነት የነበራቸው ሰው ነበሩ፡፡ ዩኒቨርሲቲውን በበላይነት ሲያስተዳድሩ የነበሩት ጀሱይትስ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ የካቶሊክ ዕምነት ተከታዮችን በመምህርነት ይቀጥሩ ነበር፡፡ ተማሪዎቹ ማጨስም ሆነ መጠጣት አይፈቅድላቸውም፡፡ የዲፓርትመንቱ ኃላፊ የሚሰጧቸውን የተለያዩ ኮርሶች በሚያሳየኝ ወቅት በጣም የገረመኝ ስለኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ኮርስ አለመኖሩ ነው፡፡ ለምን ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ ወይም መንግሥት ተማሪዎቹን እንደማያስተምሯቸው ጠየቅኩኝ፡፡ የሰውየውም መልስ እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮችን አናስተምርም የሚል ነው፡፡ ነገሩን በቀላሉ ልተወው ስላልፈለግኩኝ ለምን የሚል ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ እርሱም የፖለቲካ ጉዳይ የንጉሡ ሥራ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ሕዝብ አይመለከተውም አለኝ፡፡ በመገረም ተማሪዎቹ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚያስቡ ጠየቅኩኝ፤ እርሱም ተማሪዎቹ ስለፖለቲካ ማሰብ አይገባቸውም አለኝ፡፡ ተማሪዎቹን ባወቅኳቸው ወቅት ያስቡ የነበረው ፖለቲካ ብቻ ነበር፡፡ ሌላ ምንም አያስቡም፡፡

ሪፖርተር፡- በምን የትምህርት ዘርፍ ለማስተማር ነበር የተመደቡት?

ጆን ማርካኪስ፡- የምዕራባዊያን በተለይም የአሜሪካን የመንግሥት አወቃቀር፣ የእርስ በርስ ባለ ሁለት ሕግ አውጪ ምክር ቤት ስለመሆኑ፣ እንደሁም ስለዴሞክራሲያዊ መንግሥታት አስተምር ነበር፡፡ እነዚህ ጉዳዮች እንኳን ኢትዮጵን አፍሪካን የሚመለከቱ  አይደሉም፡፡ ተማሪዎቹ ስለማስተምረው ጉዳይ ምንም ዓይነት የማወቅ ፍላጎት አልነበራቸውም፡፡ ማወቅም ማውራትም የሚፈልጉት ስለአብዮቱ ብቻ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በወቅቱ የነበሩት ተማሪዎች እንደነ ካርል ማርክስ፣ ሌኒን፣ ፍራንዝ ፋኖንና ማኦ በመሳሰሉት ከፍተኛ ተፅዕኖ አድሮባቸው የነበረ ወቅት ነው፡፡ እርስዎ የሚያስተምሯቸው ጉዳዮች ከእነሱ ርዕዮተ ዓለም ጋር እንዴት ሊያስማሙ ቻሉ?

ጆን ማርካኪስ፡- በጣም አስቸጋሪ ወቅት ነበር፡፡ በዲፓርትመንቱ ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ ምንም አስተያየት እንዳንሰጥ ተነግሮን ነበር፡፡ ነገሩ እኔም ስለኢትዮጵያ ፖለቲካ ምንም አላውቅም፡፡ ምንም ፍላጎት ስለሌላቸው ሐሳቦች ነበር የማስተምረው፡፡ በዚህም የተነሳ ተማሪዎቹ ችላ ማለት አመጡ፡፡ ብዙዎቹ የእኔን ክፍል ትምህርት ይቀራሉ፡፡ ከመጡም ጥያቄዎችን አይጠይቁም፡፡ ድንገት ጥያቄም ከጠየቁ እኔን አውቀው ለማሳፈርና ለመረበሽ የሚወረወሩ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ አብዩቱ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ ነው ብለህ ታስባለህ? ይሉኝ ነበር፡፡ እኔም ለስለስ ባለ ቋንቋ ‹‹ማሻሻያ ይሻላል›› በማለት እመልስ ነበር፡፡ የመጀመርያ ዓመት በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ ከተማሪዎቹ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ከቀን ወደ ቀን እየተሻሻለ ባለመምጣቱ፣ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያስተምሩ የነበሩ መምህራንን ምክር ጠየቅኩኝ፡፡ መምህራኑም ከአሜሪካ በመምጣቴ የሲአይኤ ወኪል ሰላይ በማለት ሊጠረጥሩኝ እንደሚችሉ ነገሩኝ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ተማሪዎቹ በአሜሪካ ፖለቲካ ላይ ፍላጎት አለመኖሩ ተጨማሪ ምክንያት እንደሆነ አሳወቁኝ፡፡ የነበሩኝ ተማሪዎች ፅንፈኛ የግራ ዘመም ፖለቲካን አቀንቃኝ ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ከፍተኛ ሥፍራ ያላቸው እንደነ ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ ገብሩ መርሻ፣ ዋለልኝ አማኑኤል፣ ጥላሁን ግዛው ተማሪዎቼ ነበሩ፡፡ ተማሪዎቹ የሚያነቡዋቸው መጻሕፍት ለምሳሌ የፍራንዝ ፋኖንን ‹‹ሬችድ ኦፍ ዘ ኧርዝ››፣ የማኦን ‹‹ኦን ኮንትራዲክሽን››፣ የሌኒን ‹‹ኋት ኢዝ ቱ ቢ ደን›› ነበሩ፡፡ እነዚህ መጻሕፍትን እኔ ያላነበብኳቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ጓደኞቼም ተማሪዎቼ የሚያነቡትን መጻሕፍት እንዳነብ፣ እንዲሁም ሐሳባቸውን በግልጽ በክፍል ውስጥ እንዲያስተላልፉ እንድፈቅድላቸውና ስለኢትዮጵያም በጥልቅ እንድመረምር ነገሩኝ፡፡ የተማሪዎቹ የልብ ምት የነበረው የመሬት ጥያቄ ነበር፡፡ የመሬት ጥያቄ ተማሪዎቼ በተለያዩ ሰላማዊ ሠልፎች እንደ መፈክር ይዘው መውጣት የጀመሩበት ወቅት ነበር፡፡ የሁለተኛውን ዓመት ሳስተምር ተማሪዎቼ ተሻሽለው የተለያዩ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን መወያየት ጀመርን፡፡ ተማሪዎቹም እየቀረቡኝና እያመኑኝ መጡ፡፡ በሚቀጥሉት ዓመታት ግንኙነታችን እየጠነከረ መጣ፡፡ በተለያዩ ወቅቶች የዲፓርትመንቱ አባላት አንድ ላይ የምንሰባሰብባቸው ፓርቲዎች ነበሩን፡፡ በአንደኛው ፓርቲ ላይ ተማሪዎቼ ኮካ ኮላ እየጠጡ ነበር፡፡ እኔም ቢራ ወይም ሌላ አልኮል የለም ወይ? ብዬ ጠየቅኩኝ፡፡ ተማሪዎቹም ጀሱይቶች እንደማይፈቅዱ ነገሩኝ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አልኮል ካልተጠጣ ምን እንደሚጠጣ ስጠይቅ ‹ጠጅ› ብለው መለሱልኝ፡፡ ጠጅ አምጡልኝ ብዬ ጠይቄ ጠጅ መጠጣት ጀመርኩ፡፡ ከጠጅ በተጨማሪም ሲጋራም ማጨስ ቀጠልኩ፡፡ እነሱም ሁለት ጊዜ ሕጉን ተላለፍክ አሉኝ፡፡ ግንኙነታችን እያደገ ጓደኛሞች ለመሆንም የበቃነው ከዚያ በኋላ ነው፡፡ ስለንጉሡ አገዛዝም ማንበብና ማወቅም ጀመርኩ፡፡ ዘውዳዊው ባህላዊና ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ አገዛዝ ነው፡፡ ሕዝቡ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ሚና እንዲሁም ቦታ ጠንቅቀው የሚያውቁበት ሥርዓት ነው፡፡ ማኅበረሰቡ በመደብ የተከፋፈለና ታላላቅ ሰዎች ወይም ባላባቶች ፊት ሲቀርቡ በምን መንገድ ማሸርገድ እንዳለባቸው የተረዱበት ጊዜ ነው፡፡ ያ ወቅት ወደ መካከለኛው ዘመን ተመልሶ መኖር ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እንደ አገር (ስቴት) ሁሉ ነገር እየሠራ ነበር፡፡ የዘውዳዊው አገዛዝ አፄ ኃይለ ሥላሴ በፍፁም የበላይነት የአገሪቷን ጉዳይ የሚያስተዳድሩበትና የሚቆጣጠሩበት ሥርዓት ነበር፡፡ በፍፁም የበላይነት የመቆጣጠሪያቸው ማሳያ በግል ጉዳዮች እንደ ፍቺ ባሉት ሁሉ ጣልቃ ይገቡ ነበር፡፡ በጣም ድንቅ ሰው ነበሩ፡፡ ወደኋላ በተለያዩ ጉዳዮች ስማቸው በጭቃ ተለውሶ ቢጠፋም፣ አሁን ሳስበው በግርማ ሞገስ የተሞሉና ግሩም ሰው ነበሩ፡፡ የዘውዳዊውን ሥርዓት በቁጥጥራቸው ሥር አድርገው እያንዳንዱ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት አገሪቷ እንደ አገር እንድቀጥል ያደረጉ ንጉሥ ነበሩ፡፡ ይኼ ማለት ግን አገዛዛቸው ችግር አልነበረውም ማለት አይደለም፡፡ በተለያዩ አካባቢ የነበሩ ሕዝቦች ከነበረው ሥርዓት ጋር ሊጣጣሙ አልቻሉም፡፡ ይኼንን ፍፁማዊ ሥርዓትም ለማስቀጠል እክሎች መፈጠር ጀመሩ፡፡ ኢትዮጵያ ከጥቁር አፍሪካውያን አገሮች መካከል ትልቅና በጦር መሣሪያዎች የታጠቀ ሠራዊት ነበራት፡፡ ይኼ የጦር ኃይል እንደ አሜሪካና ስፔይን ባሉ አገሮች የተለያዩ ሥልጠናዎችና የጦር መሣሪያዎችን በመረዳት ይታገዝ ነበር፡፡ ኤርትራና ሶማሊያ የነበሩ ግጭቶችን ለማቀዛቀዝ ጦሩ ዘምቶ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የጎጃም ገበሬ ያነሳውን አመፅ ለመቆጣጠር ወታደሩ ከብዶት ነበር፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሠራዊት መዋጋት የሚችለውና የሠለጠነበት መንገድ ጦሩ አንድ ቦታ ላይ ሰፍሮ ተቃራኒውን በማጥቃት ላይ ነው እንጂ፣ በሽምቅ ውጊያ ምንም ዓይነት ልምድ አልነበረውም፡፡ ኢትዮጵያ ለነበረችበትም የሽምቅ ውጊያ ወታደሩ መፍትሔ ሊያመጣ አልቻለም፡፡ ከዚህም በላይ ወታደሩ በተለያዩ ብሔሮችና መደቦች የተከፋፈለ በመሆኑ በጦር አዛዦች ላይ አመፅ ማስነሳት ጀመረ፡፡ ከችግሮቹም አንዱ መንስዔ የነበረው በባሌ ሰፍሮ የነበረው ወታደር ከፍተኛ የሆነ የውኃ ችግር ማጋጠሙ እንዱ ነው፡፡ የጦር ሠራዊቱ መፍረክረክ ሲያጋጥመው የንጉሡ አገዛዝም ቀስ በቀስ መውደቅ ጀመረ፡፡

ሪፖርተር፡- ለተማሪዎቹ ማርክሲዝም ተመራጭ ርዕዮተ ዓለም ለምን ሆነ? ዓለም አቀፍ በነበረው የካፒታሊዝምና የማርክሲዝም ርዕዮተ ዓለም ክፍፍልን ተከትሎ ነው ወይስ ማኅበረሰቡ ውስጥ የነበረው በመደብ የተከፋፈለ መዋቅር መነሻ ሆኖ ነው? የመደብ ጥያቄስ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ዋና ጥያቄ ለምን ሆነ?

ጆን ማርካኪስ፡- የማርክሲዝም ርዕዮተ ዓለም ቅኝ ግዛት በተገዙና በተጨቆኑ ሕዝቦች ነፃ የማውጫ ርዕዮተ ዓለም ተደርጎ ታይቶ ነበር፡፡ እንደነ ቻይና፣ ቬትናም፣ አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ሞዛምቢክና ደቡብ አፍሪካ ባሉ አገሮች የርዕዮተ ዓለሙ ዋነኛ አቀንቃኞች ነበሩ፡፡ በዚያን ወቅት የነበሩትም ተማሪዎች ወደዚህ ርዕዮተ ዓለም ማጋደል ይኼንኑ የዓለም አቀፉን አቅጣጫ ተከትሎ ነው፡፡  የማርክሲዝም ርዕዮተ ዓለም ለነበረው ሁኔታ መልስ የሚሰጥ ነበር፡፡ ተማሪዎቹ በአቋራጭ የሚፈለገውን ልማትም ለማምጣት ሶሺሊዝምን እንደ መፍትሔ ነበር ያዩት፡፡ ፊውዳላዊው አገዛዝ በካፒታሊዝም ርዕዮተ ዓለም ውስጥ ሳያልፍ ወደ ሶሺያሊዝም ርዕዮተ ዓለም ገብቶ በፍጥነት ልማት የሚመጣበትን መንገድ መቀየስ ጀመሩ፡፡ ይኼ ደግሞ የሚሆነው የፊውዳሊዝምን አገዛዝ ካስወገዱ ብቻ ነበር፡፡ በተለይም ለዚህ ሁሉ መሠረት የሆነው የመሬት ጥያቄ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦምብ ነው ያዩት፡፡ በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች ይኼ የመሬት ጥያቄ ከብሔር ጥያቄ ጋር ተያይዞ በደቡብ ኢትዮጵያ ባሉ አካባቢዎች ከፍተኛ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ተማሪዎቹ ተገንዝበውታል፡፡ ‹‹መሬት ላራሹ›› የሚለው ጥያቄም እየታዩ ያሉትን ቀውሶችና ሊከተሉ የሚችሉ ከፍተኛ ብጥብጦች የአገሪቷን እንደ አገር የመቆም ህልውና ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳይከታት ለመመለስ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ እንደነ ዋለልኝ መኮንን ያሉ የተማሪዎች ንቅናቄ አራማጆች አንስተውት ነበር፡፡ የዘውዳዊው አገዛዝ የነበረውስ ፖሊሲ ምን ይመስላል?

ጆን ማርካኪስ፡– አፄ ኃይለ ሥላሴ የመዋሀድ ፖሊሲን ያራምዱ ነበር፡፡ የተለያዩ የብሔር ልዩነቶች ለአገሪቷ መረጋጋት ችግር ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ተረድተውታል፡፡ የባህል ውህደትን መፍጠርና በተመሳሳይ (በአንድ) ማንነት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አንድነትን መፍጠር ከጥንት ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ ሐሳብ ነው፡፡ የነበረውም ዕቅድ በተለያዩ አካባቢዎች ለምሳሌ በደቡብ አካባቢ የነበሩ ማኅበረሰቦችን የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ዕምነት ተከታይና አማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ በማድረግ በአንድ ባህል መዋጥ ነው፡፡ የነበረውም አገዛዝ ይኼንን የመዋጥ (አሲሚሌሽን) ፖሊሲ በከፍተኛ ግፊት ያራምድ ነበር፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ይኼ የመዋጥ ፖሊሲ የተሳካ ነው ለማለት ያስደፍራል፡፡ ምክንያቱም በቁጥር ብዙ የሆኑ ሰዎች ወደ ኦሮቶዶክስ ክርስቲያንነት ተቀየሩ የቦታ ስሞች ለምሳሌ አዳማ ወደ ናዝሬት ተቀየረ፡፡ የገዢውን ክፍል ለመቀላቀል ክርስቲያን መሆንና አማርኛ ማውራት እንደ ግዴታም ተወስዷል፡፡ ይኼ ፖሊሲ በሕዝቡ ዘንድ በጥልቀት ለመስረፅ ረዘም ያሉ ዓመታትን ይወስዳል፡፡ ይኼ የመዋጥ ፖሊሲም አልጋ ባልጋ አልሆነም፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡ ዋለልኝ አማራ ነበር፡፡ ነገር ግን ይኼ በግድ የመዋጥ (ፎርስድ አስሚሌሽን) ሐሳብን በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውሞታል፡፡ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ብቻ አልነበረም፡፡ በተጨማሪም የኦሮሞ ማኅበረሰብ ተቃውሞታል፡፡ በተለይ የሶማሌ ሕዝብ የመዋጥ ፖሊሲ ምን እንደሆነ በቅጥ አልተረዳውም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች በኤርትራ፣ በኦጋዴንና በባሌ የነበሩ የአመፅ እንቅስቃሴዎች ማዕከላዊውን ሥርዓት እያዳከሙት መጡ፡፡ በመጨረሻም ለመውደቂያው ምክንያት ሆኑ፡፡ ደርግ ሥልጣን እንደወሰደም ለእነዚህ ችግሮች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ሞክሯል፡፡ ወደ ተማሪዎች እንቅስቃሴ እንመለስና ተማሪዎቹ የማርክሲዝም ርዕዮተ ዓለምን የመረጡበትም ምክንያት ማርክሲዝም በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ሁሉንም ልዩነቶች በተለይም የብሔር ልዩነትን እኩል የሚያደርግና ሠራተኛውንና ገበሬውን አንድ የሚያደርግ ሥርዓት በመሆኑ ነው፡፡ የመደብ ጥያቄዎች እልባት ከተገኘላቸው የብሔር ጥያቄዎችም መፍትሔ ያገኛሉ ብለው ያምናል፡፡ ዋናው መመለስ ያለበት የመደብ ጥያቄ ነው ይሉ ነበር፡፡ ደርግም ይኼንን ርዕዮተ ዓለም ከተማሪዎች በመውሰድ ሠራተኛውን ገበሬውንና ሁሉንም ሕዝብ የሚከፋፍለው የመደብ በመሆኑ፣ የመደብ ጥያቄ መመለስ አለበት ለማለት ሐሳብ ማንፀባረቅ ጀመረ፡፡ ሌላው ከተማሪዎች ደርግ የወሰደው ሐሳብ መሬትን የጭሰኛ በማድረግ የገባር ሥርዓትን ማስወገድ ነው፡፡ መሬትን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር (ናሽናላይዝ) ማድረግን ነው፡፡ ደርግ በመሬት ላይ የወሰደው ዕርምጃ ኢትዮጵያን አንድ ዕርምጃ ወደፊት ያራመደ መሆን ይችል ነበር፡፡ ከዘውዳዊ የአገዛዝ ሥርዓት በመለየትም ኢትዮጵያ የኅብረ ብሔር አገር መሆኗንም በተወሰነ መልኩ ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ እ.ኤ.አ. በ1950ዎቹ በአሜሪካ ኮንግረስ ተገኝተው ኢትዮጵያ በሙስሊም አገሮች የተከበበች የክርስቲያን ደሴት ነች ብለው ግማሹ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሙስሊም በሆነበት ሁኔታ ተናግረዋል፡፡ የወታደራዊ አገዛዙም በቀደመው ሥርዓት የተደረጉ ስህተቶችን ፈጽሞ ለማስወገድ ተነስቶ ነበር፡፡ የቀደሙ ሥርዓቶችም ደርግም ይሁን አሁን ያለው መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ ያላደረጉት ቢኖር ሥልጣንን፣ እንዲሁም ሀብትን ከተለያዩ በአገሪቷ ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋር እኩል መከፋፈልን ነው፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ይኼንን አላደረጉም፡፡ ማሰብም አልቻሉም፡፡ ደርግም ሥልጣንና ሀብት የመከፋፈሉን ጉዳይ አላሰበበትም፡፡ በዚህም ምክንያት ከአፄው ሥርዓት በባሰ ሁኔታ ደርግ የተለያዩ አመፆችን፣ ቀውሶችንና ጦርነቶች በተለያዩ አካባቢዎች ማስተናገድ ጀመረ፡፡ በአዲሱ መጽሐፌ ‹‹ኢትዮጵያ ዘ ላስት ቱ ፍሮንቲየርስ) የፖለቲካ መስመር (ድንበር) ብዬ የምጠቅሰውም የሥልጣንና የሀብት ክፍፍልን በየአገሪቷ ጥግ (ፔሪፈሪ) ከሚኖሩ ሕዝቦች ጋር ተግባራዊ አለማድረጉን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሁለቱ መስመሮች (ድንበሮች) (ዘ ላስት ቱ ፍሮንቲየርስ) ምንድን ናቸው?

ጆን ማርካኪስ፡- የመጀመርያ መስመር ፖለቲካዊ ሲሆን፣ ይኼም ከጥንቷ አቢሲኒያ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ሥልጣንን በበላይነትና በብቸኝነት መቀራመት  ነው፡፡ ይኼ አስተዳደርም ሕዝቡ በጭቆና እንዲኖር፣ ከሥልጣን ክፍፍልም ሆነ ከሀብት አብዛኛውን የአገሪን ክፍል ያገለለበት ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ አገሪቷ ላለችበት አለመረጋጋትና ግጭቶችም መንስዔ ሆኗል፡፡ ሁለተኛው መስመር በአገሪቷ ድንበር አካባቢ የሚገኙት ከፊል በረሃማና ቆላማ ቦታዎች ኢትዮጵያ ከምትባለው አገር ጋር አለመዋሀዳቸውና ላለመዋሀድም የሚያደርጉት ትግል ነው፡፡ የፊውዳሉ የአገዛዝ ሥርዓት ከወደቀ በኋላ የወታደራዊ አገዛዝም በከፍተኛ ደረጃ ማዕከሉን ጠንካራ ያደረገ ነበር፡፡ የነበረው የተጠናከረ የወታደራዊ ኃይል በተለያዩ አካባቢዎች የተነሱትን የሽምቅ ኃይል ተዋጊዎች ለማንበርከክ አልቻለም፡፡ በተለይም የሕወሓትና የሻዕቢያ ትግል ሲፋፋም ወታደራዊውም ሥርዓት መፍረክረክ ጀመረ፡፡ ከነዚህ ሥርዓት መውደቅ በኋላም የኢሕአዴግ መንግሥትም በተለያዩ ሥርዓቶች የተሠሩ ስህተቶች እንዳይደገሙ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን በወሰደበት የመጀመርያዎቹ ዓመታት የተለያዩ የሽምቅ ተዋጊዎች በተለያዩ አካባቢዎች ነበሩ፡፡ ሥልጣንን በመከፋፈልና የተለያዩ ክልሎችን ማዕከል በማድረግ ብሔርን መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ቀረፁ፡፡ ይኼ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በአማራነት ማንነት መዋጥን መሠረት ያላደረገ ኢትዮጵያዊነትን ያስተዋወቀ ሥርዓት ነው፡፡ ማኅበረሰቦች ባህላቸውን እምነታቸውንና ማንነታቸውን ጠብቀው ዜጋ የሚሆኑበት አገር ለመፍጠር ተሞክሯል፡፡ ይህ ፌዴራሊዝም የክልል መንግሥታት ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት፣ የራሳቸውን ተወካዮች የሚመርጡበት፣ የራሳቸውን ቋንቋ የሚናገሩበትን፣ ወዘተ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ነገር ግን እንዳለፉት መንግሥታት የፖለቲካ መስመር ጥያቄውን መመለስ አልቻለም፡፡ ሥልጣን አሁንም በማዕከላዊው (በፌዴራል) መንግሥት ቁጥጥር ሥር ነው፡፡ ፌዴራል መንግሥቱ ይወስናል፡፡ የተለያዩ ክልሎች አስፈጻሚ ናቸው፡፡ ፌዴራል መንግሥቱ ሥልጣንንም ሆነ ሀብትን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ለመከፋፈልም ሆነ በጋራ ለመጠቀም ዝግጁ አይደለም፡፡ ይኼ አካሄድ ደግሞ ለሥርዓቱ ትልቅ ጠንቅ ነው፡፡ የአንድን አገር ህልውና ለመጠበቅ ኃይል ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ እንደ ቀድሞዎቹ መንግሥታት ኢሕአዴግም ተመሳሳይ ቀውስ ገጥሞታል፡፡ እንደ ቀደሙት መንግሥታትም እነዚህን ጥያቄዎች ከመመለስ ሠራዊቱን ችግሮቹን ለመፍታት ማሳተፍን መርጧል፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙዎቹ የደቡብ ግዛቶች ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በነበሩ ነገሥታት ይተዳደሩ ነበር፡፡ እነዚህን ግዛቶች የኢትዮጵያ አካል የማድረግ ስህተቶች ምንድን ናቸው?

ጆን ማርካሲስ፡- አቢሲኒያ ጥንታዊ፣ ተመሳሳይ ሕዝብና እሴት የነበራት አገር (ኔሽን ስቴት) ናት፡፡ ጥንታዊ እንደመሆኗ መጠን ለረዥም ዓመታት ደጋግሞ ከመታረስና ከአየር ንብረት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የእርሻ መሬት ችግር አጋጠማት፡፡ ከፍተኛ የመሬት ፍላጎት የመኖር ጥያቄ ሆነ፡፡ በዚህም ምክንያት በጠንካራ ወታደራዊ ኃይል በመታገዝ ወደ ተለያዩ አገሪቷ አካባቢዎች መስፋፋት ተጀመረ፡፡ ወደ ደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው የመስፋፋት ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡ የሰሜኑ ክፍል ሕዝብ በተለምዶ ነፍጠኛ ተብለው በሚጠሩት የተለያዩ የደቡባዊ የአገሪቷን ክፍል መቆጣጠር ቀጠለ፡፡ በነፍጣቸው (በመሣሪያቸው) እየታገዙ ሕዝቡን በኃይል ከመሬቱ አፈናቀሉት፡፡ መሬት ብቻ በቂ አልሆነም፡፡ ይኼ የመስፋፋት ተግባር የሠራተኛ ኃይል አስፈላጊው ነበር፡፡ በእዚህም ኢትዮጵያ የተለያዩ ግዛቶችና ሕዝቦች አገር (ኔሽን ስቴት) መሆን አቆመች፡፡ አቢሲኒያ የተስፋፋባቸው የተለያዩ ግዛቶች አቢሲኒያ አልነበሩም፡፡ አቢሲኒያውን አንድ እምነትና ተመሳሳይ ማኅበራዊ እሴቶች ያሉባት አገር ነበረች፡፡ የተለያዩ ሕዝቦች በኢትዮጵያ ውስጥ ሲካተቱ ኔሽን (ስቴት) የመሆኑም ሁኔታ ቆመ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በኃይል የተቀላቀሉት ሕዝቦች ደስተኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ የኢትዮጵያም ኅብረ ብሔራዊ ጉዞም በዚህ ተጀመረ፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የማዕከላዊ ሥርዓት አስተዳደር የተለያዩ ፖሊሲዎችን ያወጣል፡፡ ባላባቶቹ አስፈጻሚ ነበሩ፡፡ በደርግም ጊዜ በአካባቢ የነበሩ ካድሬዎቹ ከማዕከላዊ መንግሥት የሚመጣውን ማንኛውንም ውሳኔ አስፈጻሚ ሆኑ፡፡ ሥርዓቶች ቢቀያየሩም ሥልጣን የሚፈጸምበት መዋቅር አንድ ነው፡፡ የማዕከላዊው መንግሥት በተለያዩ አካባቢ የሚኖሩ ካድሬዎችን የሥርዓቱ አካል ያደረገውም ለብቻቸው ማስተዳደር ስላልቻለ ነው፡፡ በአካባቢው ያሉ ካድሬዎችም የሥርዓቱ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የኢሕአዴግ ሥርዓትም በአካባቢው ያሉ አስተዳዳሪዎችን የሥርዓቱ ተጠቃሚ በማድረግ ፖሊሲውን ለማስፈጸም ችሏል፡፡ በእኔ አስተያየት ይኼ የተረጋጋ ሥርዓት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በትክክለኛው መንገድ ውህደት የለም?

ጆን መርካኪስ፡- ፖለቲካዊ ውህደት በፍፁም የለም፡፡ በአገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕዝቦች እርስ በርስ ተዋህደዋል፡፡ ጋብቻ በመፍጠርና እርስ በርስ በመነጋገር በባህል ደረጃ ውህደት ተፈጥሯል፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ፖለቲካዊ ውህደትና መፍትሔ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የፖለቲካ መፍትሔው ምንድነው?

ጆን ማርካኪስ፡- የፌዴራሉ (የማዕከላዊ) መንግሥት ሥልጣንና ሀብትን በተለያዩ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሕዝቦች እኩል ማጋራት መቻል አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ቁጥር ያላቸውን ብሔሮችን መንግሥት ከሥልጣንና ከሀብት ማጋራት ውጪ ሊያደርግ አይችልም፡፡ ይኼ ምናልባት ከአምስት ክፍለ ዘመናት በፊት ሊደረግ ይችል ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን አይቻልም፡፡ ስለዴሞክራሲ አይደለም የማወራው፡፡ ነገር ግን ሕዝቦች ተወካዮቻቸውን የሚመርጡበት፣ ድምፃቸው የሚሰማበት የፖለቲካ ሥርዓት ሊዘረጋ ይገባል፡፡ ሕዝቦች ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበት፣ ሥልጣንንና ሀብትን የሚጋሩበት ሥርዓት መፍጠር ግዴታ ነው፡፡ ምንም እንኳን ይኼ መንግሥት ካቢኔውን በአዳዲስ ባለሥልጣናት ቢሞላም ሥልጣንና ሀብት ማጋራት ማለት ይኼ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የብሔርና የመደብ ጭቆናን ጥያቄ አስመልክቶ ማዕከላዊው አስተዳደር ሰሜኑን የኢትዮጵያን ክፍል ይመርጠዋል የሚሉ አካላት ሲኖሩ፣ ከዚህ በተቃራኒ ገዢው መደብ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል እኩል የመጨቆን ከሥልጣንም ሆነ ከሀብት ማጋራት ሁሉንም ሳይለይ በእኩል የነጠለ ነው ተብሎም ይታመናል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?

ጆን ማርካኪስ፡- የማዕከላዊ አገዛዝ ጭቆና የባህል የበላይነትን የማስፈን ሁኔታ የተተገበረው አስተዳደሩን በተቆጣጠረው የሐበሻው የገዢው የመደብ ክፍል ነበር፡፡ የሰሜኑ ጭቁን ገበሬ ከዚህ የበላይነት የሚጋራው በሐሳብ ወይም በመንፈስ ብቻ ነው፡፡ ነገር ግን የኢኮኖሚያዊ ሁኔታውን ብናይ የሰሜኑ ገበሬ ደሃ ነው፡፡ በተለይም ከደቡብ አካባቢ ካለው ገበሬ ጋር ሲነገፃፀር የነጣ ደሃ ነው፡፡ የደቡብ አካባቢ መሬት ለም ሲሆን፣ የሰሜኑ መሬት አስቸጋሪና ለብዙ ጊዜ የታረሰ በመሆኑ ለገበሬው አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይም በባለፉት አሥርት ዓመታት ወደኋላ ብንሄድ ጎጃም ወይም ትግራይ አካባቢ ምንም ዓይነት መሠረተ ልማቶች አልነበሩም፡፡ ስለዚህ ገበሬው ከነበሩት ሥርዓቶች ተጠቃሚ አልነበረም፡፡ ለዚህም ነው የተለያዩ ችግሮች እየተፈጠሩ ያሉት ትግራይን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን፡፡ አሁን የትግራይ ሕዝብ ምን እያለ ነው? ሕዝቡ ከዚህ ሥርዓት ተጠቃሚ ናቸው እያለ ይወቅሰዋል፡፡ እውነታው ግን ምንም የለውም፡፡ ለዚህም ነው በሥርዓቶች ተጠቃሚ የሚሆን ለሥርዓቱ ታማኝ የሆነው የገዢው መደብ ነው የምንለው፡፡ በኦሮሚያ ክልል ለሥርዓቱ ታማኝ የሆኑ የኢሕዴድ (ኢሕአዴግ) አባላት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ግን ሰፊውን የኦሮሞ ሕዝብ አይወክሉም፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ከየትም አካባቢ ቢመጡ ለሥርዓቱ ታማኝ የሆኑትን ሥርዓቱ ጠቅሟቸዋል ማለት ይቻላል?

ጆን ማርካኪስ፡- አዎ ማለት ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሰሜኑ ወይም ከቆላው ዝቅተኛ ቦታዎች የሚመጡ ቢሆኑም?

ጆን ማርካኪስ፡ የቆላማው ከፊል በረሃማ ዝቅተኛ አካባቢዎች በተለየ ዓይን መታየት ያለባቸው ናቸው፡፡ የዘውዳዊ የአገዛዝ ሥርዓት አካባቢውን ለመቆጣጠር ምንም ዓይነት ጫና አላደረገም፡፡ ምክንያቱም ይህ አካባቢ ምንም ዓይነት ተፈጥሯዊ ሀብት የለውም ተብሎ ስለታሰበ ነው፡፡  መሬቱም ከፊልና ሙሉ በሙሉ በረሃማ የሆነ አካባቢ ነው፡፡ ይኼ አካባቢ በዋነኝነት አርብቶ አደር የሚኖርበት ሲሆን፣ በገንዘብ ስለማይገበያይ ለረዥም ዘመናት ግብር አይከፍልም፡፡ በከፍተኛ ደረጃ የታጠቁ፣ ከቦታ ቦታ ድንበርን ጭምር አቋርጠው የሚሻገሩ አርብቶ አደሮች ናቸው፡፡ የሚተዳደሩት በራሳቸው ሕግ ሲሆን፣ የአካባቢው መሪዎችም ከማዕከላዊው መንግሥት ውጪ ያስተዳድሯቸዋል፡፡ ከአርብቶ አደሮቹም በተጨማሪም ከእጅ ወደ አፍ ግብርና የሚተዳደሩም ነዋሪዎች መሥፈሪያ ነው፡፡ እነዚህም መሬቱን አጥፍተው ቁጥቋጦዎቹን ቆርጠው አትክልቶች ይተክላሉ፡፡ መሬቱ ለም መሆኑን ሲያቆም ወደ ሌላ አካባቢ ይሰደዳሉ፡፡ የተውት መሬት ላይ እንደገና ተመልሰው መሬቱን ለማረስ ይሞክራሉ፡፡ ከቦታ ቦታ እየተመላለሱ ለዘመናት የተለያዩ መንግሥታት በራሳቸው እንዲንቀሳቀሱ ትተዋቸዋል፡፡ የደርግ መንግሥት በተወሰነ መልኩ ይኼንን ሕዝብ ከማዕከላዊው አስተዳደር ጋር ለማዋሀድ ሞክሯል፡፡ ነገር ግን በቂ ጊዜ አልነበረውም፡፡ በፖለቲካዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ መንገድ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር ለማዋሀድ አሥራ ሰባት ዓመት በቂ አልነበረም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ተጠናክሮ ይካሄድ የነበረው የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ በእነዚህ አካባቢ አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ መንግሥት የሚቆጣጠረው አካባቢ አልነበረም፡፡ ለመጀመርያ ጊዜም የኢሕአዴግ መንግሥት ይኼንን አካባቢ ለማዋሀድ እየሞከረ ነው፡፡ የተለያዩ የመንግሥት መዋቅሮች ፍርድ ቤቶች፣ የመሠረተ ልማት ማዕከላት፣ እንደ ትምህርት ቤት፣ የጤና ኬላዎች ተቋቁመው እየሠሩ ነው፡፡ ይኼ አካባቢ በከፍተኛ ሁኔታ ለግጭት የተጋለጠ በመሆኑ የተረጋጋ አይደለም፡፡ በዚህም በመንግሥት እየተደረጉ ያሉ የማዋሀድ ሙከራዎች ሙሉ በሙሉ አልተሳኩም፡፡ የፌዴራል መንግሥት እነዚህን አካባቢዎች አልተቆጣጠረም፡፡ አሁንም ግብር አይከፍሉም፡፡ ትክክለኛ ውህደት እንዲመጣ ሥልጣንና ሀብትን የሚጋሩበት ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- በብሔር ላይ የተመሠረተው የፌዴራሊዝም ሥርዓት ስህተት አለበት ወይ? ስህተቶቹስ ምንድን ናቸው? ሲጀመርስ ለኢትዮጵያ ትክክለኛ የአስተዳደር ሥርዓት ነው ወይ? የኢሕአዴግ መንግሥት እንደሚለው የተለያዩ ሕዝቦች ቋንቋና ባህል የሚከበርበትና እንደ አገር የሚዋሀዱበት ሥርዓት መፍጠር ነው ወይ? ይኼ ውህደት መጥቷል ብለው ያስባሉ?

ጆን ማርካኪስ፡- ኢሕአዴግ የተለያዩ ሕዝቦችን ዕውቅና በመስጠት ለማዋሀድ ሞክሯል፡፡ ጥያቄው የሚነሳው ማዕከላዊ መንግሥት ይወክለናል በሚሉ ሰሜነኞች ነው፡፡ ይኼ የኅብረተሰብ ክፍል ፌዴራሊዝም በአገሪቷ አንድነት ላይ ጥላሸት አጥልቷል ብለው ያምናል፡፡ እኔ ከኢትዮጵያ መገንጠል የሚፈልግ ማኅበረሰብ (ቡድን) አለ ብዬ አላምንም፡፡ ከኢትዮጵያ ተገንጥለው ወደ የት ሊሄዱ? የመገንጠል ጥያቄ ወይም የተለያዩ የብሔር ጥያቄዎችን እያነሱ ያሉ ማኅበረሰቦች ሥልጣንንና ሀብትን መጋራት፣ በመረጧቸው ሕዝብ መተዳደርን የመሳሰሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ መልስ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ያደረጋት ኢሕአዴግ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ያደረገው ነገር ቢኖር ለእነዚህ ሕዝቦች ዕውቅና መስጠትና በባህላቸው እንዲኮሩ ማበረታታት ነው፡፡ ይኼ የመገነጣጠል ፍራቻ የሚያቆመው ሥልጣንንና ሀብትን የመጋራት ጥያቄ ሲመለስ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በመጽሐፍዎ ማጠቃለያ ላይ የገበያው ሁኔታ የመሬትን ተፈላጊነት ዋጋ እየወሰነ የመጣ ኃይል እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ይኼ ደግሞ መሬት የመንግሥት ነው ከሚለው ሐሳብ ጋር ይጣረሳል፡፡ ይኼ እንዴት ሊሆን ቻለ?

ጆን ማርካኪስ፡- ወደኋላ ሄደን ታሪክን በምንመረምርበት ወቅት መሬት በጣም ጠቃሚና የሀብት እንዲሁም የተለያዩ እሴቶች አመንጪ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ጥያቄው የመሬት ተቆጣጣሪ ማን ነው? ከጥንት ጊዜ ጀምሮ መሬትን የሚቆጣጠረው መንግሥት ቢሆንም፣ የሰሜን አካባቢ ነዋሪዎች በመሬታቸው ላይ ጠንካራ መብት ነበራቸው፡፡ መሬትን ከአቢሲኒያ ገበሬዎች በጭራሽ መውሰድ አይቻልም፡፡ መሬታቸው የሚወሰደው ሲያምፁ ወይም ግብር መክፈል ሲያቆሙ ነው፡፡ መሬት በቤተሰብ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ርስት ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹አፅመ ርስት›› ተብሎ የሚጠራው፡፡ በዚህም ምክንያት መሬት ምንም ዓይነት ገበያ አልነበረውም፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ አገዛዝ የመጨረሻዎቹ ዓመታት የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሬት ወደ ግል ይዞታ እንዲዞር ከፍተኛ ጫና እያሳደሩ ነበር፡፡ አንዳንድ ሙከራዎችም በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ ታይተዋል፡፡ ደርግ መሬትን በአዋጅ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር አዋለው፡፡ ይኼ ማለት ገበሬዎቹ ማከራየት፣ መሸጥ ወይም ሰው መቅጠር አይችሉም ነበር፡፡ የገጠርን መሬት ለሕዝብ ለማድረግ የወጣው አዋጅ መንግሥት መሬትን በበላይነት እንዲቆጣጠር ያቀደ ባይሆንም፣ በተቃራኒው ደርግ ከዚህ የተለየ ሐሳብ ነበረው፡፡ በኢሕአዴግ አገዛዝ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ መሬት የመንግሥት ነው፡፡ በደርግ ከነበረው ሥርዓት የተቀየረ ነገር የለም፡፡ መሬትን መቆጣጠር ማለት ገበሬውን መቆጣጠር ማለት ነው፡፡ ይኼ ሐሳብ በተለያዩ መንግሥታት ባልተገባ ሁኔታ ተግባር ላይ ውሏል፡፡ የደርግ መንግሥት የተለያዩ የገበሬ ማኅበራትን፣ የመንግሥት እርሻዎችን በማቋቋም ገበሬውን አሰቃይቶታል፡፡ በኢሕአዴግም መንግሥት መሬት የመንግሥት ነው፡፡ በተለያዩ ልሂቃን አማካይነት መሬት ወደ ግል ይዞታ እንዲዘዋወር የሚያደርጉ ጫናዎች አሉ፡፡ መሬትን ወደ ግል ይዞታ ማዛወር ማለት በአገሪቷ ላይ ከፍተኛ ቀውስ እንዲመጣ መፍቀድ ነው፡፡ ምክንያቱም ከመሬታቸው ሊፈናቀሉ የሚችሉ ገበሬዎችን የሚሸከም የከተማ የኢኮኖሚ አቅም የለም፡፡ ትልልቅ ዘመናዊ እርሻዎች በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች እየተስፋፉ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የሚፈናቀሉ ገበሬዎች ወዴት ሊሄዱ ነው? የሚሉ ጥያቄዎች እየተነሱ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ወይም የቀድሞ ተቃዋሚዎች የሚጋጩ ሐሳቦችን ያነሱ ነበር፡፡ አንደኛው ቡድን ኢትዮጵያዊነትን ማዕከል ያደረገው የሐበሻው ቡድን፣ ፌዴራሊዝምን በፅኑ በመቃወም የጥንቱ ሥርዓት እንዲመጣ የሚፈልግ ነው፡፡ በሌላ በኩል እንደነ ዶ/ር መራራ ጉዲና፣ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስና የመሳሰሉት የሚወክሉት ማኅበረሰብ የበለጠ ፌዴራሊዝምና ሥልጣን መጋራትን ይፈልጋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ፍፁም ተቃራኒ ጉዳይ ነው የሚያወሱት፡፡ ለእነ ዶ/ር መረራ  መሬት ወደ ግል ይዞታ መዞር ያስፈራቸዋል፡፡ መሬት ወደ ግል ይዞታ መዞር የመጨረሻው መጥፎ ነገር ነው፡፡ ይኼም ሆነ ያ መሬት ወደ ግል ይዞታ መዞሩ አሁን በከፍተኛ ፍጥነት እየተካሄደ ነው፡፡፡ መሬት እየተሸጠና እየለወጠ ነው፡፡ የገበያውም ሁኔታ ለመሬት ሽያጩ ወሳኝ ሆኗል፡፡ በኦሮሚያ ያሉ ገበሬዎችም በከፍተኛ ሁኔታ እያማረሩ ያሉት ጥቂት ሺሕ ብሮች ካሳ ተከፍሏቸው፣ የተፈናቀሉበት መሬት አሁን በሚሊዮኖች ብር እየተቸበቸበ መሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– በኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት የማይታረቁ ሐሳቦች ያሏቸው ቡድኖች አሉ፡፡ አንደኛው ቡድን ፌዴራሊዝሙን የሚቃወም ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የተለያዩ የነፃ አውጪ ቡድኖችን የሚወክለውና ፌዴራሊዝሙ ትክክለኛውን የሥልጣን መጋራት እንዳልሰጣቸው የሚናገሩ ቡድን ናቸው፡፡ እነዚህን ሁለት የማይታረቁ ሐሳብ ያላቸውን ቡድኖች እንዴት አንድ ላይ ማምጣት ይቻላል?

ጆን ማርካኪስ፡- ኢሕአዴግ ኢትዮጵያን የመከፋፈልና የመገነጣጠል ሐሳብ አለው ብዬ አላምንም፡፡ በብሔር የተመሠረተ ፌዴራላዊዝምን ሲያመጡ አገሪቷን በአንድ ላይ የሚያስተዳደሩበት መንገድ ነው የቀየሱት፡፡ የተለያዩ ባህሎችን አንድ ላይ በማምጣት ቀድሞ የነበረውን የዜግነት ሐሳብ በመቀየር የማስተዳደሩን ሥልጣን በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ ሕዝቦች ሰጥተዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ግን የተደረገው ሕዝቡን ፀጥ ለማስባል እንጂ ሥልጣንን ለማጋራት አይደለም፡፡ ፌዴራሊዝሙ በኢሕአዴግ የተሰላ ጥረት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አስተዳደሩ ከሰሜን ክፍል የተውጣጣ ነው፡፡ ይኼ ሕዝብ ኢትዮጵያን ሊበታትን ነው የሚል ሐሳብ ማሰብም በጭራሽ አይቻልም፡፡ ይኼ ተልካሻ ሐሳብ ነው፡፡ እንዴት ነው የትግራይ ሰው ኢትዮጵያን ለመገንጠል የሚነሳው? በእኔ አስተሳሳብ ትግራዋይ አክራሪ ሐበሻና ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ስለዚህ ፌዴራሊዝሙ በተለያዩ የአገሪቷ ክልሎች ተነስተው የነበሩ ግጭቶችን ለማብረድና ማዕከላዊ አስተዳደር የተጠናከረበት፣ የተለያዩ ክልሎች ተንጠልጣይ ሆነው ፀጥ ብለው የሚጓዙበት ሥርዓት ለመገንባት ነው፡፡ ይኼንን ለመረዳት የተለያዩ ቡድኖች ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡ የተለያዩ ነፃ አውጪ ቡድኖች የመጡትም ይኼንን በመረዳት ነው፡፡ አሁን ዋናው ጥያቄ ይኼ የፖለቲካ ጥያቄ እንዴት ዕልባት ማግኘት ይችላል? የሚለው ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከዚህ ማጥ እንዴት መውጣት ይችላል? ወደፊት ቢቀጥል አገሪቷን ለመገነጣጠል ነው የሚለው ኃይል ያይልበታል፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ወደ ኋላ መመለስ አትችልም፡፡ ስለዚህ አጣብቂኝ ሁኔታ ላይ ነው ያለው ኢሕአዴግ፡፡ ችግሮቹን ከመፍታት በዘለለ የተለያዩ የውጭ ኃይሎች ጥያቄ ነው ማለት አያዋጣውም፡፡ ዘላቂ የሆነ መፍትሔ ለማምጣት ጥረት እያደረገ እንዳልሆነ ሊወሰድ ይችላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -