አቶ ግርማ አሸናፊ፣ ተሰናባቹ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፊል ሹም ሽሩን ታኅሣሥ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲያካሂድ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ግርማ አሸናፊ በዶ/ር ጀማል ኡመር የተተኩ ሲሆን፣ ይህን ቃለመጠይቅ ያደረግነው፣ የቀድሞው የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጀማል፣ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ኃላፊ ሆነው ከመሾማቸው አስቀድሞ ነው፡፡ አቶ ግርማ አሸናፊ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮን ላለፉት ሦስት ዓመታት መርተዋል፡፡ አዲስ አበባ ብዙ ነዋሪዎች ተጨናንቀው የሚኖሩባትና የሁሉም መናኸሪያ ከመሆኗ አንፃር ለተለያዩ የጤና እክሎች ስትጋለጥ ትስተዋላለች፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ቢሮው ምን እየሠራ ነው? በሚለው ዙሪያ ምሕረት ሞገስ አቶ ግርማን አነጋግራቸዋለች፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ ከሌሎች ክልሎች አንፃር፣ በጤና ሁኔታ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭ ስትሆን ትታያለች፡፡ የተጋላጭነቷን ስፋት ቢያብራሩልን?
አቶ ግርማ፡- ከሌሎች ክልሎች አንፃር አዲስ አበባ ስትታይ ለየት የሚያደርጓት ባህሪያት አሉ፡፡ አዲስ አበባ ባህሪዋ ሙሉ ለሙሉ ከተማ ነው፡፡ ስለሆነም በርካታ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውስብስብ ጉዳዮች አሉባት፡፡ ከአጠቃላይ ኅብረተሰቡ ሁኔታ ስትታይ በገቢም ቢሆን ከከፍተኛ እስከ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ኅብረተሰብ የሚኖርባት ናት፡፡ በአኗኗር ዘይቤም ሲታይ በርካታ ጉዳዮችን የምንቋደስባት ናት፡፡ የምንኖርባቸው አካባቢዎች ለሰው ልጆች ምቹ መሆን አለባቸው፡፡ ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ሲኖርም ጤናማ ኅብረተሰብ ይኖረናል፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ብዙው ኅብረተሰብ በጣም ተጠጋግቶ ይኖራል፡፡ ብዙ ነገር በጋራ ይጠቀማል፡፡ በጋራ የምንኖርበትን አካባቢ በጋራ የማናፀዳ ከሆነና የጋራ ግንዛቤ ከሌለ አካባቢውን ሊበክሉ የሚችሉ በርካታ ሁኔታዎች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህ የኅብረተሰቡ የአኗኗር ደረጃ፣ የገቢ ሁኔታ፣ የአካባቢ ጤና አጠባበቅ ለኅብረተሰቡ ጤና መጓደል ወይም መቃናት የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ከገጠር ለየት የሚያደርገው በርካታ ምክንያቶች ሲኖሩ፣ በከተማ መኖር ለሕክምና አገልግሎት በቀላሉ ተደራሽ መሆኑ መልካም ነው፡፡ ተደራሽነቱ ከገጠር ለየት ያለ ቢሆንም፣ በከተማ ውስጥ በጋራ ተጨናንቆ ትራንስፖርት መጠቀም፣ የምግብ አዘገጃጀትና አቀራረብና የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው በሙሉ ለኅብረተሰቡ ጤና መጓደል በቀላሉ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ ይህንን ስናይ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ በሆስፒታሎች የማስፋፊያ ሥራ ሲከናወን ጤና ጣቢያዎችም ወደ 96 ደርሰዋል፡፡ በቀደመው ጊዜ ከሞላ ጎደል ስናየው በአዲስ አበባ ከአገራችን የተሻለ የጤና አገልግሎት አለ ቢባልም፣ የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡት ግን የተወሰኑት ነበሩ፡፡ አንዳንዶቹ አንድ አንድ በሽታ ብቻ የሚያክሙ ነበሩ፡፡ ቁጥራቸውም ጥቂት ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- ሆስፒታሎቹ ጥቂት ቢሆኑም የሕዝቡም ቁጥር በኢትዮጵያ ደረጃ አሁን ካለው በግማሽ ያህል ያንስ ነበር፡፡ አሁን የሚሠሩት ይህንን የሕዝብ ቁጥር አማክለው አይደል?
አቶ ግርማ፡- አዎ፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 83 ዓ.ም. ላይ ከነበረበት በእጥፍ አካባቢ አድጓል፡፡ በተለይ ከየክልሉ ለሥራ ፍለጋና በኢኮኖሚ ችግር ወደ እየፈለሰ ከተማ የሚገባው የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡ በዚህ የተነሳ የጤና አገልግሎት ፍላጎቱ አዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ከተማ ውስጥ ያሉት ሆስፒታሎች የሚያገለግሉት የከተማውን ሕዝብ ብቻ አይደለም፡፡ የክልል ሕዝቦችም አዲሰ አበባ እየመጡ የጤና አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ አለ፡፡ በመሆኑም የከተማ አስተዳደሩ የጤና አገልግሎት ፍላጎቱ እያደገ በመምጣቱ በጥቂት ሆስፒታሎች ብቻ የነበሩ አገልግሎቶች በሁሉም ተደራሽ እንደሆኑ ለማድረግ ጥረት አድርጓል፡፡ ሁሉም ሆስፒታሎች የማስፋፊያ ግንባታዎች ተደርጎላቸዋል፡፡ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ወደ 500 ሚሊዮን ብር በመመደብ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ብቻ የነበሩት አገልግሎቶች በሁሉም ሆስፒታሎች ተደራሽ ለማድረግ ተሠርቷል፡፡
ሪፖርተር፡- በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተጨማሪ የሆስፒታል ግንባታዎች ታስበዋል፡፡ የመሠረት ድንጋይ የተቀጠላቸውም አሉ፡፡ ይህን ቢያብራሩልን?
አቶ ግርማ፡- በርካታ ሕዝብ በሚኖርባቸው ሦስት ክፍለ ከተሞች ሦስት ሆስፒታሎች ለመሥራት የዲዛይን ሥራው ከአንድ ዓመት በላይ ፈጅቶብናል፡፡ በኮልፌ ቀራንዮ፣ በላፍቶ ንፋስ ስልክና በቦሌ ክፍለ ከተሞች እጅግ ዘመናዊ ሆስፒታሎች ለማስገንባት ከአማካሪው ጋር እየተሠራ ነው፡፡ ዘመኑ የደረሰበትን የሆስፒታል ቴክኖሎጂ ተጠቅመን ለመገንባት በማቀዳችን ባሰብንበት ጊዜ ግንባታውን አልጀመርነውም፡፡ በቅርቡ ለመጀመር የሚያስችሉንን ቅድመ ዝግጅቶች ስላጠናቀቅን በቅርቡ እንጀምራለን፡፡
ሪፖርተር፡- የዳግማዊ ምኒልክ ማስፋፊያ አዲሱ ሆስፒታል ዘመናዊ ኦክስጅን ማስተላለፊያን ጨምሮ የተለያዩ ፋሲሊቲዎች ያሉት ነው፡፡ የአሁኑ ግንባታ ከዚህ የተለየ ይሆናል?
አቶ ግርማ፡- ምኒልክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሞከርነው ቢሆንም ፈተና ገጥሞናል፡፡ እስካሁን ኦክስጅኑ እየሠራ አይደለም፡፡ ኦክስጅኑ ሲገጠም የሚከታተሉት ባለሙያዎች በዘርፉ ዕውቀት ስላልነበራቸው ፈተና ገጥሞናል፡፡ ኦክስጅን የሚመረትበት ያስፈልጋል፣ የተመረተው ኦክስጅን ለእያንዳንዱ በሽተኛ ሊደርስ ይገባል፡፡ የአገራችን መሐንዲሶች ሌሎች ሕንፃዎችና በርካታ ግንባታዎች ሠርተው ሊሆን ይችላል፡፡ የሆስፒታል ግንባታ ግን የተለየ ነው፡፡ ምሕንድስናው ላይ የሕክምና ባለሙያዎችን ማሳተፍ ያስፈልጋል፡፡ የሆስፒታል ግንባታም ከሌላው የተለየ ነው፡፡ አዲስ የምንሠራቸው ሆስፒታሎች ላይ ይህ እንዳይገጥመን ከዲዛይን ጀምሮ ክለሳ አድርገናል፡፡ ለዚህም ነው ግንባታው የዘገየው፡፡
ሪፖርተር፡- የጤና ፖሊሲው በሽታን ቀድሞ መከላከል ላይ ያጠነጠነ ቢሆንም ከ60 – 80 በመቶ ለሚሆኑ በሽታዎች መንስኤ የሆነው የቆሻሻ አወጋገድ እንዲሁም የአካባቢና የግል ንፅህና ጉድለት አዲስ አበባን እየፈተናት ነው፡፡ እንደ ጤና ቢሮ ከምትሠሩት በተጨማሪ ቆሻሻን ከሚያስወግደው መንግሥታዊ አካል ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
አቶ ግርማ፡- የከተማችን የአካባቢ ጥበቃ ላይ ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል፡፡ ጤና ቢሮ በሽታን በመከላከል የሰው ልጆችን ንቃተ ህሊና ለማዳበርና ከዚህ በዘለለ በጤና ተቋማት እንዲታከሙ በሽታ የመከላከሉን ይሠራል፡፡ ፖሊሲያችን መሠረት ያደረገው ተላላፊውንም ተላላፊ ያልሆነውንም መከላከል ይቻላል በሚለው ላይ ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ትልቁ የጤና ችግር የአካባቢ ብክለት ነው፡፡ የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ከተማ ውስጥ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ኅብረተሰቡ እንዴት ቆሻሻ ማስወገድ እንዳለበት እያስተማረ ነው፡፡ ቤተሰብ ቆሻሻውን ከቤት ሲያወጣ ይህንን የሚያስወግድ አካል አለ፡፡ ፍሳሹንም እንዲሁ፡፡ በርካታ የዘርፍ መሥሪያ ቤቶች ነን በየዘርፉ የምንሠራው፡፡ በጋራ ባለመሥራታችን ብዙ ችግር እየገጠመን ነው፡፡ ለበርካታ ተላላፊ በሽታዎች ሊያጋልጡ የሚችሉ ጉዳዮች አሉ፡፡ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን የምንከተል ቢሆንም፣ ከተማው ውስጥ ከአየር ብክለት ጋር በተያያዘ ከየመኪናው የሚወጣው ጭስ ከመብዛቱ የተነሳ፣ የካርቦንዳይኦክሳይድ ልቀቱ የመተንፈሻ አካል ችግሮች እያስከተለ መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ አስም ከዚሁ ጐን ለጐን በየሆስፒታሉና በጤና ተቋማት የሚታከሙ ሕመምተኞች ምን ምን በሽታዎች አሉባቸው የሚለው በዩኒቨርሲቲዎች ይጠናል፡፡ እነዚህ ጥናቶች የሚያሳዩት ተላላፊ ከሆኑት ባላነሰ ሁኔታ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችም እንዳሉ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ተላላፊ ከሆኑት ባልተናነሰ ሁኔታ እየተስተዋሉ ከሆነ፣ የጤና ሥርዓቱ ለዚህ በሚያመች ሁኔታ የተዘረጋ ነው?
አቶ ግርማ፡- በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ይህንን ታሳቢ አድርገናል፡፡ ሆስፒታል ስንገነባ በሽታን ቀድሞ መከላከል እንጂ ሆስፒታል መገንባት ምን ያደርጋል የሚሉን አሉ፡፡ ነገር ግን ሆስፒታሎች በሽታን የመከላከል ሥራን ነው የሚሠሩት፡፡ ለምሳሌ የሳንባ በሽታን ማከም፣ መከላከልም ነው፡፡ ስለዚህ በሽታን መከላከል ያለ ጤና ተቋም አይቻልም፡፡ በመሆኑም በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የተደገፉ ምርመራዎችን ማድረግ የሚችሉ ተርሸሪ አገልግሎቶች መኖር አለባቸው፡፡ የሠለጠኑ የጤና ባለሙያዎችም ያስፈልጋሉ፡፡ ሆኖም በመሠረታዊነት በሽታን መከላከል ያለብን ሰው ታሞ ሳይሆን ሳይታመም ነው፡፡ ተላላፊ ያልሆኑትን በሽታዎች በአመጋገብ ሥርዓት፣ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የተመጣጠነ ምግብና የአልኮል መጠጥ ሥርዓት ላይ ኅብረተሰቡን በማስተማር መከላከል ይቻላል፡፡ ለካንሰር አጋላጭ ከሆኑ ነገሮች ኅብረተሰቡ እንዲቆጠብ በማድረግ መቀነስ ይቻላል፡፡ ተላላፊ የሆኑትንም ሆነ ያልሆኑትን በሽታዎች ሙሉ ለሙሉ መከላከል ባይቻልም መቀነስ ይቻላል፡፡ አገራችን ውስጥ የማህፀን በርና የጡት ካንሰር ከፍተኛ ችግር እየሆነ ነው፡፡ ችግሩ ሳይባባስ በየወቅቱ ምርመራ የሚደረግበት ሁኔታ ቢመቻች በቀላሉ በሽታውን ማቆም እንችላለን፡፡ በሽታን የመከላከልና ጤናን የማበልፀግ ሥራን ይዘን በከተማዋ 98 ጤና ጣቢያዎችና የፌዴራሎችን ጨምሮ 11 ሆስፒታሎች አሉ፡፡ ሆስፒታሎቹ በሙሉ በሥራቸው ያሉትን ጤና ጣቢያዎች እንዲደግፉ እናደርጋለን፡፡ ጤና ጣቢያዎች ደግሞ በሥራቸው ያለውን የወረዳ ሕዝብ በጤና ኤክስቴንሽን አማካይነት በመግባት፣ ሕክምና የሚፈልጉትን በቀጠናና በቤት በመለየት እየተሠራ ነው፡፡ ይህ ያስፈለገው የታመመ ሁሉ ወደ ጤና ጣቢያ ላይመጣ ስለሚችል እንዳደጉት አገሮች የግል ሐኪምና የግል ነርስ ባይኖርም፣ ሐኪም ነርስና ሌሎች የሕክምና ባለሙያዎች ያሉበት ቡድን ወደ ቤተሰብ እየሄደና በቤተሰብ ደረጃ ያለውን የጤና ችግር እየለየ ወደ ሕክምና ተቋም እንዲመጡ፣ እዚያው ቤታቸው መታከም የሚችሉትም እንዲታከሙ ከጤና ኤክስቴንሽን በዘለለ እየተሠራ ነው፡፡ በቤተሰብ ጤና ቡድን ኅብረተሰቡን ቤት ለቤት ለማከም በተለይ ተላላፊ ያልሆኑት ላይ ትኩረት ለመስጠት እየተሠራ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቤተሰብ ጤና ቡድን ወደ ቤተሰብ ገብቶ የማከሙ ሥራ በተወሰኑ ክፍለ ከተሞች በሚገኙ ወረዳዎች ተጀምሯል፡፡ ሙሉ ለሙሉ በከተማዋ የሚጀመረው መቼ ነው? ምን ዓይነት አካባቢዎች ቅድሚያ ያገኛሉ?
አቶ ግርማ፡- ገጠር ላይ በአብዛኛው ወጥ የሆነ አኗኗር አለ፡፡ በሀብትም ብዙም ልዩነት የለም፡፡ አኗኗሩ እንደ ከተማ የተፋፈገ ባለመሆኑ እንደ ከተማ ዓይነት የጤና ችግር የለም፡፡ በአዲስ አበባ በዓለም ከሚወዳደሩ ሀብታሞች ጀምሮ ጎዳና ላይ እስከሚያድረው ደሃ አለ፡፡ ስለሆነም ለዚህ የሚስማማ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ወደፊት መተግበር አለበት ብለን የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶች ዘርግተናል፡፡ ከስድስት ወራት በፊት በጉለሌ፣ በየካና በቦሌ ክፍለ ከተሞች የቤተሰብ ጤና ቡድን አገልግሎት መስጠት ጀምረናል፡፡ በዚህ ሁሉንም ቤተሰብ ለመድረስ የሚያስችል አመርቂ ውጤት አይተናል፡፡ በጣም በዝቅተኛ ደረጃ የሚኖሩትንና የጤናው ችግር በዚያው ልክ የጎላባቸውን፣ መካከለኛ ገቢ ኖሮት የከፋ የጤና ችግር የሌለበት ግን ተጋላጭ የሆነውን፣ ባለው ከፍተኛ ኢኮኖሚ የራሱን ሕክምና ድጋፍ የሚያደርግ ግን ምክር የሚፈልግ ስላለ የጤና ሥርዓቱ ይህንን መሠረት አድርጎ እንዲተገበር ይፈለጋል፡፡ አገልግሎቱን ለማስፋትና በዚህ ዓመት ከሦስት ክፍለ ከተሞች ወደ ሁሉም ለማካተት ወካይ ጥናት አድርገን ለመሥራት አቅደናል፡፡
ሪፖርተር፡- የጤና ጣቢያዎች ቁጥር በከተማዋ ቢጨምርም ሆስፒታሎች ውስጥ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶች ጤና ጣቢያዎች ውስጥ የሉም፡፡ ለጤና ጣቢያዎቹ በሙሉ የሚመጥን ባለሙያ አለ? አንዳንዶቹ ጤና ጣቢያዎች ብዙም ሰው ሳያስተናግዱ ሲውሉ አንዳንዶቹ ተጨናንቀው ይታያሉ፡፡ ጠቅላላ ሆስፒታል ከተደረጉትም የጴጥሮስ ሆስፒታል ቢታይ ተገልጋይ ብዙም የለውም፡፡ ይህ ከምን የመነጨ ነው?
አቶ ግርማ፡- አዲስ አበባ ውስጥ በፊት ጊዜ አንዳንድ ሆስፒታሎች አንድ በሽታ ብቻ የሚያክሙበት ሁኔታ ነበር፡፡ ሕዝቡ አሁንም ያንን ነው የሚያውቀው፡፡ ለምሳሌ ጴጥሮስ ሆስፒታል የሳንባ በሽታን ብቻ ያክም ነበር፡፡ አሁን በርካታ ግንባታ ተካሂዶ ጠቅላላ ሆስፒታል ሆኗል፡፡ ግን የማስተዋወቅ ሥራ ባለመሥራታችን ብዙ ሕዝብ እየተጠቀመበት አይደለም፡፡ ነገር ግን ዘመናዊና ከተማዋ ውስጥ ካሉ ሆስፒታሎች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚችል ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ አማኑኤል ወይም ጋንዲ ካልሆኑ በስተቀር ሁሉም ሆስፒታሎች ጠቅላላ አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ የአማኑኤልና የጋንዲ ሆስፒታሎችንም እያስፋፋን ስለሆነ ወደፊት ጠቅላላ አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ ከተማዋ ውስጥ ያሉት ሆስፒታሎች ውስን በመሆናቸው የሚሰጡት አገልግሎት ከአቅማቸው በላይ ነው፡፡ ስለሆነም ሆስፒታሎች ጤና ጣቢያዎችን እንዲደግፉ እየተሠራ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሆስፒታሎች የቀዶ ሕክምና መሥሪያቸውን ጤና ጣቢያ ላይ እንዲያደርጉ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ ጳውሎስ ሚሊኑየም ሜዲካል ኮሌጅ ይህንን ጀምሯል፡፡ ይህንን አሠራር ሆስፒታሎች በራሳቸው ጀምረውታል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም የጤና ጣቢያዎችን ደረጃ በማሻሻልና በቂ የሠለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት በጤና ዘርፍ ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት በዕቅዱ ተቀምጧል፡፡ መተግበሩ አለመተግበሩ የእኛ አቅም ቢሆንም፣ ጤና ጣቢያዎችም ልክ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲሰጡ ታስቧል፡፡ በማህፀን መውለድ የተቸገሩ በቀዶ ሕክምና እንዲወልዱ፣ መለስተኛ ቀዶ ሕክምና እንዲሠሩ፣ አስተኝተው እንዲያክሙ፣ የዓይን፣ የጆሮ፣ የጥርስና የአእምሮ ሕክምና እንዲሰጡ አደረጃጀቱን ቀይረናል፡፡ ነገር ግን ጤና ጣቢያዎችን ሆስፒታሎች ካልደገፉዋቸው ሁሉን በሽታ ለማከም የአቅም ውስንነት ይኖራል፡፡ ጤና ጣቢያዎች መሠረታዊ አገልግሎት በብዛት የሚሰጡት የእናቶች ጤና ላይ አትኩረው ነበር፡፡ የነፍሰጡር ክትትል፣ የቤተሰብ ዕቅድ፣ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን የሚያክሙ ጤና መኮንኖችና ነርሶች አሉ፡፡ ወደፊት እነዚህን በሁለተኛ ዲግሪ ለማሠልጠንና ሌሎች ሐኪሞችንም በጤና ጣቢያዎች ለመመደብ ታቅዷል፡፡
ሪፖርተር፡- የካንሰር ሕክምና አገልግሎት በመንግሥት ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውጭ አለመኖር ሌላው ችግር ነው፡፡ የካንሰር ሕክምናን እንደ ከተማ ተደራሽ ለማድረግ ምን ተጀምሯል?
አቶ ግርማ፡- ጳውሎስና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንዲሁም በ18 ጤና ጣቢያዎች በተለይ የካንሰር ቅድመ ምርመራው ላይ ትኩረት እንዲደረግ፣ ለሕክምናው ደግሞ በመንግሥት በኩል ጥቁር አንበሳ ብቻ ስለማይበቃ አስተዳደሩ ለካንሰር ሕክምና ብቻ አንድ ጤና ጣቢያ መድቧል፡፡ 20 ጤና ጣቢያዎች ተመርጠው አስፈላጊ ቅድመ ካንሰር መመርመሪያ መሣሪያዎች አሟልተናል፣ ባለሙያዎችም አሠልጥነናል፡፡ በዘላቂነት ከጥቁር አንበሳ ጋር በመሆን በመሠረታዊነት ሁሉም ጤና ጣቢያዎች ቅድመ የካንሰር ምርመራ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እየሠራን ነው፡፡ እንደ ከተማም ሕክምናውን በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ መስጠቱ ቅሬታ እያስነሳ ነው፡፡ ከካንሰር በተጨማሪም ከፍተኛ በጀት ተመድቦም ከዘውዲቱና ከጳውሎስ ሆስፒታሎች በተጨማሪ በምኒልክ ሆስፒታል የኩላሊት እጥበት ለመጀመር እየተሠራ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ወይም ተቆጣጥራቸው የጠፉ እንደ ዝሆኔ፣ ከቅማል ጋር የተያያዙ ተላላፊና ሌሎች በሽታዎች ዳግም እየታዩባት ነው፡፡ ይህ ከምን የመነጨ ነው? ከተማዋስ ለእነዚህም ምላሽ የሚሰጥ የጤና ሥርዓት ዘርግታለች?
አቶ ግርማ፡- ቁጥጥሩ አለ፡፡ ዋና ዋና የኅብረተሰብ ጤና አደጋ የሆኑትን የምንቆጣጠርበት የበሽታ ቅኝት ሥርዓት አለን፡፡ በእያንዳንዱ ወረዳም ሙያተኞች መድበናል፡፡ ለኅብረተሰብ ጤና አደጋ ከሆኑት ዋና ዋናዎቹ 20 በሽታዎች ተለይተው የምንከታተልበት ሥርዓት አለን፡፡ በመሆኑም የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች በየዕለቱ ሪፖርት የሚደረጉበት አሠራር አለ፡፡ ያልተለመደ በሽታ ሲከሰት ለምሳሌ አተት ሲከሰት ወዲያው ታውቋል፡፡ እኛም የምንከታተልበት ሥርዓትም አለ፣ ችግሩም በየጊዜው ይከሰታል፡፡ የአኗኗር ዘይቤያችን በጣም አስቸጋሪ በሆነበት፣ ሦስት በአራት በማይሞላ በአንድ ክፍል ውስጥ እስከ 40 ሰው የሚያድርበት፣ በትንሽ ክፍያ ተጨናንቀው አድረው ወደ ክልል ወይም እዚሁ ለሥራ የሚወጡ ሰዎች ባሉበት ሁኔታ ተላላፊ በሽታዎች ይኖራሉ፡፡ በተለይ ከቅማል ጋር ተያይዞ የትኩሳት ግርሻ ብዙ ጊዜ ይከሰታል፡፡ ታይፎይድም በከፍተኛ ሁኔታ እየተከሰተ ነው፡፡ አዲስ ከተማ፣ አራዳ ላይ ይከሰታል፡፡ ቀድሞ መከላከል ዋናው ቢሆንም፣ የእኛ ባለሙያዎች ደርሰው የሚያክሙት ችግሩ ከተከሰተ በኋላ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህንን የሚከላከል ሥርዓት የለንም?
አቶ ግርማ፡- መደበኛውን ኅብረተሰብ ቤት ለቤት በመሄድ በማስተማር የግልና አካባቢ ንፅህናውን እንዲጠብቅ በመድረስ ቀድሞ በሽታን እንዲከላከል ማድረግ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ከተማ ውስጥ ከአቅም በላይ የሆነብን ችግር ለተለያየ ሥራ ከተማ ውስጥ በጎዳናና ባልተስተካከለ የኑሮ ሁኔታ የሚኖሩትን መድረስ ነው፡፡ በከተማዋ በርካታ ሰዎች በየሥርቻውና በሕገወጥ ቤት ውስጥ እንደሚኖሩ ታዝበናል፡፡ ይህ ለበርካታ በሽታ መንስኤም ነው፡፡ በጎዳና የሚኖሩትንም፣ ደረጃውን ባልጠበቀ ቤት ውስጥ ያሉትንም ከማስተማር የዘለለ ብዙም አቅም የለንም፡፡ ውኃና መፀዳጃ እንዲኖራቸው ከሚመለከተው አካል ጋር መሥራት ነው፡፡ በአጠቃላይ የከተማው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ሲቀየር ብቻ ነው ለውጥ ማምጣት የሚቻለው፡፡ ከጎዳና ጀምሮ ሰዎች ሲታመሙ ግን ነፃ ሕክምና እንዲያገኙ እየሠራን ነው፡፡ በጎዳና የሚኖሩ በርካቶች እንዲታከሙ፣ ወደ ክልላቸው እንዲመለሱ፣ ሥራ መሥራት የሚችሉት እንዲሠሩ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን በየቀኑ ከተማ ውስጥ የሚገባ ሰው በርካታ ከመሆኑ የተነሳ የአዲስ አበባን የጤና ችግር ለመፍታት በጣም ከባድ ነው፡፡ በሁሉም የከተማዋ አካባቢ የግልና የአካባቢ ንፅህናን ካላስጠበቅን፣ ውኃና መፀዳጃ ካልገባ፣ የፍሳሽ ማስወገጃዎች ሥርዓት ካልያዙ፣ ውኃና መፀዳጃ በማያገኙ አካባቢዎች መሠረታዊ ኑሮን መቀየር ካልቻልን ጤና የሚባል ነገር አይረጋገጥም፡፡