– በቀን አንድ ሚሊዮን ዶላር ማስገኘት የሚችል አቅም እንዳለው ተገልጿል
የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በዝዋይ ከተማ፣ አዳሚ ቱሉ፣ ሞጆና ዱከም የሚገኙ ስድስት የበግ፣ የፍየልና የዳልጋ ከብት ማደለቢያና ቄራዎች እንዲሁም የተረፈ ምርት ማቀነባበሪያዎችን ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን አስጎብኝቶ ነበር፡፡ ከተጎበኙት መካከል በህንዳውያን ባለሀብቶች የተገነባውና የአላና ግሩፕ ኩባንያ አካል የሆነው ዘመናዊ ቄራና የተረፈ ምርቶች ማቀነባበሪያ አንዱ ነው፡፡
አቶ ግደይ ገብረ መድኅን፣ የአላና ፍሪጎሪፊኮ ቦራን ፉድስ ኩባንያ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ስለ ኤክስፖርት ቄራው ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹ይህ ኤክስፖርት ቄራ መሠረቱን ህንድ ያደረገና በዓለም ከ80 በሚበልጡ አገሮች ኤክስፖርት በማድረግ 2.2 ቢሊዮን ዶላር በዓመት የሚያንቀሳቅስ ሲሆን፣ በአፍሪካ የመጀመሪያውን ኤክስፖርት ቄራ በኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ግንባታውን አጠናቆ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል፤›› ብለዋል፡፡
አላና ግሩፕ በኢትዮጵያ የገነባው ፋብሪካ ሙሉ ለሙሉ በህንድ ከሚገኘው ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ግንባታውን የጀመረው እ.ኤ.አ. በ2015 ጥር ወር ነበር፡፡ በ75 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ኢንቨስትመንቱን የጀመረው ይኸው ኩባንያ፣ በዝዋይ አዳሚ ቱሉ አካባቢ በ75 ሔክታር መሬት በመረከብ ፋብሪካውን ገንብቷል፡፡ ኤክስፖርት ቄራው በቀን 3000 ሺሕ ዳልጋ ከብቶችን፣ ከአምስት እስከ ስድስት ሺሕ የሚደርሱ በግና ፍየሎችን ለእርድ እንደሚያውል ታውቋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ፋብሪካው ከራሱ ባሻገር የሌሎች ፋብሪካዎችን ምርቶች በመቀበል በተከላቸው የደምና የአጥንት ተረፈ ምርቶች ማቀነባበሪያዎች አማካይነት 80 ኩንታል አጥንት እንዲሁም 40 ኩንታል የደም ተረፈ ምርት የሚያቀነባብር ማሽን የተገጠመለት ሲሆን፣ የተቀነባበሩት ተረፈ ምርቶችም ለዶሮ መኖነትና ለዓሣ ምግብነት ይውላሉ ተብሏል፡፡
በፋብሪካው ከተተከሉት መሣሪያዎች አንዱ ከእንስሳቱ የሚወጣውን ፈርስ በማድረቅ ለኢነርጂ ምንጭነት እንዲውል የሚያስችል ምርት የሚያስገኘው ነው፡፡ ይህም ተረፈ ምርት ለኤክስፖርት ገበያ የሚውል ነው፡፡ በአንድ ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተሠራው ፍሳሽ ማስወገጃ ፋብሪካው ጥቅም ላይ ያዋለውን ውኃ አጣርቶ መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል ከማድረግ ባሻገር፣ ምንም ዓይነት የአካባቢ ብክለት እንዳይፈጠር ለመከለከል የሚያስችል ሥርዓት መሆኑን ኃላፊዎቹ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ኃይለ ሥላሴ ወረስ የኢትዮጵያ ሥጋና ወተት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንዱስትሪውን በሚመለከት ለሪፖርተር በሰጡት መግለጫ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን 11 ቄራዎች ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ቄራዎቹ ባለፈው ዓመት ኤክስፖርት ካደረጉት ምርት 102 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህም ከዘርፉ እንዲገኝ ከታቀደው ውስጥ 70 በመቶ የተከናወነበት ነው፡፡ ‹‹ዘንድሮ 157 ሚሊዮን ዶላር ለማስገባት ያቀድን ሲሆን፣ ባለፉት በአምስት ወራት 39.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ቀሪውን አላናን ጨምሮ ሦስት የኤክስፖርት ቄራዎች በቅርቡ ወደ ሥራ ስለሚገቡና ወደ ሳዑዲም መላክ ስለምንጀምር ዕቅዱ ሙሉ ለሙሉ ይሳካል ብለን እንገምታለን፤›› በማለት የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹አላናን ብቻውን ብንመለከት እንኳ ለግንባታ የሚውለውን 75 ሚሊዮን ዶላር ከራሱ ምንጮች ነው ያመጣው፡፡ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በቀን እስከ አንድ ሚሊዮን ዶላር ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሆኖም ከዶላሩ በላይ በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ የሚለው አገላለጽ በሥጋ ምርት ኤክፖርት አንደኛ በሚለው ይቀይርልናል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ‹‹በመንግሥት በኩል መሬት በሊዝ ከማቅረብ ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲያገኝ፣ 194 ኮንቴይነር ሙሉ ማሽነሪዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ እገዛ ተደርጎለታል፡፡ በቅርቡም አካባቢው ምንም ዓይነት የኢንተርኔት አገልግሎት የሌለው በመሆኑ ሥራ ከመጀመሩ በፊት እንዲገባለትና የንፁህ ውኃ አቅርቦት እንዲያገኝ ኢንስቲትዩቱ ከኦሮሚያ ክልል ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝ ያብራሩት አቶ ኃይለ ሥላሴ፣ አላና ቄራ ሥራ ሲጀምር የቁም እንስሳት ንግዱንና የእርድ አገልግሎቱን እንዲሁም በሌሎች ቄራዎች የሚታየውን የተረፈ ምርት አወጋገድ ሥርዓትን ከመሠረቱ ይቀይረዋል በማለት ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡
አቶ ግደይ የምርት አቅርቦቱን ከየት እንደሚያኙት ለሪፖርተር ሲያብራሩም፣ ፋብሪካው 90 በመቶ የተቀነባበረና አሥር በመቶ ጥሬ ሥጋ ለ80 አገሮች እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ይህም የተገነባው ፋብሪካ የአገሮቹን የጤና ጥበቃዎችና ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን በማሟላት እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ ‹‹የጤና ችግር ከሌለባቸው በስተቀር በአሁን ወቅት እየሰበሰብን የምንገኘው ከአፋርና ከሶማሌ ክልል እንዲሁም ከቦረና አካባቢ ነው፡፡ እርግጥ እነዚህ አካባቢዎች ብዛት እንጂ ጥራት ላይ ትኩረት ስለማያደርጉ ወደፊት ሥልጠናና ምክር በመስጠት ከአቅራቢዎች ጋር ለመሥራት ዕቅድ ተይዟል፡፡ የመሬት ጥያቄው ከተመለሰልን ደግሞ በአቅራቢያችን ነጋዴዎች እያመጡልን እንረከባለን ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ በፋብሪካው ከከብት ማስገቢያው ጀምሮ ፕሮሰስ ተደርጎ በካርቶን ታሽጎ ከግቢው እስከሚወጣ ያለው ሒደትና የንፅህና ሁኔታ በዶክተሮች የሚመራ ጥብቅ ክትትል ይደረግበታል፡፡ ለዚሁ ጉዳይ ብቻ የሚውል ላቦራቶሪ ተገንብቷል፡፡ ፋብሪካው ሙሉ ለሙሉ ኮምፒውተራይዝድ ማቀዝቀዣ ተገጥሞለታል፡፡ ፍሳሽ በምንም መልኩ ከግቢው አይለቀቅም፡፡ እዛው ይጣራል፡፡ የሠራተኛ አያያዝና ለአካባቢው ኅብረተሰብ የሚሰጠው ተጠቃሚነትም ተጠቃሽ ነው፡፡ ፋብሪካው በጊዜያዊነት 1500 ሠራተኞች ያሉ ሲሆን፣ ሙሉ በሙሉ ሥራ ሲጀምር 300 ሺሕ ሠራተኞች ይኖሩታል ተብሏል፡፡ ለእነዚህ ሠራተኞች የጤናና የሥራ ላይ ደኅንነትን ማረጋገጥ ግዴታችን ነው ያሉት የፋብሪካው ኃላፊ፣ ለአካባቢው ኅብረተሰብም ህንድ ላይ እንዳለው ፋብሪካ ሁሉ ደም ፕሮሰስ በማድረግ የሚገኘውን ሽያጭ ሙሉ በሙሉ ኅብረተሰቡ እንዲጠቀምበት ይደረጋል ብለዋል፡፡ ለአካባቢው ነዋሪዎች የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እየገነባ እንደሚገኝም አክለው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቁም እንስሳት አቅርቦት ችግር እንደሌለ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በአንፃሩ የኤክስፖርት ቄራዎች የግብዓት ዕጥረት እንዳለባቸው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኃይለ ሥላሴ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት ችግሩ እንዳለ አምነው፣ የአቅርቦት እጥረቱን ለመቅረፍ በቅርቡ የወጣው የቁም እንስሰት ንግድ አዋጅ ከፌዴራል እስከ ክልል ድረስ እንደሚተገበርና አሁን እየተካሄደ ያለው ሕገወጥ ንግድን ጨምሮ በዘርፉ ያሉ ሌሎች በርካታ ችግሮች እንደሚቀረፉ ጠቅሰዋል፡፡ ሆኖም ፋብሪካዎቹ የግብዓት ዕጥረት ካጋጠማቸው ወደ ውጭ የሚላከውን የቁም እንስሳት ንግድ እስከ ማስቆም ልንሄድ እንችላለን ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ከጥቂት ቀናት በኋላ ሥራ እንደሚጀምርና ወደ ኤክስፖርት እንደሚገባ የሚጠበቀው ጂግጂጋ ኤክስፖርት ቄራ ፋብሪካም በ200 ሚሊዮን ብር ሲያካሂድ የቆየውን ግንባታ ማጠናቀቁን ይፋ አድርጓል፡፡ በ35 ሔክታር መሬት ላይ የተንሠራፋውና በሶማሌ ክልል የተገነባው ይህ የኤክስፖርት ቄራ፣ ምርቱን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች እንደሚልክ ይጠበቃል፡፡