Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መተንፈስ ሲናፍቅ!

እነሆ መንገድ ከመብራት ኃይል ወደ ቦሌ ልንጓዝ ነው። አንድ ጎልማሳ ጋቢና ገብቶ ከመቀመጡ፣ “ምንድነው እንዲህ ኳስ አበደች ብሎ አብሮ ማበድ? ጭራሽ እየባሰብን ይሄዳል?” ይላል። “ከማን ጋር ነው የሚነጋገረው?” ትለኛለች ከጎኔ የተቀመጠች  ሽቅርቅር። ይኼኔ ሌላ ተሳፋሪ የጋቢናውን በር ከፍቶ ገባ። “ጉድ እኮ ነው፤” ይላል ሰሚ ያጣው ጎልማሳ። “ምኑ?” አለው አዲስ ገቢው። “በቃ እኮ ሥራ የሚሠራ ሰው የለም። ሰኞ ኳስ ነው። ማክሰኞ ኳስ ነው። ረቡዕ፣ ሐሙስ፣ ዓርብ፣ ቅዳሜ፣ እሑድ ኳስ. . . ልክ እንደ ማርክስሲዝም ሌኒኒዝም ፍልስፍና ከእኛ በላይ ላሳር የሚሉን የስፖርት ጋዜጠኞችም ተንትነውት ውለው ተንትነውት ሲያድሩ ተዓምር ያስመስሉታል። ጉድ እኮ ነው፤” ብሎ ዝም አለ ሲባል፣ “ደግሞ እኮ እኔን በጣም የሚገርመኝ ይኼ አሁን ከተማ ከተማ እያሉ አዲስ አበባን ያተራመሱዋት የጉልበት ሠራተኞች የለም? እነሱ ሳይቀሩ ለሥራ ብለው ከተማ ገብተው ‘ዲኤስቲቪ’ ቤቶችን አጨናንቀው መዋል ሆነ ሥራቸው። ምንድነው? ስትላቸው ‹እርፍና ነው› ይሉሃል። አራዳን የተካች የዘመኑ ቃል መሆኗ እኮ ነው። አሁን እኛ ማን ይሙት በየመንገዱ የምንፀዳዳ ሰዎች፣ እንኳን ኳስ መጫወቻ ንፋስ መቀበያ ሥፍራ በሕንፃ ግንባታ ግርግር የተነፈግን ሰዎች፣ የእንግሊዝ ሜዳና ኳስ ምናችን ነው?” እያለ ተንጣጣ።

“ማነህ ተረጋጋ እንጂ። የሐሳብ ብዝኃነትና ፍላጎትን ያከበረ ንግግር አይደለም የምትናገረው። ይኼ አንዱ የከተማ ዕድገትና ስፋት ውጤት ነው። ከተማ ሲሰፋና ሲለጠጥ እንዲሁ የነዋሪዎቹ ፍላጎት መዋያና መዝነኛም እየሰፋና እየተለያየ ይሄዳል። አይደለም እንዴ?” እያለ ሌላውን ተሳፋሪ ጭምር ሲያሳድምበት ሌላው ተቀብሎ፣ “ይቀልዳል እንዴ በእንግሊዝ ክለቦች ደረጃ መበላለጥ የምንከታተለው እኮ ወደን አይደለም። የእኛን የኑሮ ደረጃ ልዩነት ስፋት ለመርሳት መሆኑን አያርፍም እንዴ?” ይለዋል። ይኼኔ ጎልማሳው ፀጥ አለ። ወይ ኑሮና ሰንጠረዡ አያስብልም?

ጉዞው ተጀምሯል። ወያላው በየመንገዱ፣ “ግቡ ውኃ ልማትም ይሄዳል!” እያለ ሦስት ወጣቶችን ያባብላል። “ቦሌዎችን ጠበቅ አድርግ እንጂ! ምን ሆኗል ይኼ? ዋናው የቦሌ ሰው ነው!” ብሎ ሾፌሩ ምክር አስመስሎ ለወያላው ውስጠ ወይራ ንግግር ይናገራል። ተሳፋሪው ፈገግ እያለ ተደርበው ለሚቀመጡ ትርፍ ተሳፋሪዎች ይጠጋጋል፡፡ “ይኼ ሰውዬ የወያላነት ፍቅሩን ሳይጨርስ ነው ሾፌር የሆነው ማለት ነው? ምናለበት በሰው ሥራ ጥልቅ ባይል? የገዛ ኃላፊነታቸውን ሳይወጡ በሰው ኃላፊነት ጥልቅ የሚሉ አልበዙባችሁም?” ይላል አንዱ ሾፌሩን ሲቁነጠነጥ እያየው። “ዘንድሮ መቼ የሚያልቅ ፍቅር አለ? በተለይ የእኩይ ተግባርን ውሎ በቀላሉ አይገላገሉትም እኮ፤” ትላለች ሦስተኛ ወንበር ላይ ያለች ወይዘሮ። በዚህ መሀል አንድ መንገደኛ ጠጋ ብሎ፣  “ቦሌ?” ብሎ ጠየቀ። ሾፌሩ፣ “ግባ አሜሪካም ይሄዳል አንተ ካልክ!” ብሎ አዲስ የጨዋታ ርዕስ ቀሰቀሰ።

“እንዴት ነው ነገሩ? አሜሪካ እንዲህ እንደ ቀልድ በታክሲ መብረር ተጀመረ እንዴ?” ሲል ከኋላ መቀመጫ ያለ ወጣት ፀጉሩን እያፍተለተለ ጠየቀ። “ታዲያስ! ሰው በእግሩ እየገባ አይደለም እንዴ እንኳን በታክሲ?” ብሎ ሾፌሩ ሳቀ። “ኧረ እውነትህን ነው! ዘንድሮ በዕድልም በአጋጣሚም ሄደ ሲባል የማንሰማው የለም። የሕገወጥ ስደቱ ዜና ከልማት ዜናዎች ቀጥሎ ቁጥሩ በዝቷል። የመንደሩ ወሬ ሳይቀር እከሌ እኮ ‘ስቴት’ ገባ ሆኗል፤” ስትል ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠች፣ “በዚህ ዓይነት የሚቀር ያለ አይመስለኝም። የሚሻለው  ግን. . .፤” ብሎ ሳይጨርሰው ከልጅቷ አጠገብ የተቀመጠ ጎልማሳ በእንጥልጥል ተወው። “የሚሻለው ምን?” ሲል አንዱ አጥብቆ ጠየቀው። “የሚሻለውማ መንግሥት እንደ ቤቱ ሁሉ የትኬትና የኮቴ የምንከፍለውን እየቆጠብን እንድናጠራቅም መርዳት አለበት፤” ብሎ አረፈው። “ወይ እናት ኢትዮጵያ! እንኳንም አልሰማሽ የምትባይውን?” ሲል ከኋላ መቀመጫ፣ “የት ሄዳ ነው የማትሰማው ደግሞ?” ብለን ጠይቅነው። መልሱን መገመት ስንችል መጠየቃችን በኋላ ቆጨን!

መሀል መቀመጫ ሦስት ተጠጋግተው የተቀመጡ ወጣቶች ጨዋታ (እንደ ዕሜያቸው ሃያዎቹ መጀመርያ የሚሆን) ታክሲዋን ገዝቷታል። “አንተ ግን በምን ፍጥነት ከመርካቶ እዚህ ድረስ መጣህ? የታክሲን ችግር የምናማርረው ውሸት ነው ማለት ነው?” ይለዋል። “ኧረ ተወኝ፣ ቀጭ ቀጭ እናድርግ (እንቃም) ስትሉኝ ክንፍ አውጥቼ ነው እንጂ ደግሞ የትራንስፖርት ነገር ይወራል እንዴ?” ሲል ይመልሳል። “ይኼኔ ለሥራ ቢሉህ የሚያደናቅፍህ መቀነት ብዛቱ?” ሲል ሦስተኛው ፊት ለፊቱ ሆኖ ይነግረዋል። “ከማውራት የበለጠ እሺ አሁን እዚህ አገር ሥራ አለ ነው የምትለኝ? ሁሉም ማውራት ትቶ ዝም ብሎ ቢሠራ የለመደችው ሲቀርባት አገራችን እንዴት ሊከፋት እንደሚችል ትንሽ አታስብም? እንዲያው በፈጠረህ ወሬ ነው እንጂ ቀጥ አድርጎ ይዞን ያለው እንጂ የትኛው የተደላደለ ኑሯችን ነው?” ሲል ኮስተር ብሎ ከመርካቶ የመጣው ይመልሳል። ተሳፋሪዎች አንገታቸውን እያወዛወዙ ይስቃሉል። አኳኋናቸው ሁሉ የሚመስጥ ነው።

ወያላው ድንገት ወደ እነሱ ዞር ብሎ፣ “እሺ ሒሳብ!” አላቸው። ሁለቱ እንደተማረከ ወታደር እጆቻቸውን ከፍ አድርገው ወደ ሦስተኛው ጓደኛቸው ጠቆሙ። ወያላው እየሳቀ የሦስት ሰው ሒሳብ ሲቀበል፣ ‹‹በነካ እጅህ ለሁለት ወር ቁጠባ የምትሆን ጣል ብታደርግልን ደግሞ ሌላ አናስቸግርም ነበር፤” ብሎ ወሬ ነው ቀጥ አድርጎ የያዘን ባዩ ከፋይ ጓደኛውን ይለማመጣል። ተሳፋሪዎች በእነዚህ ብላቴናዎች ሕይወት ቀዳዳ የትውልዱን አቅጣጫና ሕይወት ለመተለም ይጣጣራሉ። ለግምትም ለጥርጣሬም የሚያስቸግር ጊዜ ከፊቱ እየታየው አንገቱን የማይነቀንቅ ከሦስቱ በስተቀር ማንም አልነበረም። ቁጭ ብሎ መብላት የለመደ ሁሉ የቀረበት ቀን የሚሆነውን አለማየት ይሻላል!

“ወራጅ!” አሉ አፍታ እንደሄድን ሦስቱ ወጣቶች። ታክሲያችን እነሱን ለማውረድ ው    ኃ ልማት አካባቢ ቆማለች። ወርደው ውስጥ ለውስጥ ጥቂት እንደተጓዙ  ከዓይናችን ጠፉ። ሾፌሩ፣ “ኧረ ሊገጨኝ ነው እያየህ በለው፤” ይላል ከፊታችን ወደ ኋላ የሚያሽከረክር ላዳ ታክሲ እየጠቆመ። “ሕግ የሚባል የለም በቃ?” ይላል ከሾፈሩ አጠገብ የተቀመጠው የሾፌሩን ሁኔታ እየታዘበ። “አቦ እረፍ። የኃይል ዕርምጃ ልትጠራብን ነው እንዴ? ፅድቁ ቀርቶብኝ በቅጡ በኮነነኝ አሉ፤” ይመልሳል  ጋቢና የተቀመጠው። ሾፌሩ፣ “ምናለበት ‘ስፖኬውን’ ቢያቃናውና የኋላውን ቢያይበት? ንገረው እስኪ! እንዲያው የዘንድሮ ሰው የኋላውን ማየት የሚባል ነገር ጠልቷል፤” ይላል። “በጣም! የኋላውን ማየት ጠልቷል ብቻ?” ትላለች ወይዘሮዋ አባባሏን እንደ ማስቲካ እያላመጠች። “እነሱ ነፍስ ካወቁ በኋላ ያለውን እንጂ ከዚያ በፊት ያለን ታሪክ እንደሆነ በጭራሽ የሚሉ በዝተዋል። ‘ስፖኬያቸውን’ ሰብረው ልቦናቸውን አሳውረው የአገርን ህልውና ካስማውን ነቅሎ ለመጣል የሚመኙ በጣም ነው የበዙት፤” ትላለች እየቆየች። የምትናገረው ለእሷ ብቻ የሚገባ ይመስላል። ላዳ ታክሲው በፈጠረው የመንገድ መጨናነቅና በተፈጠረው ትዕይንት ቀልባችን ተሰርቋል።

ወያላው  ከኋላ መቀመጫ ከጫናቸው ተሳፋሪዎች ጋር ሲጨቃጨቅ ይሰማል። “ለምን አትጠጉም? ከኋላ እኮ አራት ነው. . .” ይላል እየደጋገመ። እያጉረመረሙ ያልሰሙ መስለው ሳይመልሱለት ዝም  አሉ። ሾፌሩ መቼም ነገር ላያመልጠው የማለ ስለሚመስል፣ “ኧረ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ይዣችኋለሁ በላቸው? አይ ካሉ ‘ጠቁማቸው’ እያለ ሾፌራችን ሰውን ያዝናናዋል። ወዲያው ዞር ስንል አንጠጋም ያሉትም ተሳፋሪዎች አራተኛውን ተሳፋሪ ከመሀላቸው አስቀምጠውታል። “ወይ ‘እንቢተኝነት’ የተስማማውን እንዲህ ልኩን ሲያስገባው አልሰማ ያለውን ከርቸሌ ይከተዋል! ምናለበት አሠላለፍ መሆን ቢችልና ዋንጫ የናፈቀውን ‘አርሴን’ ድል በድል ቢያደርግልን?” ሲል አንድ ወጣት ‘እንዲያ በል አንተ!’ እያለ የአርሴናል ደጋፊ ያቅራራል። ‹ምኞት አይከለከልም› እያለ ሌላው አደብ ገዝቶ በምፀት ይስቃል! ‹‹ቀና ሲሉ መውረድ ያዝኩ ሲሉ ነጥብ መጣል ሆኗል የዘመኑ ኑሮና አርሴናል!›› የምትለው አንዲት ዝምተኛ ተሳፋሪ ናት፡፡ ጉድ እኮ ነው!

ወደ መዳረሻችን እየተቃረብን ነው። የቦብ ማርሌን ሐውልት የከበቡትን የትራፊክ መብራቶች እያየ መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ወጣቶች አንዱ “እኔ ምለው ይኼ መብራት አይበራም? አይጠፋም? በቃ ጌጥ ነው?” ይላል። “ምናለበት ትዕግሥት ቢኖርህ? ዛፉ ሳይኖር እንዴት መብራቱ ይበራል?” ይለዋል ከጎኑ። “የምን ዛፍ?” ሲለው፣ “የገና ዛፍ ነዋ፤” ብሎ ሲመልስለት ተሳፋሪዎች ያፈናቸውን ሳቅ ለቀቁት። “ግድ የለም። ዕድሜ ለጊቤ ሦስት መጠናቀቅ፡፡ አሁን በመብራት ዋስትና ራሳችንን ችለናል። በጥቂት ጊዜ ውስጥ የአምፖል ችግር ካልሆነ የማይበራ መብራት አይኖርም፤” ይላል ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመ ጎልማሳ። “እንዴ አደባባዩ ራሱ ሊፈርስ ነው ሲባል አልሰማሁም ማለት ነው?” ሲል ሌላው፣ “ቦብስ የት ሄዶ ሊዘፍን?” ትላለች ከጎኔ ያለችው ሽቅርቅር። እንዲህ ሆነናል እንዲህ እኛ!

 “ወይ ጉዴ። ዕቅድ የለሽ ሥራ እንዴት እንደሚሳካልን ታያላችሁ?” ባዩዋ ወይዘሮዋ ናት። ‹ኧረ መብራቱ ቀርቶ ይኼ አፍንጫ የሚሰረስር ቦይ ቢደፈንልን? በተለይ የዚህ ሠፈርማ የተለየ እኮ ነው። በዚህ በኩል ተመልከቱ የወጣቶች ስፖርት ማዘውተሪያ ማዕከል ግንባታውን እንዴት እንደሚያጣድፈው። በዚያ በኩል ትንፋሻችን እስኪበከል ድረስ ታፍነናል። መብራቱ ቀርቶብን አየሩን ቢለቁልን እያልን ለአቃል ብቃት እንቅስቃሴ ሳንደርስ ለዕርምጃ የሚስማማ አየር አጥተናል፤› እያሉ ተሳፋሪዎች ሲቀባበሉ ታክሲያችን ቦሌ ደርሳ ቆማለች። ‹ዋናው ነገር ጤና› አባባል ሆኖ የቀረባት አዲስ አበባ። መተንፈስ ሲናፍቅ አያሰኝም ትላላችሁ? መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት