Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኢሬቻ ክስተት - እንደ ችግር ብቻ ወይስ ትምህርት የሚወሰድበት አጋጣሚ?

የኢሬቻ ክስተት – እንደ ችግር ብቻ ወይስ ትምህርት የሚወሰድበት አጋጣሚ?

ቀን:

ክፍል ሁለት

በደጀኔ አሰፋ ዳምጠው

በልማት ሥራ ውስጥ የፕሮጀክት ዑደት አመራር (Project Cycle Management) የሚባል ጽንሰ ሐሳብ አለ፡፡ አንድ ፕሮጀክት ከንድፈ ሐሳቡ ጀምሮ ክትትልና ምዘናን (Monitoring and Evaluation) ያጠቃልላል፡፡ በክትትልና ምዘና ደግሞ ተነድፎ የተተገበረው ፕሮጀክት ዓላማውን ማሳካት አለማሳካቱን፣ የትግበራ ሥልቶች አግባብነት፣ በወጣው ወጪና በተገኘው ውጤት መካከል መመጣጠን መኖሩን/አለመኖሩን ወዘተ. ለማወቅ ይቻላል፡፡ ታዲያ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከምዕራባዊያኑ የምቀናበት አንድ ጉዳይ አለ፡፡

ይህም ከክትትልና ምዘና ማዕቀፍ ሳይወጡ በዋናነት የሚያተኩሩት ምን ውጤት አመጣ አላመጣ በሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ምን ትምህርት ተገኘበት በሚለው ላይ ነው፡፡ በመልካም ጎን (በጥንካሬ) የሚነሱ ጉዳዮችን እንዴት የበለጠ ውጤታማ ማድረግ እንደሚችሉ ያውጠነጥናሉ፡፡ ክፍተቶች (ደካማ ጎኖች) ወይም በእነሱ አጠራር ሊሻሻሉ የሚገባቸው ጉዳዮች (ከሥልት፣ ከበጀት፣ ከሰው ሀብት ምደባ፣ ከጊዜ፣ ወዘተ. አንፃር) ካሉ ደግሞ ጉዳዮቹን አንጥረው በመለየት ለወደፊቱ እንዴት ሊሻሻሉ እንደሚገባቸው ይመክራሉ፣ ይዘክራሉ፡፡ ከተገኘው ትምህርት ሁሉም ይማርበት ዘንድ ደግሞ ዋና ዋና ትምህርቶችን በመቀመር ለሌሎች ያካፍላሉ፡፡ በእነሱ አጠራር “Knowledge Sharing” ይሉታል፡፡

ከዚህ አንፃር በእኛ አገር ያለውን አሠራር በወፍ በረር ስቃኘው ከእነሱ የተለየ ሆኖ ይታየኛል፡፡ በእኛ አገር ክትትል አለ፣ ግምገማ አለ፡፡ በዚህ ደግሞ ወይ ትወድቃለህ ወይም ዕድለኛ ከሆንክ ታልፋለህ፡፡ አለቀ፡፡ በመውደቅና በማለፍ ብቻ የተገደበ አማራጭ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ምን ትምህርት ተገኘበት የሚለው ጉዳይ በውል አይጤንም፣ አይመዘንም፡፡ ግን እኮ አይደለም ፕሮጀክት ሕይወት ራሱ ከመውደቅና ከማለፍ የዘለለ ‹‹ወደፊት›› (Future) የሚባል ዕድል አለው፡፡ የሚቀረን፣ልንኖረውና ልናሳካው የምንችለው ብዙ ሕይወት፣ ብዙ መንገድ፣ ብዙ ግብ አለ፡፡ ስለዚህ አንዱ አንዱን በመጥለፍ ለመጣል፣ ሌላኛው ሌላውን ለማሳለፍ ከመራኮት ወይም በረባ ባልረባው ጊዜና ዕድልን በከንቱ ከማጥፋት ቅዱሱ መጽሐፍ ‹‹ይህም ለትምህርታችን ተጻፈ›› እንዲል፣ ለነገ ስንቅ የሚሆነን ትምህርት መቅሰሙ እንደ ግለሰብ፣ እንደ ተቋምም ሆነ እንደ አገር ጠቃሚ ሆኖ ይታየኛል፡፡

ይህንን የመንደርደሪያ ሐሳብ ያነሳሁት ባለፈው ሳምንት ለውይይት ካነሳሁት የኢሬቻ ክስተት ጋር በተያያዘ ምናልባት የሚሰጠን ትርጉም ይኖረው ይሆናል በሚል እሳቤ ነው፡፡ ኢሬቻና መሰል ክስተቶች ተከሰቱ፡፡ አለፉ፡፡ ጎርፍም፣ ድርቅም፣ ረሃብም፣ ወዘተ. ይከሰታሉ፣ ደግሞም ያልፋሉ፡፡ ብዙ ኩነቶች አልፈዋል፣ እያለፉ ነው፣ ያልፋሉም፡፡ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም አለፈ፡፡ ቀኑ መቼም ቢሆን ተመልሶ አይመጣም፡፡ በዳግም ምፅዓትም ቢሆን፡፡ ፕሮጀክት ካለቀ አለቀ፣ ቀን ካለፈ አለፈ፣ ክስተት ካለፈም እንዲሁ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን በሌላ ጊዜ ተመሳሳይ ክስተት፣ ወይም ከዚህ የከፋ ወይም ያነሰ ክስተት እንደማይከሰት እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ስለዚህ ካለፈው ክስተት እንደ አገር፣ እንደ ሕዝብ፣ እንደ መንግሥት ለወደፊት ዝግጅት የሚሆነን ምን ትምህርት ተገኘበት የሚለው መሆን አለበት፡፡ ካልሆነ ግን በክስተቶቹ ከተጎዳነው በላይ የሚጎዳን ትምህርት አለመውሰዳችን ሊሆን ይችላል፡፡

እዚህ ላይ በኢሬቻ የተፈጠረውን የሕዝብ እንቅስቃሴ በሌላ ዕይታ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ሕዝብ እኮ የመጨረሻ ሲከፋና ተስፋ ሲቆርጥ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ በዚያ ዓይነት መንገድ አያቀርብም፡፡ አንድም ዝም ማለት ሲሆን፣ ወይም በሌሎች አገሮች እንደምናየው ማለቂያ ወደሌለው አመፅ፣ የማያቋርጥ ጥፋትና ብጥብጥ መግባት ነበር ምርጫው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ይህ የሕዝብ ጥያቄ (ጥያቄው ምንም ይሁን ምን) ለእኔ የሚያሳየኝ ነገር ቢኖር ሕዝቡ አሁንም የሚሰማኝ መንግሥት አለ ብሎ እንደሚያምንና በመንግሥት ላይ ያለው እምነት ሙሉ በሙሉ አለመሟጠጡን ነው፡፡ የሚሰማ መንግሥት የለም ብሎ ቢያስብ መጮህን ለምን ምርጫው ሊያደርግ ይችላል?

በነገራችን ላይ ከዚህ መንግሥት በፊት በነበረው የደርግ አገዛዝ እንዲህ ዓይነት የሕዝብ ተቃውሞ ማድረግ ቀርቶ ማሰብ እንደማይቻል በሁሉም ኢትዮጵያዊ ሕይወት ውስጥ ያለፈ የአገር ታሪክ ነው፡፡ ነገር ግን በትጥቅ ትግል በነፍሳቸው ተወራርደው በብዙ መስዋዕትነት የተገኘው ይህ የዴሞክራሲያዊ መስመር እንዲህ ዓይነቱን የሕዝብ ጥያቄና ጥያቄን የማቅረብ ተነሳሽነትን ለምን እንደ አንድ ትልቅ የዴሞክራሲና የትግሉ ፍሬ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም? የትግሉ ፍሬ ነው ብሎ በማሰብና ብሎም ይህን ፍሬ ሕዝቡ እንደሚገባ እንዲያጣጥም ቢመቻችለት ይህ ፍሬ እንዲመጣ ላስቻሉት ለእነዚያ እውነተኛ የኢትዮጵያ ወጣቶችና ድንቅዬ የትግል ሰማዕታት ዝክር የሚሆን ሐውልት ከማቆም በዘለለ፣ በሕዝቡ ልብ ዘለዓለማዊ ክብርና ሞገስ የሚያሰጣቸው የክብራቸው አደባባይ በሆነ ነበር፡፡ አልሆነም፡፡

በዚያ ላይ መንግሥት የደረሰውን ጥፋት ከመቀነስ አኳያ የተሰበሰበውን ሕዝብ በሚገባ ለመቆጣጠር (Crowd Management) በቂ ዝግጅት አድርጓል ለማለት የሚያስችል ነገር አልነበረም፡፡ ይህን የምለው ባዶ እጁን የወጣ ሕዝብ ግፋ ቢል ከፍተኛ ጩኸት ከማሰማት በቀር ምን ሊያደርግ ይችላል ብዬ በማሰብ ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ እንደ ባቢሎን ግንብ በጩኸት የሚፈርስ አይደለም፡፡ ባዶ እጁን አልነበረም ተብሎ ከታመነ ወይም ይህን የሕዝብ መሰባሰብ ሌሎች ‹‹የጥፋት ኃይሎች›› ወደ ሌላ አቅጣጫ ሊወስዱት ይችላሉ የሚል መንግሥታዊና ሕጋዊ ሥጋት ከነበረ ደግሞ (በእርግጥ በዚያ ሰሞን እዚህም እዚያም እየታየ ከነበረው አለመረጋጋትና የፀጥታ ችግር አንፃር እንዲህ ዓይነት ሥጋት መኖሩ ምንም የሚደንቅ ባይሆንም)፣ መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት የመጠበቅ ዋነኛ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር አመርቂ ዝግጅት ነበረው ማለት አያስችልም፡፡

ቢያንስ የተወሰዱት ዕርምጃዎች ሁኔታው ከሚፈልገው ጊዜ መቅደማቸውን ልብ ይሏል፡፡ መንግሥት በዋናነት ሲያተኩር የነበረው ለደረሰው ጥፋት የሆነ አካልን ተጠያቂ ለማድረግ መረጃና ማስረጃ የማፈላለግ ሁለተኛ ጉዳይ ላይ ነበር፡፡ እዚህ ላይ የታዩ ጉድለቶችን በውል በመመዘን ለፖሊስ ሠራዊቱ፣ ለደኅንነት ኃይሉና ለመከላከያ ሠራዊቱ በሚገባ የታቀዱ የአቅም ግንባታ ሥራዎች በተከታታይነት ሊደረግላቸው ይገባል እላለሁ፡፡ እየተናገርሁ ያለሁት ስለ አንድ ኢሬቻ ወይም ስለ አንድ ብሔር ሳይሆን አገራዊ ነገር በመሆኑ፣ ምናልባት የፖሊሲ ምልከታ ሊኖረው ስለሚችል አመራሩ ለዚህ ጉዳይ ቦታ እንዲሰጠው ለማሳሰብም እወዳለሁ፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ትልቅ ጉዳይ መሆን ያለበት የኢሬቻ በዓል ለምን በሰላም ተከብሮ አላለፈም የሚለው ሐሳብ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ‹‹በሰላም ተከብሮ›› ብዬ ከምገልጸው ይልቅ ‹‹በተያዘለት የበዓል መርሐ ግብር ተከብሮ›› አላለፈም ብለው ይሻለኛል፡፡ ምክንያቱም ሰላም ማለት የጦርነት አለመኖር ብቻ አይደለም ብዬ ስለማምን፣ ሕዝቡ ደግሞ የራሱን ጥያቄ በአደባባይ መግለጽ መቻሉንና ድምፅ ማሰማቱን እንደ ትልቅ ውጤትና ዕረፍት ሊሰማው ስለሚችልም ጭምር ነው፡፡ ከበጣም መጥፎ፣ መጥፎ ይሻላል እንዲሉ ጥያቄን ይዞ ከመሞት ድምፅን አሰምቶ መሞት የሚለው ምርጫ ጥያቄውን ባቀረበው ሕዝብ ዘንድ እንደ ትልቅ ፍሬ ሊታሰብ የሚችልበት አጋጣሚም አለ ለማለት ነው፡፡ ዋና ጉዳይ መሆን ያለበት በዓሉን ለማክበር የታደመው ሕዝብ ይህንን የሚወደውን በዓል ሰውቶ እንዲህ ዓይነት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አስተዳደራዊና መሰል የፍትሕ ጥያቄዎችን ለማቅረብ ለምን ተገደደ የሚለው ሐሳብ ነው፡፡

በእኔ ዕይታ የበለጠ ሊታዘንለት የሚገባው ሕዝቡ ነው፡፡ ምክንያቱም አምላኩን በኅብረት ተሰባስቦ ለማመስገን ትውፊታዊ ወጉን ለማስጠበቅ በዓመት አንድ ጊዜ እንደ መስቀል ወፍ ከያለበት በናፍቆት ጠብቆ የሚገናኝበትንና የማንነቱ መገለጫ የሆነውን ክብረ በዓል ማክበርን ወደ ጎን ትቶ፣ በቤቱ የሚያሰላስላቸውን ያልተመለሱ ጥያቄዎችን እንደ ኢሬቻ ባሉ በጉጉት በሚጠበቁ ክብረ በዓላት የሚፈጥሩለትን የመገናኘት መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ጥያቄውን ማቅረቡ የሚያስፈርድበት ሳይሆን የሚታዘንለት ያደርገዋል፡፡ ይህም ሕዝቡ ያሉትን የትኛውንም ዓይነት ጥያቄዎች ከዚህ ቀደም የመሰብሰብም ሆነ ሰላማዊ ሠልፍ የመውጣት መብቱ ተጠብቆለት ቢሆን ኖሮ፣ በስስት የሚያከብረውን ክብረ በዓል በወጉ ሳያከብርና ይልቁኑም ውድ የሆነ ሕይወትን ባላስከፈለው ነበር፡፡

እዚህ ላይ በጣም አሳዛኝ ሆኖ ያገኘሁት ከዚህ ሁሉ ትዕይንት በኋላ ይህንን ክስተት ማን ቀሰቀሰው? ማን አስተባበረው? ስንት ሰው ሞተ? ስንት ሰው  ቆሰለ? በጥይት ነው በጭስ? በመረጋገጥ ነው በገደል? የሚሉና መሰል ጥያቄዎች እንጂ ይህ ክስተት በምን ገፊ ምክንያት ተነሳ? የሕዝቡ ዋነኛ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው? እንዴት ሊፈቱ ይችላሉ? ወዘተ. የሚሉ መሠረታዊ ነጥቦች በሚገባ ደረጃ ተነስተዋል ወይም ተብላልተዋል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምናልባት የጥልቅ ተሃድሶው ፍሬ ይመልሳቸው ይሆናል ብዬ ግን እመኛለሁ፡፡ ስለዚህ ከሌሎቹ ጉዳዮች ይልቅ እንዲህ ሕዝቡን ዋጋ ያስከፈሉት ጥያቄዎች ምንድን ናቸው የሚለው ሐሳብ ላይ ማተኮር ሁሉንም የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ ወደ ተከታዩ የመፍትሔ አቅጣጫ ለመሄድ ያስችላል፡፡ ካልሆነ ግን ይህን ያህል መስዋዕትነት የተከፈለበት የሕዝብ ጥያቄ በሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘን ይደመደማል፡፡

እዚህ ላይ መጠቀስ ያለበት ነገር የሕዝብ ጥያቄ ይመለስም አይመለስም ሌላ ጉዳይ ሆኖ፣ የሕዝቡን ጥያቄ እንደወረደ ማድመጥና መረዳት የመጀመሪያው ቁልፍ ተግባር ይሆናል፡፡ በአንፃሩ መንግሥትም ሆነ የትኛውም አካል የሕዝብን ጥያቄ እንደፈለገ የመተርጎም፣ የማስተካከል፣ የማጣመምም ወይም ወደሌላ አቅጣጫ እንዲፈስ ማድረግ ተቀባይነት የማይኖረው ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ ‹‹እኔ አውቅልሃለሁ›› ወይም ‹‹እኔ አስብልሃለሁ›› የሚል አመለካከትም ሆነ አካሄድ ʻከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነውʼ እንዲሉ፣ ሕዝብ የሚፈልገውንና የሚጠይቀውን ጉዳይ አያውቅም የሚል ምልከታ ስላለው ሕዝብን የሚያከብር አይሆንም፡፡ ሕዝብ ክቡር ነው፡፡ ሕዝብ አዋቂ ነው፡፡ ሕዝብ ለራሱ የሚያስፈልጉትን ጉዳዮች እውን ለማድረግ ለጊዜው አቅም የሌለው መስሎ ሊታይ ቢችልም ስለራሱ ግን ያሉበትን ችግሮች፣ የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች፣ እንዲመለሱለት የሚፈልጋቸውን ጥያቄዎች በሚገባ ያውቃል፡፡ ልንማርበት ወደሚገባን ትምህርት ከመግባታቸን በፊት በመጀመሪያ እንዲህ ዓይነቱን የሕዝብ መሰባሰብን ተጠቅሞ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሞክር የተደራጀም ይሁን ያልተደራጀ አካል ካለ፣ በሚከተሉት ነጥቦች በወንጀል መጠየቅ ይኖርበታል የሚል ግምት አለኝ፡፡

አንድ እንደ ኢሬቻ ባሉ ክብረ በዓላት የሕዝቡ መሰባሰብ በዋናነት በዓሉን ለማክበር በመሆኑ ነው፡፡ ይኼ ነጥብ ሁሉንም ጉዳዮች በየፈርጁ ማየት ስለሚያስፈልግ እንጂ ከላይ ካነሳሁት ጉዳይ ጋር የሚጣረስ አይደለም፡፡ ምንም እንኳን መተንፈሻ ያጣ ሕዝብ እንዲህ ዓይነቱን ክብረ በዓላት ተጠቅሞ ጥያቄን ማሰማቱ ለኢትዮጵያውያን አዲስ ባይሆንም፣ ሌሎች ሦስተኛ አካላት ግን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መገፋፋታቸውን ሕጋዊ አያደርገውም፡፡ ሁለት ኢሬቻን በመሰሉ ክብረ በዓላት ላይ የተገኘው ሕዝብ ተብሎ በጅምላ ሲጠራ በተባለው የፖለቲካ አጀንዳ የሚስማማ እንዳለ ሁሉ፣ የማይስማማም ወይም በጉዳዩ መሳተፍ የማይፈልጉ ሰዎችን ስለሚያካትት የእነዚህን ዜጎች መብት የሚጥስ ነው፡፡ ሦስት በዚህ በዓል ላይ ምንም ነገር የማያውቁ በዕድሜ ሕፃናት የሆኑ አሊያም ከችግሩ ሩጠው ማምለጥ የማይችሉ ወይም ራሳቸውን ማዳን የማይችሉ አካል ጉዳተኞች፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አዛውንቶች ወዘተ. የሚገኙበት በመሆኑ ነው፡፡ አራት በእንደዚህ መልኩ የተተገበረ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በውጤት ደረጃ በአገር ደረጃ መሠረታዊ የሚባል ለውጥን የማምጣት ዕድሉ ውስን መሆኑና ከዚህ በተጨማሪም የሚያስከፍለው ዋጋ ኢምንት ከሆነው ውጤት ጋር ሲመዘን ተገቢ (Worth Paying) ባለመሆኑ ነው፡፡ አምስት ነፃ የሆነ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድን የሚያበረታታ ባለመሆኑና ከዚያ በኋላ በመንግሥት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ወዳልተሻለ መንገድ እንዲገባ የሚያስገድዱት ስለሚሆን ነው፡፡ ስድስት እንዲህ ዓይነት ክስተት ጥሎ የሚያልፈው ትዝታ ጥሩ ባለመሆኑ የማኅበረሰቡን ሥነ ልቦና (Social Psychology) የሚጎዳ ስለሚሆን፣ ከዚያ በኋላ ሕዝቡ በተጀመሩ በዴሞክራሲያዊና በልማት ጎዳናዎች ሊኖረው የሚገባውን ተሳትፎ እንዲቀንስ ያደርጉታል፡፡ በአጠቃላይ በእነዚህና መሰል ምክንያቶች እንደ ኢሬቻ ባሉ ክብረ በዓላትም ይሁን ሌሎች ሕዝባዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን ለፖለቲካ ፍጆታ ማዋል ተቀባይነት ይኖረዋል ብዬ አላምንም፡፡

በአንፃሩ እንደኔ ዕይታ ካለፈው ክስተት የሚከተሉትን ነጥቦች መረዳትና መማር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ በመንግሥት ያልተመለሱ ነገር ግን በሕዝቡ ውስጥ ያሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችና አንገብጋቢ ጉዳዮች መኖራቸውን፣ ከዚህ ቀደም የሕዝብ ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ የሚስተናገዱበትና ሕዝብ ብሶቱንም ሆነ ጥያቄውን የሚተነፍስበት አሳታፊ የሆነ የተመቻቸ ሥርዓት በወጉ ያለመኖሩን አሊያም አለመተግበሩን፣ የተመቻቸ አሳታፊ ሥርዓት ባለመኖሩ/ባለመተግበሩ በየጊዜው ሲነሱ ለነበሩ ጥያቄዎች ከሥር ከሥር ምላሽ ባለመሰጠቱ ሳቢያ ህልቆ መሳፍርት የሆኑ ጥያቄዎች መፈጠራቸውና ጥያቄዎቹም የተወሳሰቡና ቅርፅ አልባ (Amorphous) እንዲሆኑ ማስገደዱን፣ መንግሥት አሁንም ከሕዝብ የሚነሱ ሕጋዊና ሰላማዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ ያለው ፖለቲካዊ ዝግጁነት በአመርቂ ሁኔታ እያስመሰከረ እንዳልሆነ፣ እንዲሁም የእነዚህ ጥያቄዎች አለመመለስ ብቻ ሳይሆን ምላሽ እየተሰጠበትም ያለው አግባብ አገሪቱን ወዴት ሊወስዳት ይችላል የሚል ሥጋትን ኃላፊነት በሚሰማቸው ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሥጋት መፍጠሩን ያመላክታል፡፡

ከላይ ያነሳሁት ማለትም ያልተፈቱ ጥያቄዎች ሲያድጉ ውስብስብና ቅርፅ አልባ የመሆናቸውን ነጥብ የበለጠ ለማብራራት፣ ትዳራቸውን በሕጋዊ መልኩ ከማፍረሳቸው በፊት የመጨረሻ የመታረቅ ዕድሉን ለመጠቀም የትዳር አማካሪዎች ዘንድ ራሱንና ሚስቱን ይዞ ስለሄደ ሰው ታሪክ ላካፍላችሁ፡፡ እነዚህ ባልና ሚስቶች ለረዥም ዓመታት በትዳር የዘለቁ ቢሆንም፣ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠሩ አለመግባባቶችና በተለይም በሴቷ ላይ ይደርስባት ከነበረው ግፍና በደል የተነሳ ቢመስል ቢገዘት መፋታትን አንድና አንድ ምርጫዋ ያደረገችበት ጊዜ ነው፡፡ ሆኖም ግን ለብዙ ዘመን ቢበድልም ፍቺውን ግን አልፈለገም፡፡ ባል እንዳልኳችሁ የትዳር አማካሪዎች ዘንድ ይዟት ሄደ፡፡ ከዚያም አማካሪዎቹ ከተቀበሏቸውና ተጣልተው የመጡበትን ጉዳይ እንዲያስረዱ ካመቻቹ በኋላ የመጀመሪያውን ዕድል ለባል ሰጡ፡፡

አቶ ባልም እንዲህ አለ፡፡ ‹‹. . . በመጀመሪያ ይህንን የቤተሰብ ጉዳይ እንዳብራራ ለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ፡፡ ለዚህም ሲባል ይህንን የመሰለ አሳታፊ መድረክ ላዘጋጁ አካላት በራሴና በወከለኝ ቤተሰብ ስም እንዳመሰግን ይፈቀድልኝ . . .››፡፡ ጥቂት ቤተሰባዊ ጭብጨባ ከተስተጋባ በኋላ ንግግሩን ቀጠለ፡፡ ‹‹ . . . ስለ ባለቤቴ መናገር የምፈልገው ነገር ቢኖር . . . ሚስቴን እወዳታለሁ በእጅጉም . . .  አከብራታለሁ፡፡  እዚህ ላይ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ ሚስቴን እወዳታለሁ የሚለው ነው . . .›› ካለ በኋላ ንግግሩን ለአፍታ ቆም ሲያደርግ አማካሪዎቹ እርስ በእርስ እየተያዩ መጠነኛ ፈገግታ ቸሩት፡፡ እሱ ግን ንግግሩን ቀጠለ፡፡  ‹‹. . . እንዲያውም እሷን አግብቼ በአንድ ጎጆ ኑሮ ከመጀመራችን በፊት ባለቤቴ የሌላ ሰው ሚስት ሆና ትኖር ነበር፡፡  . . . ባሏም በጣም ጨካኝ፤ አረመኔና ጡንቸኛ ነበር፡፡ ልጆቿንም በቤት ውስጥ ማሰቃየት፣ የጉልበት ብዝበዛ መፈጸምና ገፋ ሲልም አስገድዶ መድፈርን የቀን ተቀን ተግባሩ አድርጎ ይኖር የነበረ ሰው ነው፡፡ የራሱን ጥቅምና ዝና ለማስጠበቅ ሲልም ትርጉም የለሌው የቤት ለቤት ሽኩቻ እየፈጠረና የቤተሰብ ግጭትን እያነሳሳ አንዱን የቤተሰብ አካል ከሌላኛው ጋር ማጣላትና ለእንግልት መዳረግ የትዳሩ ዋነኛ መርሆዎች ነበሩ፡፡ ይህ የቀድሞ ባሏ በሚከተለው አረመኔያዊ የቤት አስተዳደር አገኘዋለሁ ብሎ የሚመኘውን ያህል እርካታ ካላገኘና በዚህ አልበቃ ሲለው፣ ከቤቱ እልፍ ይልና ከጎረቤት ጋር ጠብ ይጭር ነበር፡፡ በዚህ ግጭትም እንዲፋለሙለት በመከራ ያሳደገቻቸው ልጆቿን ይማግድባታል፡፡ የዚህ ግጭት ውጤትም አብዛኛውን ጊዜ አስከፊ የሆነ የወጣት ልጆቿ ሞትና የአካል ጉዳት ስለሚሆን፣ መላ ቤተሰቡን ለጥልቅ ሐዘንና የልብ ስብራት ይዳርጋቸው ነበር፡፡ እኔም በዚህ ጨካኝ ሰውዬ ይደርስባት የነበረውን ስቃይ በውል ተመልክቼ፣ በእርሷ ጫማ ቆሜና ሐዘኗን እንደ ራሴ ሐዘን ቆጥሬ የዛሬዋ ሚስቴንና ከተለያዩ ባሎች ያፈራቻቸውን የስስት ልጆቿን ካሉበት አስከፊ ኑሮ ለማውጣት ወሰንኩ፡፡ ነፃ ቤተሰብ እንዲሆኑ ለማስቻል የነበረኝን ምኞት ለማሳካት ይረዳኝ ዘንድም ከባልንጀሮቼ ጋር መከርኩ፡፡ በሐሳቡም በመስማማታችን እኔና ጓደኞቼ ሕይወታችንን አደጋ ላይ ጥለንና ብዙዎችን አስከትለን በእልህ አስጨራሽ ትግልና መስዋዕትነት እነሆ የዛሬ ስንት ዓመት ገደማ ከመጀመሪያ ባሏ ለማፋታት ቻልን፤›› ካለ በኋላ በኩራት ፊቱን ቀና አድርጎ ወደ ሚስቱ ሲመለከት የእርሷን ይሁንታ እንደፈለገ ቢያሳብቅበትም ንግግሩን ቀጠለ፡፡  ‹‹በእርግጥ ይህን የቤተሰብ ታሪክም ሆነ የእኔና የባልንጀሮቼን ውለታ እሷም አትዘነጋውም፤›› በማለት ዘርዘር አድርጎ የነበረውን ግፍና መከራ ተረከ፡፡

በረዥም ንግግሩ ምንም መሰላቸት እንዳልተፈጠረ በሚመስል ሁናቴ ጉሮሮውን በመቃኘት ድምፁን ለሌላ ገለጻ አስተካከለ፡፡ ቀጠለና እንዲህ አለ፣ ‹‹. . . የተከፈለው መስዋዕትነት እሷን ከቀድሞ ባሏ በማለያየት ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ይልቁን ለእርሷ የሚሆን ዘለቄታዊነቱን ያረጋገጠ፣ ግልጽና ተጠያቂ የሆነ ባል ማፈላለግ ነበረብን፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ሰዓት ከእናንተ መደበቅ የማልፈልገው ነገር ቢኖር ለእርሷ ያንን ያህል መስዋዕትነት ከባልንጀሮቼ ጋር ከፍዬ ከእኔ ሌላ የትኛውም ሰው እንዲያገባት አልፈልግም ነበር፡፡ ቢሆንም ግን ሌላ ሰው አያገባትም ብለን ብንናገር የከፈልነውን እውነተኛ መስዋዕትነት ጥያቄ ምልክት ውስጥ ስለሚያስገባው ሌላ አማራጭ መውሰድ ነበረብን፡፡ ይህም በዋናነት የባልነት መሥፈርቱን ትንሽ ውስብስብ ማድረግ፣ የባል ምርጫ ሒደቱን በበላይነት መምራትና ለተወሰነ ጊዜ እሷን የሚያስተዳድር ሞግዚት ባል መመረጥ የሚል ነበር፡፡ ከመሥፈርቱ መካከል ‹‹ፋሞክራሲ›› የሆነ ሰው መሆን አለበት የሚል ይገኝበታል፡፡ ‹‹ፋሞ›› ማለት ‹‹ፋሚሊ›› ሲሆን፤ ‹‹ክራሲ›› ማለት ደግሞ አስተዳደር ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት እናንተም እንደምታስታውሱት እሷን ለማግባት በአገር ውስጥም ሆነ ከአገር ውጭ ያሉ ሰዎችና ድርጅቶች በእጮኝነት ብፌ ላይ ተመዝግበው ተደረደሩ፡፡ ሆኖም ግን ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት እነሱን የፈለግናቸው እንዲያገቧት ሳይሆን የቤተሰብ ሕጉ ሲረቀቅ እንዲገኙ ብቻ ነበር፡፡ እኔም ለዘለቄታው የተመኘኋትን ባለቤቴን እንዳገባት የሚያስችለኝን ሕጋዊ ማዕቀፍ ፋሞክራሲነቱን በጠበቀ ሁኔታ አመቻቸሁ፡፡ ከዚያም አገባኋት፡፡ በእጮኝነት የተመዘገቡትም ሆኑ ታዛቢዎቹ ቆመው አጨበጨቡ፣›› ብሎ እርፍ፡፡ 

የነበረውን ሒደት ሲናገር በተከናወኑት ፋሞክራሲያዊ ተግባራት ትንሽ እንደ መጀነን ቢልም ባለቤቱ ግን አንገቷን እንደ ደፋች ከመቀመጫዋ ትቁነጠነጥ ነበር፡፡ የመቁነጥነጧ ምክንያትም በዚህ ዓይነቱ የጋብቻ ሒደት ውስጥ እሷ ባል የመምረጥ መብቷ እንዳልተከበረላትና በአንፃሩ ግን ሚስት የመመረጥ መብታቸውን ያስከበሩት የዛሬው ‹‹ባሏ›› እና ‹‹እጮኛ›› ተብዮዎቹ ብቻ መሆናቸውን ማስታወሷ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አጅሬ ባል ግን ንግግሩን ቀጠለ ‹‹ . . . ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድና ሐሜት በኋላ እኔ እንደ ባል እሷ እንደ ሚስት ሆነን ለመኖር በቃን፡፡ እኔም ለቤቴ ታማኝ ሆኜ፣ የቤቴም ማድጋ ከቀን ወደ ቀን እየሞላ፣ አስቤዛም ሳይጓደል ለመኖር ቻልን፡፡ በዚህ ትዳርም ብዙ የሚባሉ ትልልቅ ሀብቶችን አፈራን፡፡ ትዳሩን ከነበረበት የድህነት አደጋ ለመውጣት ሞከርን፡፡ የቤተሰቡን የትምህርትና የጤንነት ደረጃ በከፍተኛ ደረጃ ተሻሻለ፡፡ በቤተሰቡ መካከል የነበረውን የመንገድ ብልሽት ከመጠገን አልፈን ታይተው የማይታወቁ የቤተሰብ መጓጓዣ አውታሮችንና መስመሮችን ዘረጋን፡፡ አማራጭ የኃይል ምንጮችንም አጎለበትን፡፡ ከጎረቤት ጠላቶችም እየጠበቅኩ ትዳሬን አላስደፈርኩም፡፡ ባይሆን ከዚህ የሥራ ኃላፊነት ጫና የተነሳ ለባለቤቴ በቂ ጊዜ አልሰጣትም ነበር፡፡ በሚገባም አላወራትም ነበር፡፡ በሚጠበቅብኝም ደረጃ የእርሷን ሐሳብ፣ ጥያቄ፣ ምርጫም ሆነ ዝንባሌ  አልተረዳሁም፡፡ ምክንያቱም እኔ ከእርሷ የተሻለ አስባለሁ ስለምልና ኃላፊነቱም የእኔ ነው ብዬ ስለምወስድ ነበር፡፡ በዚህም ባለቤቴን ጎድቻታለሁ፣ በድያታለሁ፡፡ ባለቤቴ አሁን አልጋ ከለየች ሰነበተች፡፡ የድሮውንም ፍቅር ልትሰጠኝ አልቻለችም፡፡ ለወራትም ብሞክር ልቧ ሸፈተብኝ፡፡ ለዚህ ለተፈጠረው ችግር ነው ዛሬ በፊታችሁ ቆሜ ታሸማግሉኝ ዘንድ ወደ እናንተ የመጣሁት . . .››  በማለት ነበር አሳዛኝ የሆነውን ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ያልሆነውን ዲስኩሩን የደመደመው፡፡

አማካሪዎቹም የእርሱን ንግግር በጥሞና ካደመጡ በኋላ የመናገር ዕድሉን ለሚስት ሰጡ፡፡ ሚስት ግን አንገቷን እንዳቀረቀረች ዝም አለች፡፡ ከዝምታዋም የተነሳ አማካሪዎቹ እጅግ ተጨነቁ፡፡ እንደ መንደርደሪያ ያገለግላትም ዘንድ የራሳቸውን መላ ምት ማለትም ትዳሯን ለመፍታት እንዲህ ሊያስጨክናት የሚያስችሉ ጉዳዮች ብለው የሚገምቱትን ዋና ዋና የትዳር ጠሮች እየዘረዘሩ በማግባባት ይጠይቋት ጀመር፡፡  ‹‹. . . ባለመናገርሽ ምክንያት ተጨነቅን፡፡ እንዲያው . . . ከሌላ ሴት ጋር ሲማግጥ አግኝተሽው ነው . . . ወይስ ደግሞ . . .›› ብለው ሳይጨርሱ የዘመናት ጉዳቶቿ በዓይነ ኅሊናዋ ድቅን አለባትና ስቅስቅ ብላ አለቀሰች፡፡ ከዚያም በብዙ እንባና ንዴት እየተንቀጠቀጠች እንዲህ አለች፡፡ ‹‹. . . እ እ እ እ እንዲያው እናንተን መድፈር ባይሆንብኝ . . . እኔ የዚህን ሰው ዓይኑን እንኳን ማየት አልፈልግም . . .›› ስትል፣ በሁኔታዋ የተደናገጡት አማካሪዎች እንዲህ አሉ  ‹‹. . . ቆይ ቆይ እስቲ ተረጋጊ፡፡ እንባሽንም እንዲህ በየሜዳው መዝራት ለእርሱም ቢሆን ለተወለዱት ልጆች አይበጅም፡፡ የሴት ልጅ እንባ በወንድ ላይ ጦስና እርግማን ነው የሚያመጣው . . .››  እያሉ ለማባበልና ለማረጋጋት ሞከሩ፡፡  ቀጠሉና፣  ‹‹. . . እስቲ የበደለሽን ዘርዝረሽ አስረጂን? ዋና ዋና ጥያቄዎችሽ ምንድን ናቸው . . .›› ቢሏት እርሷ ግን ዓይኗ በእንባ እንደተሞላ እንዲህ አለች፡፡ ‹‹. . . በአጠቃላይ ዓይኑን ማየት አልፈልግም . . . ኧ ኧ ኧ ኧ ኧ  በጭራሽ ዓይኑን ማየት አልፈልግም፡፡ እንዲያው ስንቱን ስንቱን ኧረ የቱን አንስቼ ምንስ ብዬ ልናገር? ብቻ ከዚህ በኋላ ዓይኑን ማየት አልፈልግም፤›› ብላቸው እርፍ፡፡

እነርሱም እርስ በርስ እንዲህ ተባባሉ፡፡ ‹‹እንዲያው በትዳር አማካሪነት ብዙ ዓመት ስናገለግል የተረዳነው ነጥብ ቢኖር ይህ ነው፡፡ ጥቃቅን የሚባሉ ችግሮች ሲያድጉና ሲደማመሩ መጨረሻ ላይ ትልቅ ችግር የሚሆኑት፣ ጥያቄንና ችግርን  እንኳን በቅጥ ማስረዳት ከባድ መሆኑን ነው፡፡ . . . ይልቅ አሁን አንች እየሆንሽ እንዳለሽው ጥያቄዎችሽ ድቡልቡል በመሆናቸው ሳቢያ አፍና አፍንጫቸው የማይለይ ቅርፅ አልባ ይሆናሉ፡፡ . . . እንዲያውም እዚህ ላይ ትልቅ ችግር የሚሆነው ችግሩን መተንተንና በቅደም ተከተል ማስረዳት ነው፡፡ ከዚያም ጥያቄዎቹ ከጥያቄነት ዘለው ጥላቻ ይሆናሉ፡፡  በአንድ ትዳር ውስጥ ችግሩ እንዲህ ዓይነት ደረጃ ከደረሰ ትዳሩ ብዙውን ጊዜ የሚቋጨው በመለያየት ነው፡፡ ፍቺው ካላማረም አላስፈላጊ ዋጋን ሊያስከፍል የሚችልበት አጋጣሚም ብዙ አለ፡፡ ስለዚህ በእንዲህ ዓይነቱ ደረጃ ሆነው ወደ እኛ ለሚመጡ የትዳር ጓደኞች የምናካፍላቸው ምክር ቢኖር ኃላፊነት በሚሰማው መንገድ ፍቺውን እንዲያሳምሩ ነው፡፡ የእኛም ኃላፊነት የሚሆነው ከሀብት ጅምሮ እስከ ሌሎች ጉዳዪች ድረስ ሁለቱም ወገኖች የማይጎዱበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ከፍቺም በኋላ ሊኖራቸው ስለሚገባ መልካም ግንኙነት መምከር ይሆናል . . .›› ካሉ በኋላ ሻይ ቡና ለማለት የዕረፍት ጊዜ ወሰዱ፡፡ ከዕረፍት መልስ ግን ሁሉም በአንድ ድምፅ አንድ የመጨረሻ አማራጭ አቀረቡ፡፡ ይህም በትዳራቸው የተከሰተውን አደጋ ለማስወገድና መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ባልና ሚስቱ ብቻቸውን ሆነው በጥልቀት እንዲነጋገሩ የሚል ሐሳብ፡፡ ባልም በተሰጠው የመጨረሻ ዕድል ደስተኛ በመሆን በኃላፊነት እንደሚሠራና ከቤተሰቡ ጋር ተነጋግሮ እውነተኛ ለውጥን እንደሚያመጣ ቃል ገብቶ፣ በዚህ ሒደትም የሚስቱን ዕርዳታ እንደሚፈልግ አስታውቆ በብሩህ ተስፋ ምሳ ተገባበዙ፡፡

የዚህን ጽሑፍ ተከታይ ክፍል በተለይም ችግሮችን ወደ መልካም አጋጣሚነት ስለመቀየር የሚለውን በሚቀጥለው ሳምንት እንዲያነቡ በአክብሮት እጋብዛለሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...