Wednesday, February 8, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢሕአዴግ ስህተቱን ከማመን በላይ ከሕዝብ ጋር በቀጥታ ይነጋገር!

ኢሕአዴግ በቅርቡ በወጣው በንድፈ ሐሳብ መጽሔቱ አዲስ ራዕይ የመስከረም – ጥቅምት 2009 ዓ.ም. ዕትም በሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች የአገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ በስፋት ዳስሷል፡፡ በተለይ ዋነኛው የትኩረት ማዕከል የሆነው ወቅታዊው የአገሪቱና የድርጅቱ ሁኔታ፣ ‹‹እንደገና በጥልቀት የመታደስ ንቅናቄያችን አስፈላጊነት ይዘትና ፋይዳ›› በሚል ርዕስ ሥር በስፋት የተተነተነው ነው፡፡ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ኢሕአዴግ በጥልቀት ለመታደስ ግድ ያሉትን ምክንያቶች በመዘርዘር፣ ባለፉት ሃያ ዓመታት የተገኘውን ለውጥ መነሻ በማድረግ ያጋጠሙ ስኬቶችን፣ ችግሮችንና የመፍትሔ ፍኖተ ካርታ አመላክቷል፡፡ አገሪቷ ከነበረችበት የድህነት አረንቋ ውስጥ ጎትቶ ለማውጣት በተደረገው ጥረት የነበሩ ውጣ ውረዶችን፣ አገሪቱንም ሆነ የድርጅቱን የመጀመሪያ ተሃድሶ ከስኬት ውጪ ለመረዳትም ሆነ ለመግለጽ መሞከር አንድ ግዙፍ እውነታን መካድ ነው በማለት ኢሕአዴግ ዕይታውን አስቀምጧል፡፡ የተገኘውን ስኬት ከማንኛውም ዓይነት ከፉ ነገር በመጠበቅ፣ እንደገና በጥልቀት መታደስን አስምሮበታል፡፡ ይሁንና ይህ ክስተት አንድ መገለጫ መሆኑን በመቆጠም መሠረታዊውን ምክንያት አብራርቷል፡፡

      ኢሕአዴግ ፈተና የገጠመው በሁለተኛ መገለጫ መሆኑን በመተንተን፣ እንደ ገና ለመታደስ ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ሲያወሳ የመጀመርያው በአገሪቱ የተፈጠሩ አዳዲስ እውነታዎች መኖራቸውንና በአግባቡ ማስተናገድ አለመቻል ተጠቃሽ ያደርጋል፡፡ ከአንድ የዕድገት ምዕራፍ ወደ ሌላ ያለማቋረጥ ሽግግር የተደረጉ ለውጦች በራሳቸው ያደገ ነገር ይዞ መቅረብን ግድ ማለታቸው ተወስቷል፡፡ የወጣቶችን የልማትና የተጠቃሚነት ጉዳዮችን በፍጥነት፣ በስፋትና በአስተማማኝ ደረጃ መመለስ ግድ የሚል መሆኑ ተዘርዝሯል፡፡ የሕዝቡ ንቃተ ህሊና ማደጉ፣ ከዕድገቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ፍላጎቱ መጨመሩ፣ መንግሥትን የመቆጣጠር ሚናውና ፍላጎቱን ማወቁ፣ ሙስና በአገር ላይ የሚያስከትለው ጉዳት በመገንዘብ ለመታገል፣ ወዘተ መቻሉ ተተንትኗል፡፡ ይህም ሕዝቡ ምን ያህል እየተለወጠ መሆኑንና ለዚህም ዳግም ተሃድሶ አስፈላጊ እንደሆነ በኢሕአዴግ ተገልጿል፡፡

ሌላው ዋናውና መሠረታዊ ምክንያት ደግሞ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱን የሚፈታተን እየሆነ የመጣው የመንግሥት ሥልጣን የግል ጥቅም ማስከበሪያና የኑሮ መሠረት የማድረግ ዝንባሌ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ መንግሥት ራሱን ከኪራይ ሰብሳቢ አዝማሚያዎች በመጠበቅ ነፃ በማድረግ ላይ ያሳየው ቸልተኝነት፣ ኪራይ ሰብሳቢነት በመንግሥትም ሆነ ከመንግሥት ውጪ ባሉ ኃይሎች ከልክ በላይ ገዝፎ ሥርዓቱን የሚፈታተን አደጋ እንዲሆን በር ከፍቷል ብሏል፡፡ መንግሥት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተገነባ በመጣው አገራዊ አቅም በመታገዝ መሠረተ ሰፊ የሆኑ ልማታዊ ተግባራትን የሚያከናውን ግዙፍ ተቋም ከሆነ በኋላ በኮንትራት አስተዳደር፣ በግዥ፣ በግብር አሰባሰብና በመሬት ዕደላና አጠቃቀም ለከፋ ሙስና የሚጋለጥበት ሁኔታ እየሰፋ መሄዱን አምኗል፡፡ ይህ አጋጣሚ ለመንግሥታዊ ኃላፊነት መብቃት ከፍ ያለ ጥቅም ለማጋበስ እንደሚረዳ በመተማመን ሥልጣን ለመያዝ የሚደረገውን ሩጫ አባብሶታል ሲል ኢሕአዴግ አስቀምጧል፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ያጋጠመው ፖለቲካዊ ቀውስ አንድ በአንድ ሲመረመር፣ እንደገና በጥልቀት የመታደስ እንቅስቃሴን የግድ የሚል ሁኔታ መፍጠሩን በስፋት ተንትኗል፡፡

በኢሕአዴግ ግምገማ መሠረት ፖለቲካዊ ቀውሱ ሰፊ የሕዝብ ቁጥር ባላቸው የአገሪቱ ክልሎች በርከት ባሉ ከተሞችና አንዳንድ የገጠር አካባቢዎች የተቀሰቀሰ ነበር፡፡ በእነዚህ አካባቢዎች በአብዛኛው ወጣቶች የተሳተፉበት ግጭት አዘል ፖለቲካዊ መነሳሳት መታየቱን፣ ለዚህ ሁኔታ መፈጠር መሠረታዊ ምክንያቶች ደግሞ ከላይ የተዘረዘሩት ችግሮች መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ምንም እንኳ በእነዚህ ግጭቶች የተከሰተውን ቀውስ መነሻ በማድረግ፣ በተለይ ጽንፈተኛ የዳያስፖራ ኃይሎች የራሳቸው የሥራ ውጤት እንደሆነ በማስመሰል ሲያቀርቡ የከረሙ መሆናቸውን፣ ችግሩ ግን በዋነኝነት ከሥርዓቱ ጋር የተያያዘና የዚሁ መገለጫ መሆኑን መጠነኛ ጥልቀት ያለው ትንታኔ በማካሄድ ለማረጋገጥ እንደማያስቸግር ገልጾ መሠረታዊ ድክመቶቹን ይተነትናል፡፡ ስህተቶቹንም ያወሳል፡፡ በዚህም ሳቢያ ወደ ዳግም ተሃድሶ በጥልቀት ተገብቷል ይላል፡፡

ኢሕአዴግ መቼም ቢሆን ለሚያጋጥሙት ችግሮች ውጫዊ ምክንያት ከመደርደር ይልቅ ወደ ውስጥ በመመልከት ራሱን በማረም ላይ የሚያተኩር ድርጅት መሆኑን በንድፈ ሐሳብ መጽሔቱ ቢገልጽም፣ በተደጋጋሚ ለሚነሱለት የሕዝብ ጥያቄዎች የሚሰጠው ዘገምተኛ ምላሽ ግን ለቀውሱ መባባስ ምክንያት መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ኢሕአዴግ ከዚህ በፊትም ችግሮች እንዳሉበትና ለማረም እንደሚሠራ ሲወተውት ይታወቃል፡፡ ትልቁ ችግር ግን ተግባር ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ችግሮች አጋጥመውት እውነቱን ቢናገርም፣ ችግሮቹን የፈታበት መንገድ ግን ከሕዝብ ጋር አላጣጣመውም፡፡  በተለይ ከሕዝብ ጋር ተቀራርቦ በመነጋገር ችግሮችን ከመፍታት ይልቅ፣ በተለመደው ድርጅታዊ አሠራር ላይ ብቻ በማተኮር የሕዝብን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማወቅ ተስኖታል፡፡ ከቀውሱ በፊት ሕዝብን የሚያማርሩ ጥቆማዎች በብዛት ሲደርሱት ችላ ከማለት አልፎ፣ የጠላት ወሬ በማስመሰል ሲያስተባብልም ይታወቃል፡፡ አሁንም ጥልቅ ተሃድሶ ላይ ነኝ ባለ ማግሥትም ከሕዝቡ ጋር በስፋት ሲገናኝ አይታይም፡፡ በአመራር ደረጃ ለውጥ ከማድረግና ሽግሽግ ከማካሄድ ውጪ፣ ሌላው ቀርቶ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ ከሕዝብ ጋር መነጋገር ተረስቷል፡፡ የሕዝብ ጥያቄ ግን አሁንም አለ፡፡ አሁንም ወጣቶች የሚያነጋግራቸው ይፈልጋሉ፡፡ በከተማም ሆነ በገጠር የሚኖረውን የአገሪቱን ሕዝብ የሚያስተዳድረው መንግሥት ፍላጎቱን ቀርቦ ካልተረዳው፣ ጥልቅ ተሃድሶም ተባለ ሌላ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ አሁንም ሕዝብን ማዳመጥ ተገቢ ነው፡፡

በአገሪቱ  የሥልጣን የመጨረሻው ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ላለፉት 25 ዓመታት የተጓዘበትን መንገድ ሲገመግምም ሆነ፣ ያለፉትን 15 ዓመታት በተመለከተ ጥልቅ ተሃድሶ ሲያካሂድ የሕዝብን ተሳትፎ ማሰብ አለበት፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ በተገደበበት ዕድገት ቢገኝ እንደ ስኬት ሊቆጠር አይገባም፡፡ ዕድገቱ ባለቤት ይፈልጋልና፡፡ በቅርቡ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተከሰተው ቀውስ  ገንፍሎ ወጣ እንጂ፣ ችግሩ የአጠቃላይ የአገሪቱ ሕዝብ መሆኑ ሊካድ አይገባም፡፡ ኢኮኖሚያዊ ዕድገቱ በዴሞክራሲያዊና በሰብዓዊ መብቶች መከበርና በተለያዩ ነፃነቶች ካልተደገፈ ሕዝብ ጥያቄ ማንሳቱን ይቀጥላል፡፡ ባለሥልጣናትን ከመለዋወጥና የመዋቅር ለውጥ ከማድረግ ባሻገር፣ ሕዝብ በማሳተፍ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ጥረት ካልተደረገ ኢሕአዴግ የሚለው ሁሉ ፉርሽ ይሆናል፡፡ ኢሕአዴግ ውስጡን በሚገባ መርምሮ ለመሠረታዊና ለሥር ነቀል ለውጥ ሊዘጋጅ ይገባል፡፡ ይህ ለውጥ አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲከፈት፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተግባር እንዲረጋገጡ፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን፣ ሙስና እንዲወገድ፣ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖር፣ ወዘተ የመሳሰሉትን ማካተት ይኖርበታል፡፡ ያኔ ጥልቅ ተሃድሶው በውጤታማነት ተጠናቅቆ ለብሔራዊ መግባባት አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢሕአዴግ የሕዝቡን ትክክለኛ ፍላጎት ማወቅ አለበት፡፡ ከላይ አመራሩ ጀምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ካድሬ ድረስ ስህተትን ከማመን በላይ፣ ሕዝብን በቀጥታ ማነጋገርና ለሕዝብ ፍላጎት ተገዢ መሆን ይለመድ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

በኦሮሚያ ክልል በስድስት ከተሞች የተዋቀረውን ሸገር ከተማን የማደራጀት ሥራ ተጀመረ

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ስድስት ከተሞች የተዋቀረው ሸገር ከተማን...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በኢትዮ ቴሌኮም ላይ ላደረሰው ኪሳራ ክስ ተመሠረተበት

ኩባንያው በግማሽ ዓመት ስምንት ቢሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ገልጿል ኢትዮ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጠጠር ገለልተኛ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

ከ70 በላይ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ዘርፉን ሊቀላቀሉ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...

እስቲ አንገፋፋ!

እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስንነት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው...

ሆድና የሆድ ነገር (ክፍል አንድ)

በጀማል ሙሀመድ ኃይሌ (ዶ/ር) "ሆድ ባዶ ይጠላል..." "ከሆድ የገባ ያገለግላል…” ከጥቂት ዓመታት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገር ሰላም እንዳይናጋ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግ!

የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንዲገታ ተደርጎ ጠባሳው ሳይሽር፣ አገርን ሌላ አስከፊ ቀውስ ውስጥ የሚከት የሃይማኖት ውዝግብ ተፈጥሯል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም አግኝታ...

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...