Thursday, February 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በ94 ዓመታቸው ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይቀርባሉ

ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ በ94 ዓመታቸው ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይቀርባሉ

ቀን:

ዚምባቡዌ እ.ኤ.አ. በ1980 ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ነፃ ስትወጣ ነበር የማርክሲዝም ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኙ ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ የአገሪቱ የመጀመሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ብቅ ያሉት፡፡ እ.ኤ.አ. እስከ 1987 በጠቅላይ ሚኒስትርነት ካገለገሉ በኋላ፣ ፓርቲ በማቋቋም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሥልጣን ላይ ይገኛሉ፡፡

ላለፉት 36 ዓመታት አገሪቱን በአንድ ፓርቲ ጥላ ስር የመሩት ፕሬዚዳንት ሙጋቤ፣ አገሪቱ እ.ኤ.አ. በ2018 በምታካሂደው ምርጫ ዕጩ ፕሬዚዳንት ሆነው እንደሚቀርቡ ፓርቲያቸው ዛኑ ፒ ኤፍ አስታውቋል፡፡ ወደ 93ኛ ዓመታቸው እያቀኑ ያሉት ሙጋቤም፣ በ94ኛ ዓመታቸው አገሪቱ በምታካሂደው ምርጫ ለመሳተፍ ፈቃደኝነታቸውን አሳውቀዋል፡፡

ፓርቲያቸው ዛኑ ፒ ኤፍ ባካሄደው ጉባዔ ፕሬዚዳንት ሙጋቤን ዕጩ ፕሬዚዳንት አድርጎ መምረጡን ያሳወቀ ሲሆን፣ የፓርቲው ወጣት ክንፍም ‹‹ሙጋቤ የሕይወት ዘመን ፕሬዚዳንት መሆን አለበት›› ሲል ገልጿል፡፡

የፓርቲው አባላት ውስጥ ለውስጥ በመከፋፈል አደጋ ላይ ቢሆኑም፣ በአገሪቷ በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ተደጋጋሚ ተቃውሞዎች ቢደረጉም፣ ፓርቲያቸው እሳቸውን ዕጩ ከማድረግም አልተቆጠበም፡፡

አንዳንዶቹ የፓርቲው አባላት ፕሬዚዳንት ሙጋቤ ከሥልጣን እንዲወርዱ ሲጠይቁ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ሙጋቤ በፓርቲ ውስጥ ያለውን መሰነጣጠቅ በማውገዝና አንድ ማድረጋቸውን በመደገፍ የእሳቸውን ቀጣይ ዕጩ ፕሬዚዳንት መሆን ደግፈዋል፡፡

በተለይ ሙጋቤ የሁልጊዜ ፕሬዚዳንት ለማድረግ የሚሠራው የፓርቲው ወጣቱ ክፍል፣ የሙጋቤን ዕጩ ፕሬዚዳንት መሆን በደስታ ተቀብሎታል፡፡

16ኛው የፓርቲው ዓመታዊ ጉባዔ ከደቡብ ሃራሬ 300 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ማስቪንጎ ባለፈው ዓርብ ሲከናወን የተገኙት ወጣቶት ‹‹ቶንጋይ፣ ቶንጋይ፣ ባባ›› ማለትም ‹‹አባታችን ምራን፣ ምራን›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ዕድሜ ከቸራቸው እ.ኤ.አ. በ2018 የ94 ዓመት የዕድሜ ባለፀግ የሚሆኑት ሙጋቤ ከፓርቲያቸው አባላት የተወሰኑት ከሥልጣን እንዲወርዱ ጥያቄ የነበራቸው ቢሆንም፣ በፓርቲው ውስጥ ያለው ‹‹ያለመስማማትንና ግጭትን የማስወገድ ስምምነት›› አስሯቸው የሙጋቤን ዕጩነት ተቀብለውታል፡፡

የፕሬዝዳንት ሙጋቤ ‹‹የአንድ ቤተሰብ አቋም››

ለፕሬዚዳንት ሙጋቤ አንድ መሆን ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ በፓርቲያቸውም ሆነ በአገራቸው ክፍፍልን አይፈቅዱም፡፡ የተለየ አቋም ያለውንም አይቀበሉም፡፡ ‹‹አንድ ቤተሰብ ነን›› የሚል አቋምም አላቸው፡፡ ፓርቲያቸው እሳቸውን እ.ኤ.አ. በ2018 ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲወዳደሩ ካጫቸው በኋላ ባደረጉት የይሁንታ ንግግርም ያንፀባረቁት ‹‹አንድ ነን›› የሚለውን ነው፡፡

በአንድ ፓርቲ ጥላ ሥር አገሪቷን ለ36 ዓመታት የመሩት ሙጋቤ፣ በፓርቲው ውስጥ የሚታየው መሰነጣጠቅ እንዲያበቃና በአንድ አቋም እንዲፀና ለአባላቶቻቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ግጭት እንዲያከትም ተስማምተናል፡፡ የውስጥ ለውስጥ ሽኩቻ ማብቃት አለበት፡፡ የፓርቲውን ርዕዮተ ዓለም መከተል ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አንድ እንሁን፣ እኛ አንድ ቤተሰቦች ነን፣ የዛኑ ፒ ኤፍ ፓርቲ ቤተሰቦች በአባላቱ መካከል ባለው መግባባት ላይ የተሳሰሩ ናቸው፤›› ያሉት ሙጋቤ፣ በአገራቸው የተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ የምዕራባውያኑ ሸፍጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 መጀመሪያ ላይ በአገሪቱ የነበረውን ተቃውሞ በማውሳትም፣ እንደ ዓረቦቹ አብዮት የዚምባቡዌ አብዮት እንደማይኖርም ከማስጠንቀቂያ ጭምር ተናግረዋል፡፡

በሴቶችና በወጣቶች ሊግ ጠንካራ ድጋፍ ያላቸው ሙጋቤ በአፍሪካ አንጋፋው መሪ ሲሆኑ፣ አገራቸው ከቅኝ ነፃ ከወጣች ጀምሮም አንዳንዴ በተረጋጋ አንዳንዴ ደግሞ በተቃወሰ ፖለቲካ አገሪቷን ሲመሩ ከርመዋል፡፡ በአገሪቱ አዲስና ነጮችን ሳይሆን የአገሪቱ ባለቤት የሆኑትን ጥቁሮች የሚደግፍ የመሬት ፖሊሲ መዘርጋታቸው፣ አገሪቱ በተለይ እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል፡፡

ነጭ ገበሬዎችን መሬት አልባ ያደረጉበት ሥርዓት አገሪቷን ከዳቦ ቅርጫትነት ወደ ምግብ አስመጪነት እንድትሸጋገር አድርጓል፡፡ ምንም እንኳን መሬት ለጥቁር ገበሬዎች ቢከፋፈልም፣ በሙጋቤ አቋም ሳቢያ ምዕራባውያኑ የፈጠሩባቸው ጫና ተደምሮ አገሪቱ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ሙጋቤ ባላቸው የአንድ ፓርቲ አገዛዝ አቋምም የሚቃወሟቸው ተሰደዋል፡፡ አገሪቱ የገጠማትን የኢኮኖሚ ቀውስና በሕዝቡ ላይ የተጋረጠውን የገንዘብ የመግዛት አቅም ማነስ በአብዛኛው የሚደጉሙትም በውጭ የሚኖሩ የአገሪቱ ዜጎች ናቸው፡፡

‹‹ሙጋቤ አንድ ቤተሰብ በሚል ሥልጣንን ያለመልቀቅ ፍላጎት እንጂ ለግሉ ገንዘብ የማካበት ፍላጎት የለውም›› ሲል የሚገልጻቸው የሰዎች ታሪክ ጸሐፊው ማሪቲን መርዲዝ፣ ሙጋቤ ከዓመት ዓመት ሥልጣናቸውን ለማቆየት ጉልበት መጠቀማቸው፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ማሽመድመዳቸው፣ ፍርድ ቤቶችን አለማክበራቸውና ነፃ ፕሬስን መደፍጠጣቸው እንደሚያስተቻቸው ይናገራል፡፡

የዛኑ ፒ ኤፍ እና የንኮሞ የዛፑ ፓርቲዎችን በማዋሀድ ጥምር መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ሕገ መንግሥት በ1980ዎቹ በአገሪቱ የተቀረፀ ሲሆን፣ በወቅቱም ለብዙ ጥቁር ዚምባቡዌያውያን የደመወዝ ጭማሪ እንዲደረግ፣ ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲሻሻል፣ የምግብ ድጎማ እንዲሰጥ አስችለዋል፡፡ ሆኖም በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል ግጭት በመፈጠሩና ሙጋቤም የንኮሞ ዛፑን ከጥምረቱ ካቢኔ ማስወጣታቸው የጎሳ ፀብ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ይህም አገሪቱን ያናጋት ሲሆን፣ የሙጋቤ ዕርምጃም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ቀስ በቀስ እንዲያሽቆለቁል፣ ነጮችም በብዛት ከዚምባቡዌ እንዲሰደዱ አድርጓል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን አገሪቱን ሙሉ ለሙሉ በፓርቲያቸው ሥር ማድረጋቸው ችግሩን አባብሷል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1987 የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ የአንድ ፓርቲ አመራር ሥርዓት የዘረጉት ሙጋቤ፣ የተለያዩ ፓርቲዎች የተሳተፉበት የ1990 ምርጫ ጣልቃ ገብነትና ብጥብጥን አስተናግዶ ሙጋቤ ተመርጠዋል፡፡ ሙጋቤ በአገሪቱ በተከናወኑ ምርጫዎች ሁሉ ሲያሸንፉ፣ ‹‹ያሸነፉት ምርጫ በማጭበርበር ወይም በጉልበት ነው፤›› እየተባሉ በምርጫ ታዛቢዎች ሲተቹም ነበር፡፡

ምዕራባውያኑ ዘረኞች ናቸው፣ ግብረ ሰዶማውያን አፍሪካን አይወክሉም፤›› በሚል አቋማቸው የሚታወቁት ሙጋቤ፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት ባገኟቸው መድረኮች በሙሉ ምዕራባውያንን ሳይተቹ አያልፉም፡፡ ለአፍሪካ መቆርቆዝም የምዕራባውያን ሸፍጥ እንዳለበት ሁሌም ይናገራሉ፡፡ በነጮች ላይ ባላቸው የአትድረሱብን ጠንካራ አቋም የሚገለጹ ሲሆን፣ በአገራቸው ውስጥ ሕዝቡን አንድ ከማድረግ አንፃር ሰብዓዊ መብትን ይረግጣሉ ተብለው ይተቻሉ፡፡ በመሆኑም የተቃወሟቸው ሲሰደዱ፣ በአገር ውስጥ የቀሩት ፓርቲ በመመሥረት በምርጫ ለመሳተፍ ሞክረዋል፡፡ የተሳካለት ግን አልነበረም፡፡

በወጣቶችና በሴቶች ‹‹የብዙዎች አባት›› የሚል ቅፅል የተሰጣቸው ሙጋቤ በሕመም ላይ እንደሚገኙ ቢነገርም፣ እ.ኤ.አ. በ2018 ምርጫ ዕጩ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲወዳደሩ ፓርቲያቸው አፅድቋል፡፡ ዕድሜ ከቸራቸውም በ94 ዓመታቸው አገሪቱን ለመምራት በምርጫ ይሳተፋሉ፡፡ ዋናው ችግር ግን ሙጋቤ በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ በብዛት ማንቀላፋታቸው ከወዲሁ እርጅና እየመጣባቸው ብቻ ሳይሆን፣ በቅርቡ መጃጀት ይጀምራሉም እያስባላቸው ነው፡፡ ደፋሩና ያመኑበትን ነገር በአደባባይ ከመናገር ወደኋላ የማይሉት ሙጋቤ ግን በ94 ዓመታቸው ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫው አለሁ ማለታቸው አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጠጠር ገለልተኛ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

ከ70 በላይ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ዘርፉን ሊቀላቀሉ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...

እስቲ አንገፋፋ!

እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስንነት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው...