Saturday, January 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየስደት ሌላው ገጽታ

የስደት ሌላው ገጽታ

ቀን:

  ‹‹ስቃዩ ሲበረታብኝ ያገቱኝን ሰዎች ግደሉኝ ወይም ራሴን ላጥፋ አልኳቸው፡፡ ከሞትኩኝ ቤተሰቦቼ ገንዘብ ስለማይሰጧቸው እሺ አላሉኝም፡፡ እንደኔ ያገቷቸውን ሰዎች ባጠቃላይ ሲደበድቡና ሲያሰቃዩ ለምን እግሬ ወደዚህ መራኝ ብዬ አዘንኩ፡፡ ቤተሰቦቼና ልጆቼም ናፈቁኝ፤›› ይህ ወደ የመን ለመሄድ አስቦ ከኢትዮጵያ ከወጣ በኋላ በረሃ ላይ በአጋቾች ተይዞ የነበረ ጎልማሳ ከተናገረው የተቀነጨበ ነው፡፡ ጎልማሳው አጋቾች በእሱና በሌሎችም ስደተኞች  የሚያደርሱትን ሰቆቃ ሲናገር እየዘገነነው ነው፡፡

‹‹የቀይ ባህር አካባቢ የምድር ላይ ሲኦል ነው፡፡ የአጋቾቹ ድብደባ ከአቅማቸው በላይ ሆኖ የሞቱና በረሃብ ሕይወታቸው የተቀጠፈ ብዙዎች ናቸው፡፡ ያንን ስቃይ ማንም እንዲያየው አልፈልግም፤›› የምትለው እንደ ጎልማሳው በበረሃ ታግታ የነበረች ወጣት ናት፡፡ ከሁለቱ በተጨማሪ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም የገጠማቸው ውጣ ውረድ ‹‹ፌልድ ኢስተርን ድሪምስ›› (የከሸፉ የምሥራቁ ዓለም ህልሞች) በተሰኘ አጭር ዘጋቢ ፊልም የቀረበው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ነበር፡፡

ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀንን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ ዐውደ ርዕይ 16 የሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡ የስደት ጽንሰ ሐሳብ በሥዕል፣ በቅርጽ፣ በቪዲዮ ኢንስታሌሽንና አኒሜሽን ፊልም ቀርቧል፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ፊልም በአጋቾች አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ኢትዮጵያውያን ሕይወትን ያሳያል፡፡ አካላቸው የጎደለ፣ ሰውነታቸው የተቃጠለ፣ የተደፈሩና ለሰው ህሊና የሚከብድ ሌላም ስቃይ የደረሰባቸው ብዙ ናቸው፡፡ ቤተሰባቸውን ትተው ከአገር ሲወጡ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ቢሆንም ዛሬ ኑሯቸው እንዳልነበር ሆኗል፡፡

አጋቾቹ ከስደተኞቹ ቤተሰቦች ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ዘቅዝቀው ከሰቀሏቸው፣  በእሳት ካቃጠሏቸውና ከደበደቧቸው መካከል በሕይወት የሚተርፉት ጥቂቱ ናቸው፡፡ ቤተሰቦቻቸው መሬት ወይም ያላቸውን አንጡራ ሀብት አሟጠው ሽጠው ለአጋቾቹ ገንዘብ ከፍለው የተለቀቁ፣ ገንዘብ በማጣት በአሰቃቂ ሁኔታ ለወራት በአጋቾቹ እጅ የቆዩም አሉ፡፡

‹‹እንደ እንስሳ የብረት አጥር ውስጥ እንቀመጣለን፡፡ ለቤተሰቦቻችን እየደወሉ እንደሚደፍሩን ወይም እንደሚገድሉን በመዛት ያስፈራራሉ፡፡ የውኃ መያዣ ላስቲክ እያቀለጡ ጓደኛህን አቃጥል ይላሉ፡፡ ሴቶችን ብልታችሁን እንቀዳለን እያሉ ያስፈራራሉ፡፡ ባልና ሚስት ለያይተው ይደፍራሉ፤›› ሲል ሰቆቃውን በፊልሙ የገለጸ ወጣት ነበር፡፡ ‹‹እናቴ ወደ ውጭ የላከችኝ ያላትን ነገር በሙሉ ሸጣ ነበር፡፡ ስታገት ልጅሽ በሕይወት እንድትተርፍ ገንዘብ ክፈይ ተባለች፡፡ በሁኔታው አዕምሮዬ ተረብሾ ራሴን ለማጥፋት ስሞክር ጓደኞቼ አተረፉኝ፡፡ እናቴም ገንዘብ ተበድራ ስትልክ ለቀቁኝ፤›› ያለችው በሁኔታው ቅስሟ የተሰበረ ወጣት ናት፡፡

የጉዞ ስቃዩ በረሃ ውስጥ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ወደ የመን፣ ሳዑዲ ዓረቢያ ወይም ሌላ አገር ከገቡ በኋላም መከራ የማይቀርላቸውን ለመቁጠር ያዳግታል፡፡ ስደተኞች በምሥራቁም ይሁን በምዕራቡ ዓለም በተለይም በፖሊሶች ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ ከስደት ጋር ተያይዘው የሚመጡ እነዚህ ችግሮች የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ጥያቄም ናቸው፡፡ በዘጋቢ ፊልሙና በሌሎቹም የሥነ ጥበብ ውጤቶች የቀረበው ጥያቄም ይኸው ነበር፡፡ ስደት ለምን በአሉታዊ ጎኑ ብቻ ይታያል? ስደተኞችስ ለምን ስቃይ ይደርስባቸዋል?

የዘንድሮው የዓለም የስደተኞች ቀን ‹‹ኤ ደይ ዊዝአውት ማይግራንትስ ኢዝ ኢምፖሲብል ቱ ኢማጅን›› (ስደተኞች የሌሉበትን ቀን ማሰብ አይቻልም) በሚል መሪ ቃል ታኅሣሥ 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ተከብሯል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በስደተኞች ቀን ማግሥት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ የስደተኞችን ደኅንነት በተሻለ መንገድ ስለመጠበቅ ውይይት ተደርጓል፡፡ ዓለም በምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ የሰዎች ከቦታ ወደ ቦታ የመዘዋወር ፍላጎት ከፍተኛ  ሲሆን፣ ሰዎች ከአገር አገር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከዓለም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ጋር ቀጥተኛ ትስስር አለው፡፡ ስደት በአሉታዊ ጎኑ ብቻ መታየቱ ግን ለስደተኞቹ ሕይወት መመሰቃቀል መንስዔ ሆኗል፡፡

አምና 224 ሚሊዮን ስደተኞች በዓለም ዙሪያ የተጓዙ ሲሆን፣ አሁን በሁሉም አገሮች ስደተኞች ይኖራሉ፡፡ ከስደተኞቹ 65 ሚሊዮን የሚሆኑት መኖሪያቸውን ያለፈቃዳቸው የለቀቁ ናቸው፡፡ በጦርነት፣ በድህነት፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና ሌሎችም ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ሳቢያ ከአገራቸው ለመውጣት ለሚገደዱ ስደተኞች ጥበቃ የማድረግ ጉዳይም የዘንድሮው ዓለም አቀፍ ስደተኞች ቀን ትኩረት ሆኗል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን ‹‹በዓለም የስደተኞች ቀን፣ ስደት በትክክለኛ መንገድ የሚከናወንና እንቅስቃሴውም ለሰላማዊና የበለፀገች ዓለም ግንባታ አስተዋጽኦ የሚያደርግ እንዲሆን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጥሪ አቀርባለሁ፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

 ከኢትዮጵያ አንፃር ስደትን በሥነ ጥበብ ለማሳየት በብሔራዊ ሙዝየም የተዘጋጀው ዐውደ ርዕይ፣ የስደተኞች ቀን መሪ ቃል መጠሪያው ሆኗል፡፡ በኢንተርናሽናል ኦርጋናይዜሽን ፎር ማይግሬሽን (አይኦኤም) የተዘጋጀው ዐውደ ርዕዩ ታኅሣሥ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. ሲከፈት፣ በተመስገን ልጆችና በራስ ማይኪ የተቀናበረ የዳንስ ትርዒት ቀርቦ ነበር፡፡ ከአቅም በላይ በሆነ ችግር የተከሰተና ሰላማዊ የሆነም ስደት፣ በአሉታዊ ገጽታቸው ብቻ እንደሚታዩ ተንፀባርቋል፡፡

በዶ/ር ደስታ መጎ  ኪውሬት የተደረጉ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ደግሞ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላው የሚደረግን የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ያሳያሉ፡፡ በአድም ይሁን በሌላ ምክንያት አገራቸውን የሚለቁ ግለሰቦች በጉዟቸው ወቅት እንዲሁም በመዳረሻቸው የሚገጥሟቸው ፈተናዎችም ቀርበዋል፡፡

የአይኦኤም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዓለማየሁ ሰይፈሥላሴ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ በዐውደ ርዕዩ ስደተኞች ለሚሄዱበት አገር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚያሳዩ ሥራዎች ቀርበዋል፡፡ በዐውደ ርዕዩ የተሳፉ ወጣትና አንጋፋ ባለሙያዎች ስደትን ስለሚመለከቱበት ሁኔታ የገለጹበት ቪዲዮ ታይቷል፡፡  በዐውደ ርዕዩ ከቀረቡ ሥራዎች መካከል በጨረታ ተሽጠው ገቢያቸው ስደተኞችን መልሶ ለሚያቋቁም ድርጅት የሚሆንም አሉ፡፡

ሥራቸውን ካቀረቡት ውስጥ ብርሃን ቶንጌ፣ ተስፋሁን ክብሩ፣ ደስታ ሐጎስ፣ ኤልሳቤጥ ኃብተወልድ፣ ቆንጂት ሥዩም፣ ክብሮም ገብረመድኅንና ዮናስ ኃይሉ ይገኙበታል፡፡ የይስሃቅ ሳህሌ ‹‹ጆርኒ ቱኣ ኖውን›› (ወደ ማይታወቅ ቦታ) እና የበኃይሉ በዛብህ ‹‹ብሬን ድሬን›› (የተማረ ሰው ኃይል ፍልሰት ጉዞ) የተሰኙት ይጠቀሳሉ፡፡ ‹‹ውሳኔ›› በተሰኘው ቅርፅ፣ ግዙፍ መርከብ ላይ ለመውጣት የሚጣጣሩ ሰዎች ይታያሉ፡፡

ሠዓሊ ታዳኤል ንጉሥ፣ ሰዎች በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወይም ፖለቲካዊ ምክንያት መሰደዳቸው አይቀሬ ነው ይላል፡፡ ከቦታ ቦታ መዘዋወር ተፈጥሯዊና ማቆም የማይቻል ሒደት እንደሆነ ያምናል፡፡ ስደትን ጤናማ የማድረግ ጉዳይ ከተጓዦች ጀምሮ የዓለም ሕዝብ በአጠቃላይ ኃላፊነት ነውም ይላል፡፡ ‹‹ከቦታ ቦታ መዘዋወር ሰብዓዊ መብት ቢሆንም፣ ተጓዡ የሚሄድበት ቦታ ምን ሊገጥመው እንደሚችል አስቀድሞ መጠየቅ አለበት፡፡ ስደት በትክክለኛ መንገድ ካልተደረገ አስቸጋሪ ነው፤›› ሲል ይገልጻል፡፡

‹‹ቶይ ኢን ዘ ኦሽን›› (በባህር ውስጥ ያለ አሻንጉሊት) የተሰኘው ሥዕሉ እርቃኑን በባህር የሚንሳፈፍ አሻንጉሊት ያሳያል፡፡ ስለ ስደተኞች ሁኔታ በመገናኛ ብዙኃን ከሚመለከተውና ከሰው ከሚሰማው በመነሳት፣ ስደት የሚፈጥርበትን ስሜት የገለጸበት እንደሆነ ይናገራል፡፡ ዓለም ላይ ስደት በአሉታዊ ጎኑ ብቻ ስለሚታይ፣ ስደተኞችን የመቀበል ነገር አናሳ ነው፡፡ ስደተኞች የሚሄዱበትን መንገድ አውቀው መንቀሳቀስ ተቀባዮች ደግሞ ስደተኞችን በቀና መመልከት እንዳለባቸው ያስረዳል፡፡

‹‹ስደት የሚለው ቃል አሉታዊ ጎኑ ያመዝናል፡፡ ይህ እንዲሆን ያደረገው ደግሞ የሰው ልጅ ነው፡፡ ዓለም የሁላችንም እንደመሆኗ በነፃነት መንቀሳቀስ ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው፡፡ አሁን ግን ሰው ሠራሽ ድንበሮች ተበጅተው ተፈጥሯዊ እንቅስቃሴ እንደ መጥፎ ነገር እየታየ ነው፤›› የሚለው ሠዓሊው፣ ስደተኞች ከሚሄዱበት አገር እንደሚጠቀሙ ሁሉ አገሩም ከነሱ ስለሚጠቀም ሰብዓዊ ክብራቸው ሊጠብቅ እንደሚገባ ያክላል፡፡

ሠዓሊ አዲሱ ወርቁም ሐሳቡን ይጋራል፡፡ ‹‹ቻፕተር ዋን፣ ቱ ኤንድ ስሪ›› (ምዕራፍ አንድ፣ ሁለትና ሦስት) የተሰኙ ሥዕሎችን ያቀረበው ሠዓሊው፣ ስደት የሰው ልጅ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ያለ እንቅስቃሴ ነው ሲል ይገልጻል፡፡ ‹‹በተለያዩ ሃይማኖቶችም ብዙ የስደት ታሪኮች አሉ፡፡ የሰው ልጅ ከነበረበት የተሻለ ቦታ ለማግኘት ወይም በልዩ ልዩ ምክንያት ይሰደዳል፡፡ ሰዎች በችግር ተነሳስተው ወይም ያለምንም ምክንያት ወደ ሌላ አገር ሲጓጓዙ ግን ጉዳት ይደርስባቸዋል፤›› ይላል፡፡ በስደት ምክንያት ስለሚደርሰው ጉዳት የሚሰማውን ሐዘንም በሥራዎቹ ገልጿል፡፡

ሰዎች ከቦታ ቦታ አይዘዋወሩ ማለት ባይቻልም፣ ሲጓጓዙ የሚገጥሟቸውን ችግሮች መቅረፍ እንደሚቻል ያምናል፡፡ ስደተኞች በሚሄዱበት አገር ያለው ሁኔታ የተመቻቸ ካልሆነ ጉዳት ሳይደርስባቸው ወደ አገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበትም ይገልጻል፡፡ የዓለም ሕዝብ ባጠቃላይ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ለስደተኞች ጥበቃ እንዲደረግም በሥራዎቹ ይጠይቃል፡፡

አይኦኤም በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ በዓለም ከሰባት ሰዎች አንዱ ከተወለደበት አካባቢ ወጥቶ የሚማር፣ የሚሠራ ወይም ቤተሰብ መሥርቶ የሚኖር ስደተኛ ነው፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በየሁለት ሰዓቱ በአማካይ አንድ ወንድ፣ ሴት ወይም ሕፃን ስደተኛ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በዚህ ዓመት ብቻ 7,000 ስደተኞች የሞቱ ሲሆን፣ የት እንደደረሱ የማይታወቁም ሰዎች  አሉ፡፡ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ቀን በመላው ዓለም ሲከበር፣ የሕዝቦችና መንግሥታትን ትኩረት ወደ ስደተኞች ለማዞር ነው፡፡ ስደትን እንደ አሉታዊ እንቅስቃሴ ከመመልከት አወንታዊ ገጽታው እንዲታይ  የማድረግ ዓላማም ተይዟል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቅዱስ ሲኖዶስ ሦስቱን ጳጳሳት ስልጣነ ክህነታቸውን አንስቶ አወገዘ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ሰሞኑን ጥር 14...

አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ አባልነት ለቀቁ

አንጋፋው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ እየሱስወርቅ ዛፉ ከህብረት ባንክ ቦርድ...

አቶ በረከት ስምኦን ከእስር ተፈቱ

ከአራት ዓመታት በፊት በተከሰሱበት በከባድሙስና ወንጀል ስድስት ዓመታት ተፈርዶባቸው...

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው እንደገቡ የፖለቲካ አማካሪያቸው ስለ ሰሜኑ ግጭት የሰላም ስምምነት አተገባበር ማብራሪያ ለመጠየቅ ገባ]

ክቡር ሚኒስትር ጥሰውታል? እንዴ? እስኪ ተረጋጋ ምንድነው? መጀመርያ ሰላምታ አይቀድምም? ይቅርታ...