Sunday, April 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልያልተመለሱ የቅርስ ጥበቃ ጥያቄዎች

ያልተመለሱ የቅርስ ጥበቃ ጥያቄዎች

ቀን:

  ከአሥራ አንዱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አንዱ ቤተ ገብርኤል ሩፋኤል እድሳት ተደርጎለት የተጠናቀቀው አምና ነበር፡፡ ቤተክርስቲያኑ ከሁለት ዓመት በፊት ከአሜሪካ መንግሥት በተገኘ የ14 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ታድሷል፡፡ ለቤተ ጎልጎታ ሚካኤል አብያተ ክርስቲያናት እድሳት እንዲደረግ የ500 ሺሕ ዶላር ድጎማ የተሰጠው ደግሞ ታኅሳስ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡

ቅርሶችን ለመጠበቅ፣ ዕድሜያቸው ሲገፋ ለማደስ እንዲሁም ሲጎዱ ለመጠገን የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ረገድ ዓለም አቀፍ ተቋሞችና የኢትዮጵያ መንግሥትም ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በመዝገቡ ላሰፈራቸው ግዙፍነት ያላቸውና ግዙፍነት የሌላቸው ቅርሶች ድጎማ ያደርጋል፡፡ እንደ አሜሪካ መንግሥት በራሳቸው ተነሳሽነት ድጋፍ የሚሰጡም አሉ፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ከዚህ ቀደም ለዘጠኝ የኢትዮጵያ ቅርሶች እድሳት የሚውል ድጋፍ አድርጓል፡፡

ስለ ቅርስ ጥበቃና እድሳት ሲነሳ ከሚሰነዘሩ ጥያቄዎች መካከል መሰል ድጎማዎች የሚደረጉት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ላላቸው ቅርሶች ብቻ ነው ወይስ ሰፊ ዕውቅና ያላገኙትንም ያማክላሉ? የሚለው ነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግዙፍነት ያላቸው ቅርሶች ጥበቃ ሳይደረግላቸው ወይም ጥገና በሚያስፈልጋቸው ወቅት ሳያገኙ በመቅረት ሲጠፉ ተስተውሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሌላው ከልማት መስፋፋት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ግንባታዎች በዕድሜ ጠገብ ቅርሶች ላይ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተፅዕኖ ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ቅርሶችን በመጠበቅ ረገድ ምን ያህል ተሠርቷል? በቸልታ ምክንያት የታጡ ቅርሶችስ የሉም?  የልማት መስፋፋትና ቅርስ ጥበቃ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እየሄዱ ነውን?  የሚሉ ጥያቄዎች ያነሳሉ፡፡

በቅርስ ጥናት ጥበቃ ባለሥልጣን አዳራሽ በአሜሪካ መንግሥት ለቤተ ጎለጎታና ቤተ ሚካኤል የገንዘብ ድጋፍ በተደረገበት ዕለት በተከፈተው የሁለት ቀናት ዐውደ ጥናት እነዚህ አስተያየቶች ተደምጠዋል፡፡ በአውድ የታደሙ ከየክልሉ የተውጣጡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሙያዎች እንዲሁም መምህራንና ተማሪዎች፣ ግዙፍነት ለሌላቸው ቅርሶች ስለሚደረገው እንክብካቤና እድሳት ተወያይተዋል፡፡

በተለይም ከክልል ከተሞች የተውጣጡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሙያዎች፣ በዩኔስኮ ከተመዘገቡና ባይመዘገቡም በስፋት ከታወቁ ቅርሶች ውጭ ያሉት መዘንጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ አንድ ከኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የመጡ ባለሙያ፣ የጥንታዊ የሐርላ አስተዳደር ግንብ ፈራርሶ እያለቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ግንቡን በማፈራረስ ለቤት ግንባታ የሚያውሉ ግለሰቦች እንዳሉና በአፋጣኝ መፍትሔ ሊሰጣቸው ከሚገባ አካባቢዎች አንዱ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የሐርላ ጉዳይ እንደ ማሳያ ይጠቀስ እንጂ በሌሎችም አካባቢዎች እንዳልነበሩ የሆኑ ቅርሶች ብዙ ናቸው፡፡

ጥበቃ ሊደረግላቸው ሲገባ ከልማት መስፋፋት ጋር በተያያዘ ጉዳት የደረሰባቸው ቅርሶችም አሉ፡፡ ስለ ቅርሶች ጥበቃና እድሳት ሲነሳ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ቁጥር ውስንነትም ይጠቀሳል፡፡ ተባባሪ ፕሮፌሰር ፋሲል ጊዮርጊስ በወርክሾፑ ባቀረቡት ጥናት፣ በልማትና በቅርሶች ጥበቃ መካከል ሚዛናዊ አካሄድ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡ አገሪቱ ካለችበት ፈጣን ለውጥ ጋር በተያያዘ የሚከናወኑ ግንባታዎች የቅርሶችን ህልውና ከጥያቄ የሚከቱ መሆን እንደሌለባቸው ይናገራሉ፡፡ መጠበቅ የሚገባቸው ቅርሶች እንክብካቤ እንደሚያሻቸውና በልማት ምክንያት የሚነሱ ታሪካዊ አካባቢዎች ደግሞ መሰነድ (ዶክመንት መደረግ) እንደሚያስፈልጋቸውም ያክላሉ፡፡

‹‹ግዙፍነት ያላቸው ቅርሶች ሲፈርሱ ስለ ቅርሶቹ የሚገልጽ መረጃ መሰብሰብ አለበት፡፡ ታሪኩ ለቀጣዩ ትውልድ የሚተላለፈው ሰነዶቹ ሲቀመጡ ነው፤›› ሲሉ ይገልጻሉ፡፡ ስለ ቅርሶቹ የሚያስረዱ ሰነዶችን ለማዘጋጀት የሚያስፈልገው ያህል የተማረ የሰው ኃይል አለመኖሩ ግን እንደ ተግዳሮት ይነሳል፡፡ የሔሪቴጅ ኮንሰርቬሽን ትምህርት በሁለተኛ ዲግሪ መሰጠት የጀመረው በቅርቡ ሲሆን፣ የዘርፉ ባለሙያዎች ብዙም ዕውቅና ባላገኙ አካባቢዎች እየሄዱ ስለ ቅርሶቹ ጥናት በማድረግ ረገድ አመርቂ ሥራ አልተሠራም ይላሉ፡፡

ዘንድሮ በሔሪቴጅ ኮንሰርቬሽን በሁለተኛ ዲግሪ የሚመረቁ ስምንት ተማሪዎች ወደ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በመሄድ ነበር ጥናት የሠሩት፡፡ በላሊበላ ቆይታቸው ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ያነሷቸውን ችግሮች ማስተዋላቸውን ተናግረዋል፡፡ ቅርሶችን ለመጠበቅ እንዲሁም አደጋ ሲገጥማቸው እድሳት ለማድረግ በቅድሚያ ስለ ቅርሶቹ የተሠራ ጥናት ቢያስፈልግም፣ ብዙ ቅርሶች አልተጠኑም፡፡ ከዐውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል በየአካቢያቸው ያሉ ግዙፍነት ያላቸው ቅርሶችን በመጠቆም እንዲጠኑላቸው የጠየቁም ነበሩ፡፡

በቅርሶች ዙሪያ የሚሠሩት ጥናቶች ከመማሪያና ማስተማሪያነት ባለፈ ለመንግሥት ተቋሞች በግብዓትነት መቅረብ አለባቸው የሚል አስተያየትም ተሰጥቷል፡፡ የቅርስ ጥበቃና ጥገና ሙያዊ ሒደትን የተመረኮዘ እንዲሆን በትምህርት ተቋሞችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መካከል የመረጃ ልውውጥ እንደሚያስፈልግም ተመልክቷል፡፡

ተባባሪ ፕሮፌሰሩ ከቅርስ ጥበቃ ጎን ለጎን በእድሳት ረገድ፣ ቅርሶችን አድሶ ለተለያየ አገልግሎትና ጥቅም ማዋል መለመድ እንዳለበት ያስረዳሉ፡፡ ቅርሶችን ከማፍረስ፣ እድሳትና ጥገና በማድረግ ቀድሞ ከነበራቸው አገልግሎት የተለየ እንዲጠሱ ማስቻል ይመረጣል፡፡ ለምሳሌ የቀድሞ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ መኖሪያ ቤት እድሳት ተደርጎለት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዴሚ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ቅርሶችን አድሶ በነባራዊ ሁኔታ ማኅበረሰቡ የሚጠቀምባቸው በማድረግ ረገድም ይጠቀሳል፡፡

የቅርሶች ጥበቃ ጉዳይ በመንግሥት ወይም በበጎ አድራጊዎች ችሮታ ብቻ ግቡን ስለማይመታ፣ የማኅበረሰቡን  ተሳትፎ ማሳደግ የግድ ይላል፡፡ ግዙፍነት ባላቸው ቅርሶች አቅራቢያ ያለው የማኅበረሰብ ክፍል ቅርሶቹ ስላላቸው ዋጋና እንዴት መጠበቅ እንደሚቻል ግንዛቤ መጨበጥ አለበት፡፡ የቅርሶች ጥበቃ የአካባቢውን ማኅበረሰብ ያማከለ ሲሆን ቀጣይነቱንም ማረጋገጥ ይቻላል፡፡

ማኅበረሰቡ ቅርሶችን እንዲጠብቅ ከሚበረታታባቸው መንገዶች አንዱ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ ነጋሽ መስጊድ ውስጥ በቱርክ መንግሥት የሚደገፍ ፕሮጀክት እየተካሄደ ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች የዕደ ጥበብ ውጤታቸውን የሚያሳዩበት ቦታም አለ፡፡ የአንድ አካባቢ ነዋሪዎች ግዙፍነት በሌላቸው ቅርሶች ምን ያህል ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ሲገነዘቡ፣ ለቅርሶቹ የሚያደርጉት እንክብካቤ ይጨምራል፡፡

በቅርሶች ጥበቃና ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸው ዙሪያ ጥናት ያቀረቡት አቶ ፋሲል አየሁ፣ ቅርሶች የሚያስገኙት ገቢ ከሚደረግላቸው ጥበቃ ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ቅርሶች የአንድን ማኅበረሰብ ታሪክና ማንነት በማሳየት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ለቅርሶቹ ግንባታ የዋሉት ቁሳቁሶችና አሠራራቸው ለዘመናዊ ሥነ ሕንፃ መማሪያም ነው፡፡ ቅርሶች ለሚገኙበት አካባቢ ነዋሪዎች ሥራ ከመፍጠር ጀምሮ ለአገር ውስጥና የውጪ ኢንቨስትመንት መስፋፋትና የቱሪዝም ዕድገት ያላቸው አስተዋጽኦም ይጠቀሳል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ቅርሶችን ለመንከባከብና ለመጠገን የሚወጣው ወጪ ከቅርሶቹ ከሚገኘው ገቢ ጋር ቀጥተኛ ትስስር እንዳለውም አቶ ፋሲል ይገልጻሉ፡፡ ለቅርሶቹ ጥበቃ ሲደረግ ሁሉንም አካባቢዎችን ያማከለ መሆን ቢገባውም በአስቸኳይ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ግዙፍነት ያላቸው ቅርሶች ትኩረት ተነፍገው ይታያል፡፡ ስለ ቅርስ ጥበቃ ሲነገር በተደጋጋሚ የሚጠቀሱ ቅርሶችም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ፣ ጥበቃ እየተደረገላቸው ያሉ ቅርሶች ጥቂት እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ጥበቃ የሚደረግላቸው እንደ ላሊበላና አክሱም ያሉ ዕውቅ ቅርሶች ናቸው፡፡ ሌሎቹን ቅርሶች ከማድነቅ ባለፈው በቂ ሥራ አልተሠራም፤›› ሲሉም ይገልጻሉ፡፡

ለቅርሶች ጥበቃ ወይም ጥገና ማድረግ ሲያስፈልግ የዕርዳታ አድራጊዎች ትኩረት የሆኑት በዩኔስኮ የተመዘገቡ ቅርሶች ስለሆኑ ዘወትር ስለነሱ ይወራል የሚሉት አቶ ዮናስ፣ ስለተቀሩት ቅርሶች ህልውናም ይጠይቃሉ፡፡

በእርግጥ የአገሪቱ ሕገ መንግሥትና የባህል ፖሊሲውም መንግሥትና ማኅበረሰቡም ቅርሶችን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያትታሉ፡፡ ወደ 3,000 ዓመታት የሚጠጋ ታሪክ ያላት አገርን ግዙፍነት ያላቸውም ይሁን ግዙፍነት የሌላቸው ቅርሶች አንድ ትውልድ በሚያወጣው ገንዘብ ብቻ መጠበቅ ቢከብድም፣ በተቻለው መጠን በሁሉም እንዲረባረብ ጠይቀዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ በቅርስ ጥበቃና እድሳት ረገድ ከሚገጥሙ ዋና ዋና ችግሮች መካከል፣ ሥራው ከፌዴራል መንግሥት ወደ ክልሎች ወርዶ አለመታየቱ ችግር ነው፡፡ ቅርሶቹ በሚገኙባቸው አካባቢዎች የባለሙያዎች እጥረት ከመኖሩ ባሻገር፣ የቅርሶቹ ጥበቃ የማኅበረሰቡን ተሳትፎ ያማከለ አይደለም፡፡ አቶ ዮናስ፣ በልማትና በቅርስ ጥበቃ መካከል ያለው ሚዛን መጠበቅ እንዳለበት ይስማሙበታል፡፡ ‹‹የልማትም የቅርስ ጥበቃም ጥያቄ አለብን፡፡ ሁለቱን እንደየአስፈላጊነቱ ማመጣጠን ይገባል፤›› ይላሉ፡፡

ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ አስተያየት ሰጪዎችም በተመሳሳይ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በመንግሥት ትልልቅ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሁም ማኅበረሰቡ ለግብርና፣ ግጦሽና ሌሎችም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቹን ሲያከናውን የቅርሶችን ደኅንነት ታሳቢ በማድረግ እንዲሆን የጠየቁ ነበሩ፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ቅርሶች አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ በአጽንኦት የተናገሩም ብዙ ናቸው፡፡

አቶ ዮናስ በበኩላቸው፣ በአፋጣኝ ጥገና የሚያስፈልጋቸው ቅርሶች መለየት እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ ቅርሶች በሚገኙባቸው ነባራዊ ሁኔታ ተመዝነው ለእድሳት ቅደም ተከተል ሊሰጣቸው እንደሚገባም ያክላሉ፡፡

በቅርስ ጥበቃና እድሳት መንግሥት ሁሉንም የኢትዮጵያ ቅርሶች እኩል ቢመለከትም፣ ከዕርዳታ ሰጪዎች የሚመጣው ገንዘብ በዕውቅ ቅርሶች ሊያተኩር ይችላል፡፡ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሰው ደግሞ ቤተ ገብርኤል ሩፋኤል ቤተክርስቲያን እድሳት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በታቀደው መንገድ እንደተጠናቀቀ ገልጸው፣ ቀጣዩ ሥራ የሚሆነው ቤተ ጎለጎታ ሚካኤል ቤተክርስቲያን  ነው ብለዋል፡፡

የቤተክርስቲያኑ እድሳት ዩኤስ አምባሳደርስ ፈንድ ፎር ካልቸራል ፕሪዘርቬሽን (ኤኤፍሲፕ) ከያዛቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ነው፡፡ አሜሪካ በተመሳሳይ መንገድ ከ100 በላይ አገሮች የምትረዳ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ከታደሱ ቅርሶች መካከል ሐረር የሚገኘው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቤተ መንግሥትና የሼክ ኑር ሁሴን ቅዱስ ቦታ ይጠቀሳሉ፡፡

ለቤተ ጎልጎታ ሚካኤል ገንዘቡ በተሰጠበት ወቅት የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ፒተር ቮሮማን፣ ቅርሶችን መጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ታሪክ የሚቀመጥበት መንገድ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡ የወርልድ ሞኑመንትስ ፈንድ ፕሮግራም (ደብሊውኤምኤፍ) ከሰሃራ አፍሪካ በታች ያሉ አገሮች ዳይሬክተር ስቴፈን ባትል በበኩላቸው፣ የአንድ አገር ቅርሶች የአገሪቱ ዜጎች ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም መገለጫ በመሆናቸው ለጥበቃቸው መረባበረብ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶ/ር ሒሩት ወልደማርያም የኢትዮጵያን ቅርሶች ለመጠበቅ በውጪ ተቋማት የሚደረገውን ጥረት አመስግነው፣ ጎን ለጎን የባለሙያዎች እጥረትና የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማነስ ችግሮች መፈታት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...