የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለፌዴራላዊ ሥርዓት ምሥረታ መሠረት ሲሆን፣ ብሔርና ብሔረሰቦችን የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ያደርጋል፡፡ በዚህም የተነሳ ከግለሰቦች መብት ይልቅ የቡድን መብትን ያስቀድማል፡፡ የቋንቋ፣ የብሔርና የሃይማኖት ብዝኃነት ትኩረት ካገኙ ጉዳዮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀ እነሆ 22 ዓመታት አለፉ፡፡ ዘንድሮ በታሪካዊቷ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ከተማ ሐረር ተከብሮ የዋለው ኅዳር 29 የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ሲሆን፣ ይኸው ሕገ መንግሥት የፀደቀበት ቀን ነው፡፡
የፌዴራሊዝም ሥርዓት በኢትዮጵያ ሲታወጅ ዕልል ብለው የተቀበሉ ያሉትን ያህል፣ ሥርዓቱ እንግዳ የሆነባቸውም ጥቂት አልነበሩም፡፡ ባህላቸውና ቋንቋቸው ተዘንግቶና ተረስቶ፣ በማንነታቸው እንዲያፍሩ መደረጋቸውን የሚያስቡ ወገኖች በፀጋ ሲቀበሉት፣ በቀደሙት ሥርዓት አካላትና በሌሎች ወገኖች ደግሞ እንደ አጥፊና አፍራሽ ዕርምጃ ታይቶ ነበር፡፡ ሥርዓቱን ከሚደግፉ ምሁሯን መካከል የሆኑት ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ፣ ‹‹በአምባገነኑ ውድቀት ዋዜማ የነበሩት ተቃውሞዎች ታሪክና ማንነት፣ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በምታደርገው ሽግግር ዋና የፖለቲካ መሣሪያ በብሔር ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝም ሥርዓት መሆኑን ያሳያል፤›› ብለው ነበር፡፡
የፌዴራል ሥርዓቱን ከሚቃወሙት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ተሠራበት ብለው የሚያምኑትን አስኳል እንዳፈረሰ የሚሰማቸው አሉ፡፡ ሥርዓቱን በታኝ፣ ፀረ አንድነት፣ ፀረ ኢትዮጵያዊ አድርገውም ይሥሉታል፡፡ በእርግጥ የቀድሞዋ ኢትዮጵያ ‹‹የብሔረሰቦች እስር ቤት›› ነበረች ብለው የጻፉ ያሉትን ያህል፣ እነዚህ የአዲሱ ሥርዓት ተቃዋሚዎች ዘረኝነት፣ ጠባብነትና የመሳሰሉ ቅፅሎችን ለአዲሱ ሥርዓት ሲሰጡ በተደጋጋሚ ተሰምተዋል፡፡
በወቅቱ ከወጡ የፕሬስ ኅትመቶችና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች ማረጋገጥ እንደሚቻለው፣ የአዲሱ ሥርዓት አመንጪዎችም ሥርዓቱን ለመከላከል ተቃዋሚዎቻቸውን ‹‹ጠላቶች››፣ ‹‹የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂዎች›› እና ‹‹ትምክህተኞች›› የመሳሰሉ አጠቃቀሞች ያዘወትሩ ነበር፡፡ የቃላት ጦርነቱ ዛሬም ድረስ የተጠናቀቀ ባይሆንም፣ በ1997 ዓ.ም. አወዛጋቢ ምርጫ የከፍታውን ጫፍ ነክቷል፡፡
ራሳቸውን እንደ አሸናፊና ተሸናፊ አድርገው የሚቆጥሩ ኢትዮጽያዊያን ልሂቃን ስለአንድነት ያላቸው አመለካከት ፅንፍ እንዲይዙ ያደረጋቸው ይመስላል፡፡ ከዚህ የሚመነጨው አስተሳሰብ አንዱ ሌላውን ለመጣል የሚጠቀምበት መንገድ ተደርጎም ይታያል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራሊዝም ከየት ወዴት?
በደርግ ሥርዓት መጨረሻ አዲሱ የኢሕአዴግ ሥርዓት አዲስ የአገር ግንባታ ፕሮጀክት ይዞ ቢመጣም፣ አገሪቱን ከመበታተን ይታደጋል ብሎ የሚያምን እምብዛም አልነበረም፡፡ አዲሱን የፌዴራል ሥርዓት እንደ ጦር የፈሩት፣ ዛሬም ድረስ የኢትዮጵያ አንድነት ፀር አድርገው ይመለከቱታል፡፡ በተለይ ደግሞ የፌዴራል ሥርዓቱ ዋና መሠረት ብሔር መሆኑ፣ ኢትዮጵያ የዩጎዝላቪያ ዕጣ ፈንታ እንዳይገጥማት ሥጋታቸው ከፍ ያለ ነበር፡፡
የአገሪቱ ህልውና ግን እንደተፈራው ችግር አልገጠመውም፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ እንደተፈራው ኢትዮጵያን አልበተናትም፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት በጉዳዩ ላይ ተጠይቀው ምላሽ ሲሰጡ፣ ‹‹ኢትዮጵያ የቆመችው አሸዋ ላይ አይደለም፡፡ በዚሁ ሥርዓት ከተበታተነች ግን ድሮም መሠረቷ የተናጋ ነበር፤›› ብለዋል፡፡
ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ ኤርትራ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በቀላሉ ብትገነጠልም፣ ጨቋኝ ከሚሏት አገር ለመገንጠል ሲታገሉ የነበሩ ሌሎች ኃይሎች ሳይቀሩ፣ በሒደቱ ተሳታፊ ሆነው ሕዝባቸውን አሳምነው በኢትዮጵያ ጥላ ለመቀጠል ወስነዋል፡፡
ለኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሠረት የሆኑት የለንደኑ፣ የፓሪሱና የአዲስ አበባው ጉባዔዎች ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ የቀድሞ ኤፌዴሪ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በሜሪላንድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮግራም ላይ ተገኝተው በሰጡት ገለጻ፣ በተደረጉ ሕዝባዊ ውይይቶችና ጥናቶች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለሚሰጠው አዲሱ ሥርዓት የተለያዩ ክልሎች ድጋፋቸውን ከፍ ያለ ነበር ብለዋል፡፡ ሥርዓቱ ዝቅተኛ ድጋፍ ያገኘው በአዲስ አበባ (67 በመቶ) እና በጋምቤላ (59 በመቶ) ነበር፡፡ ከፍተኛውን ድጋፍ ያገኘው በአፋር (97 በመቶ) እና በኦሮሚያ (95 በመቶ) ነበር ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በእርግጥ ሕዝባዊ ድጋፋቸውን ምን ድረስ እንደሆነ መገመት ባይቻልም፣ ዛሬም ድረስ ግን በተለያዩ አካባቢዎች እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ ለማስገንጠል ጫካ የገቡ አሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በአገሪቱ ፓርላማ በሽብርተኝነት የተፈረጁት ኦብነግና ኦነግ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ አገር ግንባታ ሥርዓት ተቃርኖ በተቃዋሚዎችና በገዢው ፓርቲ በኢሕአዴግ ብቻ የሚስተዋል አይደለም፡፡ በተቃዋሚዎች መካከል የእርስ በርስ ሽኩቻ ሲፈጥርም ይስተዋላል፡፡ ኅብረ ብሔራዊ አደረጃጀት ይዘው የተዋቀሩና አንድነትን የሚያስቀድሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ብሔርን መሠረት አድርገው የተመሠረቱትን ቁጥር አንድ ጠላት አድርገው ይመለከቷቸዋል፡፡
ሁለቱም ዓይነት ፓርቲዎች አብረው ገዢውን ፓርቲ የሚፋለሙበት ‹‹አማካይ›› ሥፍራ እንዲፈጥሩ፣ የኢሕአዴግ መሥራችና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ስዬ አብረሃ ባቀረቡት ጥናት መክረው ነበር፡፡ ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ጋር በመሆን አቶ ስዬ አንድነት ለፍትሕና ለዴሞክራሲ ፓርቲን ተቀላቅለው መድረክ የተሰኘ ስብስብ መፍጠራቸው የሚታወስ ነው፡፡ የማታ ማታ ግን ቀድሞም በአቋም እሳትና ጭድ ናቸው ተብለው ሲተቹ የነበሩት አንድነት መድረክም ተለያይተዋል፡፡ በኋላ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሁለቱም የቀድሞ የኢሕአዴግ ሰዎች አንድነትን ጥለው ወጥተዋል፡፡ አቶ ስዬ አሁንም ድረስ በጉዳዩ ላይ የሰጡት አስተያየት ባይኖርም፣ ዶ/ር ነጋሶ ግን ከአንድነት አራማጅ ኃይሎች ጋር በጋራ መሥራት አይቻልም የሚል አስተያየት መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡
በውጭ ያሉት አክራሪ ተብለው የሚፈረጁት የዳያስፖራ ተቃዋሚዎችም አገር ውስጥ ካሉት በላይ የተለያየ ፅንፍ የያዙ እንደሆኑ የሚነገር ሲሆን፣ አልፎ አልፎ የኢሕአዴግን መንግሥት ለመጣል ብቻ የመተባበር መንፈስ ያሳያሉ፡፡ ለአንዳንድ የፖለቲካ ታዛቢዎች ግን ትብብሩ ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› ከሚል መርህ ውጪ አንዳችም መሠረት የለውም፡፡
የአንድነትና የብዝኃነት ገጽታ
ሚሊዮን ሺበሺ የተባሉ ጸሐፊ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ብዙ ጊዜ የመንግሥት አቋም በሚንፀባረቅበት ‹‹አጀንዳ›› ዓምድ ላይ ‹‹ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም›› በሚል ጽሑፋቸው፣ ‹‹በፌዴራላዊ የመንግሥት አወቃቀር ዕይታ አንድነት ወይም ኅብረት ማለት ብዝኃነትን በማክበርና በጋራ ጥቅምና ፍላጎት ላይ በመመሥረት አብሮ የመቀጠል ውሳኔ (ውል) ስምምነት ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ቀጥለውም ብዝኃነትን መሠረት አድርጎ የሚዋቀር የፖለቲካ ሥርዓትን ደግሞ ኅብረ ብሔራዊ የፌዴራል ሥርዓት እንደሚባል ይገልጹታል፡፡ በባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት የፌዴራል ሥርዓቱን ስኬት በሚያጎላው ጽሑፍ፣ የመሠረት ልማትና የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች መመለስና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ዕውን እንዲሆን ማስቻሉን ያትታሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በዘንድሮ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል ላይ ተገኝተው ባሰሙት ንግግር፣ ‹‹የፌዴራል ሥርዓቱ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተላበሰና አንድነትን መሠረት ያደረገ ነው፤›› በማለት ከተለመደው ወጣ ያለ አስተሳሰብ አራምደዋል፡፡ በመንግሥት ደረጃ የአቋም ለውጥ እየተደረገ ስለመሆኑ ማሳያ መስሏል፡፡
በቅርቡ መንግሥታቸው ያደራጀው አዲሱ ካቢኔ፣ ከዚህ በፊት ከተለመደው የ‹‹ብሔር ውክልና›› እና ‹‹የፖለቲካ ታማኝነት›› መሠረት ያደረገ ሹመት በአመዛኙ በመሸሽ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግርም ከዚህ በፊት ወደ ልዩነት ያደላል ተብሎ ሲታማ የነበረውን ብሔር ተኮር ፌዴራሊዝም ወደ ‹‹ኅብረ ብሔራዊነት›› እያመራ ነው ወይ የሚል ውይይት እያጫረ ነው፡፡
‹‹ኅብረ ብሔራዊ›› ጽንሰ ሐሳብን ብዙ ጊዜ የብሔር ተኮር አደረጃጀት በመቃወም አንድነትን የሚያራምዱ ወገኖች ሲጠቀሙበት የኖረ አገላለጽ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም ሆነ የመንግሥት ሚዲያዎች በብዛት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በኢቢሲ በተላለፈው ዘጋቢ ፊልም ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና ኅብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝም›› የሚለው ይገኝበታል፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በበኩላቸው በዓሉን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ‹የአገራችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀደም ባሉት ዘመናት በመካከላቸው የነበረውን የተዛባ ግንኙነት በማረም፣ በመከባበር፣ በመቻቻልና በመፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በይበልጥ እያጎለበቱ ይገኛሉ፤›› ማለታቸው ይገኝበታል፡፡ ባለፉት 22 ዓመታት አገሪቱ በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስኬት ያስመዘገበች መሆኗን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ‹‹ይሁን እንጂ በእነዚህ ዓመታት የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የሃይማኖት አክራሪነት ዋና ዋና የህዳሴ ጉዞአችን ተግዳሮቶች ነበሩ፤›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
‹‹መልካም አስተዳደር›› እና ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› የመሳሰሉት በኢሕአዴግ መዝገበ ቃላት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ሲሆኑ፣ የፌዴራሊዝም ዋነኛ የማዕዘን ድንጋይ ከሆነው የአስተሳሰብ ልዩነት ይመነጫል ተብሎ የሚታመነው የብዙኃን ፓርቲ ፖለቲካ ጉዳይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩም፣ ፕሬዚዳንቱም ሆነ የኢሕአዴግ ደጋፊ ጸሐፊዎችም ሲያነሱት አይስተዋልም፡፡
ከ22 ዓመታት በኋላ ወዴት?
አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች በቅርቡ የተፈጠረው ሁከትና አመፅ ሥርዓቱን ተቃውሞ ዩተደረገ መሆኑን ሲገልጹ፣ በዋናነት ከኦሮሚያ አካባቢ የመነጨው ተቃውሞ ግን ለፌዴራል ሥርዓቱ አፈጻጸም ጉድለትም አመላካች ነው ይላሉ፡፡
ፌዴራል ሥርዓቱ በታወጀባቸው የመጀመሪያ አሥርና ከዚያ በላይ ዓመታት ዋናው የፖለቲካ አጀንዳ የብሔር መብት መከበር ላይ ያተኮረ ብቻ እንደነበር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከል ተባባሪ ፕሮፌሰር (ዶ/ር) ዘመላክ አየለ ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ይህ አዝማሚያ ብሔርተኝነትን ያጎላ ሲሆን፣ መንግሥት የአገሪቱን አንድነት ለመጠበቅ የኢኮኖሚ ልማት ማፋጠን፣ አገራዊ አጀንዳ የሚቀሰቅሱ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማከናወንና የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን እንደ አቅጣጫ ይዞ ነበር፡፡ ሆኖም በቅርቡ ለአሥር ወራት የዘለቀው ሕዝባዊ አመፅ የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት ብቻውን ሥርዓቱ በዘላቂነት ለማስቀጠል ዋስትና አለመሆኑን ማሳያ መሆኑን ያምናሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር መንፈስም ከዚህ አኳያ ተመልክተውታል፡፡
መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን በቅርቡ ሲገልጽ፣ ብዙዎች መገንጠልን የሚፈቅደው አንቀጽ 39 እንዲከለስ የጠበቁ ይመስላሉ፡፡ ዶ/ር ዘመላክ ግን፣ ሕገ መንግሥቱ ላይ ወሳኝ የሚባል ማሻሻያ ሳያደርጉ አፈጻጸሙን ማረም እንደሚሻል ያሳስባሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ እንዳይነካ የሚፈልጉም ይኖራሉ በማለት፡፡
“Are Federal System Better than Unitary System?” በሚል ርዕስ የቦስተን ዩኒቨርሲቲ ሦስት አጥኚዎች ባደረጉት ምርምር፣ ‹‹አሃዳዊ ሥርዓት እንደ መርህ ከጥቅም ውጪ እየሆነ መጥቷል፡፡ ይህንን ሥርዓት የሚደግፍ አንድም አሳማኝ ጽንሰ ሐሳብ አልተገኘም፤›› በማለት ይንደረደራሉ፡፡
ተመራማሪዎቹ ከፌዴራሊዝም ሥርዓት የሚመነጭ አንዱ አዲሱ ባህሪ፣ ‹‹የውሳኔ አሰጣጥ ሥርዓት ከአንድ ማዕከል አውጥቶ ወደ ዳር ይወስዳል›› ካሉ በኋላ፣ በውሳኔውም ላይ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት (Veto Power) ዳር ላይ የተቀመጡ ቁጥራቸውም በርከት ያሉ እንደሚሆኑ ያስረዳሉ፡፡
ምናልባትም አንዱ የፖለቲካ ተንታኝ ምክንያቱን ሲያስረዱ ከፍተኛ የማስተዳደር ሥልጣንና ሀብት በእጃቸው ያስገቡ ክልሎች ጉልበትና አቅም ካገኙ በማዕከላዊ መንግሥት ላይ ሊያምፁ ይችላሉ በማለት ነው፡፡ ለዚህም አመላካች የሚሆነው በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ የሚታየው (የአገር ለአገር የሚመስል) ግንኙነት አዝማሚያና ከሌሎች ክልሎች የሚመጡ ዜጎችን እንደ የሌላ አገር ዜጋ የማየት ዝንባሌ ይጠቀሳል፡፡ የፌዴራሊዝም የመጨረሻ ግብ አንድነት ማምጣት ሲሆን፣ ተቃራኒውን እየሆነ እንዳይሆን ሥጋት አለ፡፡
የፌዴራሊዝም አንዱ ገጽታ ሥልጣንን ወደ ታች ወደ ሕዝብ የማውረድ (Decentralization) ሲሆን፣ የቦስተኑ አጥኚዎች በተለይ በደሃና ጠንካራ የፖለቲካ ተቋማት በሌሉባቸው አገሮች የአካባቢ አስተዳዳሪዎችና ባለሥልጣናት በቀላሉ ለሙስና የመጋለጥ፣ እንዲሁም ለድርጊታቸው ተጠያቂ የመሆን ዕድል ዝቅተኛ መሆኑንና ፀረ ዴሞክራሲያዊ አሠራር የማስፈን አዝማሚያ ሰፊ እንደሆነ ይደመድማሉ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት የሁከቱና የቀውሱ መነሻ ምክንያት የ‹‹መልካም አስተዳደር›› ችግር በማለት ጉዳዩን ቀላል አድርጎ የማቅረብ አዝማሚያ የሚታይበት ቢሆንም፣ የተከሰተው ቀውስ ከዚህ ዓይነት ሥልጣንን ከታለመለት ዓላማ ውጪ ጥቅም ላይ በመዋሉ የተነሳ እንደሆነ ግን ተቀብሏል፡፡
አንዳንድ ምሁራን የፌዴራል ሥርዓትን በቀጥታ ከብዝኃነት አስተሳሰብ ጋር የሚያስተሳስሩት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በኢትጵያ ካለው ወቅታዊ የአውራ ፓርቲ ፖለቲካ ጋር እንደሚቃረን ይሞግታሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል ከምስት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ በተካሄደው አምስተኛ የፌዴራሊዝም ዓለም አቀፍ ጉባዔ ተሳታፊ የነበሩት ማንዳል ማናንዳር የተባሉት የኔፓል ዜጋ ሪፐብሊካ በተባለው ሚዲያ እንዳስነበቡት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ፌዴራል ሥርዓት ለብዙኃኑ ሰላምና መረጋጋት አምጥቷል፡፡ ሆኖም ፓርቲን ከአገር የመለየትና የአንድ ፓርቲ አስተሳሰብን በብዙኃን አስተሳሰብ የመተካት ተግዳሮት ተጋርጦበታል፤›› በማለት አደጋውን አመላክተው ነበር፡፡ ምናልባትም ለልዩነት ዕውቅና መስጠት የማይፈልገው ኢሕአዴግ አንድ ፓርቲና አንድ አስተሳሰብ በማራመድ ቀድሞ በሕገ መንግሥቱ ሳይቀር ያሰፈረውን አስተሳሰብ በሚቃረን መንገድ እየተጓዘ እንዳይሆን ሥጋታቸውን የሚገልጹ አሉ፡፡
አንዳንድ የቀውስ ወቅት ተንታኞች ሁከቱ ሥርዓቱ በሚመራበት የአውራ ፓርቲ አስተሳሰብ ላይ የተነሳ ተቃውሞ በማድረግ የሚመለከቱ ሲሆን፣ ዶ/ር ዘመላክ ግን በዋና ዋና ፓርቲዎች መካከል ስምምነት የተመሠረተ እንደሆነ የአንድ ፓርቲ የበላይነት በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ ተፅዕኖ ላይኖረው ይችላል ይላሉ፡፡ ስምምነት ስለመፈጠሩ ግን በመጠራጠር፡፡ አቶ ልዑልሰገድ ታደሰ የተባሉ ተመራማሪ፣ “can Diversity be Accommodated: The case of Ethiopia” በሚለው ጥናታቸው፣ ‹‹ዴሞክራሲ በሌለበት እውነተኛ የፌዴራል ሥርዓት መገንባት አይቻልም፤›› የሚል ክርክር በማቅረብ፣ በኢትዮጵያ በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና የተሰጣቸው የዴሞክራሲና የብዝኃነት ጽንሰ ሐሳቦች ቢኖሩም እነዚህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማት አለመኖራቸው፣ በሥርዓቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮበታል ይላሉ፡፡
በተጨማሪም የፌዴራል ሥርዓቱ አንዱ ዓላማ የብሔር ግጭቶችን ማስወገድና ማስቀረት ቢሆንም፣ ግጭት ሲከሰት ለመፍታት የሚያስችሉ ጠንካራ ተቋማትና የግጭት አፈታት ዘዴዎች እንደሌሉም ይከራከራሉ፡፡ እንዲሁም በፌዴራል መንግሥትና በክልል መንግሥታት መካከል ያለውን ያህል፣ በክልል መንግሥታት የእርስ በርስ (Horizontal) ግንኙነት ላይ በቂ አሠራር የለም ይላሉ፡፡
አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ልዩነትን ከማስፋት ይልቅ በማጥበብ፣ ትምክህትና ጥበት የሚባሉ አስተሳሰቦችን ወደ ጎን በማለት፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ዕድላቸው መመሥረት ያለበት ከታሪካቸው የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ፣ መብቶቻቸውንና ነፃነታቸውን በጋራና በተደጋጋፊነት በማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት አስፈላጊነት ላይ በሕገ መንግሥቱ ያደረጉትን ስምምነት ከመተግበር የተሻለ አማራጭ የላቸውም የሚለው ድምፅ እያየለ ይመስላል፡፡ ይህም በአገሪቱ መሪዎችና ባለሥልጣናት ጭምር መቀንቀን ጀምሯል፡፡ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት መንገዱም እንደ መንደርደሪያ እየታየ ነው፡፡