ጂን ኪሚያኪ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ ዋና ተወካይ
ጂን ኪሚያኪ በኢትዮጵያ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ዋና ተወካይ ናቸው፡፡ መንግሥታዊው ተቋም በኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ዘርፎች ሲንቀሳቀስ ወደ አርባ ዓመታት የተጠጋ ተሞክሮ አካብቷል፡፡ ላለፉት ስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ያተኮረና ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚሳተፉበትን የፖሊሲ ምክክር ሲያዘጋጅ መቆየቱ አይዘነጋም፡፡ ይህ የፖሊሲ መድረክ ለተጨማሪ ዓመታት እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡ ይሁንና ከሰሞኑ ደግሞ በግብርና ዘርፍ ላይ ያተኮረ የፖሊሲ ምክክር መድረክ በቋሚነት ለማካሄድ መዘጋጀቱን ኪሚያኪ ይፋ አድርገዋል፡፡ የፖሊሲ ምክክሩ መንግሥት በግብርናው ዘርፍ ውስጥ የሚተገብራቸውን አሠራሮች የሚቃኝ ሲሆን፣ በዓመት ሁለት ጊዜ በየስድስት ወራት ሊካሄድ መታሰቡን ኪሚያኪ ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡ በግብርናው መስክ በተለይ በአነስተኛ አርሶ አደሮች ላይ የሚያጠነጥን ሥራ ለመሥራት የጃፓን መንግሥት ፍላጎት እንዳለው የሚገለጹት ዋና ተወካዩ፣ በአገሪቱ የግብርና ምርታማነት ላይ ስለሚታዩ ችግሮችም አውስተዋል፡፡ መንግሥት በሜካናይዝድ እርሻ ሥርዓት ሊተገብራቸው ስለሚያስባቸው ተግባራትም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የሜካናይዝድ እርሻ በተለይ በአነስኛ ገበሬዎች ማሳ ላይ ውጤታማ መሆን እንደማይችል፣ ይልቁንም በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ተግባራዊ መደረግ እንደሚገባው ይሞግታሉ፡፡ በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ሲተገብረው የቆየው የሜካናይዝድ እርሻ ውጤት ማምጣት ስላልቻለባቸው ምክንያቶች ሲያብራሩም፣ እርሻዎቹ በሚገኙባቸው ገጠራማ አካባቢዎች የሚታየው የመሠረተ ልማትና የገበያ አውታሮች ባለመሟላታቸው ሳቢያ እንደሚሆን ያምናሉ፡፡ አነስተኛ ገበሬዎችን ከማሠልጠን ባሻገር፣ ገበያን መሠረት ያደረጉ ምርቶች እንዲያመርቱ በኮንትራት ግብርና መሰል የጃፓን መንግሥት ደጋፍ ለማድረግ ስለማቀዱ፣ በሆልቲካልቸር መስክም ገበሬዎች ውጤታማ ሥራ እንዲኖራቸው ለማስቻል ስለመታሰቡ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአፍሪካ ብዙም ውጤታማ እንዳልነበረ የሚነገርለትንና አረንጓዴው አብዮት እየተባለ የሚጠራውን እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ዳግም የማነሳሳትና ዕውን የማድረግ ሥራ ለመሥራት ጃይካ መዘጋጀቱን የገለጹት ኪሚያኪ፣ በተለይ በአብዮቱ ወቅት ስኬታማ እንዳልነበር ስለሚነገርለት የበቆሎ ምርት አብራርተዋል፡፡ ምንም እንኳ በቆሎ በአፍሪካ ብዙም ውጤታማ አይደለም ቢሉም፣ አብዛኞቹ አገሮች በበቆሎ ላይ የተመሠረተ የአመጋገብ ሥርዓት እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከበቆሎ ይልቅ በሩዝ ላይ ቢሠራ ውጤት ሊመጣ እንደሚችልም ኪሚያኪ ሞግተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በበቆሎ ምርት ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ይልቅ ውጤታማ የሆነችባቸውን ምሳሌዎች ያቀረቡት ኪሚያኪ፣ ይህንን የአገሪቱን ስኬት ለሌሎች አገሮች ለማካፈል አገራቸው ፍላጎት እንዳላትም አብራርተዋል፡፡ በግብርናው መስክ የሚታዩ ሌሎች በርካታ ነጥቦች ላይ ከጃይካ ዋና ተወካይ ጂን ኪሚያኪ ጋር ብርሃኑ ፈቃደ ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ጃይካ በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ላይ ያተኮረ የፖሊሲ ምክክር መድረከ በቋሚነት ለማካሄድ ተዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ወቅት የፖሊሲ ምክክር ማድረጉ አስፈላጊነቱ ከምን የሚመነጭ ነው?
ኪሚያኪ፡- መንግሥት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውንና ሲተገብር ቆይቷል፡፡ በተለይም በሰብል ምርት መስክ ብዙ ተንቀሳቅሷል፡፡ ይሁንና በኢትዮጵያ በኩል ባለው ግብርናን የማስፋፋት አመለካከትና በእስያ ተሞክሮ መካከል ሰፊ ልዩነቶች ይታያሉ፡፡ እርግጥም በአካባቢ ሁኔታዎች፣ በአየር ንብረት፣ እንዲሁም በተፈጥሯዊ የምርታማነት መስኮች ልዩነቶች ይኖራሉ፡፡ ስለዚህም ጉልህ ልዩነቶችን ማየት ይቻላል፡፡ ይሁንና በእኛ በኩል ያሉንን ተሞክሮዎች በማካፈል ኢትዮጵያ ከእነዚህ ልምዶች በመነሳት አስፋፍታ እንድትጠቀምባቸው እንፈልጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከጥቂት ቀናት በፊት በግብርና ላይ ያተኮረ ሴሚናር አካሂዳችኋል፡፡ በስብሰባው ከተነሱት ነጥቦች መካከል አንዱ አረንጓዴውን አብዮት በአፍሪካ እንዲያንሰራራ ማድረግና በኢትዮጵያም ይህንኑ ማስፋፋት እንደሚያስፈልግ ተጠቅሷል፡፡ ነገር ግን በሰፊው የሚታመነው ይህ አብዮት በእስያ ወይም በደቡብ አሜሪካ ያሳየውን ያህል በአፍሪካ ውጤታማ መሆን እንዳልቻለ ነው፡፡ አረንጓዴው አብዮት በአፍሪካ ስኬታማ መሆን አልቻለም በሚለው መከራከሪያ ይስማማሉ?
ኪሚያኪ፡- አዎን፡፡ በዚህም ምንክያት ነው ይህንን የመወያያ ርዕስ የመረጥነው፡፡ አረንጓዴው አብዮት በአፍሪካ ውጤታማ አልነበረም ባልከው ላይ እስማማለሁ፡፡ አብዮቱ በተለይም ከሰሃራ በታች ባሉት የአፍሪካ አገሮች ውስጥ ያን ያህል ውጤታማ መሆን አልቻለም ነበር፡፡ የእኛ ፍላጎት ግን ይህንን ሁኔታ መቀየር ነው፡፡ በእኛ በኩል ለምግብነት የሚለው የበቆሎ ምርት ላይ አሁንም ፈተና እንዳለ እንገነዘባለን፡፡ በቆሎ ተስፋ የሚሰጥ ሰብል ካለመሆኑም በላይ፣ በአፍሪካ አረንጓዴ አብዮት ሒደት ውስጥ መካተት አልነበረበትም፡፡ ይሁንና በተቃራኒው የሩዝ ሰብል በአፍሪካ ተስማሚ ምርት ሊሆን እንደሚችል መከራከሪዎች አሉን፡፡ በሌሎች አካባቢዎች የተሞከሩ ቴክኖሎጂዎችና ዕውቀቶች በአፍሪካ በቀላሉ ተግባራዊ መሆን ይችላሉ፡፡ እርግጥ በርካታ የእስያ አገሮች በሩዝ መስክ አረንጓዴውን አብዮት እንቅስቃሴ አሳክተዋል፡፡ በሌላ በኩል ከሰሃራ በታች ባሉ አገሮች ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ያለ ሩዝን ከውጭ ገዝቶ የማስባት አዝማሚያ እየታየ ነው፡፡ በመሆኑም እዚሁ ማምረቱ እየጨመረ የመጣውን የሩዝ ፍላጎት ለማሟላት ያስችላል፡፡ ከኢኮኖሚ አስተዋጽኦ አኳያ ካየነውም ሩዝ ከበቆሎ የበለጠ አቅም አለው፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያውያንም ሆኑ በርካታ የአፍሪካ አገሮች የሩዝ ተመጋቢነት ባህል የላቸውም፡፡ እንዲያውም በአብዛኛው በበቆሎ ላይ የተመሠረተ የምግብ ሥርዓት በብዛት ይታያል፡፡ በአንዳንዶቹ አገሮች የዘወትር ምግብ የሚዘጋጀው ከበቆሎ ነው፡፡ ይሁንና እርስዎ ሩዝ በቆሎን የሚተካ ሰብል ነው እያሉ ነው፡፡ ምንም እንኳ የሩዝ የገቢ ንግድ ቢጨምርም ሩዝ በኢትጵያ በሰፊው ተቀባይነት ማግኘቱ ግን አጠራጣሪ አይሆንም?
ኪሚያኪ፡- በኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን በበርካታ አፍሪካ አገሮች ውስጥ በሚታው ሥነ ምኅዳራዊ ምርታማነት አቅም ላይ ነው ያተኮርነው፡፡ ለሰው የምግብ ፍጆታነት በሚውለው ምርት ላይ ያለው ውጤማታነት የሚወሰነው በማኅበረሰቡ ፍላጎት ነው፡፡ ለመግለጽ እየሞከርን ያለነው ግን ሳይንሳዊ ነጥቦችን ነው፡፡ እዚህ ሩዝ ማብሰልና መመገብ ቀላል እንዳልሆነ ተገንዝበናል፡፡ አንዳንድ የሚደርሱን አስተያየቶችም ይህንኑ ያረጋግጣሉ፡፡ ሩዝን ለምግብነት ማዘጋጀት ከጤፍ የበለጠ እንደሚከብዳቸው የሚገልጹ አሉ፡፡ ለገበሬዎችም ቢሆን ሩዝ መዝራት በቀላሉ የሚወጡት ተግባር አልሆነም፡፡ እኛም ብንሆን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ ከባድ ጊዜ አጋጥሞን ነበር፡፡ ጃፓን ከፍተኛ የሩዝ ፍጆታ ነበራት፡፡ ይሁንና የምግብ አማራጩ በመስፋፋቱና ስንዴን የማስተዋወቅ ዘመቻ በመካሄዱ፣ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ እንመገባለን፡፡ ለሕዝቡ አማራጮች እስከቀረቡለት ድረስ በአፍሪካ ያለው ሁኔታም መቀየሩ አይቀርም፡፡ ሰፊ አማራጮች ሲኖሩ የዕድገት አመላካቾች መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በበቆሎ አምራችነት አመርቂ ውጤት አስመዝግባለች፡፡ በስብሰባው ወቅት ስለዚህ ጉዳይ ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል፡፡ የእኛ ምሁራን ባደረጉት ጥናት መሠረት በአፍሪካ በአማካይ በሔክታር የሚመረተው የበቆሎ መጠን ከሁለት ቶን በታች ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2004 በኢትዮጵያ የነበረው ምርት በአማካይ በሔክታር 1.6 ቶን ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 የነበረው ምርትማነት በሔክታር በአማካይ ወደ 3.2 ቶን አድጓል፡፡ ይኼ በጣም ትልቅ አፈጻጸምን የሚሳይ ውጤት ነው፡፡ ይህንን ውጤት ለሌሎች የአፍሪካ አገሮች ማጋራት እንፈልጋለን፡፡ ይሁንና ምንም እንኳ በዚህ ደረጃ ውጤት ቢታይም ውስንነቶች ግን መታየታቸው አልቀረም፡፡ ምን ዓይነት ቴክሎጂ ጥቅም ላይ እንደዋለና ይህንን ያህል ውጤት ለማምጣት እንዳስቻለ በአግባቡ አልተጠናም፡፡ ቢሆንም ግን የአገሪቱን አመርቂ ውጤት የማስተዋወቅ ትልቅ ፍላጎት አለን፡፡ የታየው ውጤታማ የበቆሎ ምርት በምን ምክንያት እንደሆነ ለማጥናት እንፈልጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- በስብሰባው ወቅት ከተካሄዱ ውይይቶች መካከል የሜካናይዝድ እርሻም ተነስቶ ነበር፡፡ በሜካናይዝድ እርሻ መስክ ኢትዮጵያ ያን ያህል የሚጠቀስ እንቅስቃሴ የላትም፡፡ በዚህ ረገድ ምን ሊባል የሚችል ነገር ይኖራል?
ኪሚያኪ፡- በአብዛኛው ሰዎች ለግብርና ዘርፍ ማሽነሪዎችን የሚጠቀሙት ከፍተኛ የሠራተኛ ወጪ ሲያጋጥማቸው ያንን ወጪ ለመቀነስ ነው፡፡ የምርት ወጪዎችን ለመቀነስ ገበሬዎች የግብርና ማሽነሪዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ይህ በፊሊፒንስና በሌሎችም የእስያ አገሮች የታየ ተሞክሮ ነው፡፡ የሠራተኛ ጉልበት ወጪ እያየለ ሲመጣ ገበሬዎች በሰው ጉልበት ላይ ከተመሠረተ ግብርና ወይም ከእንስሳት ይልቅ ሌሎች አዋጭ መሣሪዎችን ወደ መጠቀሙ ያዘነብላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ምናልባት ሰሞንኛ የሠራተኛ ዕጥረት የሚያጋጥሙባቸው ወቅቶችና አካባቢዎች ይኖራሉ፡፡ ይህም ከሠራተኞች ከቦታ ቦታ መዘዋወርና እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ የሚጋጥም ነው፡፡ በተረፈ ግን መጠነ ሰፊ ሊባል የሚችል ሥራ አጥነት ይታያል፡፡ በኢትዮጵያ የሜካናይዝድ እርሻ ለማስፋፋትና ገበሬዎች ማሽነሪዎችን እንዲጠቀሙ የግድ የሚልበት ወቅት አይደለም፡፡ በስብሰባው ወቅትም ይህንን ተነጋግረናል፡፡ መንግሥት ግን ሜካናይዜሽን ላይ ጠንካራ አቋም ይዟል፡፡ ስለሆነም የሜካናይዜሽን አስፈላጊነትና የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ማወቅ እንፈልጋለን፡፡
ሪፖርተር፡- የሜካናይዝድ እርሻ የመጠቀም ሙከራዎች አዲስ አይደሉም፡፡ ከንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ ጀምሮ ሲተገበሩ ያልተሳኩ ፕሮጀክቶች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ በዚያን ወቅት የታየው ነገር ሜካናይዜሽን ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅና ውድ እንደሆነ ነው፡፡ ገበሬዎች በሜካናይዝድ ሥርዓት ታግዘው የሚያርሱት ተጨማሪ መሬት የላቸውም፡፡ በአማካይ ከግማሽ ሔክታር ያላነሰ መሬት ነው አብዛኛው ገበሬ የሚያደርሰው፡፡ በዚህ ሁኔታ ሜካናይዜሽንን መጠቀም ከተጨባጭ ሁኔታው የወጣ ይመስላልና በዚህ ነጥብ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው?
ኪሚያኪ፡- በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ሜካናይዜሽን ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል የታወቀ ነው፡፡ መንግሥትም ይህ ተግባራዊ እንዲሆን እየሞከረ ነው፡፡ የእኛ ፍላጎት ግን በአነስተኛ ገበሬዎች ላይ ማተኮር ነው፡፡ ከአንድ ሔክታር በታች የእርሻ መሬት ካላቸው ገበሬዎች ጋር እንዴት እንደሚኬድበት ነው አሳሳቢው ነገር፡፡ ትልልቅ የሜካናይዝድ መሣሪዎችን ወይም ትራክተሮችን ከመጠቀም ይልቅ አነስተኛ የማረሻ ማሽኖችን ወይም ትንንሽ የመውቂያ መሣሪዎችን መጠቀም፣ ከኢትዮጵያ የግብርና ሁኔታ አኳያ ሲታይ ተገቢነት ያለው አካሄድ ነው፡፡ ይሁንና እነዚህን ማሽነሪዎችም ቢሆን ገዝቶ ለመጠቀምና ባለቤት ለመሆን በኢትዮጵያ አነስተኛ ገበሬዎች አቅም የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ውድና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቃቸው ነው፡፡ ስለሆነም ማሽነሪዎቹን ማቅረብ የሚቻልባቸውን መንገዶች ማመቻቸት ይኖርብናል፡፡ ይህ ለወደፊቱ ምክክር የሚጠይቅ ነጥብ ይመስለኛል፡፡
ሪፖርተር፡- ከዚሁ ከሜካናይዜሽን ሳንወጣ በዚህ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ ሰፋፊ እርሻዎችም ቢሆኑ በኢትዮጵያ ውጤታማ መሆን አልቻሉም፡፡ አብዛኞቹ ሰፋፊ እርሻዎች ስኬታማ ለመሆን ተቸግረዋል፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ሰፋፊ መሬት ወስደው በመጨረሻው ግን ሐራጅ ሲባሉና ለኪሳራ ሲዳረጉ እየታዩ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ውስጥ ውጤታማ መሆን ያልቻለው በምን ምክንያት ነው ብለው ያስባሉ? ስህተቱስ የት ቦታ የተፈጠረ ነው?
ኪሚያኪ፡- ይህ በጣም አስፈላጊው ርዕስ ነው፡፡ በሰፋፊ እርሻዎች ምርታማነትና ውጤታማነት ላይ ተሞክሯችንን ያካተተ የምክክር መድረክ ተካሂዷል፡፡ በይፋ እንደታየው ከሆነ የሰፋፊ እርሻዎች ምርታማነት ከአነስተኛ ገበሬዎች የተሻለ አይደለም፡፡ በሰው ጉልበት ላይ መሠረት ያደረገ የሰፋፊ እርሻ ሥራን እንደ ልብ ለመከታተልና ለመቆጣጠር በጣም ከባድና የማይታሰብ ይሆናል፡፡ በጣም ሰፊ እርሻ ይዘህ በዚህ መልክ የእርሻውን ሥራ ማከናወን ካሰብክ ሊኖር የሚችለውን የግንኙነት ክፍተት መገንዘብ አለብህ፡፡ በሰው ጉልበት ላይ የተመሠረተ የሰፋፊ እርሻ ሥራን አናበረታታም፡፡ ይህንን ጉዳይ ወደፊትም እንድንነጋገርበት የምንይዘው ነጥብ ይሆናል፡፡ በተለይ በመንግሥት እርሻም ሆነ በግል እርሻዎች ላይ እንዲህ ያለውን የሰው ጉልበት መሠረት ያደረገ ግብርና መመልከት ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚታየው የሰፋፊ እርሻ ሥራ በርካታ ችግሮች የሚታዩበት ነው፡፡ እርሻዎቹ ጭልጥ ያሉ ገጠራማ አካባቢዎች ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው የመሠረተ ልማት አቅርቦት እንደ ልብ አያገኙም፡፡ ባለሀብቶቹ በዚህ ሳቢያ ችግር እየገጠማቸው ነው፡፡ መንግሥት ባለሀብቶቹ መሠረተ ልማቱን እንዲያሟሉ ሊጠብቅ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ የባለሀብቶቹን የወጪና የገቢ ሚዛንን ሊያዛባው ይችላል፡፡ ፈታኝ ሁኔታዎችን ለመቀነስና ተስማሚ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የመንግሥትና የባለሀብቶች ትብብር መኖር በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ባለሀብቶቹ ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሆኑ ማሽነሪዎችን ይዘውም ገብተው ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉ የሚያሳዩ ተሞክሮዎች አሉ፡፡ ከዓመታት ቆይታ በኋላም የአብዛኞቹ እንቅስቃሴ ውጤት አልባ መሆኑ አስገራሚ ሊባል የሚችል ነው፡፡ ስኬታማ መሆን ያልቻሉባቸው ምክንያቶች በትክክል ምን እንደሆኑ በደንብ አይታወቅም፡፡ ምናልባትም በፌዴራልና በክልል መንግሥታት መካከል ያለው የድጋፍ አሰጣጥ ችግር ወይም የቢሮክራሲው ጣጣ ለውድቀታቸው መንስዔ ሊሆን እንደሚችልም ይታሰባል፡፡ እርስዎ ትክክለኛው ምክንያት ምንድነው ይላሉ?
ኪሚያኪ፡- በእኔ ግንዛቤ መሠረታዊው ችግር የገበያና የግብይት አውታሮች አለመዳበር ወይም ከነጭራሹ አለመኖራቸው ነው፡፡ ባለሀብቶች ለሰፋፊ እርሻዎች ግብዓት የሚሆኑ የፍጆታ ዕቃዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ መለዋወጫዎችና ሌሎችም ሳይቋረጡ ከገበያው ሊቀርቡላቸው ይገባል፡፡ በአገር ውስጥ የመለዋወጫ አቅርቦት ተሟልቶ መገኘቱ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ሳይቻል ሲቀር ግን ባለሀብቱ ከእርሻ ሥራው ይልቅ መለዋወጫ ከውጭ ለማስመታት ሲል ብዙውን ጊዜ ሊያጠፋ ይችላል፡፡ ተሳክቶላቸው ማስመጣት ከቻሉም ተጨማሪ አላስፈላጊ ወጪዎችን ለማውጣት ይገደዳሉ፡፡ ስለዚህ የገበያ አውታሮች መኖራቸው የአቅርቦት ኔትወርክ በቀላሉ እንዲፈጠር ስለሚያስችሉ፣ ባለሀብቱም ላልተገባ ወጪ እንዳይዳረግ ያግዙታል፡፡ የገበያ አውታሮች የበርካታ ባለድርሻዎችን ተሳትፎ ይፈልጋሉ፡፡ ይሁንና በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ካለው ዝቅተኛ የመንገድ ኔትወርክ፣ እንዲሁም ከሚታየው ዝቅተኛ የቢዝነስ ልምድ አኳያ ገበያው በሚፈለገው መጠን ሲንቀሳቀስ አይታይም፡፡ በመሆኑም ወጪዎች ከፍተኛ እንዲሆኑ ያስገድዳሉ፡፡ ገበያ ያለ ድጋፍ እንዲሁ ሊያድግ ስለማይችል መንግሥት የገበያ አውታሮች እንዲስፋፉ ማገዝ አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- በግብርናው መስክ በቋሚነት የሚካሄድ የፖሊሲ ምክክር ነድፏችኋል፡፡ በኢንዱስትሪ መስክ እንደ ካይዘን ያሉ ተሞክሮዎች ሊገኙበት የቻለ የምክክር መድረክ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በግብርናው መስክስ ምን ዓይነት ውጤቶች እንደሚኖሩ ይታሰባል?
ኪሚያኪ፡- አረንጓዴ አብዮትን እንደገና እንዲያንሰራራ ማድረግ አንዱ ነጥብ ነው፡፡ ልንማርባቸውና እርስ በርስ ልምድ ልንለዋወጥባቸው የሚችሉ በርካታ ተሞክሮዎች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ወገን በአግባቡ መጠናት የሚገባቸው ቴክኖሎጀዎች አሉ፡፡ ገበያን መሠረት ያደረገ የግብርና ዘርፍ እንዲፈጠር ማድረግም ልንሠራበት የሚያስችለን መስክ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኮንትራት ግብርናና የሆልቲካልቸር ግብርናን በአነስተኛ ገበሬዎች ዘንድ በሰፊው እንዲተገበር የማድረግ ፍላጎት አለን፡፡ ገበሬዎች ገበያ ተኮር ማበረታቻዎችን ቢያገኙ ብዙ የማምረት አቅም እንደሚኖራቸው አስባለሁ፡፡ የገበያውን ሁኔታ መገንዘብና ገበሬዎችም ገበያ ተኮር የሆነ አሠራር እንዲከተሉ ማድረግ ጠቃሚ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አምራቾች ስለሚያመርቱት ምርት ጥናት እንዲያደርጉ የሚያስችል የሥልጠና ፕሮግራም ለመጀመር እየሞከርን ነው፡፡ ሥልጠናው ገበሬዎች የትኛውም የምርት ዓይነት ትርፋማ እንደሚያደርጋቸው እንዲለዩና እንዲያመርቱ የሚያስችላቸው ይሆናል፡፡ በዚህ መንገድ ገበሬዎችን በቀላሉ ከገበያው ጋር እንዲተሳሰሩ ከሚያስችሏቸው መካከል የኮንትራት ግብርና አንዱ ነው፡፡ ማበረታቻዎች የታከሉበት የግብርና ሥራ እንዲስፋፋ ለማድረግ ፍላጎት አለን፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለረጅም ዓመታት የቆየ የተፈጥሮ ሀብቶች የወል ባለቤትነት አለ፡፡ ይህ ሀብትን በሁሉ አቀፍ መንገድ ለማስተዳደር የሚያግዝ በመሆኑ በጣም ጠቃሚ ቢሆንም፣ የገበሬዎችን የአምራችነት ባህርይ በመንተራስ ማበረታቻ ተኮር አሠራሮችን ለመተግበር ግን አያመችም፡፡ በማበረታቻዎችና በወል ሀብቶች መካከል ሚዛኑን የጠበቀ አካሄድ መከተል ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በወል፣ በጋራ የመረዳዳት ሥርዓትን ለዘመናት በመተግበር ቆይታለች፡፡ እኛም ይህ እንደተጠበቀ ምርታማነት የሚያድግበትን አሠራር ለመፍጠር ፍላጎት አለን፡፡
ሪፖርተር፡- ከኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለየ የግብርናው ዘርፍ የረጅም ዓመታት ተሞክሮ ያላቸውና በደንብ የተደራጁ የግብርና ምርምር ተቋማት አሉት፡፡ ይህም ሆኖ ግን አነስተኛ አምራቹ ገበሬ ከዕለት ጉርስ ሊላቀቅ አልቻለም፡፡ ለዕለት ደራሽ ዕርዳታ ሲዳረግ ቆይቷል፡፡ እርግጥ ጃይካ በግብርናው ዘርፍ እዚህም እዚያም የሚያካሂዳቸው እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ በኢትዮጵያ አነስተኛውን አምራች የሚፈታተኑ ችግሮች ምንድን ናቸው ይላሉ?
ኪሚያኪ፡- አንደኛው ችግር ቀደም ብዬ የጠቀስኩት የገበያ አውታሮች አለመስፋፋት ነው፡፡ ይህ ባለመሆኑም ገበሬዎች የዕለት ጉርሳቸውን በማምረት ላይ ብቻ እንዲወሰኑ አስገድዷቸዋል፡፡ ይህ እርግጥ አሁን እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ በግብርና መስክ ለአምራቹ ተጠቃሚነት በብዙ መንገድ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ የሚችሉ በርካታ መስኮች አሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን የገበሬዎች የምርምር ቡድኖች እንዲቋቋሙ በማድረግ ስንንቀሳቀስ ቆይተናል፡፡ ይህ ፕሮጀክት ስኬታማ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ፕሮጀክቱ የገበሬዎችን ነባራዊ ዕውቀትና የተመራማሪዎችን አቅም በመጠቀም በበርካታ የገበሬዎች የምርምር ቡድኖች አማካይነት ሲተገበር የቆየ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲዎችና በምርምር ተቋማት በኩል በሰፊው ተቀባይነት የተቸረው ፕሮጀክት ነው፡፡ ሆኖም አሁንም ውስንነቶች ይታያሉ፡፡ በደንብ የሠለጠኑ ተመራማሪዎች በመስክ ላይ ማግኘት አዳጋች ነው፡፡ የግብርና ተመራማሪዎች መረጃን በትክክለኛው መንገድ የመለካትና ሁሉን አቀፍ በሆነ መንገድ የመተንተን ችግር ይታይባቸዋል፡፡ በመሆኑም ያልተቋረጠ የሰው ሀብት ልማትና ክህሎትን የማካበት ሥራ ማከናወን ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ በሥነ ሕይወት መስክ ትልቅ አቅም እንዳላት ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ብዙ ጥናትና ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው በርካታ የሰብል ዓይነቶች አሉ፡፡ ይህን ለማስፋፋት ጊዜ መጠየቁ አይቀርም፡፡ የሰብል ምርት በአብዛኛው በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚካሄድ መሆኑ የግብርና ሥራ ምን ያህል ጊዜ የሚጠይቅ፣ የግብርና ምርምር ሥራም ምን ያህል ጊዜ የሚፈልግ መሆኑን ይጠቁምሃል፡፡ ከአገልግሎትና ከኢንዱስትሪ አኳያ ግብርና ብዙ ልፋትና ጊዜ ይጠይቃል፡፡ በኢትዮጵያ የሚመረተውና ለምግብ ፍጆታነት የሚለው የግብርና ምርት በአብዛኛው በባህላዊ እሴቶች ላይ የተመረኮዘ ሆኖ ይታያል፡፡ እነዚህ በጣም ጠቃሚ በመሆናቸው ጠብቆ ማቆየቱ ተገቢ ነው፡፡ ይሁንና ከአኗኗር ለውጥና ከባህል ዘይቤ ጋር የሚለዋወጡ ነገሮችን ለመቀበል ሰዎች ፈቃደኛ እስከሆኑ ድረስ፣ የወደፊቱን የተሻለ ሁኔታ ከመፍጠር አኳያ ትኩረት ቢደረግባቸው ጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ ጃፓን በዚህ መንገድ ስትጓዝ ቆይታለች፡፡ ኢትዮጵያም ከጃፓን መማር የምትችልባቸው ተሞክሮዎች አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በግብርና ሥራ የሚተዳደረው የጃፓን ሕዝብ አንድ በመቶ ያህል እንደሆነ ይነገራል፡፡
ኪሚያኪ፡- አዎን፡፡ በጣም ጥቂት ገበሬዎች ናቸው ያሉን፡፡ ካሉን ገበሬዎች አብዛኞቹ በእርጅና ምክንያት እየተቀነሱ በመሆናቸው ችግር እያጋጠመን ነው፡፡ ነገር ግን የግብርና ምርቶችን ከውጭ በብዛት እናስገባለን፡፡ ስትራቴጂያችን ከፍተኛ እሴት ያላቸው የግብርና ሸቀጦችን ወደ መግዛቱ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ገበሬዎች ከሚያርሱት አነስተኛ መሬት በተጨማሪ የግብርና ግብዓቶች ወጪም ከፍተኛ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ለማዳበሪያ፣ ለአረምና ለተባይ መከላከያነት የሚውሉ ግብዓቶችን ለመግዛት የሚያወጡት ወጪ ከሌሎች ጋር ተዳምሮ ምርታማነታቸውን እየጎዳ ነው ቢባል ፍትሐዊ መከራከሪ ነው?
ኪሚያኪ፡- ይህ በጣም ጠቃሚ ነጥብ ነው፡፡ የኬሚካል ማዳበሪያ ወጪ በኩንታል 50 ዶላር (ከአንድ ሺሕ ብር በላይ) ገደማ ነው፡፡ ይህ ለአብዛኞቹ አነስተኛ ገበሬዎች ከፍተኛ ወጪ ነው፡፡ መንግሥት የኬሚካል ማዳበሪያ አገር ውስጥ ለማምረት መነሳቱ ምናልባት ወጪውን ለመቀነስ ያስችል ይሆናል፡፡ ሆኖም የእንስሳትና የዕፅዋት ውጤት የሆኑ ማዳበሪያዎችን መጠቀም እንደ አማራጭ መታየት ይኖርበታል፡፡ ምናልባት የእንስሳት ተረፈ ምርትን ለማዳበሪነት መጠቀም ገበሬው ላይ ተጨማሪ ወጪ ያስከትልበታል ሊባል ይችላል፡፡ ለምሳሌ ለእንስሳቱ ቦታ ማዘጋጀትና መኖ ማቅረብ ሊኖርበት ይችላል፡፡ ይሁንና እኔ ለማለት የምፈልገው ከውጭ በሚገባ ማዳበሪያ ላይ ጥገኛ ከመሆን አማራጭ መፍትሔዎችን መቃኘት እንደሚገባ ነው፡፡