Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጁፒተር እህት ኩባንያ ከቻይና ኩባንያ ጋር የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን ሊገጣጥም ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያዎችን ገጣጥሞ ለገበያ ለማቅረብ ተዘጋጅቷል 

የጁፒተር ኩባንያዎች እህት ኩባንያ የሆነው ማይባብ ኤሌክትሮኒክስ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ፣ ከቻይና ኩባንያ ጋር በመሆን የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን በአገር ውስጥ ለመገጣጠም መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡ ኩባንያውን በእሽሙር ሽርክና ለመሥራት ተዋውሏል፡፡

ማይባብ ኩባንያ ከቻይናው ሼንዘን ክሎዉ ማኑፋክቸሪንግ ኩባንያ ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት ሁሉንም ዓይነት የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎች በአገር ውስጥ ለመገጣጠም የሚያስችል ፋብሪካ ገንብተው አጠናቀዋል፡፡ የማይባብ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ብሥራት እንዳብራሩት ከሆነ፣ መገጣጠሚያ ፋብሪካው በመጪዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ ከ300 ሺሕ ያላነሱ ቆጣሪዎችን ማምረት ይጀምራል፡፡ በመጪው ዓመትም ይህንን አቅሙን ወደ 900 ሺሕ ቆጣሪዎችን በማምረት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ለማቅረብ ተስፋ መሰንደቁን አቶ መላኩ አብራርተዋል፡፡

በሼንዘን ክሎው ኤሌክትሮኒክስ ኩባንያ የአፍሪካ ሽያጭ ዳይሬክተር ሁ አን እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ መገጣጠም የሚጀምረው ፋብሪካ፣ ከግብፅ፣ ከናይጄሪያና ከጋና በመቀጠል አራተኛው ኩባንያ ይሆናል፡፡ 

የኤሌክትሪክ ቆጣሪ መገጣጠሚያ ፋብሪካው ሥራ መጀመር በቅርቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተቋሙ በሁለት ዓመታት ውስጥ እንዲቀርቡለት ካወጣው የ1.2 ሚሊዮን ቆጣሪዎች ጨረታ ጋር መገጣጠሙ ጥሩ አጋጣሚ እንደተፈጠረለት አቶ መላኩም ሆኑ ሚስተር ሁ አን ጠቅሰዋል፡፡ ማይባብ ጨረታውን ቢያሸንፍ የመጀመሪያውን ምዕራፍ ከቻይና በማስመጣት፣ ቀሪዎቹንም እዚሁ ከሚገጣጥማቸው ውስጥ ለማቅረብ ፍላጎት እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ማይባብ ኤሌክትሮኒክስ የ70 ከመቶ የባለቤትነት ድርሻ ሲኖረው፣ ሼንዘን ክሎዉ በበኩሉ ቀሪውን 30 በመቶ እንደሚጋራ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ማይባብ ኤሌክትሮኒክስ ከሰርቢያው ጋሌብ ግሩፕ የሚያስመጣቸውን የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪዎች በአገር ውስጥ ለመገጣጠም የሚያስችለውን ፋብሪካ መገንባቱንና በአጭር ጊዜ ውስጥም ከስምንት እስከ 10 ሺሕ መሣሪዎችን ለገበያ ለማቅረብ መዘጋጀቱን አቶ መላኩ ገልጸዋል፡፡ በዚህ መሠረት ጋለብ ግሩፕ ለማይባብ የሚገጣጠሙትን ሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪዎች ከማቅረብ ባሻገር ለ20 ቴክኒሻኖች ሥልጠና እንደሚሰጥ ተነግሯል፡፡

አቶ መላኩ እንዳብራሩት ለሁለቱ ፋብሪካዎች ተከላና ለማሽነሪዎች በጠቅላላው 5.5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል፡፡ ከዚህ ውስጥ አራት ሚሊዮኑ ለቆጣሪ መገጣጠሚያው የዋለ ሲሆን፣ 1.5 ሚሊዮኑ ደግሞ ለሽያጭ መመዝገቢያ ፋብሪካ የዋለ ነው፡፡ ማይባብ ኤሌክትሮኒክስ ማኑፋክቸሪንግ በአዲስ አበባ ገርጂ አካባቢ በሁለት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሁለቱን ፋብሪካዎች ጎን ለጎን እንደገነባ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ማይባብ ኩባንያ የጂፒተር ትሬዲንግ፣ የጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል እንዲሁም ጄቢ ኮንስትራክሽን እህት ኩባንያ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች