Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመብራት ያጠፋቸው

መብራት ያጠፋቸው

ቀን:

ልትመረቅ ቀናት ቀርቷታል፡፡ ወላጆቿና የቅርብ ዘመዶቿ ለምርቃት በዓሏ ድግስ ዝግጅት ወገባቸውን አስረው ሽር ጉድ ማለት ጀምረዋል፡፡ እሷም በተለየ ምክንያት ቀኑ የተገፋውን የመመረቂያ ጽሑፏን በሁለት ቀናት ውስጥ አጠናቅቃ ማስረከብ ነበረባትና ሙሉ ትኩረቷን በጽሑፏ ላይ አድርጋ አንዳንድ ያልተሟሉ ነገሮች ማስተካከል ይዛለች፡፡

እስከ ሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ቁጭ ብላ ስትሠራ ከቆየች በኋላ ወራት የፈጀባት የመመረቂያ ጽሑፏን በማጠናቀቋ ዕፎይታ ተሰምቷት ወደ አልጋዋ አመራች፡፡ በማግስቱ ግን ፈጽሞ ያልጠበቀችው ነገር አጋጠማት፡፡ ዘይነብ ሙስጠፋ ከእንቅልፏ ስትነቃ ሙዚቃ የማድመጥ ልምድ አላት፡፡ ለዚህም ገና ከእንቅልፏ እንደነቃች ከጎኗ ወደሚገኘው ኮምፒውተር እጇን ሰዳ አንድ ሙዚቃ ልትከፍት ሞከረች፡፡ ድምፅ ግን አልነበረም፡፡

ምናልባት የኤሌክትሪክ ኃይል ጠፍቶ ይሆን በሚል መብራት በማብራት ኤሌክትሪክ መኖር አለመኖሩን አረጋገጠች፡፡ ከዚያም ደጋግማ ኮምፒውተሩን ለማብራት ሞከረች፡፡ የተለየ ነገር አልነበረም፡፡ ኮምፒውተሩ ፀጥ እንዳለ ቀረ፡፡ የምትሆነው ግራ እስኪገባት ተደናገጠች፡፡ ወራት ፈጅቶ የሠራችው መመረቂያ ጽሑፏ ያለው ፀጥ ባለው ኮምፒውተሩ ውስጥ ነው፡፡ ለማሠራት ሞክራ ነበር፡፡ ነገር ግን አልተሳካላትም፡፡ ኮምፒውተሩ በከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ግፊት እንደተቃጠለ፣ አዲስ መቀየር እንዳለበትና ውስጡ ያሉ ፋይሎችም ሊገኙ እንደማይችሉ ተነገራት፡፡ ድንጋጤዋ እንዲህ ነው ተብሎ የሚገለጽ አልነበረም፡፡

ይኼ ሊፈጠር ይችላል ብላ ሥጋት አድሮባት አያውቅም ነበር፡፡ መመረቂያ ጽሑፏን ስትሠራም ለማንኛውም ብላ የያዘችው መጠባበቂያ አልነበራትም፡፡ በኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ በተፈጠረው ቀውስ የመመረቂያ ጽሑፏን በወቅቱ ለማስረከብ እንዳትችል ሆነች፡፡ አጋጣሚው በእሷና ቤተሰቦቿ ላይ ጭንቀት የፈጠረ ነበር፡፡ በምርቃት ፕሮግራሙ ላይ ላትገኝ የምትችልበት አጋጣሚ ተፈጥሮ እንደነበረም ታስታውሳለች፡፡

በኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ንብረት ላይ ለሚደርስ አደጋ በሚመለከተው የመንግሥት ተቋም ካሳ እንደሚከፈል መረጃው ቢኖራትም የመመረቂያ ጽሑፏ በገንዘብ ሊካስ እንደማይችል ስለምታውቅ አሳስቧት ነበር፡፡ ኮምፒውተሩን በራሷ ደጋግማ ለማሠራት ሞክራም ነበር፡፡ ሁኔታው ካሳ የመጠየቅ ሐሳብ ቢያጭርባትም ካሳ ለማግኘት አሰልቺ ውጣ ውረድ መኖሩን፣ እንዲያም ሆኖ የሚገኘው የካሳ መጠን እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን ከዚህ ቀደም ከሞከሩ ሰዎች ስለሰማች ትታዋለች፡፡

ከንፋስ፣ ከፀሐይ ብርሃን፣ ከጂኦተርማል፣ ከሃይድሮጅን፣ ከውኃ ከመሳሰሉት ምንጮች የሚገኘው የኤሌክትሪክ ኃይል በአሁኑ ወቅት የዓለምን ሁኔታ ይቆጣጠራል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ባደጉት አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋረጠ ማለት እንቅስቃሴ ቆመ ማለት ነው፡፡ በጤናው፣ በትራንስፖርት፣ በትምህርቱና በሌሎች ዘርፎች ያለ ኤሌክትሪክ መንቀሳቀስ አስቸጋሪ የሆነበት ጊዜ ላይ ተደርሷል፡፡ መጠኑ ይለያይ እንጂ ይኼ በአገር ውስጥም እየተንፀባረቀ ያለ እውነታ ነው፡፡ ሰዎች የዕለት ጉርሳቸውን የሚያበስሉት በኤሌክትሪክ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የክልል ከተሞችም ቢሆን ምግብ ለማብሰል፣ ልብስ ለመተኮስ፣ ከሠል ማቀጣጠል እየቀረ ያለ ይመስላል፡፡ አብዛኛው የሰዎች የየዕለት እንቅስቃሴ ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋር በተቆራኘበት በዚህ ጊዜ በተደጋጋሚ የሚከሰተው የኃይል መቆራረጥ ነገሮችን ከባድ እያደረገ ይገኛል፡፡

እሑድ ከሳምንቱ ቀናት በተሻለ ፀጉራቸውን የሚሠሩ ደንበኞች የሚበዙበት በመሆኑ አገልግሎት ሰጪዎቹ ጠቀም ያለ ገቢ የሚያገኙበት ዕለት ነው፡፡ ለዚህም ማልደው ከእንቅልፋቸው በመነሳት ደንበኞቻቸውን ለማስተናገድ ደፋ ቀና ማለት ይጀምራሉ፡፡ በክፍሉ ውስጥ የተደረደሩት ካስኮች ተይዘው ሶፋ ላይ ተቀምጠው ወረፋ የሚጠባበቁ ሴቶች የሚኖሩትም እሑድ ቀን ነው፡፡ ቀይ ዩኒፎርማቸውን ከላይ ደርበው የሚያስፈልጋቸውን ግብዓቶች በመልክ በመልኩ አዘጋጅተው በላይ በላይ እየተከተሉ ወደ ውበት ሳሎኑ የሚመጡ ሴቶች ፀጉርን ያጥባሉ፣ ይጠቀልላሉ፣ ይተኩሳሉ፡፡ በዚህ መሀል የኤሌክትሪክ ኃይል ሲቋረጥ ተገልጋዩም ሠራተኞችም ክፉኛ ይበሳጫሉ፡፡

እንዲህ ባሉ የሥራ ቀናቶች በተደጋጋሚ ጊዜ ኤሌክትሪክ ሲጠፋ ደንበኞችም ሠራተኞችም ይበሽቃሉ፡፡ ቁጭ ብሎ ለመጠበቅ ትዕግስቱ የሌላቸው ደንበኞች ተስፋ እየቆረጡ ወደየቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ የፀጉር ቤቱ ባለቤት ትዕግስት ዘውዴ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚፈጠረው የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ሥራዋን እንዳይበድለው፣ ደንበኞቿን እንዳያርቅ በ25,000 ብር ጀነሬተር ገዝታለች፡፡ ኤሌክትሪኩ ጠፍቶ የሚቆይ ከመሰላት ጀነሬተሩን ታበራለች፡፡ ይህ ሥራዋ እንዳይቋረጥ ቢያግዛትም የኃይል አጠቃቀሙ ከፍተኛ ስለሚሆን እንደማያዋጣት ‹‹ናፍጣ በጣም ይፈጃል፡፡ ለኤሌክትሪክ የምከፍለውን ሦስት ዕጥፍ ነው የሚያስወጣኝ፡፡ በተለይም ደግሞ ደንበኞች በማይበዙበት የሣምንቱ ቀናት ውስጥ ለአንድና ለሁለት ሰው ጀነሬተር መለኮስ በጣም አክሳሪ ነው፤›› ትላለች፡፡ በተለይ ከሰሞኑ እየታየ ያለው ከፍተኛ የሆነ የኃይል መቆራረጥ እንደሷ ላሉ ትልቅ ፈተና መሆኑን ትናገራለች፡፡

ኢምፔሪያል አካባቢ የሚገኝ የአንድ ሡፐር ማርኬት ባለቤት ናቸው፡፡ የእንስሳት የሥጋ ውጤቶችና ሌሎችም ለምግብነት የሚውሉ ነገሮች ከሌሎች ሸቀጣሸቀጦች ጎን ለጎን ይሸጣሉ፡፡ ‹‹እኛ ጋ መብራት ቢያንስ በቀን አንዴ ይጠፋል፤›› የሚሉት አቶ አበራ የሺጥላ (ስማቸው ተቀይሯል) በአካባቢው በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰተው የኃይል መቆራረጥ ማቀዝቀዣ ውስጥ የሚቀመጡ የምግብ ዓይነቶች እንዳያበላሹ ለሰዓታት ይዞታቸውን ጠብቆ ሊያቆይ የሚችል ማቀዝቀዣ እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ፡፡ ይሁንና ኤሌክትሪክ ለሰዓታት ተቋርጦ በሚቆይባቸው ጊዜያት ማቀዝቀዣ ውስጥ ያሉ የምግብ ዘሮች መበላሸት፣ ሽታ ማምጣት ይጀምራሉ፡፡፡ በዚህም አንዳንድ የምግብ ዓይነቶችን አውጥተው ለመጣል ይገደዳሉ፡፡

ሄድ መለስ እያለ እንደዚህ ከሚፈጥረው ችግር ባሻገር ድንገት ኃይል ጨምሮ የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችን ያቃጠለባቸው እንደ ዘይነብ ያሉም ብዙ ናቸው፡፡

‹‹ሠራተኛዬ ስቶቭ ለኩሳ ወጥ እየሠራች ነበር፡፡ ደንገት አንድ አስደንጋጭ ነገር ተከሰተ፡፡ በቤቱ ውስጥ የፍንዳታ ድምፅ ተሰማ፡፡ ወጥ ሲሠራበት የነበረው ስቶቭ የእሳት ብልጭታ አሳየ፡፡ በዚያው ቅፅበት ድስቱ ወደ ላይ ተስፈንጥሮ በመነሳት ወጡ ተገለበጠ፤›› ስትል ከሁለት ዓመታት በፊት ተከስቶ በነበረ የኃይል መዋዠቅ የተፈጠረውን ገነት ዮሐንስ ትናገራለች፡፡ እንደ ፊልም በአዕምሮዋ ተቀርፆ የሚታወሳት ይኼ ብቻ ቢሆንም በአጋጣሚው ሌሎችም ንብረቶችን አጥታለች፡፡ በምትኖርበት ሣሪስ አካባቢ ያሉ አንዳንድ ጎረቤቶቿም የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎቻቸው ተቃጥሎባቸው እንደነበር ታስታውሳለች፡፡

የጽሑፍ ሥራ የምትሠራበት ዴስክቶፕ ኮምፒውተር በመቃጠሉ ከሌላ ሰው ላፕ ቶፕ ተውሳ ለመሥራት ተገድዳለች፡፡ ቴሌቪዥንም ተቃጥሎባታል፡፡ ዲቪዲና ዲኮደርም ተበላሽቶባታል፡፡ እሷም ሆነች ጎረቤቶቿ ወደ ሚመለከተው አካል በመሄድ ካሳ የጠየቀ ግን አልነበረም፡፡ ‹‹ሰዎችን ስጠይቅ ብዙ ውጣ ውረድ እንዳለው ነገሩኝ፡፡ ዕቃው የራሴ ስለመሆኑ የሚያሳይ ደረሰኝ፣ ግብር የተከፈለበት ደረሰኝና ሌሎችም በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉ መረጃዎች እንደሚጠይቁ ሲነግሩኝ መፍትሔ ለሌለው ነገር ከምለፋ ብዬ ተውኩት፤›› ትላለች፡፡ ሰሞኑን ተፈጥሮ በነበረ የኃይል መዋዠቅም አምፖል ተቃጥሎባቸው እንደነበር ትናገራለች፡

ሃና ማሪያም አካባቢ የሚኖሩት ወይዘሮ አበባ ማሞም ባለፈው ሳምንት ተመሳሳይ ነገር ገጥሟቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ኤሌክትሪክ የጠፋው እሑድ ቀን ነበር፡፡ ከሰዓታት በኋላ ‹‹ሊመጣ ይችላል›› በሚል ዕምነት የተለያዩ ምግቦችን አዘጋጅተው ማቀዝቀዣ ውስጥ አድርገው ነበር፡፡ ሰኞ ለሥራ ከቤት እስከወጡበት ሰዓት ድረስ ግን አልመጣም፡፡ ሥራ ውለው ሲመለሱ ግን ነገሮች በነበሩበት ሁኔታ አልጠበቋቸውም፡፡ በ6,000 ብር የገዙት የውኃ ማጣሪያ ማሽን፣ ከዓመታት በፊት የተገዛ ትልቅ ማቀዝቀዣ ተቃጥሎ ነበር የጠበቃቸው፡፡፡ ሪፖርተር እስካናገራቸው ሰኞ (ባለፈው ሳምንት) ከሰዓት ድረስም ማጣሪያውም ሆነ ማቀዝቀዣው አልተሠራም ነበር፡፡

ንብረታቸው የተበላሸው በኤሌክትሪክ ችግር ቢሆንም ለፈጠረባቸው ኪሳራ ካሳ የመጠየቅ ሐሳብ እንደሌላቸው ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ገብረእግዚአብሔር ታፈረ እንደሚሉት ደረጃውን የጠበቀ የመሠረተ ልማት አለመኖር፣ እንዲሁም የኃይል መዋዠቅ የሚያስከትለውን አደጋ መቆጣጠር የሚችሉ መከላከያ ዕቃዎች (ቮልቴጅ ስታብላይዘር) አለመጠቀም የኃይል መዋዠቅ እንዲከሰትና በኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ላይም የመቃጠል አደጋ እንዲደርስ እያደረጉ ይገኛል፡፡ በአብዛኛው የሚከሰተውም ኤሌክትሪክ ተቋርጦ በሚመለስበት ወቅት ቮልቴጅ (ኃይል) ጨምሮ በሚመጣበት ጊዜ ነው፡፡

እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች በንብረት ላይ አደጋ ሲያጋጥም አደጋው በተከሰተ በ24 ሰዓት ውስጥ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሪፖርት ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ይኼ ካልሆነ ግን ከቆይታ አንፃር አደጋው በምን ምክንያት ተከሰተ? የሚለውን አጣርቶ ተገቢውን ካሳ መስጠት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ሪፖርት እንደተደረገ መሥሪያ ቤቱ ባለሙያዎችን ቦታው ድረስ በመላክ የአደጋውን መንስኤ እንዲያጣሩና ካሳ ይገባል? አይገባም? የሚለውን እንዲወስኑ እንደሚያደርግ አቶ ገብረእግዚአብሔር ይናገራሉ፡፡

የደረሰው አደጋ በጥገና የሚስተካከል ከሆነ ሕጋዊ ከሆኑ ድርጅቶች ፕሮፎርማ በመሰብሰብ እንዲያሠሩ፣ ያሠሩበትንም ደረሰኝ ለመሥሪያ ቤቱ እንዲሰጡ፣ አዲስ መግዛት የሚያስፈልግም ከሆነ እንደዚሁ ከተለያዩ አቅራቢ ድርጅቶች ፕሮፎርማ መሰብሰብና ዋጋውን አወዳድሮ መግዛት፣ የገዙበትን ደረሰኝም ለመሥሪያ ቤቱ በመስጠት ያወጡት ገንዘብ እንዲከፈላቸው እንደሚደረግ ይገልጻሉ፡፡

‹‹ይኼ ሒደት እስከ ሳምንት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚያልቅ ነው፡፡ ኅብረተሰቡም ሕጋዊ በሆነ መንገድ የሚሠራበትን አሠራር ሊያደንቅ ይገባል፡፡ ደንበኞች በአሠራሩ ላይ ቅሬታ ካላቸውም ሕጋዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንዲፈተሽ ይደረጋል›› ብለዋል፡፡

እሳቸው ይኼንን ቢሉም አፈፃፀም ላይ ባሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ብዙ ሰዎች ተስፋ ቆርጠው መብታቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ እንደሚገደዱ በምሬት የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎች አሉ፡፡ ‹‹በንብረት ላይ የደረሰን አደጋ በ24 ሰዓት ሪፖርት ተደርጎ አፋጣኝ ምላሽ ሊሠጥ አይደለም፤ በአንድ ሠፈር ውስጥ መብራት ጠፍቶ ኑ ሥሩ ሲባሉ ሳይመጡ ቀናት ይቆጠራል፤›› በማለት ከፍተኛ የሆነ አፈጻጸም ክፍተት መኖሩን የሚናገሩ አሉ፡፡

አንድ ጉዳይ ለማስፈጸም ያለው ቢሮክራሲም ምነው ቢቀር የሚል ስሜት የሚያሳድር መሆኑን በመግለጽ የራሳቸውን አማራጭ የሚፈልጉ እንደ ገነት፣ ዘይነብና ወ/ሮ አበባ ያሉ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

‹‹የካሳ አከፋፈል ሥርዓቱ በርግጥ አርኪ አይደለም፡፡ የደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት ሌሎች አማራጮችን ማየት እንሞክራለን፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ በዘላቂነት ችግሩን ለመፍታት መስከረም ወር መጨረሻ አካባቢ የተጀመረ ፕሮጀክት መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ከሰሞኑ በከተማው ውስጥ ተፈጥሮ ለነበረው የኃይል መቆራረጥ ኃይለኛ ንፋስ ምክንያት መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅትም እንደተስተካከለ በመግለጽ በ163 ሚሊዮን ብር በጀት የተጀመረው ፕሮጀክት የከተማዋን የኤሌክትሪክ አገልግሎት እንደሚያሻሽለው፣ መሰል የተፈጥሮ ክስተቶችም በኃይል አቅርቦት ላይ የሚኖራቸውን ተፅዕኖ እንደሚቀንስ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ንፋስ በመጣ፣ ዝናብ በመጣ ቁጥር፣ ኃይል የሚቋረጠው ያለው መሠረተ ልማት አሮጌና አቅም የሌለው በመሆኑ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ዝናብና ንፋስን መቋቋም የሚችል አዲስ የመሠረተ ልማት የሚዘረጋ ነው፤›› ሲሉ ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታበት ነው ያሉትን ፕሮጀክት ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢሰመጉ የቀረበበትን የገለልተኝነት ጥያቄ አስተባበለ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በመካከለኛው ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...