– ነፍሰጡሮች በኢንዱስትሪ ስፍራዎች የመቀጠር ዕድላቸው አናሳ ነው
በአበባ አብቃይ፣ በጨርቃ ጨርቅና በቆዳና ሌጦ ፋብሪካዎች ውስጥ የሚሠሩ ሴቶች የተመቻቸ የሥራ ሁኔታ ባለመኖሩ ለዘርፈ ብዙ ችግሮች መጋለጣቸውን፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ከአውሮፓ ኅብረት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ ያሠራው የሠራተኛ ሴቶችን የሥራ ሁኔታ የሚዳስስ ረቂቅ ጥናት አመለከተ፡፡
በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሚገኙ በ20 የአበባ፣ የጨርቃ ጨርቅ እንዲሁም ቆዳና ሌጦ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሠሩ 400 ሴቶችና 100 ወንዶች ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት፣ በተለይ ሴት ሠራተኞች የሥራ ፈቃድ ማግኘት ከመቸገራቸውም በላይ ዝቅተኛ ደመወዝ ተከፋይ ናቸው፡፡
ረቂቅ ጥናቱን የሠሩት አቶ ፈይሰል አዶ እና የጣሊያን ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ተመራማሪ ሚስተር አሌክሳንድሮ ቪሲኒ እንደሚሉት፣ በቅጥር ላይ ነፍሰ ጡርና ልጅ ያላቸው ሴቶች መገለል ይደረግባቸዋል፡፡ አብዛኞቹ ቀጣሪዎችም ልጅ ያላቸውንና ነፍሰጡር ሴቶችን ለመቅጠር ፈቃደኞች አይደሉም፡፡ ይህ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ፣ በፖሊሲዎችና መመሪያዎች የማይፈቀድ ሲሆን፣ ጥናት የተደረገባቸው አብዛኞቹ ፋብሪካዎች ይህንን የሚያደርጉትም በህቡዕ ነው፡፡
በጥናቱ፣ በዕድሜ ከገፉት ይልቅ ለወጣቶች ቅድሚያ እንደሚሰጥ፣ የጎላ ባይሆንም በፖለቲካ አመለካከት፣ በብሔር፣ በቋንቋና በአካል ጉዳት ሳቢያ አድልኦ ታይቷል፡፡
ከመጋቢት 2008 ዓ.ም. እስከ ኅዳር 2009 ዓ.ም. ባሉት ወራት የተሠራው ይኸው ጥናት እንዳመለከተው፣ በጥናቱ ከተሳተፉት ሠራተኞች 54 በመቶ ያህሉ በድርጅታቸው ከእርግዝናና ከወሊድ ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎች ምን እንደሆኑ አያውቁም፤ 59.4 በመቶው ደግሞ ድርጅታቸው ከወሊድ ጋር በተያያዘ ፈቃድ እንዴት መውሰድ እንዳለባቸውም አላሳወቃቸውም፡፡ ብዙ ሴቶችም ለወሊድ ፈቃድ እንደወጡ በዛው ወደ ሥራ ሳይመለሱ ይቀራሉ፡፡
ይህንን በተመለከተ የጥናቱ አቅራቢ ሚስተር አሌክሳንድሮ እንዳሉት፣ ጥናቱ ከተደረገባቸው ፋብሪካዎች ብዙዎቹ የወለዱ ሴቶች ሊያጠቡ የሚችሉበት ስፍራ ስለሌላቸውና፣ ለወለዱ ሴቶች ልጆቻቸውን እንዲያጠቡ የዕረፍት ሰዓት ስለማይሰጡ ሴቶቹ ሥራቸውን ለመልቀቅ ይገደዳሉ፡፡
27.8 በመቶ የሚሆኑት የጥናቱ ተሳታፊዎች ሥራ ለመቀጠር በሚመጡበት ጊዜ እርጉዝ መሆንና አለመሆናቸው እንደሚታይ ሲገልጹ፣ 24.8 በመቶው ደግሞ ቀጣሪዎች እርጉዞችን ለመቅጠር አይፈልጉም ብለው እንደሚያስቡ ተናግረዋል፡፡ ነፍሰጡሮች የእርግዝናና የወሊድ ሕክምና ክትትል ለማድረግ ፈቃድ እንደማያገኙ በዳሰሳ ጥናቱ ተመልክቷል፡፡
የሥራ አመዳደብና ኃላፊነትን በተመለከተ አብዛኞቹ የጥናቱ ተሳታፊ ሴቶች ዝቅተኛ ክህሎትና ትንሽ ዕውቀት በሚጠይቁ ስፍራዎች የሚሠሩ ሲሆን፣ ከልማድ ጋር ተያይዞ ‹‹ይህ የሴት›› ‹‹ያ የወንድ›› ሥራ የሚለው የማኅበረሰቡ ብሂል በአብዛኞቹ ጥናቱ በተካሄደባቸው ድርጅቶች ውስጥ ታይቷል፡፡ የሰውነት ጥንካሬ፣ ጡንቻና ጉልበት የሚጠይቁ ሥራዎች ለወንዶች፣ ቀለል ያሉ ሥራዎች ለሴቶች የተሰጡበት ሁኔታ በጥናቱ የታየ ሲሆን፣ በቤተሰብ ውስጥ ሴት ለቤተሰቧ አጋዥ ተደርጋ እንደምትቆጠረው ሁሉ በድርጅቶቹ ውስጥም እንደ አጋዥ ሆና ታገለግላለች እንጂ እምብዛም በኃላፊነትና ውሳኔ ሰጭነት ቦታ አትገኝም፡፡
የቅጥር ዋስትናን በተመለከተ፣ ጥናቱ ከተካሄደባቸው ከአሥሩ ሰባቱ የሥራ ቅጥር ውል ሲኖራቸው፣ ብዙ ቁጥር ያላቸው ደግሞ በጊዜያዊ ሆኖ ያለምንም የቅጥር ስምምነት ፊርማ የሚሠሩ ናቸው፡፡ በጥናቱ ከተካፈሉ ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ የኮንትራት ውል ፈርመው የተቀጠሩ ቢኖሩም፣ 29.2 በመቶ ያህሉ በምን ዓይነት የሥራ ውል ስምምነት እንደተቀጠሩ አያውቁም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በቀጣሪያቸውና በሠራተኞች መሀል የተደረገ የቅጥር ፊርማ አለመኖሩ ነው፡፡
በሳምንት ሰባቱንም ቀናትና በቀን ሊሠሩ ከሚገባቸው ሰዓት አሳልፈው የሚሠሩ መኖራቸው፣ ከአሥሩ ሦስቱ የዓመት ፈቃድ እንደማያገኙ፣ በሕመም ጊዜ ለሚቀሩት እንደማይከፈላቸው፣ ምንም የሕመም ፈቃድ የማያገኙ እንዳሉ፣ ከጥናቱ ተሳታፊዎች ግማሽ ያህሉ ብቻ ትርፍ ሰዓት ለመሥራት ወይም ላለመሥራት የመምረጥ መብት እንዳላቸው እንዲሁም አንዳንዴ ትርፍ ሰዓት በነፃ መሥራት መኖሩም በጥናቱ ተመልክቷል፡፡
ደመወዝን በተመለከተ ጥናቱ በተካሄደባቸው 20 ድርጅቶች ውስጥ የወንዶች አማካይ ክፍያ ወደ 1115 ሲደርስ የሴቶች 836 ብር ነው፡፡ አንዳንድ ፋብሪካዎች ሥራ ላይ በሰዓቱ ለተገኘ፣ በዓል ሲሆንና በሥራው ጎበዝ ለሆነ የማበረታቻ (ቦነስ) ብር ይሰጣል፡፡ ሆኖም በአንድ ዓይነት የሥራ መደብ ከሚሠሩ ወንዶችና ሴቶች፣ የሴቶቹ ክፍያ ያነሰ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በተለያዩ መድረኮች የተነሳውና መንግሥትም በፖሊሲው ያስቀመጠው የሠራተኞች ደኅንነቱ በተጠበቀ ስፍራ የመሥራት መብት እምብዛም ተግባራዊ አለመሆን ዛሬም ላይ እያታየ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል፡፡ ኩባንያዎች የሠራተኞችን ደኅንነትና ጤና የሚያስጠብቅ የሥራ ድባብ እየፈጠርን ነው ቢሉም፣ በሠራተኞች በኩል ቅሬታ አለ፡፡
የጥናቱም ግኝት ያሳየው፣ አብዛኞቹ ሠራተኞች የሚሠሩባቸው ፋብሪካዎች ደኅንነታቸው ያልተጠበቀና ሠራተኞችን ለአደጋ ተጋላጭ የሚያደርጉ አጋጣሚዎች ያሉባቸው ናቸው፡፡ ከአሥር ሠራተኞች ሰባቱ በሚሠሩበት ስፍራ ራሳቸውን ከአደጋ ለመከላከል የሚያስችላቸው አልባሳት፣ ከአደጋ የመከላከያ ቁሳቁስ የሌላቸው ሲሆን፣ 72 በመቶ የሚሆኑ ሠራተኞች በሚሠሩበት ቦታ ማድረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄ በቀጣሪ በኩል ምንም መረጃ እንዳልተሰጣቸውና ስለሚደርስባቸው ጉዳትም ምንም እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ሠራተኞች የሥራ ቦታ ደኅንነትና ራስን ከጉዳት መከላከልን በተመለከተ ያለው ክፍተት በሥራቸው በሥራቸው ደስተኛ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
አብዛኞቹ ሠራተኞች ንፁህ መፀዳጃ ቤት፣ ሳሙናና የመጠጥ ውኃ ማግኘት ችግር እንደሆነ ሲገልጹ፣ ለምሳሌ ጥናቱ ከተካሄደባቸው ስምንት የአበባ አምራች ኩባንያዎች አብዛኞቹ ለሠራተኛ ምቹ የሆነ የሥራ ስፍራ እንደሌላቸው ጥናቱ አመልክቷል፡፡
በሠራተኛ ማኅበራት መደራጀትን በተመለከተ ሁሉም በጥናቱ የተካተቱ ድርጅቶች የሠራተኛ ማኅበር ያላቸው ሲሆን፣ ማኅበሮቹም እያደጉ ነው፡፡ አብዛኞቹ ማኅበራትም የሠራተኛውን ፍላጎት ለመጠበቅና መብት ለማስከበር የተመሠረቱ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ የጋራ የድርድር መድረክ ያላቸው ሲሆን፣ በሠራተኛና በአሠሪ መሀል አለመግባባት ሲፈጠርና የመብት ጥያቄ ሲኖር በድርድር ለመፍታት ይሞክራሉ፡፡ የሴቶች የማኅበራቱ አባልነት እያደገ ቢመጣም፣ አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙባቸው ማኅበራት ቢኖሩም፣ በአመራሩ ላይ የሚገኙት ግን ጥቂት ናቸው፡፡ ይህንን አስመልክቶ አቶ ፈይሰል እንደሚሉት፣ የሠራተኛ ማኅበር አመራሮች በምርጫ የሚመጡ ሲሆን፣ ብዙ ሴቶች ባሉበት መድረክ እንኳን ወንዱ እንዲመራ ዕድል የመስጠት ሁኔታ አለ፡፡ ይህም ሴቶቹ ራሳቸው ሴት በአግባቡ ላይመራን ይችላል ከሚል አመለካከት የተነሳ ድምፃቸውን ላሉት ጥቂት ወንዶች የሚሰጡበት ሁኔታ መኖሩን ያሳያል፡፡ በማኅበረሰቡ ለሴቶች ሲሰጥ የነበው ስፍራም የራሱን ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡
ከ18 እስከ 35 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ 75 በመቶ ያህል ሠራተኞችን ያካተተው የዳሰሳ ረቂቅ ጥናት፣ በተለይ ሴት ሠራተኞች በምቹ ሁኔታ እየሠሩ እንዳልሆነ አመላክቷል፡፡
በረቂቅ ጥናቱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰላማዊ ኢንዱስትሪ ግንኙነት ማስጠበቂያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ገብሩ፣ ጥናቱ ከሠራተኛ ወገን ብቻ ከሚሆን የኢንዱስትሪ ሰላማዊነትን የሚቆጣጠረውን መንግሥታዊ አካል እንዲሁም አሠሪውን ቢያካትት ግኝቱ የተለየ ሊሆን ይችል እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የሥራ ቦታ ምቹ ነው ብሎ መደምደም ባይቻልም፣ የኢንዱስትሪ ሰላማዊነትን ለማረጋገጥ መንግሥት ያስቀመጣቸው ሕጎች፣ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች ስላሉ፣ አሠሪዎች ይህንን እንዲተገብሩ የሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል በጥናቱ ቢሳተፍ መልካም ነበር ብለዋል፡፡
ሠራተኞችንና አሠሪዎችን በተመለከተ ፖሊሲዎችም ሆኑ መመሪያዎች ቢኖሩም ተግባራዊ አለመሆናቸው ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሲነሳ መቆየቱን፣ ሕጎች ቢኖሩም በሠራተኛ ላይ የሚፈጸም አድልኦም ሆነ የመብት ጥሰት በህቡዕ እንደሚፈጸም በመጥቀስ ጥያቄ ያነሳንላቸው አቶ ፍቃዱ፣ የሥራ ቦታ ጉዳይ አሠሪ ሠራተኛ መንግሥትን የሚመለከት በመሆኑ በጥናቱ ላይ የአንድ ወገን መሆኑን አልስማማበትም ብለዋል፡፡ ሆኖም መንግሥት የሠራተኛ መብትን የጣሰ ልማትና በዚህ የሚመጣ የኢኮኖሚ ዕድገትንም አይፈልግም ብለዋል፡፡
በማኅበር መደራጀትን በተመለከተ የሠራተኛ መብት መሆኑን፣ ይመራናል የሚሉትን አካል ውክልና የሚሰጡትም አባላቱ መሆኑን የገለጹት አቶ ፍቃዱ፣ ሴቶች በሠራተኛ ማኅበር በኃላፊነት እንዲመጡ፣ ከታች ጀምሮ መሠራት አለበት ብለዋል፡፡
ለሴቶችም ሆነ ለሠራተኛው ምቹ የሥራ ሁኔታ ተፈጥሯል ብላችሁ ታምናላችሁ ወይ? በሚል ላነሳነው ጥያቄም፣ ሁሉም ነገር ደረጃውን የጠበቀ ነው ብለው እንደማያምኑ፣ ሆኖም የአሠሪውንም ሆነ የሠራተኛውን ችግር መፍታት እንደሚገባ ይናገራሉ፡፡ ብዙ ደጋፊ ፖሊሲዎች መኖራቸውን ያስታወሱት አቶ ፍቃዱ፣ ሠራተኛውም ሆነ ቀጣሪው ሕጎችን እንዲተገብሩና በሕጉ ተጠቃሚ ነን ብለው እንዲያምኑ አስተሳሰባቸውን መለወጥ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ውይይቱን የመሩት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው፣ በመንግሥት በኩል የሥራ ቅጥር ስምምነት እንዲኖር ፖሊሲው ቢያስቀምጥም ይህንንና ሌሎች መብቶችን ጨምሮ በአሠሪዎች በኩል እየተተገበሩ አለመሆናቸውን፣ ችግሩም የፖሊሲና የመመሪያ እጦት ሳይሆን እነዚህን የሚተገብር አሠሪ፣ ተተግብረዋል ወይ ብሎ የሚቆጣጠር በቂ የሰው ኃይል አለመኖሩ ችግሩን አጉልቶታል ብለዋል፡፡
ሴቶችን ለማግለል አንድ አሠሪ ግልፅ የሆነ መስፈርት ማውጣት አይጠበቅበትም ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ሴቶች በሥራ ቦታ እየተገለሉ፣ ዝቅተኛ ደመወዝ እየተከፈላቸው መሆኑ ጥናቱ በተሠራባቸው 20 ድርጅቶች ስለታየ፣ የታዩትን ችግሮች ለመፍታት መንግሥት፣ አሠሪና ሠራተኛ አብረው መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡
በረቂቅ ዳሰሳ ጥናቱ ላይ ታኅሣሥ 6 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዝማን ሆቴል በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ከተካፈሉት ውስጥ ያነጋገርናቸው የሠራተኛ ማኅበራት ተወካዮች እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ርካሽ ጉልበት አለ መባሉም ለሠራተኛው መብት መጣስ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ሠራተኛውን ውል አስፈርመው በኮንትራት ወይም በቋሚነት ከመቅጠር ይልቅ በቀን ሒሳብ በመቅጠር የሚያሠሩም አሉ፡፡ ይህ ደግሞ ሠራተኛው በመብቱ እንዳይጠቀም አድርጎታል፡፡
የጥናቱ አቅራቢዎች ችግሩ እንዳለ በመጥቀስ፣ መሠረታዊ የሠራተኞች መብት ላይ ግንዛቤ መስጠት፣ የሥራ ቦታ ግንኙነት ላይ ውይይት እንዲዳብር ማድረግ፣ ለሠራተኞች በጽሑፍ የተደገፈ የቅጥር ኮንትራት እንዲኖር፣ ዝቅተኛ የክፍያ መጠን እንዲቀመጥ፣ ፆታን መሠረት ያደረገ የሥራ ክፍፍልን መቀነስና ፆታዊ ጥቃትን መከላከልን እንደ መፍትሔ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡