Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየዱር እንስሳት ሕገወጥ ዝውውር በረቀቀ ዘዴ መከናወኑ የመከላከሉን ሥራ አደናቅፎታል ተባለ

የዱር እንስሳት ሕገወጥ ዝውውር በረቀቀ ዘዴ መከናወኑ የመከላከሉን ሥራ አደናቅፎታል ተባለ

ቀን:

ወንጀሉ የሚፈጸምበት ዘዴ የረቀቀ መሆኑና የባለድርሻ አካላት ወንጀሉን የመከላከል አቅም አለመጣጣም፣ የዱር እንስሳትና ውጤቶቻቸው ሕገወጥ ዝውውርን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት፣ እያደናቀፈው እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

ወንጀሎቹ የሚፈጸሙት የላላ ጥበቃ በሚታይባቸው ድንበሮች ላይ መሆኑ፣ በአገሪቱ ያሉት የዱር እንስሳትን ትክክለኛ ቁጥር የሚያሳይ አገራዊ መረጃ አለመኖሩ፣ የበጀት እጥረትና የማኅበረሰቡ አመለካከት ዝቅተኛ መሆን ለችግሩ መባባስ ተጨማሪ ምክንያት መሆናቸውን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡

ከአውራሪስና ከዝሆን ጥርስ በተጨማሪ የጅብ፣ የአንበሳ፣ የአቦሸማኔ ግልገሎች የወንጀሉ ሰለባ ናቸው፡፡ የሰጎን እንቁላልና የተለያዩ የእባብ ዝርያዎችም በሕገወጥ መንገድ ከአገሪቱ እየወጡ ይገኛሉ፡፡

‹‹አገሪቱ የሕገወጥ የዱር እንስሳትና ውጤቶቻቸው ዝውውር ምንጭም መሸጋገሪያም ነች፡፡ የአቦሸማኔ ግልገሎች ከሶማሌ ወደ የመን ከየመን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ይላካሉ፡፡ የተለያዩ ተሳቢ እንስሳትም የሚወጡበት ሁኔታ አለ›› ያሉት የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳውድ ሙሜ፣ ባለሥልጣኑ ችግሩን ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ስምጥ ሸለቆ፣ ጅግጅጋ፣ አሳይታ፣ በሰቃ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ የዝውውሩ ዋና ዋና መስመሮች መሆናቸውም ታውቋል፡፡ ‹‹ወንጀሎቹ የሚፈጸሙት የሕግ ተፈጻሚነት ክፍተት ባለባቸው አካባቢዎች ነው፡፡ ክፍተቱን ለመሙላትም በተመረጡ 59 ቦታዎች ላይ ለሚገኙ ባለሙያዎች ሥልጠና ሰጥተናል፡፡ በሕገወጥ ዝውውር የሚወጡ የዱር እንስሳትን በስፋት ከሚገዙት ከዓረብና ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ጋር ወንጀሉን መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ሁለት ጊዜ ያህል ተወያይተናል፡፡ ቺታህ ኮንሰርቬሽን ፎረም ለማቋቋምም ስምምነት ላይ ደርሰናል›› ብለዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ተልዕኮ በአገሪቱ የሚገኙ የዱር እንስሳትና መኖሪያ አካባቢያቸውን በኅብረተሰቡና በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ማስጠበቅ ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የሚቻለው በዱር እንስሳትና አካባቢያቸው ላይ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባራትን መቀልበስ ሲቻል ነው፡፡ ለዚህም በዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ውስጥና ከዱር እንስሳት ጥበቃ ቦታዎች ውጪ የሚፈጸሙ ሕገወጥ ተግባሮችን መከላከል ላይ ያተኮሩ ሥራዎች እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

የባለሥልጣኑ የኅብረተሰብ አጋርነትና የዱር እንስሳት ጥበቃ ትምህርት ዳይሬክቶሬት በማቋቋም ለኅብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች እንዲሠራ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ ለፌዴራልና ለክልል ፖሊሶች፣ ለመከላከያ ሠራዊት፣ ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንና ለኢሚግሬሽን ባለሙያዎች ሥልጠና በመስጠት ሕገወጥ ዝውውሩን ለመቀነስ ጥረት እንደሚደረግም አቶ ዳውድ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ይህንን ያሉት ረቡዕ ታኅሳስ 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በወመዘክር ሕገወጥ የዱር እንስሳት ዝውውር በተለይም አቦሸማኔ ላይ ትኩረቱን አድርጎ በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ነው፡፡ ፕሮግራሙን ያዘጋጀው የአሜሪካ ኤምባሲ ሲሆን የቺታህ ኮንሰርቬሽን ፈንድ መሥራች ፓትሪሺያ ትሪኮሬቺ ሕገወጥ የዱር እንስሳት ዝውውር ምን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ችግሩን ለመቅረፍም የባለድርሻ አካላት ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...