Friday, February 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ክልሎች በብሔር ብሔረሰቦች በዓል አዘጋጅነት ሰበብ ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን እየሳዩ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግሥት የጸደቀበት ቀን ነው፡፡ ይህንን ቀን መነሻ በማድረግ በያመቱ የብሔር ብሔረሰቦች በዓል መከበር ከጀመረ 11 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ የመጀመሪያው በዓል በፌደሬሽን ምክር ቤት አሰባሳቢነት ከተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በተወከሉ የባህል ቡድኖች አማካይነት በአዲስ አበባ ስብሰባ ማዕከል ባህሎቻቸውን በማሳየትና ስለፌደራሊዝም ሲሞፕዝየም በማካሄድ የተጀመረው አከባበር በተከታታይ በተለያዩ ክልሎች እየተካሄደ አሁን ላይ ደርሷል፡፡

ይህ የበዓሉ መሠረታዊ ፓለቲካዊና ማኅበራዊ መገለጫው ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደሚታየው ከሆነ በዙር እንዲከበር መደረጉ በአዘጋጆቹ ክልሎች ላይ የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሌላኛው መገለጫው እየሆነ መጥቷል፡፡

ከሦስት እስከ አራት ሺሕ የሚገመት ቁጥር ያለው የበዓሉ ታዳሚ ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው ይጓጓዛል፡፡ ከተነሰቡት ጀምሮ በዓሉ እስከሚከበርበት ክልል ድረስ ባለው ጉዟቸው መካከል የሚገኙ ሆቴሎችና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች  የሚያገኙት ኢኖሚያዊ ጠቀሜታ እያደገ መምጣቱ እየታየ ነው፡፡ በዓሉን በሚያዘጋጀው ክልል የሚካሄደው ዝግጅትና የሚያስገኘው የኢኮኖሚ ጥቅምም እየተበራከተ መጥቷል፡፡ ከወትሮው በተለየ መልኩ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችና አዳዲስ ግንባታዎችም በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቁበት አኳኋን እየታየ ነው፡፡  እንግዶችን ያለምንም እንከን በመጡበት አኳኋን ለመሸኘት አዘጋጁ ክልል ከሚያከናውናቸው ሥራዎች በተጨማሪ፣ በግል ባለሀብት የሚገነቡ ሆቴሎች ከወትሮው በተለየ ፍጥነት በመጠናቀቅ ለአገልግሎት መብቃት ጀምረዋል፡፡ ቀደም ሲል የተገነቡትም አቅማቸውን በማሳደግና ተጨማሪ የሰው ኃይል በመቅጠር ሰፊ የሥራ መስክ እየፈጠሩ መጥተዋል፡፡  በብሔር ብሔረሰቦች በዓል ዝግጅት ተጠቃሚ እየሆኑ ከመጡት መካከል የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል፣ የጋምቤላና የቤንሻንጉል እንዲሁም የዘንድሮውን በዓል ያዘጋጀው የሐረሪ ክልል ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ክልሎች በረዥም ጊዜ ሒደት አቅደው ለመሥራት ያልተሳካላቸውን መሠረተ ልማቶች፣ በዓሉ በፈጠረው አጋጣሚ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ያሟሉ ስታዲየሞችና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን መገንባት ችለዋል፡፡ እንዲሁም በግል ባለሀብቶች የባለኮከብ ሆቴል ባለቤት ለመሆንም በቅተዋል፡፡

አቶ አብዱልመሊክ በከር የሐረሪ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባዔና የብሔር ብሔሰረቦች በዓል ዝግጅት ዓብይ አስተባባሪ ናቸው፡፡ 11ኛው የብሔር ብሔረሰቦች በዓል በክልላቸው መዘጋጀቱ ምን ዓይነት የኢኮኖሚ መነቃቃት እንደተፈጠረ በሪፖርተር ተጠይቀው ሲመልሱ እንዲህ ብለዋል፡፡

‹‹በመጀመሪያ ራስን ችሎ ለማስተዳደር የሚያዙ ዕቅዶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሐረሪን የሚያስቸግራት የንፁህ ውኃ መጠጥ አቅርቦት፣ የመንገድ ግንባታ፣ ብዙ ጊዜ ፈጅቶ የነበረው የባህል ማዕከል ሥራዎች ነበሩ፤›› ያሉት አቶ አብዱልመሊክ፣ በበዓሉ ምክንያት ለ150 ሺሕ ሰዎች የሚውል ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የ3.4 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ግንባታ፣ ከ2500 በላይ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሽን ያካተተ የባህል ማዕከል ግንባታ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በጠቅላላው በሚሊዮኖች የሚቆጠር በጀት በመመደብ ሥራዎቹ እንዲጠናቀቁ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ ግንባታዎች ሰበብ የተንቀሳቀሰው የኢኮኖሚ ዘርፍ እስከዛሬ ከነበረው እንደሚበልጥ አብራርተዋል፡፡

 አቶ አብዱልመሊክ እንደገለጹት፣ በክልሉ በ1.8 ቢሊዮን ብር በጀት በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ታቅዶ የነበረው የስታዲየም ግንባታ ነው፡፡ ይሁንና በዓሉ እንዲከበርበት በማሰብ 680 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎ በ10 ወራት ውስጥ የስታዲየሙ የመጀመሪያ ደረጃና የሜዳ ማልበስ ሥራ እንዲጠናቀቅ በማድረግ፣ ለበዓሉ እንዲደርስ መደረጉን አቶ አብዱልመሊክ አብራርተዋል፡፡ በሐረሪ ክልል ለብዙ ጊዜ ችግር ሆኖ የቆየውን የሆቴል አገልግሎት ዕጥረት ለመቅረፍም በአጭር ጊዜ ውስጥ 43 ክፍሎች ያሉት የእንግዳ ማረፊያ በመንግሥት ወጪ ሊገነባ መቻሉን አፈ ጉባዔው ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹እነዚህ ፕሮጀክቶች በዓሉን ለማዘጋጀት ከተቀበልን በኋላ ታቅደው የተሠሩ ናቸው፡፡ በእነዚህ የሥራ ጊዜያት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ ዕድል አግኝተዋል፤›› ያሉት አቶ አብዱልመሊክ፣ በበዓሉ ምክንያት ኢኮኖሚው ትልቅ ለውጥ ለማምጣቱ ማሳያ እንደሆነ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በሐረሪ ክልል በግል ባለሀብቶች እየተገነቡ ከነበሩ ባለአራት ኮከብ ደረጃ ሊያገኙ እንደሚችሉ ከሚጠበቁ ሦስት ሆቴሎች ውስጥ፣ በዓሉ ከመድረሱ ቀደም ብሎ የተጠናቀቀው ወንደር ላንድ ሆቴል ተጠቃሽ ነው፡፡ የሆቴሉ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ኢብራሂም እንደገለጹት፣ በሦስት ዓመት ውስጥ በ70 ሚሊዮን ብር ወጪ እንዲገነባ ዕቅድ በማውጣት ሥራውን የጀመሩት ቢሆንም፣ በዓሉ እየደረሰ በመምጣቱ ምክንት ተጨማሪ አንድ ሚሊዮን ብር በመመደብ ከተያዘለት ጊዜ ቀድሞ እንዲጠናቀቀቅ በማድረግ ለበዓሉ ሲባል ሥራ መጀመሩንና በአሁኑ ወቅትም ለአንድ መቶ ሰዎች የሥራ ዕድል እንደፈጠሩ ገልጸዋል፡፡

ክልሎች የስታዲዮም ግንባታዎችን በማካሄድ ለበዓሉ ዝግጅት ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በመሆኑም በሐረሪ ክልል ከዲዛይኑ ጀምሮ እስከ ግንባታው ሥራ ድረስ በአገር በቀል ተቋራጮች የተገነባው የክልሉ ዓለም አቀፍ ሲታዲየም ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ 360 አልጋዎች ያሉት ሆቴልና ስታዲየምን በአንድ አጣምሮ የያዘ ግንባታ ነው፡፡

አዋ አባድር ሁለገብ ስታዲዮም የሚል ስያሜ የተሰጠውን ስታዲየም ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ እንዲገነባ ለማስቻል በተደረገው እንቅስቃሴ፣ የመጀመሪያው ዙር ግንባታ ተገባዶ ለበዓሉ እንዲደርስ ተደርጓል፡፡ ግንባታው ሲጀመር በቀን ከአንድ ሺሕ  እስከ 2500 የሚደርሱ ሠራተኞችን በመቅጠር ለታሰበለት ቀን አድርሰነዋል ያሉት፣ በአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን የአዋ አባድር ሁለገብ ስታዲዮም ግንባታ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ፍሰሐ ገብረ ሚካኤል ናቸው፡፡ ‹‹ሥራው ሲካሄድ በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁ በርካታ ወጣቶች የሰብ ኮንትራት ሥራ በመስጠት ከመደገፍ ባሻገር፣ የቀሰሙት ልምድ ራሳቸውን ችለው የተቋራጭ ሥራዎችን እንዲሠሩ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

በበዓሉ ወቅት የሚቀርቡ የንግድ ትርዒቶች፣ የመዝናኛ ኮንሰርቶች፣ የክልሉን ባህላዊ አልባሳት የሚሸጡ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ፣ ካፍቴሪያዎችና ሬስቶራንቶች በሐረሪና በሌሎችም ክልሎች የሚያስገኙት ኢኮኖሚ ጠቀሜታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችን ዓመታዊ በዓል በበላይነት የሚመራውና የሚቆጣጠረው የፌደሬሽን ምክር ቤት ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ተራው ለደረሰው አዘጋጅ ክልል ምን ዓይነት ድጋፍ እንደሚያደርግ ያብራሩት፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረ ሥላሴ ናቸው፡፡

ምክር ቤቱ የማስተባበሩን ሥራ በማከወናን በክልሎች ለሚያከናውኗቸው የግንባታ ሥራዎች ከፌዴራል መንግሥት የማማከር ድጋፍ ይሰጣል ያሉት አቶ ገብሩ፣  በግንባታቸው ወቅት ችግር ካጋጠማቸውም በአፋጣኝ ለመፍታት የሚያስችሉ መትፍሔዎችን በማፈላለግ ዕገዛ ያድጋል ብለዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች