በኮንስትራክሽን ዘርፍ ውስጥ የሚታዩ ችግሮች በሳይንሳዊ ጥናቶች ሊፈቱ እንደሚባ ተገለጸ፡፡
ይህ የተገለጸው ሁለተኛው አገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ሥራዎችና ቤቶች ልማት ዘርፍ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስርን ለማጠናከር ዓርብ ታኅሳስ 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በዋሽንግተን ሆቴል በተዘጋጀ ዓውደ ጥናት ላይ ነው፡፡ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን በኮንስትራክሽን ሥራ የተሰማሩ ኩባንያዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጋራ በመለየት፣ ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈቺ የሆኑ ጥናቶች በማካሄድና የቴክኒክ ምክር በመስጠት ለዘርፉ ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
ዓውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉ ባለፉት አሥር ዓመታት ለአጠቃላይ አገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በየዓመቱ 12.43 በመቶ ዕድገት እያስመዘገበ ሲሆን፣ ለአገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት ያለው ድርሻ 5.3 በመቶ ነው፡፡ ነገር ግን የዘርፉን አኅጉር አቀፍ ብሎም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት በዘርፉ ጥቅም ላይ እየዋሉ ካሉ ቴክኖሎጂዎችና የአሠራር ሥርዓቶች፣ እንዲሁም አጠቃላይ ውጤታማነት አንፃር ሲታይ አነስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ኢንጂነር አይሻ አስረድተዋል፡፡
በኮንስትራክሽን ሥራዎችና ቤቶች ልማት ዘርፍ ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ማጠናከር በአገሪቱ ያሉትን የትምህርት ተቋማት፣ የምርምርና ሥርፀት ዘርፉን፣ እንዲሁም በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን በማስተሳሰርና ቅንጅታዊ አሠራር በመፍጠር የጋራ ጥናትና ምርምር ማድረግ፣ ከጥናትና ምርምር የሚገኙ ውጤቶችን ወደ ኢንዱስትሪው እንዲሰርፅ በማድረግ፣ በተጨማሪም ከኢንዱስትሪው የሚመጡ የምርምር ጥያቄዎችን ወደ ምርምር ተቋም በመላክ የማማከርና ተዛማጅ አገልግሎትን በመስጠት፣ አገሪቱ ያላትን ሀብት በአግባቡ እንድትጠቀም ማድረግ ቀዳሚ የመንግሥት አጀንዳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. የተመሠረተው አገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ሥራዎችና ቤቶች ልማት ዘርፍ ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ስድስት ንዑስ ቀጣና ፎረሞች ያቋቋመ ሲሆን፣ 16 ዩኒቨርሲቲዎችን በአባልነት ይዟል፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዮሴፍ ብሩ እንደተናገሩት፣ ብሔራዊ ፎረሙ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ተዋንያንና ዩኒቨርሲቲዎች በመተባበር በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ጥናቶች እንዲካሄዱ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ዶ/ር ዮሴፍ ለሪፖርተር እንደገለጹት ዘገምተኛ ምርታማነት ዕድገት፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ አለመጠቀምና ወጪ ቆጣቢ የግብዓት አጠቃቀም ሥርዓት አለመኖር በዘርፉ ከሚታዩ ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ረገድ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ እምቢተኝነት እንዳለ የገለጹት ዶ/ር ዮሴፍ፣ ግትር ኢንዱስትሪ እየተባለ እንደሚጠራ ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ በፖሊሲ ደረጃ ሲታይ ኪራይ ሰብሳቢነት የዘርፉ ዋነኛ ችግር ተደርጎ መለየቱን የገለጹት ዶ/ር ዮሴፍ፣ በቁጥጥር ሥርዓት በፈቃድ አወጣጥና የብቃት ማረጋገጫ አሰጣጥ ላይ ማሻሻያዎች ማድረግ ሊያስፈልግ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡
ከተመሠረተ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የኮንስትራክሽን ሥራዎችና የቤት ልማት ኢንዱስትሪ ዩኒቨርሲቲ ትስስር ሥራዎች ላይ የታዩ ክፍተቶች በውይይት መድረኩ ላይ ተገልጸዋል፡፡
በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ፎረም ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉጌታ ዳዲ፣ ዩኒቨርሲቲዎችና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የተለያዩ ፍላጎቶች እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ዕውቀትን፣ ጥናቶችን ማሳተም፣ የገንዘብ ድጋፍና አዳዲስ ጥናቶችን ማካሄድ እንደሚፈልጉና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው መረጃዎችን፣ ምርቶችን፣ ገበያና ትርፍ እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡
ምሁራን ያጠኑት ጥናት ይሰረቅብኛል የሚል ሥጋት እንደሚያድርባቸው የገለጹት ዶ/ር ሙሉጌታ፣ በኢንዱስትሪው ዘርፍ በኩል ለጥናቶች የገንዘብ ድጋፍ ያለማድረግ፣ ለምርምር የሚላኩ ተማሪዎችን ያለመቀበል ችግሮች እንደሚታዩ አስረድተዋል፡፡
በኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር ኢንጂነር ዛህራ አብዱልሃዲ በበኩላቸው፣ ከጥናት የሚገኙ ውጤቶች ጠቀሜታ ላይ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆንና ለምርምር የሚሆን ገንዘብ የመመደብ ችግር እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎች ለጥናት የተመደበ በጀት መጠን የማወቅ ፍላጎት፣ የምርምር ውጤት ባለቤትነት ለሌላ ወገን ይሰጥብኛል የሚል ሥጋት እንደሚታይባቸው ኢንጂነር ዛህራ ገልጸዋል፡፡
የሕንፃ ተቋራጮች ማኅበር ተወካይ በዩኒቨርሲቲዎች የሚካሄዱ ጥናቶች በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን የሚፈቱ መሆን እንዳለባቸው ጠይቀዋል፡፡ ምርምሮቹ የሚካሄዱት የኮንትራክተሩን ፍላጎት መሠረት አድርገው መሆን እንዳለበት የገለጹት ተወካዩ፣ በግብዓት አጠቃቀም ወጪ ቆጣቢ በመሆኑ በቴክኖሎጂዎች ላይ ጥናቶች ቢካሄዱ ጠቀሜታቸው የጎላ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ጥናቶቹ መሬት ላይ ወርደው ሊተገበሩ የሚችሉ መሆን አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡
ሌሎች ተሳታፊዎች በበኩላቸው የገንዘብ እጥረት ለጥናትና ምርምሮች ዋነኛ እንቅፋት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የተለያዩ ኢንዱስትሪዎች ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ሰነድ ከፈረሙ በኋላ ወደ ተግባር ሳይለወጡ የሚቀሩት በአብዛኛው በበጀት እጥረት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በርካታ ጥናቶችና ምርምሮች ተሠርተው ጥቅም ላይ ሳይውሉ በመደርደሪያ ላይ እንደሚቀሩ የገለጹት ሌላው ተሳታፊ የጥናት ድግግሞሽ እንደሚታይ ገልጸዋል፡፡ አንዱ ዩኒቨርሲቲ አንድ ምርምር ይሠራል፣ ከትንሽ ጊዜ በኋላ ሌላው ዩኒቨርሲቲ ተመሳሳይነት ያለው ምርምር ያካሂዳል፡፡ ይህ በአገር ሀብት ላይ ብክነት ያስከትላል ያሉት ተሳታፊው፣ በዩኒቨርሲቲዎች መካከል የመረጃ ልውውጥ ሊኖር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በኮንስትራክሽን ዘርፉ ያሉ ችግሮችን በሳይንሳዊ ጥናትና ምርምሮች በሚገኙ ውጤቶች መፈታት አስፈላጊነት፣ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውና በዩኒቨርሲቲዎች የተመሠረተውን ትስስር ማጠናከር ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ መሆኑ ተገልጿል፡፡