በ1999 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረውና በ1.5 ቢሊዮን ዩሮ ወጪ የተጠናቀቀው ጊቤ ሦስት የኃይል ማመንጫ ግድብ፣ 1,870 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ቢችልም 900 ሜጋ ዋት ኃይል በማመንጨት ላይ ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ ቅዳሜ ታኅሳስ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. የተመረቀው ጊቤ ሦስት ግድብ ባጠራቀመው የውኃ መጠን ነው 900 ሜጋ ዋት በማመንጨት ላይ የሚገኘው፡፡ እያንዳንዳቸው 187 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚችሉ አሥር ተርባይኖች ቢኖሩትም፣ ግድቡ ያጠራቀመው ውኃ አነስተኛ በመሆኑ ነው ከአቅም በታች ኃይል የሚያመነጨው ተብሏል፡፡ ግድቡ በቂ ውኃ ማጠራቀም ሲችል ግን ሁሉም ተርባይኖች ሙሉ በሙሉ ሥራ እንደሚጀምሩ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡
ጊቤ ሦስት የጊቤ አንድ (184 ሜጋ ዋት) እና የጊቤ ሁለት (420 ሜጋ ዋት) ተከታይ በመሆን በግልገል ጊቤ ወንዝ ላይ ነው የተገነባው፡፡ ከአጠቃላይ የግንባታ ወጪው 60 በመቶ ከቻይና መንግሥት ሲገኝ፣ በመንግሥት የተሸፈነው 40 በመቶ ነው፡፡ ግንባታውን ያከናወነው ደግሞ የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ነው፡፡ የጊቤ ሦስት ግድብ 246 ሜትር ከፍታ፣ 630 ሜትር ርዝመት ሲኖረው ውኃ የመያዝ አቅሙ ደግሞ 1.5 ቢሊዮን ሜትር ኩብ መሆኑ ታውቋል፡፡ ቅዳሜ ዕለት ከመመረቁ ቀደም ብሎ ኃይል በከፊል ማመንጨት የጀመረ ሲሆን፣ ሙሉ ለሙሉ ማመንጨት (1,870 ሜጋ ዋት) ሲጀምር ደግሞ የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት 4,200 ሜጋ ዋት እንደሚያደርስ ታውቋል፡፡