Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ስንቱ ተፈትሎ ስንቱ ተሸመነ?

ሰላም! ሰላም! እነሆ ማንጠግቦሽ ባሌ ለምን ወጉ ይቅርበት ብላ ነው መሰል በሬዲዮ ስሜን ጠርታ ‹ስምህን አውሰኝ› የሚለውን ዘፈን ጋበዘችኝ። በአንዴ የዝነኝነት መንፈስ ውርር አድርጎኝ ዙሪያ ገባዬን ቁልቁል ማየት ጀመርኩ። እንግዲህ አስቡት? በሬዲዮ ስሜ ተጠራ ብዬ አካባቢዬን ያቃለልኩ፣ ሕዝብ በድምፁ ተወካዩ አድርጎ ቢመርጠኝ ምን ልሆን እንደምችል? ለካ አንዳንዱ ወዶ አይደለም የመጣንበትን ረስቶ የምንሄድበትን የሚያቀዣብረን ብዬ ከራሴ ጋር አውርቼ ዝም አልኩ። እህ ለማን ይወራል ታዳያ ይኼ? ትርጉምና የነገር አፈታት እያስተዛዘቡን እያያችሁ እስኪ አሁን እንዲህ ያለ ጨዋታ ስትጫወቱ። የተጋበዝኩት ዘፈን ሳያልቅ የቀጠርኳቸው ደንበኞቼ እንዳይደውሉ ፈጣሪን ስማፀን ዘፈኑ ተቋረጠ። መብራት የጠፋ መስሎኝ በሞባይሌ ሬዲዮ ልከፍት ስጣደፍ አንድ ለዛ ሙጥጥ የሆነ የሁካታ ዘፈን ቀጠለ። ቅጥል አልኩ።

ኋላ ለባሻዬ ልጅ ሳጫውተው በእሱ ቤት አሹፎ ሞቶ፣ ‹‹የተቃወሚዎችህ ሴራ ነው፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ታዲያ እኔም ስልኬ ካልጮኸ ከነበርኩበት ሥፍራ መንቀሳቀስ አልችልም ነበርና ያ ሞዛዛ የሁካታ ዘፈን ሰባት ደቂቃ ደልቆ እስኪያልቅ ብክንክን ብዬ አስጨረስኩት። ድሮስ ምን ምርጫ አለህ አትሉኝም? ውበትና ሙዚቃ እንደ ተመልካቹ ነው ባዮች መሆን አለባችሁ። መቼም እንዲህ ስትሉ ካርል ማርክስ ቢሰማችሁ መደብና ኪነት ምንም ቢሆን ምን ተነጣጥለው አያውቁም። ኪነት ሁሉ የወከለው መደብ ማሳያ ነው እያለ ቅጽ በቅጽ ላይ የጻፈበትን ዘመን ታስረግሙት ነበር። ግን ግን እንዴት ነው የእኛ የውበት፣ የእውነትና የኪነት ብስለት ከመደቡም ከአተያዩ ማዕዘንም ሆነ ከምኑም ከምኑም የሌለበት መሰለሳ? ለእኔ ብቻ ነው? መቼም ነገር በማስረጃና በምሳሌ ነውና የሚያምረው እስኪ የደላላ ስልኬ እስኪጮህ ትንሽ ላብራራላችሁ። አይዟችሁ በመሀል በመሀል እንዳይሰለቻችሁ እንደ ዘመኑ ማኅበረሰባዊ ሚዲያዎች ሙዚቃና የኢንተርኔት መረጃ እገርብላችኋለሁ!

ይኼውላችሁ ዘመኑ እንደምታዩት ሥር ነቀል ለውጥ ያለሥር ሰደድ መረጃና ዕውቀት እያመጣብን ተቸገረን። የት ነን? የት ነበርን? ወዴት ነን? መሰል ጥያቄዎች አፍ እስኪያሲዝ ድረስ ሁሉም ተናጋሪ፣ ሁሉም አዋቂ ሁሉም ፈራጅ ሁሉም ነብይ ሆነ። በበኩሌ ሐሳብን በነፃነት መብት እጄንም እግሬንም አውጥቼ ብስማማም በመዘባረቅና ሐሳብን በነፃነት በመግለጽ ሒደት መሀል ሰፊ ልዩነት ያለ ይመስለኛል። ይኼንን ስል ያ ቦጅባጃ ተለማጅ የአስረሽ ምቺው ሙዚቃ ዘፍኖ እንዳበቃ፣ ስለሙዚቃ በተለይ ስለአገራችን ሙዚቃ ከእኔ በላይ ላሳር ያሉ ወጣቶች አየሩን ተቆጣጠሩት። ገና ከመጀመራቸው አንደኛው፣ ‹‹እዚህ አገር ለጥበብ ክብር የሚሰጥ ሰው የለም፤›› ብሎ በጠቅላላው ወቃን። ይሁን ብዬ እሰማለሁ።

ከዚያ ወዲያው ይኼንን ብሎ እንዳበቃ፣ ‹‹እንዲያውም አንዴ የሆነ ጋዜጣ ላይ ስለጥበብ ያለንን ውስን ዕውቀትና የማቃለል ስሜት የሆነ ጽሑፍ አንብቤ ነበር፤›› አለና አረፈዋ። አስቡት እንግዲህ። ዕውቀቱ ይሁን። ግን ለጥበብ ክብር የሌለበት አገር ነው ብሎ በጅምላ የሚወቃን ደፋራችን እዚያው ላይ የጋዜጣውን ስም፣ ያነበበውን ጽሑፍ፣ ታትሞ የወጣበትን ቀን፣ እንዲያው እሱ እንኳ ቀርቶ የጸሐፊውን ስም ሳይጠቅስ ‹የሆነ የሆነ ብሎ ሲያቃልለው ስትሰሙ ትዝብት አይጨርም? እንግዲህ ተቺውና ተተቺው እንዲህ በተምታቱበት አገር፣ መምታቱ ሳያንስ አየሩን የተቆጣጠሩት አዋቂዎቻችን ከሦስት ዓረፍተ ነገር ሁለቱን ‹አክችዋሊ፣ ኤቬንቹዋሊ፣ ክሪቲካሊ› እያሉ በመግባባት ናፍቆት እያንከራተቱን ስትሰሙና ስታዩ፣ ቅድም እንዳልኳችሁ ምን ላይ ነበርን? የት ነን? ወዴት ነው የምንጓዘው? ብሎ ጥያቄ ምን እርባና ምንስ ትርጉም ኖሮት ይጠየቃል? አገኛችሁኝ?

ዛሬ እንዲህ መዓት በማውረድ የተወጠርከው ሚስትህ የጋበዘችህን ዘፈን ስላቋረጡት ነው ስትሉኝ ሰማሁ መሰል? ሽሙጡስ ሽሙጥ ነው። መቼስ ‹አጥብቆ ጠያቂ የእናቱን ሞት ይረዳል› በሚል አጥብቆ መጠየቅን በመርዶ ጠሪና መከራ ናፋቂ አስተሳሰብ ተርጉሞ በሚረዳ ወገን መሀል ነኝና ለግዜው ይኼን ልተወው። ምክንያቱም ደንበኞቼ ወዲያው ደወሉና እኔም ከተመጥኩበት ተነስቼ ሄድኩ። ደንበኞቼ ሻጮች ናቸው። የሚሸጡት የወንድማቸውን አውቶብስ ነው። የአውቶብሱን ጥሬነት ሳይና ከገበያው አነስ ባለ ዋጋ ሊሸጡት እንዳሰቡ ስረዳ በወሬ በወሬ አወጣጣቸው ጀመር። ‹‹ምን እባክህ ምን እንዳስነኩት አናውቅም፤›› አለኝ አንደኛው። ያኔ ነው የወንድማቸው ንብረት መሆኑን የተረዳሁት። ኋላ አፍታተው ሲነግሩኝ ይኼ ምናምን አቅምሰውት አብደበን ያሉት ወንድማቸው አስተዳደጉንና ጭምትነቱን በሚቃረን ሁኔታ የማይጠየቁ ጥያቄዎችን እየጠየቀ፣ ማኅበረሰቡ ደፍሮ የማይናገራቸውንና ሲነገሩም የሚፀየፋቸውን፣ ፆታዊና ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦችን እየጠየቀና በድፍረት አቋሙን እየሰበከ ማኅበራዊ ሕይወቱ ተጎሳቁሎ ኖሯል። ሰው ደግሞ ማኅበራዊ ኑሮው ከተጎሳቆለ፣ ወዳጅ ቤተሰብ እየፈራው እየተጠራጠረው ከመጣ ባያብድም ያው አበደ ነው በእኛ ፍረጃ።

ብቻ ነገሩ ጥርት ሳይልልኝ እንዲሁ ስለማላውቀው ሰው ስብሰለሰል ሰነበትኩ። ውሎ አድሮ ያ አውቶብስ ጆሮውን ተባለ። እኔም ኮሚሽኔ እጄ ገባ። ግን ነገሩ እየከነከኝ ውሎ ሲያድር ለባሻዬ ልጅ አጫወትኩት። እሱም፣ ‹‹እንደ ዋዛ ጉዱ ካሳን ሆኖባቸው ይሆናላ፤›› ብሎኝ አለፈው። ‹አገሬን የገሬ ሰው ካስለቀቀኝ እኮ ቆየ› ብሎ ለሰብለ የነገራት ትዝ አለኝ። ነው ወይስ እናንተም ምን የረባ ያወራል ብላችሁ አትጠይቁኝም? እኔም ካልተጠየቅኩ አልናገርም ብዬ ተዘግቼ ቀረሁ እንዳለው ሆኖ የዚያም ሰው ነገር የሚናገረውን የሚያዳምጠው፣ የሚጠይቀውን በአግበቡ የሚመለስለት አጥቶ ይሆን ብዬ አሰብኩ? የምሬን እኮ ነው። ከገበያው እኩል ሰው የአዕምሮ በሽተኛ የበዛው እንዲሁ ስታስቡት የሚናገረውን የሚሰማው የሚጠይቀውን የሚመልስለት ብስል እየጣ አይመስላችሁም ግን?

ብቻ እኛ አውቶብስ ተቃጥሎ ወይ ተገልብጦ ወይ በሌላ ነገር የእንጀራ ገመድ ሲዘጋ ካልሆነ በቀር፣ እንዲህ ባለው ነገር አንድ ሰው ኑሮው ሲቃወስ አገር የሚቃወስ አይመስለንም። ማስመሰል ተክነን የማይመስለን ነገር ብዛቱን ስታስቡት ደግሞ ሌላው ጉድ ነው። ጉድ እኮ ነው።  ታዲያ እኔና ባሻዬ መቼ ዕለት እንዲሁ የባጥ የቆጡን እያነሳን እየተጫወትን ሳለ በቴሌቭዢን ምን እናያለን? የአንድ የአገራችን ዩኒቨርሲቲ የቋንቋዎች ጥናት ምሁር ስለፍቅር እስከ መቃብር ሲተነትኑ። ባሻዬ በዘመኔ ከቅዱሳን መጻሕፍት ሌላ አንድ ብቻውን ተመስጨ ያነበብኩት የፈጠራ ድርሰት እያሉ መጽሐፉንና ደራሲውን ያሞካሻሉ። ከምሁሩ አንድ ተምህርት እንቀስማለን ብለን አሰፍስፋናል። ይናገራሉ ንግግራቸው ግራ ነው። በአማርኛ ጀምረው በእንግሊዝኛ ይጨርሱታል።

‹‹የጉዱ ካሳ ማድነስ?›› ሲሉ ምሁሩ፣ ባሻዬ ‹‹ማድቤት ማለቱ ነው?›› ይሉኛል ወደኔ ዞረው። ‹‹እኔ ምን አውቄ?›› እመልሳለሁ። ‹‹ኢንተለክቹዋሊ ስታስበው በፍቅር እስከ መቃብር ድርሰት ውስጥ ያሉት ካራክተሮችና ስቶሪው ጭምር ከዘመኑ አድቫንስ ነው፤›› ሲሉ ምሁሩ ባሻዬ፣ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር ብሎ የጻፈ ፈረንጅ ይኖር ይሆን?›› ይሉኛል። ያው ትከሻዬን ሰብቄ ዝም እላለሁ። ምሁሩ ሲያደናብሩን ባሻዬ ወደ እኔ እየዞሩ በጥያቄ ሲያፋጥጡኝ እንዲሁ የጓንጉቸር ትርዒት እያየን ምሁሩ ስለትንተናቸው ተመስግነው ዝግጅቱ አለቀ። ኋላ ባሻዬ ቆዝመው ቆይተው፣ ‹‹እኔ ምልህ?›› አሉኝ። ‹‹እርስዎ የሚሉኝ?›› ስላቸው፣ ‹‹እንዲያው እንዲህ ከስልሳዎቹ አንስቶ ወደ ውስጣችን እያየን ውስጣችን ያዳፈነብንን ብርሃን ከመለኮስ፣ እንዲህ በረንጅ አፍ መፍቻና በፈረንጅ ቅብ ሀተታ ነገር ዓለሙን የምናጨመላልቀው ምን ነክቶን ነው?›› ሲሉኝ ዝም አልኩ። በልቤ ግን እንዲህ ብያለሁ፣ ‹ጉዱ ካሳ ጉዱ ካሳ ሲያጫውተን ይሆናላ!› ድንቄም ጉድና ካሳ አትሉም!

በሉ እንሰነባበት! የሚያተርፈው አትርፎ የሚከስረው ከስሮ በብቅል ጭማቂ የትካዜ አምሮቱን የጨዋታ ጉጉቱን ሊወጣ የሰርክ መቃጠሪያችንን ግሮሰሪ ደርሰናል። አስቴር አወቀ ‹ወይ ኑሮ ወይ ኑሮ› ትላለች። አድማጭ ‹እንዲያ በይ› እያለ ይወዛወዘል። ‹ሀብታም ደሃ ሳይል ሁሉን አስተካዡ. . .› ስትል ጋባዥና ተጋባዥ ብርጭቆውን እኩል እያነሳ ይቻረሳል። የባሻዬ ልጅና እኔ ጥጋችንን ይዘን በትዝብት ስንቁለጨለጭ አንድ የማናውቀው ሰው ጠጋ ብሎ፣ ‹‹መታዘብ ክልክል ነው?›› ብሎ ጆሯችን ላይ ጮኸ። የባሻዬ ልጅ ጠጋ ብሎ በጆሮዬ፣ ‹‹በዓለም ላይ ሐበሻ ብቻ እንደሆነ ታውቃለህ ከሰኞ እስከ ሰኞ የሚጠጣው?›› ይለኛል። ‹‹ኑሮ!›› አልኩት አስቴር አወቀን ኮርጄ።

ይኼን ስለው፣ ‹‹ህሊናና ሆድ አላረጅ እያሉ ዕድሜ ፍሬን እንደበጠሰ መኪና ቁልቁል ወደ ማብቂያው ሲገሰግስ ስታይ፣ አንዳንዴ አንተም ብትሆን እኮ መተንፈሻ ያምረሃል፤›› አለኝ፡፡ ደግሞ ሌላው ብድግ ብሎ፣ ‹‹አንዱ እኮ ነው። ስም አልጠራም። ደግሞ እኮ አብሮ አደጌ ነው። ምጥ እንደያዛት ሴት በጭንቅ በጥብ እግሬ ላይ ወድቆ ቤትህን አስይዘህ ገንዘብ ካልተበደርክልኝ አለኝ። በወር በሁለት ወር ካልመለስኩልህ ከምላሴ ፀጉር አለ። በአብሮ አደግ ይጨከናል?›› ሲል አድማጩ በተማሪ ቤት ድምፅ ‹አይጨከንም!› ይላል። ‹‹እኔም አልጨከንኩም። በወሩ ምን ሰማህ አትሉኝም?›› ሲል አሁንም ጀማው ‹ምን?› ይለዋል። ‹‹አሜሪካ ገብቷል ለካ? እኔና ቤቴ ሀራጅ ወጥተናል ለካ?›› ሲል የሆታ ሳቅና ፉጨት ተከተለው። ሁሉም ብርጭቆውን አንስቶ ‹ቺርስ› ሲለው እኔና የባሻዬ ልጅ ተያይተን በሐዘኔታ አንገታችንን ነቀነቅን። ክሕደት፣ እምነት፣ ፍቅር፣ ደባ፣ ማጣትና ማግኘት በየቤቱ የሚሰማውን ጉድ ለማሰብ ስሞክር ራሴ ሊፈነዳ ደረሰ፡፡ ስንቱ ተፈትሎ ስንቱ ተሸመነ? መልካም ሰንበት!  

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት