Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አያያዝ ያላማረባቸው ምርቶች

ከሰሞኑ ወደ አንድ ወዳጄ ቤት በእንግድነት ባቀናሁበት ወቅት አንድ ነገር ታዘብኩኝ፡፡ የሦስት ወር ልጇን የታቀፈችው ባለቤቱ አራስ ልጇን አጥብታ ጋደም ካደረገቻት በኋላ እኔን ለማስተናገድ ተፍ ተፍ ማለት ጀመረች፡፡ ወደ ኩሽና እያመራች ሳለች ግርታ የፈጠረብኝን ትዕዛዝ ለሠራተኛዋ ስትሰጥ ሰማሁ፡፡ ‹‹እከሊት … እባክሽ ማሙሽን ደጅ አውጪው ቶሎ በይ…›› አለች፡፡

ማሙሽ ሊባል የሚችል ሕፃን በሌለበት ቤት ውስጥ የምን ማሙሽ ነው? የሚል ጥያቄ ለማቅረብ ጉሮሮዬን ስጠራርግ፣ የቤት ሠራተኛዋ የምግብ ዘይት የያዘ ቢጫ ፕላስቲክ አንጠልጥላ ወጣች፡፡ ማሙሽ የተባለው የምግብ ዘይቱ መሆኑን ያወቅሁት የወዳጄ ባለቤት ስታብራራልኝ ነበር፡፡ ገለጻዋ በአጭሩ ሲብራራ የምግብ ዘይቱ እንደ አራስ ልጅ ጠዋት ጠዋት ፀሐይ ላይ ካልወጣና ካልቀለጠ በቀላሉ ጥቅም ላይ አይውልም፡፡ ይደርቃል፡፡ የጠዋት ፀሐይ ስለሚሞቅም ‹‹ማሙሽ›› ተባለ ብላ ፈገግ አሰኘችኝ፡፡

የመርጋት ባህሪይ ስላለው ሙቀት ካልነካው በቀር  ስለማይቀልጠው የምግብ ዘይት የቅጽል ስም ሳልሰማ መቆየቴን እንዳላዋቂ ቆጠረችው፡፡ እንደ አንድ ወዳጄ አባባል ነገሩ መራራ ቀልድ ነው፡፡ የስያሜ አሰጣጡና የተነፃፀረበት መንገድ ግን ሳያስገርመኝ አልቀረም፡፡ ከዚህ ገጠመኝ ባሻገር ‹‹ማሙሽ›› በየቀኑ ፀሐይ ላይ የመውጣቱ ጉዳይ ትክክል ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ ግን ሳይሞግተኝ አልቀረም፡፡ እንዲህ ያሉ ምግብ ነክ ምርቶች በፀሐይ መቀቀላቸው የሚያስከትለው የጎን ጉዳት ይኖር ይሆን? ፈታኝ ጥያቄ ነው፡፡ የምግብ ምርቶች እንዲህ ባለው መንገድ ለአገልግሎት ማመቻቸት ስለማመከር ነገሩ ከነከነኝ፡፡ እስካሁንም ይህ ነው የሚባል ምላሽ አላገኘሁለትም፡፡  

ከምግብ ነክ ምርቶች ጋር በተያያዘ እንደ ዘይቱ ሁሉ ፀሐይ ጠገብ ምርቶች እየተበራከቱ የመምጣታቸው ነገር አሳሳቢ መሆኑን ለማስታወስ ነው፡፡ በየአካባቢው መጠናቸው ይለያይ እንጂ የተለያዩ ሸቀጣሸቀጦችን የሚቸረችሩ መደብሮች በርካታ ናቸው፡፡ የትኛውም የኅብረተሰብ ክፍል ሳይጎበኛቸው ከማይውሉት መደብሮች አብዛኛዎቹ ፈሳሽም ሆነ ጠጣር ምርቶችን የሚይዙበት መንገድ ምቾት እንደማይሰጥ  እንታዘባለን፡፡

በእነዚህ መደብሮች ከዳቦ ጀምሮ በየዕለቱ ለምግብነት የምናውላቸው ሸቀጦች መገኛ ናቸው፡፡ ያለመታደል ሆኖ ዳቦና ላምባ በአንድ ፈርጅ የሚሸጥባቸው መደብሮች ማግኘት ከባድ አይሆንም፡፡ የአይጥ መርዝና ብስኩት ጎን ለጎን የተደረደረበት መደብር ብንፈልግም አናጣም፡፡

አንዳንዶቹ መደብሮች በጆኒያና በማዳበሪያ ሞልተው የሚያስቀምጧቸው እንደ ምስር፣ ሽንብራ፣ ክክ፣ ሩዝ፣ መኮሮኒ፣ ዱቄት ያሉትን ሸቀጦች በማጨቅ የእህል መሸጫ መጋዘን ከመምሰላቸው ባሻገር ምርቶቹን የሚያስቀምጡበት መንገድና አያያዝም ጥሩ ስሜት አይፈጥርም፡፡

 በጆንያና በማዳበሪያ ተሞልተው የተቀመጡና የሚቸረቸሩ ምግብ ነክ ምርቶች አያያዝ አንዳንዴ አስደንጋጭ ይሆናል፡፡ በንጽህና የሚይዙ እንዳሉ ሁሉ በአግባቡ ለመያዝ ደንታ የሌላቸው ባለመደብሮች የሸማቹን ጤንነት ሊጎዱም ይችላሉ፡፡ በጆንያ ሞልተው ያቆሙትን ምግብ ነክ ምርት ከአይጥ ለመከላከል ‹‹የአይጥ መርዝ›› የያዘውን ወጥመድ በጆንያዎቹ መካከል ሲሾጉጡ ምንም ግድ የማይሰጣቸው ቸርቻሪዎች የሚሸጡልን ምርት በእርግጠኝነት በአይጥ መርዝ ያልተበከለ ስለመሆኑ ምን ማረጋገጫ ይኖረናል?

እንደ ቡና ያሉ ምርቶችን በጆንያ ተሞልተው እየተቸረቸሩ መሸጣቸው አዲስ ባይሆንም፣ በዚህ መንገድ መሸጡ ችግር እንዳለው የሚያውቀው ሸማቹ ስንት ነው? ቡና በባህሪው እንደ ጋዝ ያሉ ነገሮች በቅራቢያው ካሉ በመሳብ ጣዕሙን ይቀይራል፡፡  እንዲህ በብትን የሚሸጡ ምርቶች የመገልገያ ጊዜያቸው ማለፍ አለማለፉን ለመለየትም እንቸገራለን፡፡ በማዳበሪያ ውስጥ እንዳለ ሳይሸጥ የቆየ ሩዝ መልኩን እየቀየረ እንኳ ያለከልካይ ይሸጣል፡፡

በሠለጠነው ዘመን በጆንያ የተቀመጠ በርበሬና ሽሮ ተሰፍሮ የመሸጡ ነገርስ አያስተዛዝብም፡፡ በርበሬ አለን ለማለት በጆንያ ተሞልቶ ለአዋራ መጋለጡ እየታየና በቀላሉ ለብክለት መጋለጡ በግልጽ እየታወቀ ይሸጣል፡፡ ሸማቹም ይገዛል፡፡

ከሸማቾች ደህንነት ጋር የሚያያዘውና በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እየተስፋፋና እየተለመደ የመጣው የታሸጉ ውኃዎችና የለስላሳ መጠጦች አያያዝም ሌላው መነጋገሪያ ነው፡፡

የታሸጉ ውኃዎች፣ የለስላሳ መጠጦችና መሰል ምርቶች ከመደብር ውጭ ተደርድረው ፀሐይና ቁር ሲፈራረቅባቸው ይውላሉ፡፡ የታሸጉ መጠጦችን በየመደብሮቹ ደጃፍ ደርድሮ ማስቀመጥ እንደ ፋሽን ተይዟል፡፡ ‹‹ማሙሽ›› ከተባለው ዘይት የበለጠ ከጠዋት እስከ ማታ በፀሐይ ሲንቃቁ የሚውሉ በርካታ ምርቶችን እያየን ነው፡፡

የጤና ባለሙያዎች እንዲህ ያለው ነገር መሆን የማይገባው ተግባር መሆኑን ያረጋግጣሉ፡፡ በተደጋጋሚ በፀሐይ የሚንቃቁ ምርቶች ተፈጥሯዊና ኬሚካላዊ ይዞታቸው ቀይሮ ስንጠቀምባቸው ጤና ሊነሱን የሚችሉበት አጋጣሚ ሰፊ ስለመሆኑም ይናገራሉ፡፡

በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋ የመጣው የምግብ ነክ ምርቶች አያያዝ ሥርዓት ጉድለት ሊገታ ይገባዋል፡፡ ለጤና አደገኛነቱ ግልጽ እስከሆነ ድረስ እንዲህ ዓይነቱን አያያዝ ማስቆም ግድ ይላል፡፡ በየመደብሩ ንጽህናቸው በተጓደለ መያዣዎች የተቀመጡ ምርቶችም ቢሆኑ በሥርዓቱ መቀመጥ እንደሚኖርባቸው ነጋሪ ባያስፈልግም የባለመደብሮች ኃላፊነት፣ የሸማቹም ጠንቃቃነትና እምቢ ባይነት መዳበር አለበት፡፡

የታሸጉ ለስላሳ መጠጦችና የውኃ ምርቶችን ለፀሐይ አጋልጦ ያስቀመጠ በንጽህና ቦታ መቀመጥ ሲገባቸው ከመደብሮቹ ውጭ ካኖረ መደብር አለመሸመት ሊከተል የሚችለውን አደጋ በቀላሉ መከላከል ያስችላል፡፡ አምራቾቹም ቢሆኑ እንዲህ ባለው መልኩ ምርቶቻቸው ሲጉላሉ እያዩ ዝምታና ቸልታን ማብዛታቸው ኋላ ጉዳቱ ለእነሱም ስለሚሆን ቢያስብቡበት መልካም ነው፡፡ ‹‹አያያዝህን ካላስተካከልክ ምርታችንን አንሸጥም›› የማለት ድፍረት ቢኖራቸው ሥጋቱን መቀነስ ይቻላል፡፡

የሸማቾችን ደህንነት ለመጠበቅ በሕግ የተቋቋመ ተቋም ስላለ ሥራውን በመገንዘብ ግዴታውን መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

   

  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት