Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትብሔርተኝነት አዳላጭ መንገድና አደገኛ ድጥ ነው

ብሔርተኝነት አዳላጭ መንገድና አደገኛ ድጥ ነው

ቀን:

በገነት ዓለሙ

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በሕግ መንግሥት ጉባዔ የፀደቀበት ኅዳር 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ዘንድሮም የተከበረው ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀበትም (ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም.)፣ ‹‹ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ ውሏል›› ከተባለበትም ከነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም ‹‹ተገንጥሎ›› አሥራ አንደኛው የብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል ተብሎ ነው፡፡ ቁጥሩም ሆነ ስያሜው ያስገርማል፡፡ ልክ የዛሬ 22 ዓመት የተመዘገበን ድል ይኼን ያህል ዓመት ሆነው ብሎ ሥሌት ሳይሆን ተራ ቁጥር ለመናገር፣ ዘግይቶ መከበር መጀመሩም ሆነ ከጊዜ በኋላ አዲስ ስያሜ የተሰጠው መሆኑ በጭራሽ ምክንያት አይሆንም፡፡

በኢትዮጵያ የብሔር/ብሔረሰቦች መብት መከበርም አማራጭ የሌለው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የአንድነት መነሻና መሠረትም ነው፡፡ የብሔር/ብሔረሰቦች ጥያቄም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አጠቃላይ የዴሞክራሲ ጥያቄ አካል እንጂ በተገላቢጦሽ የሁሉ ነገር መፍቻ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ የፀደቀበትን ቀን የብሔር/ብሔረሰቦች ቀን ተብሎ የሚከበረው፣ ዛሬም ከሃያ ሁለት ዓመታት በኋላ ከዚያ በፊት አሥራ ሰባት ዓመት ሙሉ በበረሃ ትግል ውስጥ ሲባል እንደነበረው በኢትዮጵያ ዋናው ቅራኔ ወይም ጥያቄ የብሔር ብሔረሰቦች ነው ተብሎ ከሆነ አሁንም ገና አልገባንም፣ ‹‹መከራ›› አልመከረንም ማለት ነው፡፡

- Advertisement -

ከዚህ ቀደም የዛሬዎቹ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶቸ ገና ተራ በተራ እንደተመሠረቱ በተለይም ሕወሓት ዋናው ቅራኔ (ጥያቄ) የብሔር ነው አሉ፡፡ ከዚህ ያልተስተካከለ አተያይ ወጥተው የሁሉም ብሔረሰቦች የትግል አስኳል ዴሞክራሲያዊ ነፃነት፣ ፍትሕና ከድህነት መውጣት መሆኑን ለማየትና በእነዚሁ የጋራ ጥቅሞች ላይ ትኩረቱን ለማደላደል የበቃ ድርጅት ሳይፈጠር ቀረ፡፡ የኢሕአዴግ ዋናው አባልና መሥራች ድርጅት የቀድሞው ወይም የመጀመርያው ክልል ገብ ዕይታውና አደረጃጀቱ፣ በኋላ ከመጣው ባለ ብዙ ብሔረሰቧን ኢትዮጵያን ‹‹ነፃ ከማውጣት›› ፍላጎትና አጋጣሚ ጋር ግጭት በፈጠረ ጊዜም፣ አገራዊ የአተያይና የጥንቅር ለውጥ (ትራንስፎርሜሽን) በማድረግ (ለምሳሌ ከዴሞክራሲያዊ ቡድኖች ጋር ኅብረት በመፍጠር በየአካባቢው ነፃ የሕዝብ እንቅስቃሴዎችን በማነሳሳትና ከእነዚሁ ጋር በመሸራረብ) ችግሩን ለማቃለል አልጣረም፡፡ ይልቁንም ጥበታቸውንና ባይተዋርነታቸውን መጋረድ ብቻ ሞከረ፡፡

ሕወሓት በተለይ የኢትዮጵያን ሌሎች ብሔረሰቦች ያቀረበው ያንኑ የትግራይ ነጠላ መንግሥት ለማቆም ይሆነኛል ብሎ የያዘውን የብሔር ጥያቄ ቁንጮነት ተሸክሞ ነበር፡፡ ዋናው ጩኸቱና መፈክሩም ‹‹የአማራው የበላይነት፣ የብሔረሰቦች እስረኝነትና ሙሉ ለሙሉ መብት እስከ መገንጠል›› ሆነ፡፡ በዚህ ጩኸቱና መፈክሩም በኢትዮጵያ ሕዝብ በዋናው የዴሞክራሲ ጥያቄ ላይ ጥላ አጥልቶ፣ በፀረ ዴሞክራሲያዊ ውዥንብር የሕዝብን ፀረ ደርግ ትግል ሊያስጠቃና በገዛ ራሱ ላይም ‹‹አገር የማፍረስ›› ክስ ሲጎትት ኖረ፡፡ ክሱ እየበረታ ሲወጥረው ‹‹የብሔሮች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት መረጋገጥ አንድነትን እንጂ መነጣጠልን አያመጣም፣ በመፈቃቀድ…›› ወዘተ የሚል ትንተና አምጥቶ፣ አብሮ መኖርንና መለየትን ነባራዊ አስገዳጅነት የሌለበት የቢሻኝ ውሳኔ ብቻ እያስመሰለ የበለጠ ግራ አጋባ፡፡

የብሔሮች መብት የዴሞክራሲ መብቶች አንድ ጣት እንጂ ሁለመናው አይደለም፡፡ ብቻውን ስለሰቀሉትና ‹‹እስከ መገንጠል!›› እያሉ ስለለፈፉትም የአንድነት ዋስትና አይሆንም፡፡ አስተማማኝ አንድነት በዴሞክራሲያዊ ትስስር የሚዘማመድና ዕድገትን በመመገብ የሚጠና ነው፡፡ ለፀረ አንድነት ውንጀላም ማርከሻውስ ነጋ ጠባ መማልና መገዘት ሳይሆን ግንዱን ዘንግቶ ብቃይ ላይ ከማተኮር መላቀቅ፣ ከብሔርና ከጎጥ ጎጆ ወጥቶ የሕዝቦችን መሠረታዊ የጋራ ጥቅሞች ፊት ለፊት ደቅኖ የማሳየትና ሰፊ የትግል ትስስር እንዲፈጠር መሥራት ነው፡፡

የኢሕአዴግ መሥራች አባል ድርጅት የሆነው ሕወሓት ይኼንን ተግባር (በኅብረ ብሔር ፓርቲም ሆነ በግንባር አቅጣጫ) ሊወጣ ይቅርና በአቋም ሙሉ አምሳያው ከሆነው ኢሕዲን ጋር እንኳን ሊዋሀድ አልሞከረም፡፡ ኋላ ላይ እንደታየውና ዛሬም አደባባይ በወጣ ሹክሹክታና ሚሥጥር እንደሚወገዘው ‹‹የሚሰግርባቸው በቅሎ ድርጅቶች›› ከመፍጠር ያለፈ እንቅስቃሴ ማምጣት አልቻለም፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላም የኢትዮጵያ የችግሮች ሁሉ የበላይና የዴሞክራሲ ሁለመና የብሔሮች ጥያቄ ሆኖ አረፈው፡፡ የብሔር ብሔረሰብ ትንንሽ ፓርቲዎች ረቡ የብሔር ብሔረሰብ ውክልና ገና ከመነሻው በሕዝብ ድጋፍ የማይመዘን የራስ በራስ ሹመት ሆነ፡፡ የአማራ ሕዝብ ጥቅም ውክልና የኢሕዲን/ብአዴን፣ የትግራይ ሕዝብ የሕወሓት፣ የኦሮሞ የኦሕዲድ፣ የደቡብ ሕዝቦች የደሕዴግ፣ ወዘተ እያለ ቀጠለ ኢሕአዴጋዊ ያልሆነ ሌላ አለሁ ባይ ሕዝብን የማይወክል የጥቂቶች ጥርቅም ተባለ፡፡

ከፖለቲካ እስከ ትዳር ትክክል የሚባለው አተያይና አቦዳደን ብሔረሰባዊ ሆነ፡፡ ከተወራረሰ ገጽታ ይልቅ ልዩ ወይም የብቻ የሆኑ መለያዎችን መፈለግና ማጉላት ሚዛን ደፋ፡፡ የብሔር/ብሔረሰብ ማንነት በሆነ ማኅበረሰብ ባህልና ቋንቋ በመቀረፅ የሚገለጽ ከመሆን አልፎ የትውልድ ጀርባን መርመሮ የጠራና ያልጠራ እስከ መለየት ደረስ ፈር ለቀቀ፡፡ በተለያየ ደረጃ የሚታይ የማኅበራዊ ቅልቅሎች ገጽታን እንደ በጎና ተፈጥሮአዊ እውነት የመቀበልና የማክበር ችግር በረከተ፡፡ በተዋሳኝ ብሔረሰቦች ዘንድ ያለ ጉራማይሌ ማኅበራዊ ጥንቅር በተለይ በከተሞች ዘንድ ያለ ከአማርኛ ተናጋሪነት ጋር የተሳሰረ ውጥንቅጥ ስብስብ፣ በብሔርተኞች ዘንድ እንዳልተፈለገ ዕድገትና ችግር ተቆጠረ፡፡ ብሔረሰባዊ መካለስ ወይም መሰባጠር የሚታይባቸውና በአዲሱ አከላለል የተቆረጡ ማኅበረሰቦች፣ በብሔርተኞች ጥንቅር የማጥራት ወይም እውነተኛ ብሔራዊ ባህልና ቋንቋን የማስፋፋት እንቅስቃሴ መረበሽ ግድ ሆነባቸው፡፡ ጉራማይሌ ባህልና አነጋገር፣ ከሌላ ብሔር ጋር መጋባትና መዋለድ ‹‹የሚያስንቅ›› ሲሆን ታየ፡፡ እንዲህ ያለውን ‹‹የማይፈለግ ገጽታ›› የሚያደክም የባህል ‹ዘመቻ›› ተከፈተ፡፡ ብሔርተኛ ንቃቱ ተዛመተ፡፡ በመኖሪያም በሥራ ቦታም ብሔራዊ ማንነትን መለየትና መምረጥ ግድ ሆነ፡፡ የራስንና የልጆችን መጠሪያ መቀየርና የሌላ ብሔር የትዳርን ጓደኛን መፍታት ድረስ ሄዷል የተባለ ቀውስ ተከሰተ፡፡ ‹ብሔር የለኝም ኢትዮጵያዊ ነኝ› ያለ (ከተለያየ ብሔር በመወለዱ ምክንያት የተቸገረው፣ የብሔር ፖለቲካን መቃወም የፈለገውና የብዙ ብሔሮችን እውነትነት በ‹‹አንድ ሕዝብ›› ምኞት የተካው ሁሉ ተደምሮ) ‹‹የብሔሮችን መብት የሚፃረር ትምክህተኛ›› ተደርጎ ተመደበ፡፡ በአንዱ ወይም በሌላው ብሔር ውስጥ ራስን አለመመደብም ሆነ ብሔርተኛ አለመሆን መብት መሆኑም ተዘነጋ፡፡

በብሔር ቡድን ውስጥ መግባት ያልፈቀደና የብሔር ጉዳይን እንደ ሃይማኖት ያላጠበቀ፣ በብሔር ማንነቱ የሚያፍር ተደርጎ ተወሰደ፡፡ ብሔሩን ሲጠየቅ ይቆጣ የነበረውን ለማለዘብ አማራውንና ከአማራና ከሌላ ብሔር የተወለደውን ‹‹ውህድ›› በአማራ ብሔርተኝነት ሠልፍ ውስጥ ለማስገባት ያለመ (አንዳርጋቸው ጽጌ 1985 ዓ.ም.) መጽሐፍም ተጻፈ፡፡ ከውስን ታሪካዊ መረጃ ጋር አፈታሪኩን እያዛመደና እያሳደደ አኩሪ የብሔር ታሪክ የማሰናዳት ጥድፊያም ተያዘ፡፡ የከዚህ ቀደሙ ያለ የሌለ ግፍ ተቆጠረ፡፡ ተራ ፌዝና ብሽሽቁም እየተለቃቀመ የበደል ማስረጃና የሕዝብ ስሜት ማደፍረሻ ሆነ፡፡

የብሔርተኛነት እንቅስቃሴ አመጣጥ ከከበርቴው መደብ ጋር የተያያዘ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ዕድገት በመጓደሉ ብሔርተኛ ንቅናቄው የታየው ዘግይቶ ከፀረ ቅኝ አገዛዝ ንቅናቄዎችና ከሶሻሊስት እንቅስቃሴ መስፋፋት ጋር ተያይዞ መሆኑን መገንዘብ ችግር ሆነና አፄ ቴድሮስም የአማራ ብሔራዊ መንግሥትና ክልል ባለመፍጠር (ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ ገጽ 35-7) ተተቹ፡፡

ሁሉንም ብሔርተኛ ማድረግ አጠቃላይ ሥልት ሆነ፡፡ የብሔር ጭቆና የሌለበት አማራውም ሳይቀር በግድ ብሔርተኛ ካልሆንክ፣ ‹‹ብሔር ብሔር›› ካላልክ ኢትዮጵያዊነትህን እስካጠበቅህ ድረስ ለሌላው አደጋ ነህ ተብሎ ተወጠረ፡፡ ብሔርተኛ አለመሆን ከ‹‹ምርጥ ኢትዮጵያዊነት›› ጋር ተምታታ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች የሚያያይዛቸው መፈቃቀድ መሆኑ ሲሰበክ፣ የዚህ የመፈቃቀድ አንድ ትልቅ ጉዳይ ከእርስ በእርስ ትርምስ አምልጦ የማደግ ጥቅም መሆኑ ነጥሮ ሳይወጣ ቀረ፡፡ መፈቃቀዱ የዘፈቀደ ምርጫ እስኪመስል ድረስ አንዱ ለማኝ፣ ሌላው ተለማኝና እወጣለሁ እያለ አስፈራሪ ወይም ለሌላው ሲል የሚቆይ እስኪመስል ድረስ የመፈቃቀድ አመለካከት ተምታታ፡፡ በመነጠልም ሆነ በአንድነት ጥቅምና ጉዳት ላይ ሕዝብ ያለው በግልጽ የመወያየት መብት ነውር ይመስል ታፍኖ ታለፈ፡፡

ከሕገ መንግሥቱ በፊት (በጥር 1984 ዓ.ም.) የክልሎችን ዳር ድንበር የሚወስን መስተዳድሮችን የሚያቋቁም አዋጅ ወጣ፡፡ አከላለሉ ላይ መለስተኛ ለውጥ ያደረገው ሕገ መንግሥት ፀደቀና የኢሕአዴግ አባልና አጋር ድርጅቶችም ‹‹በዴሞክራሲያዊ አግባብ›› ተመርተው ‹‹በየርስታቸው› መንግሥታት ሆኑ፡፡ በቋንቋ መተዳደር፣ መዳኘት፣ መማርና መጻፍ ይብዛም ይነስ ተቻለ፡፡ ኢሕአዴግ አለኝ የሚለው አኩሪ ለውጥ ይኼው ብቻ ሆነ፡፡

ከዚህ በተረፈ ‹‹ቅድሚያ ለአካባቢው ብሔር ተወላጅ›› ‹‹የብሔራዊ ተዋጽኦን ማመጣጠን›› ይፋ ፖሊሲ ሲሆን ጎሰኝነትም ቀናው፡፡ ተዛነፉ የአካባቢው ብሔር አባላት ልዩ መብት ባለማግኘታቸው የመጣ ይመስላል፡፡ ተዛነፉም በ‹‹በጎ አድልኦ›› ይወገድ ይመስል ‹‹መጤ›› ወይም አናሳ የማኅበረሰብ አባላት በውስጥና በውጭ የትምህርትና የሥልጠና ውድድር፣ በሥራ ቅጥር፣ በዕድገትና በሹመት ላይ የሚንገዋለሉበት አሠራር መጣ፡፡ ውጤትና ብቃት ዋና መመዘኛ ከመሆን ወጣ፡፡ ‹‹በጎ አድልኦው›› ተዛነፍን በማስተካከል ዓላማ ይጀመር እንጂ፣ ያለፈ በዳይነትንና አድሏዊነትን በዛሬ ተራ የማወራረድ ውስጣዊ ግፊት ነበረው፡፡ ግፊቱ እየተሠራጨ በኢንቨስትመንት ፈቃድ፣ በመሬት አሰጣጥ፣ በግብር አተማመን ውስጥ ሳይቀር ገባ፡፡ በሕግ የተፈቀደ ‹‹ማበረታቻ›› ይመስል አሠራሩ ተስፋፋ፡፡ ሌላው ቀርቶ በዕለታዊ ግጭቶች የወንጀልና የፍትሕ ብሔር ክሶች ቅኝትና አፈታት ከብሔር ተወላጅነት ጋር ይናብብ ገባ፡፡ በአንድ ብሔረሰብ ውስጥ ሳይቀር በጎሳ ደረጃ መፈላለግና መወጋገን አዋቂነት እየሆነ መጣ፡፡

ከአንድ ብሔረሰብ በላይ ባቀፉ የአስተዳደር አካባቢዎች በብሔራዊ መብት/ድርሻ ሽፋን የሥልጣን፣ የበጀት፣ የዕርዳታ እህል፣ የግዛት ድርሻ ሥሌቱና የጥቅም ማስፊያ ዱለታውና ፍትጊያው ከክልል እስከ ወረዳ ተስፋፋ፡፡ በሒደቱ ጥቂት ብልጣ ብልጦች ሲከብሩና የመክበሪያ መንገዳቸውን ሲያመቻቹ ለብዙኃኑ ግን ትርፉ በመጠቀሚያነት መታመስ፣ መሸካከርና በፀብ መደራረስ ሆነ፡፡

ከከብት አርቢው ተነቃናቂነት ጋር ያልተጣጣመው የውኃና የግጦሽ የክልል ይዞታነት የብሔርተኞች ቅስቀሳ ተጨምሮበት ተጎራባች ማኅበረሰቦችን ማጋጨቱ ጨመረ፡፡ እያንዳንዷን ነገር በጎሰኛ ዓይን ማየትና መመዘን ተስፋፋ፡፡ ከእኔ ብሔር፣ ከእኔ ጎሳ ምን ያህል ተሾመ? የተመደበው ወይም የተሾመው ወይም የተመረጠው ወይም የወረደው ብሔሩ ከየት ነው? በሬዲዮና በቴሌቬዥን መግለጫ የሚሰጠው ከየት ብሔር ይመስላል? በፀቡ የተመታው ማነው?  መቺውስ?  ወዘተ እያሉ የግል ግጭቶችን ጭምር በብሔረሰባዊ ጥቃት እስከ መጠርጠር ድረስ አዕምሮ ተጠመደ፡፡ የሌላ ብሔር አባል ወይም ለአካባቢው አዲስ የሆነ ሰው ግንባታ ሲያካሂድ ሲያዩ፣ ሌላው ቀርቶ ካርታ አንሺ የአፈርና የዕፅዋት ተመራማሪ ሲያዩ መሬቴ፣ ማዕድኔ እያሉ በስስት ማለቅ ተበራከተ፡፡ ይኼንን በመሰሉ ለዕድገትም፣ ለሰላምም፣ ለዴሞክራሲም እንቅፋት በሆኑ ችግሮች ተተብትበናል፡፡ የዚህ ሁሉ አድራጊ ፈጣሪ በሁለት ሠፈሮች ከትሞ ተምሬያለሁ፣ ፖለቲከኛ ወይም ታጋይ ነኝ ባዩ ክፍል ነው፡፡

በአንድ በኩል የጎሰኛ አበጣባጭነትና የአስተዳደር ጥፋቶች በሚያስከትሏቸው ብልሽቶች ተጎትተው የገቡ ብዙ የዴሞክራሲ ናፋቂዎች የዘቀጡበት፣ ድፍን ‹‹ኢትዮጵያዊነትን›› ብቻ መስማት የሚፈለግበት ሠፈር አለ፡፡ በዚህ ሠፈር ውስጥ ኢትዮጵያን በአምላክ የተመረጠች አገር አድርጎ የሚያስበው ‹‹ብሔሮች››፣ ‹‹ሕዝቦች›› የሚሉ ቃላት መስማት እንኳን የሚያቅረው፣ በቋንቋ መማርና መተዳደር ከመበታተን አደጋ ጋር የሚምታታበት ሁሉ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል የብሔርተኝነት ሠፈር አለ፡፡ በዚህ ውስጥ ከኢሕአዴግ የብሔር ድርጅቶች አንስቶ አንዱን ወይም ሌላውን አካባቢ ለመቁረስ እስከሚታገሉት ድረስ ተሠልፈዋል፡፡ ባልንጀራነትን የግድ በብሔር ማንነት ሳይሆን በግለሰባዊ ማንነት ለመመዘን የሚጥረውና በጎሰኝነት ጉድጓድ ውስጥ ላለመውደቅ የሚፍጨረጨረው ‹‹በብሔሩ የሚያፍር፣ ብሔሩን የሚክድ›› እየተባለ ይጎነተላል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ፣ ሕዝቦች (አገሮች) ቅኝ የተገዙባት ኢምፓየር ነች›› እየተባለ የሻዕቢያ ዓይነት ሐሰትና ቅጥፈት ይበዛታል፡፡

ሁለቱም ሠፈሮች የኢሕአዴግንና የአጋሮቹን የአገዛዝ ችግሮች (የመልካም አስተዳደር ችግሮች ይባላል በህዳሴው ቋንቋ) እየተመገቡ እርስ በእርስም እየተመጋገቡ ሲስፋፉ ኖረዋል፡፡ ሁለቱም ለየብቻቸው የምለው ምን ይፈይዳል?  ምን ይጎዳል?  የሚል የኃላፊነት ጥያቄ ሳያሸማቅቃቸው በነፃ ይራመዳሉ፣ ይንቀሳቀሳሉ፡፡  

መገንጠልን የትግል ግብ አድርጎና በልዩ ልዩ የፈጠራ ታሪክ ደጋግፎ ለማሳካት መታገል ምን ያህል ትርጉም የለሽ ሊሆን እንደሚችል የኤርትራ ትግል አስተምሮናል፡፡ በኤርትራ ያሉ ሕዝቦች ያ ሁሉ የሰላሳ ዓመት ደም ፈስሶ ዴሞክራሲና ፍትሕ ሊያገኙ ይቅርና ከጦርነት እንኳን የመገላገል ዕድልን ሻዕቢያ አልፈቀደላቸውም፡፡ እርግጥ ነው ዛሬ የኤርትራ ሕዝቦች በ‹‹ፀረ ቅኝ የነፃነት ትግል›› የሚምታቱበትና የሚወናበዱባት ሁኔታ የለም፡፡ ለቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብም የኤርትራ ትግል ማስፈራሪያና የገዢዎች መነገጃ ሲሆን የኖረበት ታሪክ አክትሟል፡፡ በዚህ ረገድ ዛሬ ሁለቱም እውነቱን ለመረዳት ችለዋል፡፡ ሻዕቢያ መንገድ የሳተና በደም የነገደ መሆኑ ወለል ብሎ ታይቷል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ኤርትራን ቅኝ ገዛች›› ባይነቱም ሐሰተኛነቱ ተጋልጧል፡፡ ያውም ‹‹ኢትዮጵያ የኤርትራ ቅኝ ሆነች›› የሚል ተቃራኒውን ፈጥሮ፡፡

የኤርትራ የነፃነት ትግል ማስፈራሪያነት ከኪሳራ ጋር ቢያከትምም ሻዕቢያ ኢትዮጵያን (ኤርትራንም) የማጥፋት ተግባሩን አላቆመም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ከመገንጠልና ድንበር ከማስከበር ጣጣ ጋር ከመጓተት አልተላቀቁም፡፡ በኦሮሞ ብሔርተኛነት ውስጥ የሚታይ የ‹‹ሐበሻ ቅኝ ገዢነትና ኢምፓየር››ን እታገላለሁ ባይነት የሻዕቢያን የድሮ ቦታ ተረክቧል፡፡ የኢሳያስ መንግሥትም ኢትዮጵያን የማፍረስ መሣሪያ አድርጎ እየተገለገለበት ነው፡፡

ከኢትዮጵያ የተላቀቀች ነፃ ኦሮሚያን የሚሹ ብሔርተኞች የሚሉትንስ ያውቁ ይሆን? በመጀመርያ አድልኦንና በደልን በጋራ የመታገል ሥልት ገዢዎች ከሕዝብ የሚነጠሉበት መሆኑን፣ በዚህ ፋንታ መገንጠልን የመምረጥ አካሄድ ደግሞ ‹‹እናት አገር ወይም ሞት›› በሚል ዓይነት መፈክር ሥር ብዙ ደጋፊ አሠልፎ አንዱን በሌላው እያጣፉ ለመኖር የሚመች መሆኑን፣ ወደ ሌላ አገር ሳንሄድ የኤርትራ ትግል ልምድ ደንበኛ ትምህርት ሰጥቶናል፡፡

በሌላ በኩል የኦሮሞ ሕዝብ ጉዳይ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ፣ ከደቡብ እስከ ሰሜን የተዘረጋና ከብዙ ብሔረሰቦች ጋር የተሳሰረ የአጠቃላይ ኢትዮጵያ ጉዳይ እንደመሆኑ፣ የመነጠል ጥያቄ ብዙ ብሔሮችን ያደራረሰ መተላለቅ ሊከተልበት የሚችል፣ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያ ልነጥል ከማለት ብዙም አለማነሱን ለመረዳት ጥልቅ ምርምር አይጠይቅም፡፡ ከየትኛውም የአገሪቱ ብሔር ይበልጥ ሰፊ መልክዓ ምድራዊ ሥርጭትና የቁጥር ብዛት ያለው ሕዝብ፣ ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ተባብሮ የብዙኃን ዴሞክራሲን ሊያሰፍን የሚችልበትን የተሻለ የትግል አማራጭ መሸሽስ በምን መከራከሪያ ትክክል ይባላል? የተፈለገው ሥልጣን ከሆነ ከመነጠል መንገድ ይልቅ ለዴሞክራሲ ተጋግዞ መታገሉ የበለጠ ይቀላል፡፡

ሻዕቢያ ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተለየ ሥነ ልቦና ባህል ያለው አንድ የኤርትራ ብሔር፣ አንድ ሕዝብ ተፈጥሯል የሚል ሐሰት ሲያመልክ እንደነበር ሁሉ፣ ሐበሻነት ኦሮሞን የማይጠቅስ አድርገው የሚያስቡና በኦሮሞና ‹‹ሐበሾች›› (ትግሬ፣ አማራ፣ አገው) መካከል የባህል የሥነ ልቦና ተዛማጅነት የሌለበት መስመር ሊያበጁ የሚሞክሩ፣ የኦሮሞን ወይም የሌላውን ብሔር ብሔረሰብ ሕዝብ ታሪክ ከአጠቃላይ ኢትዮጵያ ታሪክ ለመነጠል የሚለፉ፣ የየጁ መሳፍንት ኦሮሞነት ለማጥፋት ላጲስ የቸገራቸውና ሌላው ቀርቶ የጥቁር ሕዝብ መኩሪያ የሆነውን የአድዋ ድል ላለመቀበል የሚንፈራፈሩ የኦሮሞ ብሔርተኞች አሉ፡፡

ኢትዮጵያ በመሠረቱ ኦሮሞአዊ ልትባል የምትችል አገር ሆና ሳለ በኦሮሞ ፖለቲከኞች አካባቢ የመነጠል ጠባብ ዕይታ ብዙ ዕድሜ ማግኘቱ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ትግል እምብርት የመሆንና ረዥሙን ኦሮሞአዊ ሒደት በዘመናዊና በሠለጠነ መንገድ ዳር የማድረስ ኃላፊነትን ለመውሰድ አለመቻሉ አሳዛኝ ትራጀዲ ነው፡፡ የዛሬውን እውነት ትተው የምኒልክን ዘመቻዎች፣ የኦሮሞን ሕዝብ የጭሰኝነትና የክርስቲያንነት ታሪክ እያብሰለሰሉ ደረት ሲመቱና ሲቃጠሉ የሚውሉ፣ ከናካቴውም ከጥንት ከጠዋቱ እንደገና ታሪክ ‹‹ሀ›› ብሎ ለመጀመር የሚቃዡም አሉ፡፡

በሕዝብ ላይ የደረሰን ያለፈም ይሁን የቅርብ ጉዳት እየነካኩ መጨስና ማጫጫስ፣ እንዲያም ሲል የትናንትን ጉዳት በዛሬዎቹ ላይ የማወራረድ ዝንባሌ ሕዝብን ወደ ማፋጀት ከመምራት በስተቀር ለዕድገት አንዲት ጠብታ እንደማያዋጣ ታይቷል፡፡ በደም የጨቀየ ታሪክ ዓለማችን የተገነባችበት ሆኖ እያለ በኢትዮጵያ ልዩ ነገር የተፈጸመ አስመስሎ ማላዘን አጥፊ ነው፡፡ በሚዛናዊ አዕምሮ የኢትዮጵያን ታሪክ ለመገንዘብ የሚሞክር ሰው በደቡብ ሕዝቦች ላይ የደረሱት ቅጣቶች (ቃጠሎዎች፣ ዘረፋዎች፣ ጭፍጨፋዎች፣ በባርነት የመነዳት፣ የሰለባና የፉነና ድርጊቶች . . . ) ለ‹‹ባዕድ›› ሕዝብ ታስበው የተፈጸሙ እንዳልነበሩ በሰሜኑም ሕዝብ ላይ (ያውም ለረዥም ጊዜ) ሲፈጸሙ እንደነበሩ ማስተዋል አይቸግረውም፡፡ በ1770 (እ.ኤ.አ) ጎንደር የደረሰው ጀምስ ብሩስ እንደመሰከረው የጦር ምርኮኛን መስለብ፣ የዓይን መጎልጎል፣ ጆሮን አፍንጫን እጆችን ወይም እግሮችን መቁረጥና የመሳሰሉት ቅጣቶች የማንኛውም ሰው ፍርኃትና የማንኛው ውጊያ ውጤት ነበሩ፡፡

ከምኒሊክ ዘመቻዎች ጋር ተያይዞ በደቡብ የታየው የመሬት ንጥቂያም በሥረ መሠረቱ የጦርነት ውጤት፣ የቅጣትና የምርኮ አንድ መገለጫ ነበር፡፡ ምኒልክን የተዋጉት (እምቢ ያሉት) አርሲ፣ ሐረር፣ ወላይታ ከሌሎች ቅጣቶች ሌላ የመሬት መነጠቅ ሲደርስባቸው ‹‹በሰላም›› እጅ የሰጡት ግዣቶች ግን ከዝርፊያ ድነው ዓመታዊ ግብር እየከፈሉ እንደ ቀድሟቸው እንዲተዳደሩት ትተው የነበሩት ለዚሁ ነበር፡፡

በአጠቃላይ የገባርነት ሥርዓት ከሰሜን ወደ ደቡብ የመሻጋገር ሒደት ውስጥ በሰሜን ያልነበረ የጭሰኝነት ሥርዓት በደቡብ መምጣትም፣ በዘመቻዎች አሸናፊ የነበሩት የነፍጠኛ ኃይሎች በራሳቸው ሊሠሩበት ከሚችሉት እጅግ የበዛ የመሬት ምርኮ የመገኘት ዕድል ሁኔታ የጎተተው ነው፡፡ ይህ አዲስ ኢኮኖሚያዊ ግንኙነትን መለስ ካለ በኋላ ግን መቆሚያ አልነበረውም፡፡ የደቡብ ሕዝቦች በልዩ ልዩ መልክ መሬታቸውን እየተነጠቁ አጠቃላይ ምርኮ መውደቅ እስኪመስል ድረስ ለጭሰኝነት ሰቆቃ ተዳርገዋል፡፡

ይኼንን እውነት አጠንክሮ ለማሳየት የደቡብ ሕዝቦች ባርነት ገቡ፣ ሁለተኛ ዜጋ ሆኑ ብሎ ማለት አያስከፋም፡፡ ከዚህ ርቆ ወጥቶ በሰሜኑ ሕዝብና በደቡብ መሀል የነፃ (ምርጥ) ሕዝብና የምርኮኛ (ገባር) ሕዝብ የመሆን ልዩነት ለመሥራት መሞከር ስህተት ላይ ይጥላል፡፡

ሁሉንም ሕዝቦች አንቆ የነበረውን አጠቃላይ የሥርዓቱን የአስገባሪነት የጋራ ባህርይ ከማየት ያደናቅፋል፡፡ በደቡብ ተደራጅቶ የነበረው የከፋ ምዝበራና ጭቆና ይነስም ይብዛ፣ ነባርና አዲስ የተፈለቀቁ የደቡብ ገዢዎችን ያካተት እንደበረ ከማየትም ይከለክላል፡፡ ለማንኛውም ግን በየትኛውም በቂም ሆነ በቂ ባልሆነ፣ ስም ያለውም ይሁን የሌለው ምክንያት ተነሳ ብሔርተኛነት አዳላጭ መንገድና አደገኛ ድጥ ነው፡፡ ላስረዳ፡፡

በኢትዮጵያችን ውስጥ ብሔርተኝነት በ‹‹ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት›› ስም ተሹሞ በስፋት የሚገኝ እንደመሆኑ አዳላጭነቱን ጠጋ ብሎ ማየት ጠቃሚ ነው

በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካው ዕቅዶች የብዙ ሰዎችን ጥቅም አቀራርቦ መያዝና ብዙዎችን ለመሳብ መብቃት ከባድ ሥራ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ሲተያይ በብሔርተኝነት ተቧድኖ ድጋፍ መፈለግ ከሁሉም የቀለለ ነው፡፡ የፖለቲካ ትግል ልምምድ ትንሽም የሌላቸው፣ ይኼ ይቅርና የፖለቲካ ንድፈ ሐሳባዊ አስተሳሰብ ያላበጁ ሰዎች ፕሮግራም ልትባል የማትችል ወረቀት አዘጋጅተው፣ ብሔርተኛ ብሶትን እያንጎራጎሩ የብሔር ድርጅት ነኝ ሲሉ አጋጥሞኛል፡፡ የብሔርተኛ መንገድ የሚጋጩ አስተሳሰቦች ያላቸውን ሰዎች፣ ዴሞክራቶችንና ፀረ ዴሞክራቶችን፣ ፋሽስታዊ ዝንባሌ ያላቸውን ጭምር በብሔር ተቆርቋሪነታቸው ብቻ አብረው መንጋፈፍ እንዲችሉ የተመቸ ነው፡፡ ብሔርተኛ አስተሳሰብና አደረጃጀት በተዘረጋበት ሥርዓት ውስጥ ምርጫ ቢካሄድም፣ መራጩ ሕዝብ ፓርቲዎችን ባላቸው ፕሮግራም ከማማረጥ ፈንታ ባመዛኙ ብሔር ብሔረሰቡን ‹‹ይወክላል›› ለተባለ ቡድን ዕጩዎች ድምፁን የመስጠት ሁኔታ ውስጥ ይወድቃል፡፡

አመለካከቱ ሙሉ ለሙሉ በብሔርተኝነት ገደብ ውስጥ የገባ ሰው፣ ብሔሩን ከሌላ ብሔር ጋር በእኩል ዓይን ለማየትና ለመመዘን ይሳነዋል፡፡ የብሔሩን ወግና ባህል በሒስ ዓይን ከማየት ይልቅ እንደወረደ መካብ ያጠቃዋል፡፡ የብሔሩን ባለታሪኮች ጥሩ ሥራቸውን የማብዛትና ድክመታቸውን የመከለል (የማሳነስ) ፍላጎት ይስበዋል፡፡ የበላይ ከነበረ ብሔር ወይም ገዢ መደብ ጋር ብሔሩ የነበረውንና ያለውን ታሪክ በመረዳት ረገድም፣ በደልና ጥቃትን የማነፍነፍና ከዚያ አኳያ አዛብቶና አጡዞ የመተርጎም ፍላጎት የምልከታና የማሰብ ሚዛኑን እየታገለ ያስቸግረዋል፡፡ ብሔራችን ተበድሏል፣ እነዚህና እነዚህ አልተሟሉለትም የሚባለው ነገር ብዙ አየር እየተሞላ አንዳንዴም የትግሉ ሁለንተና ሆኖ፣ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር የሚያገናኙ ዓበይት ጥቅሞች እንዳይጤኑ ሊሸፍን የሚችለው ከዚህ የተነሳ ነው፡፡ ከሌሎች ጋር ያለው የአብሮነት፣ የእኩልነትና የልማት ትግል ምልከታ ውስጥ ሳይገባ የሚካሄድ የድሮና የዘንደሮ የበደል ድርደራ ወደ ቅያሜ የሚያንሸራትት ድጥ አለው፡፡ ከትምክህት ወገኖች ጋር መተራረብ ታክሎበት በፈላ ስሜት መታወር ሊከተል ይችላል፡፡ በአገራችን ተሞክሮ መሰል ችግር እንግዳ አይደለም፡፡

የብሔር ብሔረሰብ ካባ መጎናፀፍ የብሔር ወገንተኝነትን ያጠበቀ ስሜታዊ ድጋፍ የሚገኝበት ጥሩ መደበቂያ መሆን ስለሚችል ሥልጣን ፈላጊዎችና ሙሰኞች ሽፋን አድርገው ይነግዱበታል፡፡ እነሱ የፈጠሩት ድርጅት የያዘውን አቋም የብሔር ብሔረሰቡ አቋም ያደርጉታል፡፡ ድክመታቸው ሲተችና በእነሱ ላይ የተወረወረውን ትችት ብሔር ብሔረሰባቸው ላይ እንደተወረወረ አድርገው ለማምታታት ይመቻቸዋል፡ ‹‹ድሮም… እየተባልክ ትዘለፍና ትናቅ ነበር ዛሬም ይኼው . . . ›› እያሉ ስሜት ውስጥ መክተት የተለመደ ዘዴያቸው ነው፡፡ ለማምታታትም ጠቅሟቸዋል፡፡ ምክንያቱም ብሔረተኛ ተቧድኖና እንቅስቃሴ የቡድን ማንነትና ፍላጎትን ከብሔር ብሔረሰብ ማንነትና ፍላጎት ነጥሎ በማየትና በመረዳት በኩል የበኩሉን አሳሳችነት ይፈጥራል፡፡ ብሔር ብሔረሰብን በደፈናው ሥራዬ ብሎ የሚያወግዝና የሚሳደብ የከተማ እብድ በኢትዮጵያ ሊታይ የቻለው (ከደርግ ውድቀት በኋላ) ከዚህ አሳሳችነት የተነሳ ነው፡፡

ለቅስቀሳ የሚውለው በደል ወይም ፖለቲካዊ ጉዳይ ሁሉንም ብሔር ብሔረሰብ የሚመለከት ሲሆን፣ እንኳን የሁላችንም ችግርና ጥቅም ነው ከማለት ይልቅ የብሔርተኛ ትግል የራሱን ብሔር ብቻ የሚመለከት አስመስሎ በተናጠል የመጮህ ፀባይ ያጠቃዋል፡፡ የፖለቲካ ጥያቄ የተናጠል ብሔርተኛ ጩኸት ሲሆን፣ ሌላው ወገን የራሱ ብሔርተኛ ንቅናቄ ወይም ሌላ የትግል አማራጭ ከሌለው በስተቀር ድርሻው ተመልካችነት ይሆናል፡፡ የብሔርተኛ ንቅናቄ በተፈጠረበት አካባቢ ያለ ውሁድ ኅብረተሰብ፣ በተለይ ገዢ የሚባለው ብሔር አባላት ምንም በደል ባይደርስባቸውም የብሔርተኛ እንቅስቃሴ መፈጠሩ ብቻውን ሥጋታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ብሔረተኛ እንቅስቃሴው ክልላዊ ሥልጣን ሲይዝም ሥጋታቸው ይቀጥላል፡፡ ትምክህትም ሰለባውን ያበዛል፡፡ የብሔርተኛ ትግሉ ተገንጥሎ የመውጣትን ጥያቄ የጨመረ ከሆነ ደግሞ፣ መገንጠልን ከማይደግፍ ወገን ጋር በሞላ መቃረን ይፈጠራል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች የትግል ኃይል ይከፋፈላል፡፡

የትኛውም ዓይነት የብሔር ብሔረሰብ ብሔረተኛነት በውስጤ ያለ ሀብትና ጥቅም ቅድሚያ ለብሔር ወገኔ ይሁን የማለት ቁልቁለት አብሮት ይኖራል፡፡ በዚህ ቁልቁለት ከተንደረደሩ ማረፊያው አድሎአዊነት ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ከተወደቀ ከሌላው በበለጠ ለብሔር ብሔረሰብ ወገን መታመንና ከሌላው አብልጦ የብሔር ብሔረሰብ ወገንን ማቅረብና መጥቀም ይመጣል፡፡ ጥቅቅሞሹ በግልጽና በድብቅ መንገድ ወደ ልዩ ልዩ የሥራ መስክ፣ ወደ ትምህርት ምዘና፣ ወደ ኢንቨስትመንትና የመሬት ምሪት ሊሻገር፣ የፖሊስና የዳኝነት ሥራን ሊበክል ይችላል፡፡ ሲበክልም ታይቷል፡፡ የአድሎአዊነት ችግር መኖር ከ‹‹ሚዳላለት›› ብሔር ውጪ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ቅሬታ ላይ ይጥላል፡፡ የእኩል ዜጋነት ዕምነታቸውን ይሰብራል፡፡ ትምክህተኛና ተቃራኒ የሆኑ የፖለቲካ መስመሮችን ያነሳሳል፡፡ አድልኦ ባልተፈጸመበት ሥፍራና ጊዜም በይሆን ይሆናል መጠራጠርና ሐሜት እንዲራባ ያደርጋል፡፡ ሐሜቱ ደግሞ በፋንታው የብሔርተኛ ሹምን እልህ እያጋባ ማናለብኝነትና አድሏዊነትን ያባብሳል፡፡ ይኼ ሁሉ የአካባቢውን ሰላማዊ ኑሮና ልማት የሚበድል ነው፡፡

በደሉ በዚህ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ‹‹የሚዳላለት›› ብሔር የተጠቃሚነት ስም ይትረፈው እንጂ ተበዳይነቱ በእሱ ይብሳል፡፡ አድልኦን ፈቅዶ እስከተቀበለው ወይም እስካልተቃወመው ድረስ የነፃነትንና የአኩልነትን ጣፋጭነት ማጣጣም አይችልም፡፡ በራሱም ላይ አድልኦ ይጠራል፡፡ በብሔር የተጀመረው ማዳላት የዘመድ፣ የትውውቅና የሽርክና ድር እየሠራ ይስፋፋልና ‹‹የብሔር ወገኖች››ም የአድልኦ ተጠቂነት አይቀርላቸውም፡፡ እንዲያውም ‹‹የብሔር ወገኔ››፣ ‹‹ለብሔሬ የቆመ›› ባይነት ሚዛናዊ አስተውሎቱን እያደበዘዘበት የጥቅመኞች መነገጃ መሆኑን ለማጤን ከሌላው የበለጠ ጊዜ  ሊወስድበትና ብዙ ሊጠቃ ይችላል፡፡

በአድሏዊነትና በጥበት ስሙ የጎደፈ የአስተዳደር አካባቢ ወደ ሥፍራው ሊመጣ የሚችለውን ተወላጅ ያልሆነ አልሚ የማስቀረት ጉዳትም ያስከትላል፡፡ የክልል ልማት በክልል ተወላጅ፣ የአገርም ልማት በአገር ተወላጅ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በዛሬው የግሎባላይዜሽን ዘመን ልማት እንዲሳካ ከተፈለገ ባለሀብትንና ባለቴክኖሎጂን ከየትም ይሁን ከየት እየሳቡ ልማትን እንዲያስፋፋ አደርጎ የመንከባከብ ብልህነት ነው፡፡ አገርነት ይቅርና አኅጉርነት ጠብቦ የብሔር፣ የአገርና የአኅጉር ድንበር ሳይገድባቸው በተያያዙ ጥቂት ግዙፍ ኩባንያዎች ሥር በምትመራ ዓለም ውስጥ ሆነን፣ የብሔር ብሔረሰብ ዕድልንና ልማትን በትንሽ ክልል ደረጃ ከማሰብና ‹‹የብሔር አባሎቻችን ክልላችሁን አልሙ›› ከሚል ጠባብ ማዕቀፍ መውጣት አይበዛብንም፡፡ በዚህ አቅጣጫ ከታሰበ ሐዋሳ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ዋና ከተማ ስትሆን፣ ከሁሉም በለጠ የልማት ማዕከል መሆናቸውን በማስተዋል ሲዳማዎች መደሰት ይገባቸዋል፡፡ ሁሉም ዜጋ መልካም ውኃ እንዲጠጣ፣ የትኞቹም አካባቢዎችና ወንዞች ከብክለት እንዲፀዱ፣ ሁሉም ከተሞች ቆሻሻና ፍሳሻቸውን ለገጠሩም ሆነ ለከተማው ጤና ችግር በማይሆን ዘዴ እንዲያስወግዱ ከማሰብና ከመታገል ፈንታ፣ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ውስጥ በመሆኗና የመጠጥ ውኃና የፍሳሽ አገልግሎቷ በኦሮሚያ ላይ የተደገፈ ስለሆነ ክፍያ ልትፈጽም ይገባል የሚል አስተሳሰብ ዘንድሮም ያላቸው ካሉ ወደ ኋላ ቀርተዋል፡፡ ‹‹በክልሎች ውስጥ ፌዴራላዊ መንግሥት ለኢንቨስትመንት መሬት ሲወስድ ኪራይ ይከፍላል ወይ?›› የሚል ጥያቄ በተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ መነሳቱም አስገራሚና የማይጠበቅ ይሆናል፡፡ በፌዴራል መንግሥት የድጎማ ገንዘብ ድርሻ ሥሌት ላይ ከመብሰልሰልም፣ በአጠቃላይ የልማት ሥርጭት ሚዛናዊነትና ዕድገትን የማጠጋጋት ጥረት ረገድ እየተሠራ ያለውን መመርመር ይበልጣል፡፡

የድርሻ ጉዳይ ሌላ ዓይነት መንፀባረቂያም አለው፡፡ በኅብረተሰቡ ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ሀብት ክፍፍል ከብሔር ብሔረሰብ አኳያ የሚያሰሉና የአማራ፣ የጉራጌ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የሐረሪ ወዘተ ምን ያህል ሀብታም አለ? ምን ያህል ካፒታልስ ደርሶታል? እያሉ ለሕዝብ ብዛት ጋር የሚያነፃፅሩ ተፈጥረዋል፡፡ የዚህ ዓይነት ሥሌት ኅብረተሰቡን ለማቃቃር የሚውል መበላለጥን እየፈለጉ ከማቅረብ በስተቀር የሚሰጠው ጥቅም የለም፡፡ ሰንጠረዥና ቀመር ሠርቶ የዚህ ወገን ድረሻ በዝቷልና ከዚህ ወዲህ ይቀነስ፣ ወይም የዚህኛው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ቆሞ የዚህኛው ይስፋ ሊባል አይችልም፡፡ ያልተመጣጠነ ዕድገት አጠቃላይ የሰው ልጅ ታሪክ ባህርይ ነው፡፡ ማድረግ የሚቻለው አድሏዊነት መወገዱንና አቀራራቢ የልማት ፖሊሲ መኖሩን በትግል ማረጋገጥና በዚያ ውስጥ መጣር ነው፡፡ የዚህ ዓይነት ፖሊሲ ተይዞ ሲጣርም እንኳን፣ ከአድልኦ ውጪ በሆኑ ሌሎች ምክንያቶች መበላለጥ መከሰቱ አይቀርም፡፡

የብሔርተኛ የድርሻ ሥሌት በፖለቲካ ሥልጣንም ውስጥ ይገባል፡፡ በኦሮሞ ድርጅቶች አካባቢ ኦሮሞዎችና ኦሮሚያ በኢትዮጵያ አኮኖሚ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ሁሉ፣ በፖለቲካውም ቁልፍ ሚና ሊይዙ ይገባል የሚል አመለካከት አለ፡፡ የሕወሓቶችን ገዢነት ተገቢ አለመሆን ለማመልከት ሲባል የትግራይ ሕዝብ ቁጥር ተደጋግሞ ሲጠቀስ ይሰማል፡፡ እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውስጥ ባለው አስተዋፅኦና በቁጥሩ ብዛት ልክ የሥልጣን ድርሻው ይመጠን የሚባል ከሆነ የሚወራው ስለዴሞክራሲ አይሆንም፡፡

በዴሞክራሲና በኢኮኖሚ ግንባታ ትግሉ ውስጥ ኦሮሞዎች የአሰባሳቢነቱንና የአንቀሳቃሽነቱን ቁልፍ ሚና መጫወት አለባቸው ማለት ተፈልጎ ከሆነ፣ የኦሮሞ ፖለቲካ ምሁራን በደንብ ያላስተዋሉትን ኃላፊነት የሚያስገነዝብ ትልቅ እውነት ነው፡፡ ዋና ታጋይና አታጋይ መሆን በሥልጣን ወደ መምራትም ይወስዳል፡፡ በአራቱም ማዕዘን ከመሀል እስከ ዳር በሰፊ መልክዓ ምድር ተሠራጭቶና አብላጫውን የብሔር ቁጥር ይዞ መገኘትም በርካታ የሥልጣን ወንበር ለማግኘት የሚመች ነው፡፡ የምንነጋገረው ስለዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ሥልጣን ከሆነ የድርሻ ሥርጭቱን በስተመጨረሻው የሚወስነው የሕዝቦች ድምፅ ነው፡፡ ራሱን በራሱ እያረመና እያጎለበተ የሚራመድ ዴሞክራሲ እስካለና ምርጫና የምርጫ ውጤት እስከተግባቡ ድረስ የትኛውም ብሔር ብሔረሰብ አባላት የሥልጣን ወንበር መበርከት/ማነስ ወይም ርዕሰ ብሔርነትን መያዝ ችግር አይሆንም፡፡ ችግር የሚመጣው የትንሹም ይሁን የትልቅ ብሔር የበላይነትን እንደ መብት/እንደ ሥርዓት ለመዘርጋትና ለማቆየት ሲፈለግ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...