ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ የካቶሊክ ጳጳሳት ጉባኤዎች ኅብረት (አመሰያ) የሚያዘጋጀውን 19ኛውን ዓለም አቀፍ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ጉባኤ ልታስተናግድ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ እምብፁዓን ካርዲናል ብርሃነየሱስ ፕሬዚዳንትነት የሚመራው አመሰያ፣ ጉባኤውን በ2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ እንደሚያካሂድና ጉባኤውንም ለማስተናገድ ቅድመ ዝግጅቱ እየተከናወነ መሆኑ ቤተክርስቲያኒቱ በላከችው መግለጫ አስታውቃለች፡፡
ይህ ከ300 በላይ ተሳታፊዎች የሚገኙበት ጉባኤ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲካሄድ፣ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያኗ አጋጣሚውን በመጠቀም አገሪቱ ያላትን የሰላምና የመከባበር ባህል ከሌሎች ወንድሞና እህቶች ጋር ለመካፈል የምትጠቀምበት አጋጣሚ መሆኑን ተገንዝባ፣ የአስተናጋጅ ኃላፊነቱን መቀበሏን የቤተክርስቲያኒቷ ምክትል ጠቅላይ ጸሐፊ ዶ/ር አባ ሥዩም ፍራንሷ ገልጸዋል፡፡
‹‹በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተመሠረተ ሕያው ብዝኃነት፣ ሰብአዊ ክብርና ሰለማዊ አንድነት ለአመሰያ ሀገራት›› (Vibrant Diversity, Equal Dignity, Peaceful Unity in God in the AMECEA Region) የሚል መሪ ቃል ያለውን 19ኛውን የኅብረቱን ጉባኤ፣ የመላው ኢትዮጵያውያንና በጎ ፈቃድ ያላቸውን ወገኖች ትብብር እንዳይለይ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤቱ ጠይቋል፡፡ የጉባኤው ዝግጅት ታኅሣሥ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በሁሉም አህጉረ ስብከት፣ በኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ በሚገኘው የኅብረቱ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት፣ እንዲሁም በምሥራቅ አፍሪካ ደረጃ በይፋ መጀመሩ ታውቋል፡፡
አመሰያ በሚለው ምኅፃረ ቃል በሰፊው በሚታወቀው ኅብረት ውስጥ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ማላዊና ዛምቢያ አባላት ሲሆኑ፣ ጂቡቲና ሶማሊያ ተባባሪ አባላት ናቸው፡፡
አመሰያ ሐቻምና በማላዊ ዋና ከተማ ባካሄደው 18ኛው ጉባኤ፣ ኅብረቱን ለአራት ዓመታት ኢትዮጵያ በብፁዕ ካርዲናል ብርሃነየሱስ አማካይነት በፕሬዚዳንትነት እንድትመራ መምረጡ ይታወሳል፡፡