Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

እዚህ ከተማ ውስጥ አስገራሚ ጉዳዩች ይገጥሙናል፡፡ እኔ የታዘብኳቸውን እስኪ አንቡብልኝ፡፡ ብዙ ጊዜ መጠጥ ቤት ውስጥ አንዳንድ ሰዎች ያጋጥሟችኋል፡፡ ድንገት አንድ ጉዳይ ይነሳና በዚያ መነሻ፣ ‹‹እከሌና እከሊትን እኮ አውቃቸዋለሁ፡፡ እንዲያውም ዛሬ ምሳ አብረን ነው የበላነው፡፡ በጣም እንቀራረባለን እኮ፣…ጲሪሪም…ጲሪሪም…›› ይሏችኋል፡፡ ‹‹እከሌ›› የጦር ጄኔራል ወይም ‹‹እከሊት›› ሚኒስትር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የተለየ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስፈራራት ሲፈልጉ የትልልቅ ሰዎችን ስም ከለላ በማድረግ ብዙ ነገር ይዘበዝባሉ፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ዕብድ ይመስሉኛል፡፡

አንድ ጊዜ አንዱ የአንድ ታዋቂ ሚኒስትር ስም ይጠራና፣ ‹‹ትናንት ሸራተን አብረን ውስኪ ስንጠጣ ነው ያመሸነው፤›› ይላል፡፡ በሰውየው ንግግር በጣም የተገረመ ሌላ ሰው፣ ‹‹ከማን ጋር?›› ይለዋል ለማጣራት ፈልጎ ነው፡፡ የሚኒስትሩን ስም እንደገና ይጠራለታል፡፡ ሰውየው በጣም ተናዶ ስለነበር፣ ‹‹በቃህ! እሱ እንኳን ውስኪ ኮካ እንኳ አይጠጣም፡፡ አንተም በቅጡ የማታውቀውን ስም እያነሳህ አፍህን አትክፈት፤›› ሲለው ጭጭ ይላል፡፡ አጋጣሚ ባገኘ ቁጥር የታዋቂ ሚኒስትሮችንና ወታደራዊ ሹማምንትን ስም እየጠራ፣ ብዙዎችን ሲያሸማቅቅ የነበረ ዋተኔ ከዚያ በኋላ እዚያ ቦታ ድርሽ ሳይል ቀረ፡፡ አንዳንዴ እኮ ደፋር አያሳጣን ያስብላል፡፡

እኔ ከዚህ ቀደም እንዲህ ዓይነት በርካታ ሰዎችን ታዝቤያለሁ፡፡ የዛሬ አንድ ዓመት ገደማ አንዱ ቢሮዬ ይመጣና ስፖንሰርሺፕ ይጠይቀኛል፡፡ እኔ በኃላፊነት የምመራው መሥሪያ ቤት እሱና ቢጤዎቹ የሚያዘጋጁትን በዓል 200 ሺሕ ብር በመክፈል ስፖንሰር እንዲሆን ነው ጥያቄው፡፡ ይህንን ገንዘብ ለሠራተኞቻችን በቦነስ መልክ ብንሰጥ ምን ያህል የተቀደሰ ተግባር እንደሆነ በሚገባ ስለማውቅ እንደማይቻል እነግረዋለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ሰውየው ቴአትር ጀመረ፡፡ ‹‹እኛ እኮ የኢሕአዴግና የመንግሥት ደጋፊዎች ስለሆንን ብዙ ድርጅቶች ቃል ገብተውልናል፡፡ የእናንተ ድርጅት ይህንን ገንዘብ ቢሰጥ መንግሥት በጥሩ ዓይን ያየዋል፡፡ ተጠቃሚም ትሆናላችሁ…›› እያለ ሲያቅራራ ደሜ ፈላ፡፡ ስለዚህ መናገር ነበረብኝ፡፡ ‹‹ሰማህ በአገራችን ውስጥ የሚፈለገው ጥገኝነት ሳይሆን ሕግና ሥርዓት አክብሮ እየሠሩ ማደግ ነው፡፡ አይቻልም ስልህ እሺ ብለህ መሄድ እንጂ፣ እንዲህ ዓይነቱን ርካሽና ተራ ወሬ መዘብዘብ አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ስለዚህ ውጣ!›› ስለው ተንሿኮ ሄደ፡፡ ሾካካ፡፡

የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የፖለቲካ ድርጅትን፣ የታዋቂ ግለሰቦችን፣ የሀብታሞችን፣ ወዘተ ስም እየጠሩ የሚያጭበረብሩ ብዙ አሉ፡፡ በዘመኑ አጠራር ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› ይባላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ደግሞ መጠጥ ቤቶች፣ ሬስቶራንቶች፣ መዝናኛ ሥፍራዎችና መሥርያ ቤቶች አካባቢ አይጠፉም፡፡ አሁን አሁን የከተማችን ታዋቂ የመጠጥና የምግብ ቤቶች የእነዚህ ግለሰቦች መናኸሪያ እየሆኑ ናቸው፡፡ እነዚህ ንግድ ቤቶች በተለይ የዘመናችን ወጣት ሀብታሞች ውስኪና ቮድካ የሚጎነጩባቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ በተለያዩ ምክንያቶች እጅ መንሻ ሰጥተው ላጋጠማቸው ችግር መፍትሔ የሚፈልጉ ሰዎች መቃጠሪያ ናቸው፡፡ በስም ተጠቃሚ የሆኑ ዋተኔዎችም እንዲህ ዓይነቱን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ኪራይ ይሰበስባሉ፡፡ እነሱ ስለማይሳካላቸው ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› ለሚባሉ ተላላኪዎች ባለጉዳዮችን ያስተላልፋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት የሚፀየፉ ኩሩ ኢትዮጵያውያን እህህህ….. እያሉ ይበግናሉ፡፡ 

በቅርቡ አንደኛው ታዋቂ መጠጥ ቤት ተገኝቻለሁ፡፡ አራት ሆነው ‹‹ጎልድ ሌብል›› ጠርሙስ ውስኪ አስወርደው ከሚጎነጩት መካከል አንዷ ሴት ናት፡፡ በአነጋገሯ ፈጠን፣ በአስተያየቷ ደፈር፣ በአጠጣጥዋ ጠንከር ያለች ናት፡፡ የሲጋራ አያያዝዋና አጫጫስ ቄንጧ ልዩ ነው፡፡ በየመሀሉ በተደወለላት ወይም ራሷ በደወለች ቁጥር የታዋቂ ሰዎች ስም ይነሳል፡፡ ‹‹በእኔ ይሁንብህ ወይም ይሁንብሽ›› በታጀበው አነጋገሯ ስማቸውን በምታነሳቸው ታዋቂ ሰዎች አማካይነት ጉዳያቸውን እንደምታስፈጽም በድፍረት ትናገራለች፡፡ ስልኳን አንስታ መነጋገር በጀመረች ቁጥር ሁላችንም እንድንሰማ ድምጿን ከፍ አድርጋ መሆኑ ገበያ ፍለጋ እንደሆነ ያስታውቃል፡፡ 

የዚህችን ሴት ድፍረት ሲታዘብ የነበረ አንድ የማላውቀው ሰው፣ ‹‹ይቅርታ እዚህ አገር ማፈር ቀረ እንዴ?›› በማለት ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ ‹‹ይኸው እንደምታየው ነው፤›› አልኩት፡፡ ‹‹የእኔ ወንድም በየደረስክበት እኮ ማንም እየተነሳ የባለሥልጣን ወይም የታዋቂ ሰው ጓደኛ መሆኑን ይነግርሃል፡፡ ይኼ በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳቅቅ ተግባር ነው…›› ብሎኝ ሒሳቡን ከፍሎ ውልቅ አለ፡፡ ከጎኔ የተቀመጡ ሁለት ሰዎች በሴትየዋ የድፍረት ንግግር መነሻ ወግ ይዘዋል፡፡ የሰዎቹ ወግ ሌላ ገጽታ ያስቃኘናል፡፡

አንደኛው፣ ‹‹አንድ ጊዜ 100 ሺሕ ብር ከባንክ አውጥቼ ወደ ቢሮ ልሄድ መኪናዬን ለማስነሳት ስሞክር እምቢ አለኝ፡፡ ቢሮዬ ቅርብ ስለነበር ፌርማታ ላይ የቆመ ሚኒባስ ወያላ ሲጣራ ሮጥ ብዬ ገባሁ፡፡ እንደገባሁ ሚኒባሱ በፍጥነት መጓዝ ሲጀምር፣ ሳላውቅ የገባሁበት ሚኒባስ አራት ወጠምሻ ጎረምሶች ተጭነውበታል፡፡ ሁኔታው ስላላማረኝ ስልኬን አውጥቼ ‘ኢንስፔክተር ከኋላህ ያለው ታክሲ ውስጥ ነኝ አቁሙልኝ’ ብዬ ‘ወራጅ’ ስል ሾፌሩ በድንጋጤ ሲያቆምልኝ ተንደርድሬ ወረድኩኝ፡፡ ይህ ዘዴ በድንገት ባይመጣልኝ ኖሮ ጉድ ሆኜ ነበር፡፡ አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት ብልጥነት ከመዘረፍም ከመገደልም ያድናል…›› እያለ ሲያወራ ይኼም አለ ለካ አልኩ፡፡ ቢያንስ ሰውን ከማስፈራራትና ከመዝረፍ ይኼኛው ሳይሻል ይቀራል? ለማንኛውም በሬዲዮም ሆነ በቴሌቪዥን ስለመልካም አስተዳደር ዕጦትና ስለሙስና መንሰራፋት ተወርቶ ቡራ ከረዩ ሲባል፣ በየሥርቻው ደግሞ ምድረ ‹‹ጉዳይ ገዳይ›› አገር ያምሳል፡፡ ጥልቅ ተሃድሶው ይህንንም ይካተታል? ወይስ አያውቀውም?

(መክብብ ወሰን፣ ከበቅሎ ቤት)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...