Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተር​የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ይፈተሽ

​የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት ይፈተሽ

ቀን:

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት የቀድሞው ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አህመድ ቱሳ ከኃላፊነታቸው ከተነሱ በኋላ በሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ፣ ኅዳር 21 ቀን 2009 ዓ.ም. በተሰራጨው ዜና ላይ ስለሰጡት አስተያየትና ወደ ፊት በአቶ አህመድ ቱሳ ምትክ ለሚሾመው አዲስ የሥራ ኃላፊ ትምህርት ሰጪ እንዲሆንና የድርጅቱን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት እንዲያስችል በማሰብ ይህ ጽሑፍ በድርጅቱ ሠራተኞች አማካይነት የቀረበ ነው፡፡

በሪፖርተር ጋዜጣ አማካይነት አቶ አህመድ ቱሳ በኃላፊነት ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ ሦስት ዋና ዋና ስኬቶችን ማስገንዘባቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህንም አንድ በአንድ ከዚህ በታች እንመለከታቸዋለን፡፡

     አንደኛ በ2003 ዓ.ም ሦስቱ መሥሪያ ቤቶች ማለትም የቀድሞው ንግድ መርከብ፣ ባህር ትራንዚት አገልግሎትና የደረቅ ወደብ አስተዳደር ጠቅላላ ገቢ 4.7 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ በ2008 ዓ.ም. በአራት ዕጥፍ ጨምሮ 16.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል ብለዋል፡፡

- Advertisement -

   ይህ ግን እርሳቸው ያስመዘገቡት ስኬት ሳይሆን፣ አዳዲስ ዘጠኝ መርከቦች ተገዝተው ወደ ሥራ በመግባታቸው፣ የመልቲ ሞዳል ኦፕሬሽን ሥራ መንግሥት በሰጠው አቅጣጫ መሠረት በአዋጅ በመጀመሩ፣ የደረቅ ወደቦች ወደ ሥራ በመግባታቸውና የአገሪቱ የገቢ ዕቃ መጠን በዓመት ከ24 በመቶ በላይ በአማካይ እያደገ በመምጣቱ እንዲሁም በ2008 ዓ.ም ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ፣ ማዳበሪያ፣ የድንጋይ ከሰል፣ ስኳር የመሳሰሉት ብትን ዕቃዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በመደረጋቸው የተገኘ ነው፡፡  

    በተጨማሪም የቀድሞው ንግድ መርከብ አክሲዮን ማኅበር ለብቻው እስከ 960 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ሲያስመዘግብ ቢቆይም፣ አሁን ሦስቱ መሥሪያ ቤቶች ተዋህደው የሚያስመዘግቡት የተጣራ ትርፍ ግን ከ760 ሚሊዮን ብር መዝለል ያልተቻለበት ምክንያት ከፍተኛ የአሠራር ሥርዓት ችግር በመኖሩ፣ ሥራው በሙያተኞችና ለሥራ ፍቅር ባላቸው ዜጎች ሊመራ ባለመቻሉ ነው፡፡ እንዲሁም ሥራና ሠራተኞችን ያላገናኘ ምደባ በመካሄዱ በርካታ ሠራተኞች ድርጅቱን እየለቀቁ በመሄዳቸው መሆኑም በዋናነት የሚጠቀሱ ችግሮች ናቸው፡፡

     ሁለተኛ በመልቲ ሞዳል ኦፕሬሽን በ2004 ዓ.ም. የነበረው 10 ሺሕ ኮንቴይነር የማንሳት አቅም በ2008 ዓ.ም 175 ሺሕ ኮንቴይነር ሆኗል ብለዋል፡፡ ይህም ከላይ በተመሳሳይ በተጠቀሰው ምክንያት ያደገ ሲሆን፣ የመልቲ ሞዳል ኦፕሬሽን የአሠራር ሥርዓት በባህሪው ቀስ በቀስ እያደገና በባህር ወደቦችና በደረቅ ወደቦች ያለው የመሠረተ ልማት፣ የሰው ኃይል፣ የአሠራር ሥርዓት፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተላበሱ ዘመናዊ መሳሪያዎች የመሳሰሉት በሒደት እየተሟሉና እየተስተካከሉ ሲሄዱ አቅም እየጎለበተ እንደሚሄድ ይታወቃል፡፡ ይህም መንግሥት በመደበው ከፍተኛ በጀትና የሎጂስቲክስ ዘርፉን ከገባበት ትርምስ ለማውጣት በተደረገ ጥረት ጭምር እንጂ አቶ አህመድ ቱሳ በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ዘመናቸው ያስመዘገቡት ስኬት ብቻ ሆኖ ሊታይ አይችልም፡፡

     ሦስተኛ የደንበኞች እርካታን በተመለከተ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በገለልተኝነት እንዲያጠና አስደርጌ እርካታው 71.6 ከመቶ ደርሷል ብለዋል፡፡ በመሠረቱ ይህ ጥናት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምሁራን እንዲጠና ሲደረግ ልዩ ልዩ ወጪዎችን ጨምሮ አምስት ሚሊዮን ብር ያህል ክፍያ እንደተፈጸመ ሰምተናል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራን የአካዴሚክ ዕውቀታቸው ከፍተኛ መሆኑ ባይካድም፣ በቪፒንግ ሎጅስቲክስ ዘርፍ በድርጅቱ ውስጥ ውጭ አገር በመሄድ ከፍተኛ የዕውቀት ክህሎትና የሥራ ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች እያሉ ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመሄድ የተደገው ጥናት ውስጡ ሌላ ነገር ሊኖረው እንደሚችል ያመለክታል፡፡

      የድርጅቱ ባለሙያዎች ከአሁን በፊት መንግሥት ባስጠናው የመልቲ ሞዳል ኦፕሬሽንና የደረቅ ወደቦች ግንባታ እንዲሁም በሌሎች አገር አቀፍ ጥናቶች መሠረት ያለክፍያ በነፃ አገልግሎት ማበርከታቸው እየታወቀ ለምን ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መሄድ አስፈለገ ተብሎ በተለያዩ ስብሰባዎች ሠራተኛው ወቀሳ ቢያቀርብም ምንም ዓይነት ተሰሚነት አልላገኘም፡፡

     ስለሆነም የሪፖርተር ጋዜጣ በአቶ አህመድ ቱሳ ዙሪያ ያቀረባቸው የአሠራር ድክመቶች ማለትም በርካታ ሠራተኞችና ባለሙያዎች ድርጅቱን እየለቀቁ መሄዳቸው፣ የደንበኞቹ እርካታ እየወረደ መሆኑና የደረቅ ወደቦች ከባቡር መስመር ጋር እንዲገናኙ አለመደረጉ በዘገባው መወሳታቸው ትክክለኛ መሆኑን እያረጋገጥን፣ በአሁኑ ጊዜ በድርጅቱ ላይ የተደቀኑትን ዋና ዋና ችግሮች ነቅሰን በማውጣት የሥራ አመራር ቦርዱና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚኒስትርና የትራንስፖርት ሚኒስትሩ ተገቢውን ማስተካካያ እንዲያደርጉ በአክብሮት እንጠይቃለን፡፡

አቶ አህመድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከሆኑበት ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በድርጅቱ ውስጥ ለረጅም ዓመታት ያገለገሉ ሠራተኞች ምንም ዓይነት የሥራ ምደባና የቅጥር ደብዳቤ ሳይሰጣቸው ደመወዝ እየተቀበሉ እንዲሠሩ መደረጉ፣ የሠራተኞቹን ሕገ መንግሥታዊ መብት የሚጥስ ተግባር መሆኑ ተፈትሾ ሠራተኞቹ ተረጋግተው እንዲሠሩ የሚያስችላቸው የቅጥር ደብዳቤና የሥራ ምደባ በአግባቡ እንዲሰጣቸው አስፈላጊው መመርያ እንዲሰጥ እንጠይቃለን፡፡     

በአሁኑ ጊዜ የድርጅቱ ከ70 በመቶ በላይ ገቢ የሚገኘው ከኪራይ መርከቦች ሲሆን፣ የራሳችን አዳዲሶቹ ዘጠኙም መርከቦች ተደማምረው የሚያስገኙት ገቢ ከ30 በመቶ አይበልጥም፡፡ ይህም በጥልቀት ሊፈተሽ የሚገባውና የራሳችንን መርከቦች አጠቃቀም ለማሻሻል ልዩ ምርመራ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ለመጠቆም እንወዳለን፡፡ የመርከብ ወኪሎች የአሠራር ሁኔታም መፈተሽ አለበት፡፡

የድርጅቱ ሒሳብ ሳይዘጋና በውጭ ኦዲተሮች ሳይመረመር ለብዙ ጊዜያት ወደ ኋላ ስለቀረ ለሙስናና ለብክነት የተጋለጠ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ለዚህም እንደ መፍትሔ የተወሰደው ከአሁን በፊት ችግር አለበት ተብሎ በግምገማ ከድርጅቱ በጡረታ የተሰናበቱ ግለሰቦችን እንደገና በመቅጠር መፍትሔ ለማምጣት መሞከር ነው፡፡ ይህ በድርጅቱ ሀብትና ንብረት ላይ መቀለድ እንደሆነ ይሰማናል፡፡ ስለሆነም ይህ አማራጭ ለምን እንደተፈለገና የድርጅቱን ሒሳብ ለመዝጋት ያልተቻለበት ምክንያት ምን እንደሆነ በዝርዝር እንዲፈተሸና እንዲመረመር እንጠይቃለን፡፡

ድርጅቱ ከፍተኛ መጠን ያለውን የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ለመርከቦች ነዳጅ፣ ለመለዋወጫ፣ ለጥገና፣ ለዕቃ ማራገፊና መጫኛ፣ ለወኪሎች ኮሚሽን፣ ለወደብ ኪራይ፣ ለኢንሹራንስ፣ ለኪራይ መርከቦች ክፍያ፣ ለትጥቅና ስንቅ፣ ለደመወዝና ለመሳሰሉት እንደሚያወጣ ይታወቃል፡፡ በዚህ ዙሪያ በርካታ አጠራጣሪና የሙስና ተግባራት የሚፈጸሙ ስለመሆናቸው በርካታ አመላካች ጉዳዮች አሉ፡፡ ከአሁን በፊትም በኢንስፔክሽን ቡድን የተጠኑ ሥራዎች በመኖራቸው በዚህ ዙሪያ ጥልቅ ፍተሻና ምርመራ ቢደረግ በርካታ ጉዳዮች ጎልተው እንደሚወጡ በማመን አስተያየታችንን እናጠቃልላለን፡፡  

(ከየኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሠራተኞች)

*  *  * *  *

ተቆጣጣሪ ያጣው የሐዋሳ ነጭ ጋዝ ሽያጭ

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየወጣበት በመንግሥት ድጎማ ለተጠቃሚው ሕዝብ የሚቀርበው ነጭ ጋዝ ዋና ዓላማው ኅብረተሰቡ ለማገዶነት የደን ውጤቶችን እንዳይጠቀም ብሎም የደን መጨፍጨፍን ለመከላከል እንዲቻል ታስቦ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን ድጎማ በተደረገለት ነጭ ጋዝ ተጠቃሚው ሕዝቡ ሳይሆን የሸቀጣሸቀጥ ነጋዴዎችና የነዳጅ ማደያ ሠራተኞች ሆነዋል፡፡

በተለይ በአሁኑ ወቅት በሐዋሳ ከተማ ውስጥ ከነዳጅ ማደያዎች ነጭ ጋዝ ማግኘት የማይታሰብ እየሆነ ነው፡፡ ሽያጩ የሚከናወነው ሌሊት ሲሆን፣ በበርሜል  ለነጋዴዎች ብቻ እየቀረበላቸው ነው፡፡ አነስተኛ ሊትር ለመግዛት የሚጠይቁ ተጠቃሚዎች የሚያገኙት ምላሽ አልቋል የሚል ነው፡፡ ዛሬ አርባ ወይም ሃምሳ ሺሕ ሊትር ያስገባ ነዳጅ ማደያ በማግሥቱ አልቋል እያለ ሰውን ይመልሳል፡፡ ማደያው ውስጥ ጋዙ እያለም ቢሆን ለምን ለኅብረተሰቡ አይሸጥም ብሎ የሚጠይቅ አካል የለም፡፡

በአሁኑ ወቅት በሐዋሳ ከተማ ነጭ ጋዝ ማግኘት የሚቻለው ከሸቀጣሸቀጥ መደብሮች ነው፡፡ መደብሮቹ ወደ ነዳጅ ማደያነት ተቀይረዋል፡፡ ንግድ ፈቃዳቸው የነዳጅ ሽያጭንም ያካተተ ይመስል ነጭ ጋዝ እንሸጣለን የሚል ማስታወቂያ ለጥፈው ይታያሉ፡፡ በመደብሮቹ አንድ ሊትር ነጭ ጋዝ እስከ 30 ብር ይሸጣል፡፡ እንግዲህ የከተማውን የነጭ ጋዝ ተጠቃሚ ለእንደዚህ ዓይነት ብዝበዛ ያጋለጡት የከተማው የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ብሎም የከተማው አስተዳደር ናቸው፡፡ የሕዝብ ጥያቄ ሲነሳ አንድና ሁለት ማደያዎችን ማሸግ መፍትሔ አይሆንም፡፡ መፍትሔው ትክክለኛ የቁጥጥር ሥርዓት በመዘርጋት መንግሥት በድጎማ ያቀረበውን ነጭ ጋዝ ሕዝቡ በአግባቡ እንዲጠቀም ማድረግ ነው፡፡

(ማቲዎስ ሸመሎ፣ ከሐዋሳ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...