Friday, June 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክመሻሻል ያለባቸውና እንከን የበዛባቸው ሕገ መንግሥታዊው የመገንጠል ሥነ ሥርዓቶች

መሻሻል ያለባቸውና እንከን የበዛባቸው ሕገ መንግሥታዊው የመገንጠል ሥነ ሥርዓቶች

ቀን:

በውብሸት ሙላት

      ሰሞኑን በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃንን ከተቆጣጠሩ አጀንዳዎች ውስጥ አንዱ አሁን በሥራ ላይ የሚገኘው ሕገ መንግሥት ከማርቀቅ ጀምሮ እስከ ማጽደቅ ድረስ ያለፈባቸውን ሒደቶች የሚዘክረው ነው፡፡ የአጀንዳው ዓላማ የሚመስለው ከማርቀቅ እስከ ማጽደቅ በነበሩት ሒደቶች ውስጥ የነበረውን ውይይት፣ ክርክርና የሕዝብ ተሳትፎ በማሳየት ከጅምሩም የሕዝብ ሕገ መንግሥት ነው፤ ብሎም ቅቡልነትን (Legitimacy) የተጎናጸፈ መሆኑን ማሳየት ይመስላል፡፡ በሚዲያዎች የሚቀርቡትን፣ የአርቃቂዎቹንና የአጽዳቂዎቹን ቃለ ጉባዔዎች እንዲሁም በማብራሪያነት መልክ ለሕዝብ የቀረበውን ሰነድ ለተመለከተ ሰው በአጨቃጫቂነታቸው እንደ ዋና አጀንዳ የነበሩት ጉዳዮች የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የመገንጠል መብት በሕገ መንግሥቱ መካተት፣ መሬት የመንግሥት ይሁን የግል የሚለው፣ በዋናነት ብሔርን መሥፈርት ያደረገው የፌደራል አወቃቀር፣ የባንዲራው ቀለም፣ የፌደራል መንግሥቱ የቋንቋ ምርጫና በተወሰነ መልኩ የሕገ መንግሥቱ መግቢያ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡

      ይህ ጽሑፍ የሚዳስሰው ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅም ሆነ ሲጸድቅ እንዲሁም ኋላ ላይ ፖለቲከኞችም ይሁኑ ምሁራን ብዙም ትኩረት ካልሰጠባቸው ጉዳዮች አንዱ የሆነውን የመገንጠል ሥነ ሥርዓትን ወይም ሒደትን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅም ይሁን ሲጸድቅ እጅግ ካጨቃጨቁት ጉዳዮች ዋነኛው አንቀጽ 39 ንዑስ ቁጥር 1 ላይ የተገለጸው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ያለምንም ገደብ መገንጠልን በሕገ መንግሥቱ የመካተቱ ነገር ነው፡፡ በዚህ አንቀጽ ውስጥ የተዘረዘሩት ሌሎች አራት ንዑሳን አንቀጾች ግን ከጅምሩም ትኩረት አልሳቡም ወይም አልተሰጣቸውም፡፡ የመገንጠል መብት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና እንዲኖረው በትጋት የተከራከሩትና  የሚከራከሩት ሰዎች ከሚያነሷቸው ምክንያቶች መካከል ቀዳሚውና ዋነኛው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር አብረው መኖር  ካልቻሉ ያለ ጦርነት ወይም በሰላም ለሚለያዩበት ሁኔታ ዋስትና ይሰጣል የሚል ነው፡፡ በመሆኑም መገንጠልን የመረጡ ቡድኖች ደረጃ በደረጃ ሊከተሏቸው የሚገቡ አምስት ሥነ ሥርዓቶች በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር አራት ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ‘የሠይጣን ጆሮ አይስማና’፣ አንድ ብሔር መገንጠል ቢፈልግና እነዚህን ሥነ ሥርዓቶች በመከተል ምንም ዓይነት ጦርነት ወይንም እልቂት ሳይኖር በሰላም የመገንጠልን መብት ሥራ ላይ ለማዋል ማስቻላቸው ግን ፍተሻ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ ጽሑፍ እነዚህን ሥነ ሥርዓቶች ያሉባቸውን እንከኖች በማሳየት የመገንጠል መብትን ሥራ ላይ ማዋል የሚፈልግ ብሔር ቢኖር በሰላም ለመለያየት የማያስችሉ መሆናቸውን በመጠቆም መሻሻል ያለባቸው መሆኑን ያመላክታል፡፡

      መገንጠል በዘፈቀደ የሚፈጸም ድርጊት እንዳይሆን በማሰብ ሥነ ሥርዓቶቹ ቀድመው ተቀምጠዋል፡፡ የመገንጠልን ጉዞ ለሚመርጥ ተጓዥ፣ መንገዱ እንዲህ ነው፡፡

  1. መገንጠልን የሚፈልገው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ምክር ቤት በ2/3ኛ መገንጠሉን ሲደግፍ፣
  2. የፌደራሉ መንግሥት በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ሲያዘጋጅ፣
  3. መገንጠሉን አብዛኛው ሕዝብ ሲደግፈው፣
  4. የፌደራሉ መንግሥት ሥልጣን ሲያስረክብ፣
  5. የንብረት ክፍፍል ሲካሔድ፡፡

እነዚህ የመገንጠያ መንገዶች ናቸውና ተራ በተራ እንያቸው፡፡     

የምክር ቤት ውሳኔ

      በመጀመሪያ፣ መገንጠል የሚፈልገው ብሔር የራሱ ምክር ቤት ሊኖረው ግድ ነው፡፡ ምክር ቤቱም በ2/3ኛ ድምፅ የመገንጠሉን ሐሳብ ካልደገፈ በስተቀር ቀጣዮቹ ሥርዓቶች ምንም ፋይዳ የላቸውም፡፡ በመሆኑም ጥያቄው በዚሁ ተኮላሸ ማለት ነው፡፡ በሴንት ኪትስ እና ኔቪስም (ከኢትዮጵያ 12 ዓመታት በመቅደም የመገንጠል መብትን በሕገ መንግሥቷ ያካተተች ባለ ሁለት ክልሎች አገር ናት፡፡) መጀመሪያ የኔቪስ ደሴት ሕግ አውጭ ምክር ቤት በ2/3ኛ የድጋፍ ድምፅ መስጠት አለበት፡፡ ከዚያ በኋላ ይኼው ምክር ቤት በሕዝበ ውሳኔ ወቅት ለኔቪስ ደሴት መራጮች  የሚያቀርበውን አማራጮች ሕዝቡ ድምፅ ከመሰጠቱ ቢያንስ ከዘጠና ቀናት በፊት ማሳወቅ ይጠበቅበታል፡፡ አማራጮቹም፣ ከሴንት ኪትስ ተለይቶ ነፃ አገር መመሥረት፣ ከሌላ አገር ጋር መቀላቀል ወይንም አለመለየት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በካናዳም፣ ለሕዝበ ውሳኔ የሚቀርበው ጥያቄ ግልጽ መሆን እንዳለበትና ቀድሞ በአገሪቱ ፓርላማ መጽድቅ አለበት፡፡

      በኢትዮጵያ የብሔሩ ምክር ቤት ለመገንጠሉ አጀንዳ የ2/3ኛ የድጋፍ ድምፅ ከሰጠ ይኼንኑ ውሳኔ በጽሑፍ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤትም ጥያቄው ከደረሰው ጀምሮ በሚታሰብ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ማዘጋጀት አለበት፡፡ በኔቪስ ደሴት ግን ሕዝበ ውሳኔውን የሚያከናውነው የፌደራል መንግሥቱ ሳይሆን ራሷ ደሴቷ ናት፡፡ የምርጫ ኮሚሽኑም የሚዋቀረው የደሴቷ ገዥ የሚሾመው ሰብሳቢ፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትርን አማክሮ ሁለት በድምሩ ሦስት አባላት ባሉት የምርጫ ኮሚሽን አማካይነት ይከናወናል፡፡

“የማሰላሰያ ጊዜ”

      ብሔሮች ከኢትዮጵያ ከመፋታታቸው በፊት የማሰላሰያ ጊዜ ባይቀመጥም የፌደራሉ መንግሥት በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያዘጋጅ መደንገጉ ወይንም በጣም አጭር ጊዜ አለመሆኑ መገንጠል የሚፈልገው ብሔርም እንዲያስብበት፣ ቅስቀሳና የማሳመን ሥራ የማከናወኛ ጊዜ በመሆን ሊያገለግል ይችላል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ አንድነትን ለሚሰብኩትና የሚደግፉት የማግባባትና የመቀስቀስ ተግባራቸውን በዚህ ወቅት ለማከናወን ዕድል ያገኛሉ፡፡ በመሆኑም ይህ  እንደ ማሰላሰያ ጊዜ ሊወሰድ ይችላል፡፡

      የመገንጠያ ሥነ ሥርዓት በሕገ መንግሥቷ አበጅታ የነበረችው ሩሲያ ግን ከዚህ የተለየ የማሰላሰያ ጊዜ ነበራት፡፡ የሩሲያ ሪፐብሊኮች (ክልሎች) ለመገንጠል በትንሹ አምስት ዓመት ይፈጅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ሕዝበ ውሳኔ ተደርጎ በ2/3ኛ ድምፅ ድጋፍ ካገኘ በኋላ በድጋሚ በአምስተኛ ዓመቱ መጨረሻ ላይ የማረጋገጫ ሕዝበ ውሳኔ በማከናወን ድምፅ መስጠት ከሚችለው ከሪፐብሊኩ ነዋሪዎች ውስጥ 2/3ኛው መገንጠልን መደገፋቸው መረጋገጥ አለበት፡፡ በመሆኑም ሐሳባቸውን ሊቀይሩ ከቻሉም ዕድል ይሰጣል፡፡ ይህ አድራጎት ሽማግሌዎች ባልና የሚስት ለማስታረቅና ለማግባባት የሚጠቀሙበትን ስልት ያስታውሰናል፡፡ ባልና ሚስት ተጣልተው ጉዳያቸው በሽምግልና እንዲታይላቸው ለመረጧቸው ሽማግሌዎች ብሶታቸውንና በደላቸውን ማሰማት ሲጀምሩ፣ ሽማግሌዎች የጠቡን ምንጭ ጊዜያዊነት ወይም ጥንካሬ ለመረዳት ሁለቱንም ወገኖች ‹‹እስኪ ከማሸማገላችን በፊት ጉዳዩን ነት ይንካው፤›› በማለት ይመልሷቸዋል፡፡

      ‹‹ነት›› ማለት፣ ብዙ በገጠር አካባቢ የሚኖር ሰው እንደአንሶላ የሚጠቀሙበት የለሰለሰ (የታረበ) የበሬና የላም ቆዳ ነው፡፡ ‹‹ነት ይንካው›› ሲባል ባልና ሚስት ጥልና ብሶታቸውን ከማሰማታቸውና ውሳኔ ከማሳለፋቸው በፊት አብረው በአንድ ነት ላይ ተኝተው አድረው በድጋሚ እንዲያጤኑት ለማድረግ ነው፡፡ በንዴት የተፈጠረ፣ በድንገት የተከሰተ ከሆነ ነቱ ላይ ይቀራል፡፡ የመረረና የከረረ ከሆነ አንድ ነት ላይ መተኛት ስለማይችሉም የችግሩን መጠን ለመረዳት ይቻላል፡፡

      የሩሲያዎች ሕገ መንግሥት ‹‹ነት ይንካው›› የሚለውን አካሔድ የተከተለ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አምርረው በ2/3ኛ ድምፅ ከወሰኑም በኋላ አምስት ዓመት ነት ማስነኪያ ወይም ማሰላሰያ ጊዜ ሰጥተዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛን ሕገ መንግሥት ስናየው አፍን ሞልቶ ለማሰላሰል፣ ‹‹ሽልም ከሆነ መግፋቱን ቂጣም ከሆነ መጥፋቱን›› ለማወቅ የሚያስችል ጊዜ እንዳልተሰጠው መረዳት ይቻላል፡፡ የፌደራሉ መንግሥት በሦስት ዓመት ጊዜ ሕዝበ ውሳኔ እንዲያስፈጽም፣ እንዳያጓትት የጊዜ ጣሪያ ከማስቀመጥ በዘለለ በወሩም ይሁን በዓመቱ ማዘጋጀትን አይከለክልም፡፡

ሕዝበ ውሳኔ

      የሕዝበ ውሳኔ ውጤት ላይ ተፅዕኖ የሚያሳርፉ ሁኔታዎችም ብዙ ናቸው፡፡ የጥያቄው ዓይነት ለምሳሌ ኤርትራ እንዳደረገችው ‹‹ነፃነት›› ወይስ ‹‹ባርነት›› ሊሆን ይችላል፡፡ መቼም ማንም ጤነኛ ሰው ‹‹ባርነትን›› ሊመርጥ አይችልም፡፡ ከዚህ አንፃር የሴንት ኪትስና ኔቪስ ጥሩ ተሞክሮ አላቸው ማለት ይቻላል፡፡ አማራጮቹ ለምን እንደተመረጡ የሚያሳይ ማብራሪያ ጭምር ውሳኔ ከመሰጠቱ ቢያንስ ዘጠና ቀናት ቀደም ብሎ ሕዝብ እንዲያውቃቸው ማድረግን ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ አድርገውታል፡፡ እንደ ኤርትራው ኃላፊነት የጎደለው አድራጎት ላለመፈጸም ነው፡፡

      በኢትዮጵያ የፌደራሉ መንግሥት ሕዝበ ውሳኔ አዘጋጅቶ ድምፅ ከሰጡት ውስጥ፣ ከግማሹ በአንድ ሰው ከፍ ያለ፣ ለመገንጠል ይሁንታውን ከሰጠ፣ ብሔሩ ከኢትዮጵያ ጋር የነበረው ጋብቻ ፈረሰ ማለት ነው፡፡ የሩሲያው ሁለት ጊዜ በሚከናወኑት ሕዝበ ውሳኔዎች በእያንዳንዳቸው ሕዝቡ ቢያንስ 2/3ኛው የድጋፍ ድምፅ ካልለገሰ በስተቀር መገንጠል አይቻልም፡፡ በኔቪስም 2/3ኛ የድጋፍ ድምፅ ማግኘት ግድ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት እ.ኤ.አ. በ1998 በኔቪስ የነበሩት የገዥው ፓርቲም ይሁን ተቃዋሚዎች መገንጠልን በመደገፍ በምክር ቤቱ በ2/3ኛ ድምፅ አሳልፈውት ኋላ ለሕዝቡ ሲቀርብ 61.7 በመቶ ብቻ ድጋፍ በማግኘቱና ሁለት ሦስተኛ ስላልሞላ የኔቪስ ሕዝብ ሳይገነጠል ቀርቷል፡፡ ከዚህ አንፃር አንቀጽ 39(4) የማሰላሰያ ጊዜ ካለመኖሩ በተጨማሪ እንደ ተራ ጉዳይ መለኪያውን ተራ የአብላጫ ድምፅ ሆኗል፡፡ በተራ አብላጫ ድምፅ እንዲህ አቅልሎ ማስቀመጥ ቢያንስ ሁለት መሠረታዊ ችግሮች አሉት፡፡

      ችግር ቁጥር አንድ፣ መገንጠሉን የሚወስኑት ከጠቅላላው የብሔሩ አባላት አናሳው ሊሆኑ መቻላቸው ነው፡፡ የብዙኃኑን ዕድል አናሳዎች እንዳሻቸው ሊያሽከረክሩት ይችላሉ፡፡ ድምፅ በሚሰጥበት ወቅት ለአካለ መጠን ያልደረሱ፣ የአዕምሮ ሕሙማን፣ በሕግ እንዳይመርጡ የተከለከሉ ሕዝቦች በሕዝበ ውሳኔው ተሳታፊ ስለማይሆኑ እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች በትንሹ የብሔሩን 20 በመቶ እንኳን ይሸፍናሉ ቢባል፣ ድምፅ የሚሰጠው ቀሪው 80 በመቶ  ይሆናል፡፡ ከዚህ ውስጥ በተራ አብላጫ ድምፅ ውሳኔው ሲሰጥ የሰማኒያው ግማሽ 40 በመቶ ስለሚሆን ዞሮ ዞሮ 40 በመቶን ከዘለለ መገንጠሉ ዕውን ሆነ ማለት ነው፡፡ ይህ መምረጥ የማይፈልገው፣ በተለያዩ ምክንያቶች ድምፅ መስጠት ያልቻለው ሲደማመርበት እየተመናመነ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡

      በኔቪስ ሕዝበ ውሳኔ ጊዜ ድምፅ ለመስጠት ተመዝግቦ ከነበረው ውስጥ መጨረሻ ላይ ድምፅ የሰጠው 58 በመቶ ብቻ ነበር፡፡ ተራ አብላጫ ቢሆን ኖሮ ኔቪስ ተገንጥላ ነበር፡፡ በካናዳም ኪውቤክ ልገንጠል ብላ ሕዝበ ውሳኔ ብታደርግም ውሎ አድሮ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዴሞክራሲ ማለት ተራ አብላጫ ድምፅ ማለት ብቻ እንዳልሆነና ለካናዳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይኼንን የሚያብራራ ሕግ እንዲወጣ አስተያየት ስለሰጠ ኪውቤክ ለመገንጠል ከፈለገች አንዱ ቅድመ ሁኔታ በሕዝበ ውሳኔ ወቅት መገንጠሉ በ2/3ኛ የድጋፍ ድምፅ መታጀብ እንዳለበት ሕግ አውጥቷል፡፡ ይህ እንግዲህ የብዙኃኑን ዕድል በተወሰነ መልኩ ከፍ ያለ ቁጥር ያለው ሕዝብ ቢደገፍ መልካም መሆኑን ስላመኑ ነው ማለት ይቻላል፡፡

      ችግር ቁጥር ሁለት፣ አንገነጠልም ባዮች ቢያሸንፉ በሌላ ጊዜ ለመገንጠል ሕዝበ ውሳኔ ሊኖር ሲችል እንገነጠላለን ባዮች ካሸነፉ ግን ድጋሚ ለመወሰን የሚኖር ዕድል የለም፡፡ ስለሆነም እዚህ ግባ በማይባል ቁጥር ተበልጠው መገንጠልን የተቃወሙ ሰዎች ‹‹ብዙኃን ይመውኡ›› የሚለው የዴሞክራሲ መርሕ ወደ ከፋ አፋኝነትና ጨፍላቂነት ስለሚቀየር፣ ቢያንስ ድጋሚ አቋማቸውን አጢነው እንዲወስኑ ዕድል ስለማይሰጥ ተራ አብላጫ ፍትሐዊነት ይጎድለዋል፡፡

      ለመገንጠል የሚደረግ ሕዝበ ውሳኔን በተመለከተ አራት ነጥቦችን እናንሳ፡፡ የመጀመሪያው ድምፅ መስጠት የሚችሉት መገንጠል የሚፈልግው ብሔር ባለበት ክልል ውስጥ የሚኖሩት የብሔሩ አባላት ብቻ ናቸው ወይስ በሌላ ክልሎችና አገሮችም ጭምር የሚኖሩትን ያካትታል? የሚለው ነው፡፡ በምርጫ ሕጉ የሚገዛ ከሆነ በአካባቢው ኗሪ መሆንን ይጠይቃል፡፡

      ሁለተኛው መገንጠሉን በሚፈልገው ብሔር ክልል ውስጥ ያሉ ሌሎች ብሔሮችና ብሔረሰቦች ሚናቸው ምንድን ነው? ለምሳሌ የአማራ ብሔር አሁን ያለውን ክልል ይዞ መገንጠል ቢፈልግ የአማራ ሕዝብ ምክር ቤት የሚባለው የክልሉ ምክር ቤት ነው፡፡ ነገር ግን የአማራ ክልል ምክር ቤት የአማራ፣ የአዊ፣ የኻምራ፣ የአርጎባና የኦሮሞ ሕዝብን ያቀፈ ምክር ቤት እንጂ የአማራ ሕዝብ ስላልሆነ እንዴት ሊወስን እንደሚችል ግልጽ አይደለም፡፡ የእነዚህ ብሔረሰቦች ተወካዮች ከተነሱ ምክር ቤቱ ጎዶሎ ነው የሚሆነው፡፡ ድምፅ የሚሰጡ ከሆነ በሌሎች መብት ውሳኔ ሰጭ እየሆኑ ነው ማለት ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር በአማራ፣ በትግራይና በሐረር በዋናነት የሚያጋጥም ሲሆን ኦሮሚያ፣ አፋርና የኢትዮጵያ ሶማሌም የብሔሩ አባላት ያልሆኑ የምክር ቤት አባላት ካሉ ድምፅ መስጠት ይችላሉ ወይም አይችሉም የሚለው ጥያቄ አስቸጋሪ ነው፡፡ ድምፅ የማይሰጡ ከሆነም ሌላ ችግር መውለዱ አልቀረም፡፡ ለአብነት የአማራ ሕዝብ መገንጠል ቢፈልግ በክልሉ ውስጥ የሚገኙት ብሔረሰቦች የአማራ ሕዝብ ውሳኔ ሲሰጥ ‘ቁልጭ፣ ቁልጭ’ እያሉ ውሳኔውን ከመጠበቅ ውጭ አማራጭም ተሳትፎም አይኖራቸውም፡፡ ምንም እንኳን የአማራ መገንጠል ወይንም አለመገንጠል ውጤት እነሱንም ጭምር የሚመለከትና ተፅዕኖ ያለው ቢሆንም ውሳኔው ውስጥ ተሳታፊ መሆን አይችሉም፡፡

      ሦስተኛው፣ መገንጠሉን በሚፈልገው ክልል ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ኗሪዎች ድምፅ የመስጠት ጉዳይና መገንጠሉ ከተፈጸመ በኋላ ስለሚኖራቸው ዕጣ ፋንታ የሚመለከት ነው፡፡ በሩሲያ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 72 በዋናነት ነፃ አገር የመመሥረት ወይም የመገንጠል መብት የታወቀላቸውም ለሪፐብሊኮቹ እንጂ ለብሔሮች አይደለም፡፡ ድምፅ የሚሰጡት በሪፐብሊኩ በቋሚነት የሚኖሩት ብቻ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን የመገንጠልን ጥያቄ ያቀረበው ብሔር አባላት  እንጂ ሌሎቹን የክልሉን ኗሪዎች አይመለከትም፡፡

      ከላይ የተነሱት ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ጭብጥ በተመለከተ የካናዳና የኪውቤክን ልምድ ማየቱ ጠቃሚ ነው፡፡ ኪውቤክ ልገንጠል ብላ ሕዝበ ውሳኔ አከናውና ለትንሽ ከግማሽ ከፍ ያለው ሕዝብ መገንጠልን ቢቃወምም፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ሲሰጥ በካናዳም ይሁን በዓለም አቀፍ ሕግ የተናጠል መገንጠል የሚባል መብት ስለሌለ ኪውቤክ ባሰኛት ጊዜ በተናጠል መገንጠል አትችልም፤ ከሌሎቹ ክልሎችና ከፌደራል መንግሥቱ ጋር መደራደር አለባት በማለቱ ይህንኑ የሚያጠናክር ሕግ አውጥታለች፡፡ የተናጠል መገንጠል እንደማይቻልም አስረግጣ ደንግጋለች፡፡ በኢትዮጵያም፣ ለብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተናጠል መገንጠል እንዲችሉ ሆኖ የተቀረጸ ቢሆንም ቢያንስ የሚገነጠለው ብሔር በሚያስተዳድረው ክልል ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚደራደሩበት ዕድል መመቻቸት አለበት፡፡

      ሦስተኛውን ጭብጥ በተመለከተ ካናዳ እንደ ፌዴራል መንግሥትነቷ ሕግ ስታወጣና ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ኪውቤክም ተጨማሪ ሕጎችን ማውጣት እንዳለባት አስተያየት ሰጥቶ ስለነበር እሷም በበኩሏ ብትገነጠል የእንግሊዝኛ ተናጋሪና ነባር ብሔሮችን መብት እንደምታከብር የሚገልጽ ሕግ ወዲያውኑ አውጥታለች፡፡

      የመጨረሻው ሕዝበ ውሳኔውን ከሚያስፈጽመው አካል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ሕዝበ ውሳኔ የሚያደራጀው የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡ ይህንና ሌሎች ምርጫዎችን ለማስፈጸም ደግሞ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የተቋቋመው ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ይኼው ተቋም ነው ሕዝበ ውሳኔውንም ሊያስፈጽም የሚችለው፡፡ ይህ ተቋም የቀሪዋ ኢትዮጵያ ተቋም ነው፡፡ የመራጮች ምዝገባ የሚያከናውነው፣ ታዛቢዎችን የሚያስመርጠው፣ ቅሬታም ቢኖር የሚመረምረው ይኼው ተቋም ነው፡፡ ለመገንጠል የሚፈልገው ብሔር በፍትሐዊነት ወይንም በእኩልነት የሚወከልበት ወይም በራሱ የሚያስፈጽምበት ሕገ መንግሥታዊ መዋቅርም አካሔድም የለም፡፡ በሴንት ኪትስና ኔቪስ፣ ኔቪስ ለመገንጠል ሕዝበ ውሳኔ ስታከናውን አስመራጮቹ ከላይ እንደተገለጸው በራሷ በኔቪስ ገዥ የሚሰየሙ እንጂ በፌደራል መንግሥቱ የሚቋቋም አስመራጭ አይደለም፡፡ ምርጫ ቦርድ ያው ነፃና ገለልተኛ ተቋም ነው ሊባል ቢችልም፣ የቄሳርን ድምፅ የሕዝብ ድምፅ ከማድረግ ላይቦዝን ይችላል፡፡ እንዲህ ሲሆን ያው ግጭት መፈጠሩ አይቀርም፡፡

 

ሥልጣን ማስረከብ

      የሥልጣን ርክክብና የንብረት ክፍፍል ከውሳኔ በኋላ የሚመጡ ሒደቶች ናቸው፡፡ መገንጠሉ ተመራጭ ከሆነ፣ በኢትዮጵያ ከሥልጣን ርክክብ በፊት የሚጠበቅ ምንም ዓይነት ጓዝ የለም፡፡ በሩሲያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱ፣ ሒደቶቹ በትክክል ስለመፈጸማቸው መርምሮ ካጸደቀ በኋላ ነው መገንጠሉ የሚጸናው፡፡ በኢትዮጵያ እንደዚህ ዓይነት ሥልጣን ለፌደራሉ መንግሥት አልተሰጠውም፡፡ እንግዲህ ይኼ የሕዝብ ድጋፍ ሲገኝ ነው፡፡ እዚህ ላይ አብሮ መታየት ያለበት የመገንጠል ጥያቄ በድጋሚ መነሳት የመቻሉ ወይም አለመቻሉ ነገር ነው፡፡

      አሁንም ወደ ቀድሞው የሩሲያ ሕገ መንግሥት ስናማትር ከአሥር ዓመት በኋላ ድጋሚ የመገንጠል ጥያቄ ማንሳት እንደሚቻል ተገልጿል፡፡ በአንድ ወቅት በተደረገ ድምፀ ውሳኔ ‹‹አንገነጠልም አብረን እንኖራለን›› ማለት ለዘለዓለም አንገነጠልም ማለት ላይሆን ይችላል፡፡ በሴንት ኪትስ እና ኔቪስ የመገንጠል መብት ያላት የኔቪስ ደሴት በመሆኗና የመገንጠል ሥርዓትን ሙሉ በሙሉ የምታስተዳድረው ራሷ በመሆኗ ድጋሚ ማንሳትን አይከለክላትም፡፡ በእኛም ሕገ መንግሥት የመገንጠል ሥነ ሥርዓት ሲደነገግ ይኼው ጉዳይ መካተት ነበረበት፡፡ አልበለዚያ ግን ግጭትንና ጦርነትን እንዲያስቀር የታሰበው መብት ዓላማውን አያሳካም፡፡ ወይም ደግሞ ገደብ ስለሌለው በየዓመቱ ወይም በተወሰኑ ወራት ልዩነት ድጋሚ የመገንጠል ጥያቄ ቢነሳ በተጠየቀ ቁጥር ሕዝበ ውሳኔ ሲደረግ ሊኖር ማለት ነው፡፡

የንብረት ክፍፍል

      የንብረት ክፍፍልን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ በሕግ በሚወሰነው መሠረት እንደሚፈጸም በመግለጽ አልፎታል፡፡ ብሔሮች ተገንጥለው አዲስ ሉዓላዊ አገር ሲመሠርቱ ልክ ባልና ሚስት ከተፋቱ በኋላ ንብረት እንደሚከፋፈሉት ሁሉ በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ሊከናወን ይችላል፡፡ ከመገንጠሉ በፊት ከተለያዩ ተቋማትና አገሮች የተወሰዱ ብድሮችና ሌሎች ዕዳዎች የክፍፍሉ አካል መሆን አለባቸው፡፡ በአንቀጽ 39(4)(ሠ) መሠረት ግንጠላ የሚከናወነው ‹‹በሕግ በሚወሰነው መሠረት የንብረት ክፍፍል ሲደረግ ነው፤›› በማለት ተደንግጓል፡፡ ይህን ሕግ ሊያወጣ የሚችለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባወጣውና ተገንጣዩ ብሔር እንደ ብሔር ሳይደራደርበት በወጣ ሕግ አማካይነት የንብረት ክፍፍል ይደረግ ቢባል ተቀባይነት ያለው አይመስልም፡፡ ሁለተኛው አተረጓጎም ዓለም አቀፍ ሕጎችም ያው ሕጎች በመሆናቸው የንብረት ክፍፍል የሚፈጸመው የኢትዮጵያ ፓርላማ ባወጣው ሳይሆን እነዚህን ሕጎች ለማመልከት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የዓለም አቀፉ ልምድ የሚያሳየውና የሚያረጋግጠውም ይኼንኑ ነው፡፡ ስለዚህ ንብረት ክፍፍሉ በዓለም አቀፉ ሕግ መሠረት እንጂ በኢትዮጵያ ሕግ ሊሆን አይችልም፡፡ መገንጠሉ ከተከናወነ በኋላ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት የሚዳኝ በኢትዮጵያ ሕግ ሊሆን አይችልም፡፡ በተገነጠለች አገር ላይ የቀድሞ እናት አገሯ ሕግ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡

      ሁለተኛው ነጥብ ‹‹ንብረት›› የሚለው ምንን ያመለክታል? የሚለው ነው፡፡ ንብረት የሚለው ዕዳን እንዲያካትት ተደርጎ አልተገለጸም፡፡ የዕዳ ክፍፍልን ኢትዮጵያ ወዳና ፈቅዳ የተወችው ይመስላል፡፡ እንደኤርትራ ጎጆ የማውጣት ልማዷን ለማስቀጠል ይሆን?

      የንብረት ክፍፍል በዓለም አቀፍ የአገሮች የአወራረስ ሕግ (State Succession) መሠረት የሚከናውን ነው፡፡ የአገሮች የአወራረስ ሕግን በተመለከተ በልማድ የዳበረና እነዚህን ልማዳዊ ሕግጋት አካትቶ የወጣ ‘የቬና ስምምነት’ በመባል የሚታወቅም አለ፡፡

የአገሮች የአወራረስ ሕግ ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፊል ከቅኝ ግዛት ነፃ ለወጡ፣ ለተበታተኑ (እንደ ሶቬየት ኅብረትና ዩጎዝላቪያ)፣ ለሚገነጠሉ፣ በጋራ ለሚዋሃዱ (እንደሁለቱ የመኖችና ጀርመኖች)፣ ለሚቀላቀሉ አገሮች (ሀዋይን አሜሪካ እንደቀላቀለቻት፣ ክሬሚያ ወደ ሩሲያ እንደፈረጠጠችው) ተፈጻሚ የሚሆን ሕግ ነው፡፡

      የአወራረስ ሕግ የቀድሞዋን አገር ዓለም አቀፋዊ ግንኙነትን የሚመለከቱ መብትና ግዴታዎችን ማን መውሰድ እንዳለበት መመርያዎች አሉት፡፡ ሶቪየት ኅብረት ስትፈራርስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በፀጥታው ምክር ቤት ቀድሞ የነበራትን ቋሚ መቀመጫ ማን ይውረስ? በሌሎች እንደ ዓለም አቀፎቹ የገንዘብ ተቋማት ውስጥ የነበረውን መብት ለማን ይሰጥ? የሚለውን ይሸፍናል፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያ ከኢትዮጵያ ቢገነጠል፣ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ ለኦሮሚያ ነው ወይስ ለቀሪዋ ኢትዮጵያ የሚሰጠው? እንደማለት ነው፡፡

      ሌላው ኢትዮጵያ የብዙ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ፈራሚ ናትና እነዚህ ስምምነቶች የሚመለከቱት ተገንጣዩን ነው ወይስ ኢትዮጵያን? ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ የንግድ ድርጅት አባል ብትሆን አባል ሆኖ የመቀጠሉ የማንኛቸው መብት ነው የሚሆነው? እንደዚህ ዓይነት ብዙ ጣጣዎች አሉ፡፡ በቅኝ ግዛት ዘመን የዳበረው መርሕ የፀዓዳ ሰሌዳ (Clean Slate) የሚባለው ነው፡፡ አገሮች ከዕዳ ንጹህና ጽዱ ሆነው ነፃ የመውጣት፣ ሀብቱን ለቅኝ ተገዥ፣ ዕዳውን ለቅኝ ገዥ የሚያደርግ መርሕ ነው፡፡ ቤልጅየም ከኔዘርላንድስ በ1830፣ ኩባ ከስፔን በ1898፣ ፓናማ ከኮሎምቢያ በ1903፣ ፊንላንድ ከሩሲያ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ሲለያዩ ወይም ሲገነጠሉ ይኼው የፀዓዳ ሰሌዳ መርሕ ነው የተተገበረው፡፡ ይህ መርሕ እያደገና እየተሻሻለ የሄደ እንጂ ለቅኝ ግዛት ብቻ ተፈጻሚ ሆኖ የቀረ አይደለም፡፡

      ንብረትን (ቅርሶችንም ጨምሮ) እና ዕዳን በተመለከተ እያደገ የመጣው መርሕ ግንጠላው የተከናወነበትና ተገንጣዩ በስምምነት እንዲከፋፈሉ የሚጠይቅ አካሄድ ነው፡፡ ዩጎዝላቪያ ስትበታተን የግልግል ኮሚሽኑ ይኼንኑ ነበር ሲያበረታታ የነበረው፡፡

      ለክፍፍል የሚቀርበው ዋናው የመንግሥት ወይም የሕዝብ ንብረት ነው፡፡ የመንግሥት ሀብት የቱና ምን እንደሆነ በአገር ውስጥ ሕግ ነው ሊታወቅ የሚችለው፡፡ የመንግሥት ንብረት የሚለው ለአገልግሎት መስጫ የተቋቋሙና የልማት ድርጅቶችንም ይጨምራል፡፡

      በተገንጣዩ ድንበር ውስጥ የሚገኙ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች የተገንጣዩ፣ ቀሪው ደግሞ ግንጠላው የተከናወነባት አገር ንብረት ሆኖ እንደሚቀጥል ነው ዓለም አቀፍ  ሕግ የሚያሳየው፡፡ አንድ አካባቢ ወይም በአንድ የብሔር ይዞታ ሥር ብቻ ብዙ ግንባታዎችንና የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን (ፋብሪካዎች፣ የኃይል ማመንጫዎች፣ ቢሮዎች ወዘተ) ማፍራት በግንጠላ ጊዜ ጉዳቱ ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ከሁለቱም ውጭ ያሉ ንብረቶችን ደግሞ፣ በተመጣጣኝ ሁኔታ ይከፋፈላሉ፡፡ ለሚንቀሳቀሱ ንብረቶችም ቢሆን መርሑ ያው ነው፡፡ አማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ የፌደራልም ይሁኑ የክልሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች፣ አማራ ቢገነጠል ይዞ ይገነጣል እንጂ እንዲመልስ አይገደድም፤ በያዙት መርጋት እንጂ!

      ቅርሶችን በተመለከተም ክፍፍል ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለምሳሌ አፋር ቢገነጠል፣ ሉሲ የቀሪዋ ኢትዮጵያ ሆና እንድትቀጥል ሳይሆን ለአፋር እንድትሰጥ ነው ሕጉ የሚጠይቀው፡፡

      የአገር ዕዳን በተመለከተ ከሀብት በበለጠ ሁኔታው ውስብስብ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ስም የተፈጸሙ ብድሮች ለተገንጣዩ ክልል ጥቅም የተደረጉ ቢሆን እንኳን፣ አበዳሪው አካል የተዋዋለው ከኢትዮጵያ ጋር በመሆኑ ዕዳውን አበዳሪው ሳይስማማ ወደሌላ ማስተላለፍ አይቻልም፡፡ የበርታ ብሔር ቢገነጠል ታላቁን የህዳሴ ግድብ ይዞ የሚገነጠል ስለሆነ ለእሱ ግንባታ ኢትዮጵያ የተበደረችውን ገንዘብ  (ዕዳውን)፣ ትሸከማለች፤ የቦንድ ሽያጩንም ትከፍላለች፤ አፋር ቢገነጠል ለተንዳሆና ለመታሃራ ስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ኢትዮጵያ የተበደረችው ገንዘብ ካለ አፋር ፋብሪካውን ይዞ ሲጓዝ ኢትዮጵያ ዕዳዋን ስትገፈግፍ ትኖራለች ማለት ነው፡፡

      የተለያዩ አገሮች ሲለያዩ ንብረታቸውንና ዕዳቸውን እንዳላቸው የሕዝብ ብዛት መጠን በስምምነት የተከፋፈሉም አሉ፡፡ ቼክ ከአጠቃላዩ ሀብት 2/3ኛ ስትወስድ ስሎቫኪያ ደግሞ እንደሕዝቧ 1/3ኛ ሲከፋፈሉ፤ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያም ወራሽ አገሮችም የተለያዩ ፐርሰንቶችን በመጠቀም ተከፋፍለዋል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...