በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 አብነት አደባባይ አካባቢ በመገንባት ላይ ያለ ሕንፃ አካል የሆነውን የመሠረት ጉድጓድ በመቆፈር ላይ ከነበሩ 14 የቀን ሠራተኞች አራቱ በናዳ ምክንያት ሕይወታቸው አለፈ፡፡ አስከሬናቸውን ለማግኘትም አምስት ሰዓታት ያህል ፈጅቷል፡፡
አደጋው የተከሰተው ማክሰኞ ኅዳር 4 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀኑ 7 ሰዓት ከ33 ደቂቃ አካባቢ ሲሆን፣ የቀን ሠራተኞቹም የባለ 20 ፎቅ ሕንፃ አካል የሆነና በግምት 10 ሜትር ያህል የሚርቅ ጉድጓድ ውስጥ ሆነው እየቆፈሩ ነበር፡፡
የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ እንደሚሉት፣ ለሕንፃው ግንባታ 32 የቀን ሠራተኞች ሲኖሩ 14ቱ በጉድጓድ ቁፋሮው ላይ ነበሩ፡፡ በሥራ ላይ እያሉ ከላይ ድንጋይ እየተናደ መምጣቱን ያዩ ስድስት ሠራተኞች ሮጠው ሲያመልጡ፣ አራቱ ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ተርፈዋል፡፡ አራቱ ግን የድንጋይ ናዳው ወርዶባቸው ከሥር ተቀብረው ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ከአማራ ክልል የመጡትና ዕድሜያቸው ከ21 እስከ 25 የሚገመተው ሟቾቹ በሙሉ ወንዶች ሲሆኑ፣ ሥራውን ከጀመሩም ገና ዘጠነኛ ቀናቸው ነበር ተብሏል፡፡
ከሐምሌ 2008 ዓ.ም. እስከ ታኅሳስ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ድረስ ከግንባታ ጋር በተያያዘ 21 ሰዎች መሞታቸውንና 24 መጎዳታቸውን፣ በ2008 በጀት ዓመት ደግሞ 27 ሞተው በ34 ላይ ጉዳት መድረሱን ያስታወሱት አቶ ንጋቱ፣ ሟቾቹ በሙሉ የቀን ሠራተኞች ናቸው ብለዋል፡፡
የቀን ሠራተኞች ጉልበት እንጂ ዕውቀቱ እንደሌላቸው በመጠቆም ሥራ ተቋራጮች የቀን ሠራተኞችን ደኅንነት ማስጠበቅ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ ሞትና የአካል ጉዳት እየተመዘገበ የሚገኘውም በመንግሥት፣ በግልና በድርጅት የግንባታ ፕሮጀክቶች ውስጥ መሆኑን አክለዋል፡፡