Friday, July 12, 2024

የአዲስ አበባው የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫና ውስብስብ ስንክሳሮች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር ሩዋንዳ ርዕሰ ከተማ ኪጋሊ 27ኛውን የአፍሪካ ኅብረትን ዓመታዊ የመንግሥታትና ርዕሰ ብሔሮችን ጉባዔ እንደ እ.ኤ.አ. ከሐምሌ 17 እስከ 18 ቀን 2016 ነበር ያዘጋጀችው፡፡ በወቅቱም ከሚጠበቁ ጉዳዮች ውስጥ ትልቁን ሥፍራ የያዘው ኅብረቱን ለቀጣይ አራት ዓመታት በዋና በሊቀመንበርነት ማን ሊረከበው እንደሚችል ነበር፡፡ በተለይም ከሁለቱ ቀናት ጉባዔ ቀደም ብሎ የመጀመሪያዎቹን አራት ዓመታት የሥራ ዘመናቸውን አጠናቀው የነበሩትና ለሁለተኛ ጊዜ ከመወዳደር ራሳቸውን ያገለሉት የወቅቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማን ለመተካት፣ ከሦስት አገሮች የተወከሉና ኅብረቱ ከተመሠረተበት እ.ኤ.አ. ከ1963 ጀምሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በርከት ያሉ ዕጩዎች መቅረባቸው ነበር፡፡

ይህ ደግሞ ለሊቀመንበርነቱ የሚደረገውን ፉክክር ከምንጊዜውም በላይ ተጠብቂ እንዳደረገው ተነግሮለታል፡፡ እንዲሁም ይኸው ምርጫ በወቅቱ የአኅጉሪቱ መሪዎች አብላጫውን ድምፅ ለየትኛው ዕጩ ሊለግሱ ይችላሉ የሚለው የበርካቶችን ቀልብ ገዝቷል፡፡ ለዚህም ተጨማሪ ምክንያት ሆኖ የሚነሳው ከኪጋሊው ጉባዔ አራት ዓመታት ቀደም ብሎ በነበረው ተመሳሳይ ምርጫ፣ የአሁኗ ሊቀመንበር ዶ/ር ድላሚኒ ከቀድሞው ሊቀመንበር ጋቦናዊው ዣን ፒንግ ጋር ከእልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ አሸናፊ ሆነው ወደ መንበሩ መምጣታቸውም እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በዕጩነትም ቀርበው ዕጣ ፈንታቸው በኪጋሊ ይወሰናል ተብሎ ቀርበው የነበሩትም የቦትስዋና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶ/ር ፔሎኖሚ ቬንሰን ሞይታይ ከደቡባዊ አፍሪካ የልማት ትብብር አገሮችን (ሳድክ)፣ ኡጋንዳዊቷ (ከፖለቲካዊ ሚናቸው ይልቅ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት የረጅም ዓመታት ልምድ ያካበቱት) ዶ/ር ስፔሺዮዛ ንያይጋጋ ዋንዲራ ካዚብዌ የምሥራቅ አፍሪካን ማኅበረሰብ አገሮችን በመወከል፣ እንዲሁም የኢኳቶሪያል ጊኒ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የምዕራባዊ አፍሪካ የኢኮኖሚክ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) አገሮችን የወከሉት አጋፒቶ ምባ ሞኩይ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ጉባዔው የተጠናቀቀው የሦስቱን ዕጩዎች አሸናፊ ሳይለይ ነበር በይደር በሚቀጥለው ወር በአዲስ አበባ ለሚዘጋጀው ጉባዔ የተላለፈው፡፡ ከሦስቱ አንዱ ዕጩ አሸናፊ የሚያደርገውን የ54ቱን አባል አገሮች መሪዎች ድምፅ ቢያንስ የ2/3ኛውን ድምፅ ማግኘት ይጠበቅባቸው የነበረ በመሆኑ ነው፡፡

የኅብረቱ መዋቅራዊ ሥርዓት

እ.ኤ.አ. ሐምሌ 9 ቀን 2002 የቀድሞው አፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) ወደ አፍሪካ ኅብረት ሲቀየር፣ የኅብረቱ የመጨረሻ የውሳኔ ሰጪነት ሥልጣን ያለው የአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ በመባል የሚታወቀው አካል የሁሉንም አባል አገሮች ርዕሳነ ብሔሮችና መንግሥታት የተካተቱበት ነበር፡፡ የዚህ ጉባዔ ሊቀመንበር ከእነዚሁ የአባል አገሮች መሪዎች በዙር ለአንድ ዓመት የሚመረጥ ቢሆንም፣ ሚናውም የኅብረቱ ስማዊ ሥልጣን እንዳለው ነው የሚታመነው፡፡ ይህ ጉባዔ የወቅቱ ሊቀመንበር በሆኑት የቻድ ፕሬዚዳንት ኢድሪስ ዴቢ የሚመራ ሲሆን፣ በመጪው ጥር ወር ከኅብረቱ የመሪዎች 28ኛ ጉባዔ በኋላ ይጠናቀቃል፡፡ የአፍሪካ ኅብረትን በዋና ጸሐፊነት የሚያስተዳድረውና በተዋረድ ሁለተኛው አካል የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሆኖ፣ በአዲስ አበባ መቀመጫውን ያደረገ ነው፡፡ የኮሚሽኑም ዋና ሊቀመንበር በመሆን በኅብረቱ የበላይ ውሳኔ ሰጪው ጉባዔ ለአራት ዓመታት የሥራ ዘመን የሚመረጥ ነው፡፡ ዋና ተግባሩን በተመለከተም የኅብረቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ የኮሚሽኑ ሕጋዊ ወኪልና የሒሳብ ሹምነትን ያጠቃልላል፡፡ ተጠሪነቱም ቢሆን በቀጥታ ለአፍሪካ ኅብረት አስፈጻሚ ካውንስል (ምክር ቤት) ይሆናል፡፡

የሥራ ዘመናቸው ባለፈው ዓመት የተጠናቀቀው ተሰናባቿ ሊቀመንበር የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ የአገር ውስጥ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ድላሚኒ ዙማ ናቸው፡፡ ምክትላቸው ደግሞ ኬንያዊው ኤራስተስ ምዌንቻ ሲሆኑ፣ በኅብረቱ የአሠራር ሥርዓት መሠረት የእሳቸውም የሥራ ዘመን ከሊቀመንበሯ እኩል ተጠናቆ ለአዲሱ ተመራጭ ምክትል ሊቀመንበር በማስረከብ ይሰናበታሉ፡፡

እንደሚታወቀው የኮሚሽኑን ሊቀመንበርነት ለተሿሚው ግለሰብ ሊያስገኝ የሚችለው ዝናና አኅጉራዊ ዕውቅና ብቻ ሳይሆን ወክለው ለመጡበት አገርና አካባቢያዊ ቀጣና የሚያጎናጽፈው አስተዋጽኦ ጉልህ ተደርጎ ስለሚቆጠር ምርጫው ትልቅ ሥፍራ ሊሰጠው ችሏል፡፡ ይህ ደግሞ የአዲስ አበባውን የመሪዎቹን ጉባዔ ከፍ ባለ ጉጉት እንዲጠበቅ ከወዲሁ ማድረግ ችሏል፡፡ ሌላው ምክንያት በ27ኛው ጉባዔ ላይ ቀርበው በነበሩት ሦስት ዕጩዎች ላይ ሦስት ዕጩዎች ተጨምረው ፉክክሩ ወደ ስድስት ቢያድግም የኡጋንዳዋ ዕጩ ዶ/ር ካዚምብዌ ከዕጩነት ራሳቸውን በማግለላቸው፣ አምስት ዕጩዎች እየተፎካከሩ ነው፡፡

ከእነዚህም ውስጥ በቀዳሚው ያልተሳካ ምርጫ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበርን ወክለው በዕጩነት የቀረቡትን ዶ/ር ካዚምብዌን ተክተው የቀጣናው ሌላ ዕጩ ሆነው ብቅ ያሉት ኬንያዊቷ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የ55 ዓመቷ አሚና መሐመድ አዲስ ክስተት በመሆን ብቅ ብለዋል፡፡ እንዲሁም የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ልዩ ልዑክ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት ሴኔጋሊያዊው አብዱላዬ ባቲሊ ለኮሚሽኑ ሊቀመንበርት አራተኛው ዕጩ ሆነው በቅርቡ ተቀላቅለዋል፡፡ ነገር ግን ከዕጩዎቹ ለየት ባለ የፖለቲካ ማንነታቸው አምስተኛው ዕጩ ሆነው የቀረቡት ቻዳዊው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ ሙሳ ፋኪ መሐማት አንዱ ክስተት ሆነዋል፡፡ የምርጫ ፉክክሩ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ቀስ በቀስ ወደ ጋለና የከረረ ወደሚመስል ደረጃ መድረሱን የሚያሳዩ ፍንጮች መታየት ጀምረዋል፡፡

ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ ብቻ የቀረው ምርጫም፣ የአፍሪካ ኅብረት በታሪኩ ካደረጋቸው ምርጫዎች በተለየ ሁኔታ የፉክክሩ ግለት ከመሟሟቁ ባሻገር፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ዕጩዎች በይፋ በሕዝብ ፊት ክርክር ማድረጋቸው ነው፡፡ ቢመረጡ ምን ምን ሊያከናውኑና ሊያሻሽሉ የሚችሉ አጀንዳቸውን እንዲገልጹ መደረጉ መጪውን ምርጫ ቀልብ ሳቢ አድርጎታል፡፡ ዓርብ ኅዳር 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ዕጩዎቹ የመጀመሪያቸውን ክርክር ሲያደርጉ ቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ሲያገች ኅብረቱ በራሱ ድረ ገጽ፣ ማኅበራዊ ገጾችና በቀጥታ ሥርጭት ለአፍሪካዊያን አሠራጭቷል፡፡

ለጎስቋላዋ አኅጉር ያላቸው ህልም

ለቻይናው የሚዲያ ተቋም ሲሲቲቪ በወኪል ጋዜጠኝነት በማገልገል ላይ በሚገኘው ግሩም ጫላና ባልደረባው አወያይነት (Moderators) ዓርብ ምሽት የመጀመሪያውን ክርክር ያካሄዱት አምስቱ ዕጩዎች፣ ከተመረጡ ለአኅጉሪቱ ሊሠሩ የሚችሉትን ዕቅድ በተጨማሪ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች መልሶቻቸውን ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን ከሁሉም ዕጩዎች መደመጥ እንደተቻለው በአብዛኛው ጉዳዮች ባሏቸው ዕይታዎች ላይ ከመከራከር ይልቅ፣ በቀጥታ ለታዳሚዎቻቸው ሐሳባቸውን ሲገልጹ አምሽተዋል፡፡ ከታዳሚዎች ጋር በወሳኝና በአንገብጋቢ አኅጉራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ስምምነት ያላቸው ይመስል ነበር፡፡

ለአብነትም ያህል በወጣቶች ጉዳይ ሁሉም ዕጩዎች ያላቸውን ዕይታና ሊሠሩ በሚገቡዋቸው ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አቋም መጋራታቸው ተስተውሏል፡፡ ‹‹በወጣቶቻችን ላይ የግድ ማንኛውንም መዋዕለ ንዋይ ሆነ ሌላ አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ ልናፈስ ይገባል… በተጨማሪም በአኅጉራችን ባሉ ቦታዎች ሁሉ ግጭቶችን ለመፍታት ወጣቶች ቦታ ተሰጥቷቸው ተሳትፏቸውን ልናረጋግጥ ይገባናል…›› በማለት ነበር የኬንያዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሚና መሐመድ የገለጹት፡፡ ሴኔጋላዊው ባቲሊ በበኩላቸው፣ ከሥራ አጥነት ጋር ተያይዞ ያለውን የወጣቶች ችግር ለመቅረፍ በአኅጉሪቱ መጠነ ሰፊ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በክርክር ሥነ ሥርዓት ወቅት ሌላው የተነሳው የንግድ እንቅስቃሴን ወደላቀ ደረጃ ማሳደግና በአባል አገሮች መካከል ውህደትን የማጠናከር ጉዳይ ሌላው የመከራከሪያ አጀንዳ ነበር፡፡ ‹‹እኔ ከተመረጥኩ አባል አገሮች ቪዛን በተመለከተ ያሉዋቸውን ሕጎችን እንዲከልሱ እተጋለሁ፡፡ ማንኛውም ነገር ከቪዛ በኋላ ነው የሚመጣው፤›› በማለት ዕቅዳቸውን የገለጹት ቦትስዋናዊዋ ዕጩ ቬንሰን ሞይታይ ናቸው፡፡

የቻድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሳ ፋኪም በተመሳሳይ አጀንዳ ያላቸውን ዕቅድ ባስረዱበት ወቅት፣ ‹‹ዛሬም ድረስ ነፃነታችን ከተረጋገጠ ከ60 ዓመታት በኋላ ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ሥፍራ ያለምንም ችግር (ያለምንም ቪዛ) መሸጋገር የማንችልበትን ሁኔታ ይዘን ልንቀጥል አይገባንም፡፡ የፈለገ ዘመዶቹ ወይም የቤተሰብ አባላት ወደሚገኙበት ሥፍራ ያለ ገደብ እንዲንቀሳቀስ የሚደረግበትን ሁኔታ ለማምጣት እሠራለሁ፤›› ሲሉ ነበር ያስረዱት፡፡

በተጨማሪም አምስቱ ተፎካካሪ ዕጩዎች ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ አቋም ያሰሙበት ሌላኛው ፍሬ ነገር፣ አባል አገሮች ኅብረቱ ሥራውን ለማከናወን የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ድጋፍ በተመለከተ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እያሳዩ ባለመሆናቸው፣ ከአኅጉሩ ውጪ በሚገኝ ገንዘብና ዕርዳታ ላይ መንጠላጠሉን ያሳዩበት ጉዳይ ሆኖ ተስተውሏል፡፡

‹‹ይህ ትልቅ ቅሌት ነው፡፡ አፍሪካ ሁሉም ነገር አላት፡፡ አሁን የሚያስፈልገው በጎ ፈቃደኝነት ወይም ቅንነት ብቻ ነው፤›› በማለት አፍሪካ ራሷን መርዳት የምትችልበት ሀብት እጥረት እንደሌለባት ጨምረው ያስረዱት ሙሳ ፋኪ ነበሩ፡፡

ሴኔጋላዊው ባቲሊ በበኩላቸው፣ ‹‹አፍሪካ አኅጉራችንን በተመለከተ ሁላችንም ሞራላዊ ግዴታችን ልንወጣ የሚገባን ትክክለኛው ጊዜ ላይ ነን፤›› ብለዋል፡፡

ባህል ሆኖ የቆየው የባዕድ ልሳን ተፅዕኖ

የዘንድሮውን ምርጫ ከቀደሙት ጊዜያት የተለየ ገጽታ ያላበሰው በተሳታፊ ተፎካካሪ ዕጩዎች የቁጥር መብዛት ብቻ ሳይሆን፣ የዕጩዎች ስብጥር ለቦታው መሥፈርት ብቃት፣ የትምህርት ደረጃና ልምድ የገዘፈ ክብደት መሰጠቱ ጎልቶ እየታየ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በኅብረቱም ታሪክ ሆነ ቀደም ባለው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (አአድ) ታሪክ ለሊቀመንበርነቱ ቦታ እንደ ቀዳሚ መመዘኛ ወይም ባህል ተደርጎ የቆየው፣ አባል አገሮችን በሚናገሩት ቋንቋ መሠረት አድርጎ በፈረቃ ከሁለት ቀጣናዎች የመምረጥ ባህል ነበር፡፡ በተለይ የአንግሎፎንና የፍራንኮፎን (እንግሊዝኛ ተናጋሪና ፈረንሣይኛ ተናጋሪ) የተባሉ ሁለት ጎራዎችን መሠረት ያደረገ ምርጫ ነበር፡፡ በዘንድሮው ምርጫ የቀረቡት ዕጩዎች በአንፃሩ ከሁለቱ ጎራዎች በተጨማሪ ሌሎች ቋንቋዎች (ዓረቢኛና ስፓኒሽ) ተናጋሪዎች ተካተውበት በመቅረባቸው፣ ልማዳዊውን የመምረጫ መሥፈርት በማስቀረት የተሳታፊ ግለሰቦች ብቃትና ልምድ ወይም ልሂቅነትን (Merit Based) ያደረገ ምርጫ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምት ተሰጥቶታል፡፡ በእርግጥ ይህ ግምት እውነት ከሆነ በበጎ ሁኔታ ቢታይም፣ ለሌሎች ግን ብዙም እየተዋጣላቸው አይመስልም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ለምርጫው ውጤት ብቸኛ ወሳኙ የአባል አገሮች መሪዎች ብቻ መሆናቸው ይጠቀሳል፡፡

ኬንያዊቷ አሚና መሐመድና ቦትስዋናዊው ዶ/ር ቬሴንት ሞይታይ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ጎራውን ሲወክሉ፣ ሴኔጋላዊው ባቲሊ የፈረንሣይኛ ተናጋሪውን በመወከል ለመመረጥ ዘመቻውን የተቀላቀሉ ናቸው፡፡ ሌላኛው ዕጩ የኢኳቶሪያል ጊኒው ሞኩይ ከምዕራቡ ቀጣና ቢገኙም የስፓኒሽ ተናጋሪ ናቸው፡፡ አምስተኛው ዕጩ ቻዳዊው ፋኪ ፈረንሣይኛና ዓረቢኛ ተናጋሪ ናቸው፡፡ የዕጩዎች ቁጥር መብዛትና የቋንቋ ስብጥራቸው እ.ኤ.አ. ጥር 31 ቀን 2017 ለሚደረገው ምርጫ የአባል አገሮች መሪዎችን ከቀጣናዊ ወገንተኝነት ይልቅ፣ ለዕጩ ግለሰቦች ብቃትና ልሂቅነት ትኩረት ለመስጠት ያስገድዳቸዋል የሚለው መላምት እያደገ መጥቷል፡፡

‹‹ብልጥ ልጅ እየበላ…›› የሞሮኮ ዳግም አመጣጥ

የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የሥራ ዘመን ለአራት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን፣ ለሁለተኛ ጊዜ መወዳደር ይችላል፡፡ ዶ/ር ድላሚኒ ዙማ በራሳቸው ፈቃድ ለሁለተኛ ጊዜ መወዳደሩን ባለመፈለጋቸው ቢወጡም፣ በኅብረቱ ትልቅ ተፅዕኖ አላቸው ከሚባሉት አንዷ የሆነችው አገራቸው ደቡብ አፍሪካ ዕድሉን ጎረቤታቸውና የሳድክ አባል ለሆነችው ቦትስዋናዊ ዕጩ ድጋፏን በይፋ ለመስጠት የቀደማት አልነበረም፡፡ ይህም ደግሞ በኪጋሊው ጉባዔ ታይቶ የነበረ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ቦትስዋናዊዋ ዶ/ር ሞይታይ ከአብላጫው 2/3ኛ ድምፅ በጥቂት ዝቅ ያለ ውጤት ቢያገኙም፣ ከሦስቱ ተወዳዳሪዎች ግን ከፍተኛ ድምፅ አስመዝግበው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ይህ ደግሞ በቀጣዩ የአዲስ አበባ ጉባዔ እኚሁ ዕጩ የማሸነፍ ዕድላቸው የተሻለ ሊሆን እንደሚችል ከኪጋሊው ጉባዔ በኋላ ተገምቶም የነበረ ቢሆንም፣ የኋላ ኋላ ግን የኬንያዊቷ አሚና መሐመድ ወደ ፉክክሩ መቀላቀል የጉባዔውን ተጠባቂነት ከፍ አድርጎታል፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች በድጋሚ የሚጠበቀውን የአብላጫ ድምፅ በዕጩዎች ማሟላት አስቸጋሪ እንዳይሆንና ድጋሚ ምርጫው ወደ ተጨማሪ ዙሮች እንዳይሸጋገርም እያሰጋቸው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዶ/ር ድላሚኒ ዙማ ለተጨማሪ ጊዜ በቢሮአቸው እንዲቆዩ የኮሚሽኑ አስፈጻሚ ጉባዔ ሊጠይቃቸው ይችላል፡፡ አለበለዚያ ጊዜያዊ የሽግግር ሊቀመንበር ወደመምረጡ ፊቱን ሊያዞር ይችላል፡፡

ወትሮም ምርጫው የአባል አገሮች መሪዎችን ሽኩቻ የሚመስል ክርክር ውስጥ የሚከታቸው ሲሆን፣ እንደየመጡበት ቀጣና የየራሳቸውን ቋንቋ ተናጋሪ ዕጩዎችን ለማስመረጥ ፍጭት ውስጥ ሲገቡ ነበር፡፡ ምናልባትም ይህ ዓይነቱ ሽኩቻ ሌላ ዓይነት ይዘው ያለው የአቋም ልዩነት ሊፈጥር ይችላል የሚል እምነት ያሳደረ አዲስ ጉዳይ ብቅ ብሏል፡፡ ይህም ከ32 ዓመታት መገለል በኋላ ዓረባዊቷ ሞሮኮ ወደ አባልነቷ ለመቀላቀል በእንቅስቃሴ ላይ መሆኗ ነው፡፡

ሞሮኮ ለሕዝባዊት ሰሃራዊ ዓረብ ዕውቅና በመስጠቱ ሳቢያ እ.ኤ.አ. በ1984 ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባልነት ረግጣ በመውጣት ተቃውሞዋን ከውጭ ሆና ስታስተጋባ መቆየቷ ይታወሳል፡፡ እስካሁንም ድረስ ሰሃራዊ ዓረብን እንደ ግዛቷ በመቁጠር በአኅጉራዊው ተቋሙም ሆነ በሌሎች የተሰጣትን ዕውቅና ለማስቀልበስ አቋሟን እንዳፀናች ነው፡፡ ነገር ግን ከሦስት አሠርት ዓመት መገለል በኋላ አሁን ወደ አፍሪካ ኅብረትነት ወደተቀየረው ተቋም በመመለስ፣ ከውስጥ ሆኜ እታገላለሁ በሚል አዲስ የአቋም ለውጥ ‹‹ሕፃን ልጅ እየበላ ያለቅሳል›› ዓይነት ስትራቴጂ ይዛ ነው ብቅ ያለችው ሲሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡

የድጋሚ አባልነት ጥያቄዋም በአዲስ አበባው ጉባዔ ተቀባይነት አግኝቶ አባል አገሮች እንኳን ደህና ለቤትሽ አበቃሽ ብለው እንደሚቀበሏት ይጠበቃል፡፡ ሞቅ ላለው አቀባበል ደግሞ የሞሮኮዋ ንጉሥ መሐመድ ስድስተኛ የደለበ የገንዘብ ካዝና ትልቁ ሚስጥር ሊሆን እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ ንጉሡም ቢሆኑ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኅብረቱ ተፅዕኖ አላቸው የሚባሉ አገሮችን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች መሪዎችን በስልክ ሲያባብሉ መቆየታቸው ይነገራል፡፡ ወደ ኅብረቱ በሙሉ ቀልብ መመለሳቸውን እንደማሳያ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አጋርነታቸውን ለማሳየት የንግድና የኢንቨስትመንት ስምምነቶች ማድረግ ጀምረዋል፡፡ ለአብነትም ያህል 3.7 ቢሊዮን ዶላር የሚፈስበት የማዳበሪያ ፋብሪካ በኢትዮጵያ ለመገንባት የተደረገው ስምምነት አንድ ማሳያ ነው፡፡ እንዲሁም ከሩዋንዳ መንግሥት ጋር 18 ያህል ስምምነቶች ተደርገዋል፡፡  

መቀመጫውን ጆሃንስበርግ ያደረገው ኢንስቲትዩት ኦፍ ሴኩሪቲ ስተዲ (አይኤስኤስ) የተባለው ተቋም ባቀረበው ጥልቅ ሪፖርት የሞሮኮን የመመለስ ፍላጎት አስመልክቶ ባሳተመው ትንታኔ፣ ‹‹አስደሳች የመልሶ መቀላቀልና የምዕራብ ሰሃራዊን ዕውቅና ለማስነሳት ያለሙ ጥንድ ስትራቴጂዎች›› ይዛ መመለሷን ገልጿል፡፡ ሞሮኮ በፈረንሣይኛ ተናጋሪዎችና በመካከለኛው የአፍሪካ አገሮች እንደ አለት የጠነከረ ድጋፍ እንዳላት የሚገልጸው አይኤስኤስ፣ የደቡብ አፍሪካዊቷ ዶ/ር ድላሚኑ ዙማ ከኅብረቱ ሊቀመንበርነት መነሳት አጥብቃ እንደምትፈልገውም ይገልጻል፡፡ በተለይ ዶ/ር ዙማ ሞሮኮ ከሌሎች አገሮች ጋር መልካም ግንኙነት እንዳይኖራት ፍላጎት አላቸው የሚል እምነትና በአገሮች ተቀባይነት እንዳይኖራት ተፅዕኖ ያደርጋሉ የሚል ድምዳሜ መኖሩን ያብራራል፡፡

ይህ ደግሞ ሚዛን የሚደፋ ሀቅ ከሆነ ዶ/ር ዙማ ከአገሮች ጋር በተለይም ከደቡብ አፍሪካ፣ ከዚምባቡዌና ከአልጄሪያ ጋር በመጣመር የሞሮኮን የመመለስ ጥያቄ ውድቅ ለማድረግ፣ ወይም የመመለሻ በሩን ዝግ ሆኖ እንዲቆይ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል የሚል ግምት አሰጥቶታል፡፡ በተጨማሪ ሞሮኮ ተመልሳ የምዕራብ ሰሃራዊን ዕውቅና በማስነሳት ከአባልነት የማስወገድ ህልሟ እውን እንዳይሆን አድርጓል የሚል አንድምታ እንዳለው የአይኤስኤስ ትንታኔ ያብራራል፡፡ በኪጋሊው ጉባዔ በተለይ የምዕራብ አፍሪካ ፈረንሣይኛ ተናጋሪ አገሮች ለቦትስዋናዋ ዶ/ር ቬንሰን ሞይታይ ድምፅ ከመስጠት ይልቅ በድምፀ ተአቅቦ ለማለፍ መወሰናቸውን አይኤስኤስ አመልክቷል፡፡ በመጪው ጉባዔ ግን ለቦትስዋናዋ ዕጩ ድምፃቸውን የነፈጉት የምዕራብ አፍሪካ አገሮች አዲስ ሆነው ለሚቀርቡት ዕጩ ሴኔጋላዊው ባቲሊ ድጋፋቸውን እንደሚቸሩ የጥናት ተቋሙ ግምቱን አስቀምጧል፡፡ ሴኔጋልም ብትሆን ለሞሮኮ ወደ ኅብረቱ መመለስ ስትታትር የቆችና የምዕራባዊ ሰሃራዊን ከኅብረቱ መወገድ የራሷን ቅስቀሳ ስታደርግ መቆየቷንም አውስቷል፡፡

ይሁን እንጂ በሌላ በኩል ኬንያዊቷ አሚና መሐመድና አገራቸው የሞሮኮን መመለስ ደጋፊ እንደሆነች ይኸው ተቋም ይገልጻል፡፡ ይህ እውነታ ደግሞ ምናልባትም አሚና እንግሊዝኛ ተናጋሪ ከሆኑ አገሮች ውስጥ የደቡብ አፍሪካ፣ የዚምባቡዌንና የአልጄሪያን ድጋፍ በምርጫው ወቅት ላያገኙ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል፡፡ በተጨማሪም የአሚና በዕጩነት መቅረብ የሞሮኮ ደጋፊ የሆኑ አገሮችን ድምፅ የመስጠት ፍላጎት ለሁለት ሊከፍለው እንደሚችል፣ ለባቲሊ ሊሆን የሚችለውን ድምፅ በመቀነስ ለቦትስዋናዋ ዶ/ር ቪሴንት ሞይታይ የዕድል በር የሚከፍት አጋጣሚ እንደሚፈጥር ፍንጭ ይሰጣል የሚልም እምነት እንዳለው የጥናት ተቋሙ አመልክቷል፡፡

ከዘ ሔግ የሚመጣው ሌላው ፈተና

ለአዲስ አበባው ጉባዔ መሪዎቹ በምርጫውም ሆነ በሌሎች ተያያዥ አኅጉራዊ ጉዳዮች በተቀራረበ አቋም ሆነ የጋራ ውሳኔ ላይ እንዳይደርሱ፣ አይሲሲ የተባለው ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ጉዳይ ተጠባቂ መሆኑን ሌሎች ማሳያዎች ሊነሱ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የዓርብ ዕለቱ የዕጩዎች ክርክር ከመዘጋጀቱ በፊት በነበረ የቅድመ ክርክር ዝግጅት ወቅት የተፈጠረ አንድ ዓብይ ክስተት እንደነበረ ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡ ለዕጩዎች ለማቅረብ ታስበው ከነበሩ የውይይት አጀንዳዎች መካከል የአይሲሲ ጉዳይ መነሳቱ፣ በራሱ ከዋናው የክርክሩ ዕለት በፊት አወዛጋቢ ሆኖም ነበር፡፡ በተለይም ኬንያዊቷ ዕጩ አሚና ከአይሲሲ አባልነት የመውጣት ጉዳይን የተመለከተ አጀንዳ የሚነሳ ከሆነ፣ ከክርክሩ ራሳቸውን ሊያገሉ እንደሚችሉ አስፈራርተው እንደነበር ከናይሮቢ የወጡ መረጃዎች አመልክተው ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ደግሞ ቀድሞ ክርክሩን ለመምራት ተቀጥራ የነበረችውን ደቡብ አፍሪካዊ ጋዜጠኛ ካሪማ ብሮውንን ከአወያይነት ሚና ውጪ እንደሆነች ጋዜጠኛዋ ከሳምንት በፊት ገልጻለች፡፡ ‹‹ለምን እንዳስቀሩኝ እንኳ ማብራሪያ አልተሰጠኝም፤›› ያለችው ጋዜጠኛዋ፣ ‹‹ቀደም ብለን ልናነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎች አጠቃላይ ሰብዓዊ መብቶችን የሚመለከቱ ከመሆናቸው ጋር በተያያዘ ነበር፡፡ የአይሲሲን አጀንዳ ለማንሳትም አቅደን ነበረ፤›› በማለት ገልጻለች፡፡

ኬንያ እ.ኤ.አ. ከ2007 ድኅረ ምርጫና በቀጠለው ብጥብጥ ከአንድ ሺሕ በላይ ኬንያውያን ተገድለው ከነበረበት ሁኔታ ጋር፣ የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታና ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ድረስ ለመቅረብ መገደዳቸው ይታወሳል፡፡ እንዲሁም በአይሲሲ የእስር ማዘዣ የተቆረጠባቸው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር ከአንድ ዓመት በፊት ደቡብ አፍሪካን በጎበኙበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ አሳልፈው ከመስጠት ይልቅ ተፈላጊውን ‹‹ወንጀለኛ›› መሪ ወደ ካርቱም አስመልጠዋቸዋል የሚል ውዝግብ ተቀስቅሶ ደቡብ አፍሪካ ከአይሲሲ አባልነት ለመውጣት ሒደቱን ጀምራለች፡፡

የኬንያ ፕሬዚዳንትና ምክትላቸው ላይ ተመሥርቶ የነበረው ክስ በኋላ እንዲቀር የተደረገ ቢሆንም፣ የኬንያ መንግሥት የአፍሪካ አገሮች ከሮሙ ስምምነት አባልነት እንዲወጡ መወትወቱን ቀጥሎበታል፡፡ ደቡብ አፍሪካም የኬንያን ዕርምጃ አጥብቃ መደገፏን በጉልህ እያሳየች ትገኛለች፡፡ እንዲሁም ከኬንያም ሆነ ከሱዳን ጋር የተጠበቀ ግንኙነትና ወዳጅነት ያላት ኢትዮጵያም ብትሆን የሮሙ ስምምነት ፈራሚ ባትሆንም፣ የፀረ አይሲሲ አቋምን በግምባር ቀደምትነት ከሚያራምዱ አገሮች አንዷ ነች፡፡ ይህንኑም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ይህንን በተለያዩ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች በግልጽ ያራምዱ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከእሳቸውም ሕልፈት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ገና በጠዋቱ ወደ ሥልጣን መንበሩ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ ይህንኑ ተመሳሳይ አቋም አጠናክረው ቀጥለውበታል፡፡ ይልቁንም፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ በአፍሪካ ላይ ብቻ ለይቶ ያነጣጠረና የዘረኝነት ሴራ እየፈጸመ ነው፤›› በማለት ትችት እ.ኤ.አ. በ2013 በአፍሪካ ኅብረት ጉባዔ ላይ ማቅረባቸው አይዘነጋም፡፡    

በዚህም ጉዳይ መጪው ጉባዔ የምርጫ ተግባሩን በቀላሉ ለማከናወን ያዳግተዋል የሚል ግምት ከወዲሁ እየተሰጠው ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ ከአይሲሲ ለመውጣት መደበኛ ሒደት የጀመሩት ደቡብ አፍሪካ፣ ቡሩንዲና ጋምቢያ ናቸው፡፡ ነገር ግን ምንም እንኳ የፀረ አይሲሲ የዘመቻ ጩኸት ጎልቶ እየተሰማ ቢመጣም፣ በአኅጉሪቷ እየታየ ያለው ገጽታ ግን እየተወሳሰበ ነው የሚሉ ተንታኞች ይደመጣሉ፡፡ ለአብነትም ያህል በጥቅምት ወር በዘ ሔግ በተስተናገደው 15ኛው ‹‹አሴምብሊ ኦፍ ስቴት ፓርቲስ›› የአይሲሲ አባል አገሮች ጉባዔ ለፍርድ ቤቱ ድጋፋቸውን በመግለጽ፣ ሊጠናከር እንደሚገባው ድምፃቸውን አጉልተው ሲናገሩ ከተደመጡት አገሮች አብዛኞቹ የአፍሪካ አገሮች ነበሩ፡፡ በተለይም ቦትስዋና፣ ጋና፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ሌሴቶ፣ ማሊ፣ ናይጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ሴኔጋልና ኮትዲቯር በዋነኝነት ይጠቀሳሉ፡፡  

የእነዚህ አገሮች አሠላለፍ ደግሞ በተለይም በኬንያዊቷ ዕጩ ላይ የራሱ የሆነ አስቸጋሪ ተፅዕኖ ማሳረፉ የማይቀር ነው፡፡ ኬንያ የያዘችውን ፀረ አይሲሲ አቋሟን ካልተወች የምዕራብ አፍሪካ አገሮች ድምፅ ወደ ቦትስዋናዊዋ ዕጩ ሊያጋድል እንደሚችልም ፍንጭ ይታያል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ከግማሽ በላይ በሳድክ ጎራ ሥር ያሉ የደቡባዊው አፍሪካ አገሮች ድምፅ ደግሞ ፀረ አይሲሲ አቋም ካላቸው አገሮች ጎራ ለተወከሉት ለአሚና መሐመድና ለባቲሊ ሊያጋድል ይችላል፡፡ በአመዛኙ ደግሞ ወደ ባቲሊ ሊያጋድል እንደሚችል የማይቀር ነው፡፡  ሌላው መጠነኛ ውስብስብ ጉዳይ ተደርጎ መነሳት የሚችለው ጉዳይ አይሲሲ ለመልቀቅ የመውጫ በሩን እያማተሩ ካሉት አገሮች ውስጥ ደቡብ አፍሪካ፣ ቡሩንዲና ጋምቢያ የተጋፈጡት የፖለቲካ ወይም የደኅንነት ቀውስ በራሱ ይጠቀሳል፡፡

የአፍሪካውያን ወጣቶች ሥራ አጥነት፣ ወደ ሜዲትራኒያን በአደገኛ ሁኔታ አቋርጦ ወደ አውሮፓና መካከለኛው ምሥራቅ መፍለስ፣ ድህነትና የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች በአኅጉሪቷ የገዘፉ ፈተናዎች በመሆን መቀጠላቸው በስፋት ይተችበታል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ፈተናዎች የአዲስ አበባው ጉባዔ የአኅጉሪቱን መሪዎች እ.ኤ.አ. ከጥር 30 እስከ 31 ቀን 2017 ለማስተናገድ ከሁለት ወራት ያነሱ ጊዜያት ቀርተውታል፡፡ ምናልባትም ጉባዔው የአፍሪካ ኅብረትን ስም በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ጎኑ ሊያስጠራ የሚችል ታሪክ አስመዝግቦም ሊያልፍ ይችላል ተብሎም እየተጠበቀ ነው፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -