Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹ጊፍቲ›› የሐረሪ ሴቶች መለያ

‹‹ጊፍቲ›› የሐረሪ ሴቶች መለያ

ቀን:

በሐረሪ ክልል አንዲት ሴት ልጅ ከሰባት ዓመቷ ጀምሮ ስፌት መልመድ በቀደመው ጊዜ ግዴታዋ ቢሆንም፣ አሁን ላይ በፍላጎቷ የምታከናውን ነው፡፡ ለስፌት ለየት ያለ ቦታ በሚሰጠው ሐረሪ፣  የቤት ማስዋቢያዎችና በየግድግዳው የሚሰቀሉ ጌጣጌጦች የስፌት ውጤቶች ናቸው፡፡

ወይዘሮ ፋጡማ ሀሰን ይባላሉ፡፡ በአሚር አብዱላሂ አዳራሽ መግቢያ ላይ በሚገኘው  የስፌት መሸጫ ሱቅ ውስጥ በማኅበር ተደራጅተው ይሠራሉ፡፡ ስፌት መሥፋት የለመዱትም ከልጅነታቸው ጀምሮ ነው፡፡ የቁርዓን ትምህርት ተምረው ወደ ቤት ሲመለሱ ከእናታቸው ስር ሆነው የስፌት ሙያ ይማሩ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡

ወይዘሮ ፋጡማ የተለያዩ ስፌት መገልገያ ዕቃዎችን የሚሠሩት ከአለላ፣ ከአክርማ፣ ከገብስ ገለባ፣ ከክር እንዲሁም ከስንደዶ ነው፡፡ ከሚሠሯቸው ስፌቶች መካከል የዳቦና የእንጀራ ማቅረቢያ፣ በተለይ በሐረሪ ክልል ልዩ ሥፍራ የሚሰጠው ‹‹ጊፍቲ›› ተጠቃሽ ናቸው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ጊፍቲ የሚሠራው በቀለም የተነከሩ አለላና አክርማ ከተባሉ የስንደዶ ዓይነቶች ነው፡፡ አንድ ጊፍቲ ሠርቶ ለመጨረስ ከሦስት እስከ አራት ቀናት ይፈጃል፡፡ ጊፍቲ ከጌጥነት ባለፈም የተለየ ትርጉም አለው፡፡ የሚሠራውም በአንድ ቤተሰብ ውስጥ በሚኖሩ ሴት ልጆች ቁጥር ልክ ነው፡፡ በቤቱ መግቢያ ትይዩ ባለ ግድግዳ ላይ የሚሰቀል ሲሆን፣ በቤት ውስጥ ያላገቡ ሴት ልጆች መኖራቸውንም ማሳያ ነው፡፡ ቤተሰቡ ውስጥ ካሉት ሴት ልጆች አንዷ በምታገባበት ወቅት ከተሰቀሉት ጊፍቲዎች መካከል አንድ ተቀንሶ ይሰጣታል፡፡

 አንድ ጊፍቲ ይዛ ከቤት የወጣች ሙሽራ፣ ጊፍቲውን መልሳ ግድግዳ ላይ አትሰቅልም፡፡ የሙሽራዋ ውድ ጌጣጌጦችና በስጦታ የምታገኛቸው፣ የመዋቢያ ዕቃዎች ማስቀመጫ ይሆናል፡፡

አንዲት ሴት በተዳረች ማግስት የሴቷ ቤተሰቦች ሁለት ዓይነት ሙዳዮች በማዘጋጀት፣ በአንደኛው ዕጣን በሌላኛው ማስቲካ ሞልተው ለሙሽሪት ይልካሉ፡፡ የወንዱ እናትም በስፌቶቹ ዕጣን፣ ኩል፣ ውኃና ማስቲካ እያደረጉ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ይልካሉ፡፡ ዕጣኑ ሲጨስ፣ የወንዱ ቤተሰቦች ማስቲካውን ተካፍለው እየበሉ ይመርቋታል፡፡

አንዲት ሴት ካገባች ከአራት አስከ አምስት ወር ድረስ ባሉት ጊዜያት ሁለት የእንጀራ መሶብ ሰፍታ ለባለቤቷ እናት መላክ ግዴታዋ ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ከሥራ ጋር የማይመቻት ከሆነ ገዝታም ቢሆን መላክ ይጠበቅባታል፡፡ ‹‹ሻልዳገርት›› የሚባለው የስፌት ዓይነት ደግሞ በቀደሙት ጊዜያት ወንዶች ሲያገቡ የሚሠጣቸው የስጦታ ዓይነት ነው፡፡ ለወንዶች የሚያስፈልጉ የንፅህና መጠበቂያ እንደ ምላጭ፣ ጥፍር መቁረጫ፣ ሳሙና ላሉ ዕቃዎች ማስቀመጫም ነው፡፡ የስፌት ዓይነት ‹‹አፈተ ሙዳይ››  ለሴት ልጆች ሻሽ ማስቀመጫም የሚያገለግል እንደሚሆን ወይዘሮ ፋጡማ ይናገራሉ፡፡

ሌላው በክር ስፌት ከሚሠሩት መካከል የሙስሊም ቆብ ነው፡፡ ሦስት የቆብ ዓይነቶች ሲኖሩ፣ ለወጣት ወንዶች፣ ለወንዱ ሙሽራና ለአዛውንቶች የሚሆኑ ናቸው፡፡

በ11ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ለሐረሪ ክልል እንደ መለያ ሆኖ የቀረበው  የሙሽራ ጌጣጌጥና መዋቢያ ዕቃ ማስቀመጫ ጊፍቲ ነው፡፡ ስድስት በስድስት የሆነው ጊፍቲ፣ በውስጡ ከእንጨት የተሠራ መመገቢያ፣ ስትዋብ የምትቀመጥበት መደብ እንዲሁም ጌጣጌጦች ለሕዝብ ዕይታ ቀርበዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...