Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህል‹‹ሐረር ኢትዮጵያ››

‹‹ሐረር ኢትዮጵያ››

ቀን:

ከአዲስ አበባ በ552 ኪሎ ሜትር ርቀት በምሥራቁ ክፍል የምትገኘው ሐረር፣ 11ኛው የብሔር ብሔረሰቦችን በዓል እንድታዘጋጅ ከተመረጠች ጊዜ ጀምሮ ስታሰናዳቸው ከነበሩት መርሐ ግብሮች አንዱ የሆነውን ሙዚቃዊ ቴአትር በቀድሞው ስታዲየም የቀረበው በዋዜማ ነበር፡፡

ሙዚቃዊ ቴአትሩ ከቀድሞው የሐረር ከተማ ግንባታ አንስቶ ባለቤትነቷን ጨምሮ የሚያሳይ ነበር፡፡ በተለያየ ወቅት ያስተዳደሩት አሚሮች ከተማዋን እንዴት በፖለቲካ፣ በባህልና በንግድ ያስተዳድሯት እንደነበር ያሳያል፡፡

ቴአትሩን ለመመልከት የክልሉ ተወላጆች ትርኢቱ ከሚጀምርበት ሰዓት ቀደም ብለው ነበር በስታዲየሙ የተገኙት፡፡ ኃይለኛ ቅዝቃዜ በአካባቢው የነበረ ቢሆንም ተመልካቾቹ የተሰማቸው አይመስልም፡፡ ቴአትሩ ከመጀመሩ በፊትም ሙሉ ስታዲየሙ በመብራት ደምቆ የሐረሪ ባህላዊ ሙዚቃ ይደመጥ ነበር፡፡

ኅዳር 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ከምሽቱ ሦስት ሰዓት አካባቢ የስታዲየሙ መብራቶች ደብዘዝ ማለት ጀመሩ፡፡ በመቀጠልም አዛን በማለት፣ ሐረር በ13ኛው ክፍለ ዘመን ምን እንደምትመስል፣ ከዛም በ16ኛው ክፍለ ዘመን እንዴት የምሥራቅ አፍሪካ የንግድ ማዕከል እንደነበረች ቀረበ፡፡ ነጭ በነጭ የለበሱ በርካታ ወጣቶች የተሳተፉበት ቴአትሩ፣ የሐረርን በሮች ማለትም በድሪ በሪ፣ አስመዲን በሪ፣ ስጉዳጥ በሪ፣ አሱስም በሪና አሮብ በሪ ታይተውበታል፡፡ እነዚህ ነጫጭ የለበሱ ተዋንያን እንደ አጥር በመደርደር፣ የበር ድምፅ በማስመሰል በመካከላቸው ክፍተት እየፈጠሩ በወቅቱ የነበረውን የነጋዴዎች መውጣትና መግባት ለማሳየት ሲሞክሩ ከተመልካቹ ከፍተኛ አድናቆት ተችሯቸዋል፡፡ በአሚሮች የነበረው አገዛዝን አስመልክቶ የቀረበው የቴአትሩ ክፍል ይህም ዛሬ ለምን ገናና አልሆነም? የሚል ቁጭት ከተመልካቹ አስነስቷል፡፡

‹‹ሐረር ተሞሸረች›› የሚለው የቴአትሩ ክፍል ሐረር አሁን ያለችበትን የሚያሳይ ነበር፡፡ ይህ በንዋይ ደበበ ሙዚቃ ‹‹ቆንጅት ከሐረር ናት›› ታጅቦ ተመልካቹን በሐሴት ቁጭ ብድግ ያስባለ ነበር፡፡ ታዋቂ ድምፃውያን የሐረር አምስት በሮቿን ሲጠሩ ነጫጭ የለበሱ ወጣቶች ደግሞ በበሮቹ ቅርጽ ተደርድረው ወደ ስታዲየሙ ሲገቡ የክልሉን ፕሬዚዳንት ጨምሮ ብዙዎች በጭብጨባ አጅበዋል፡፡ በቴአትሩ መጨረሻም የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን አልባሳት የለበሱ ተዋንያን በነዚህ በሮች ሲወጡና ሲገቡ ታይቷል፡፡     

‹‹ሐረር ኢትዮጵያ›› የተሰኘው ይህ ሙዚቃዊ ቴአትር ከጥንታዊቷ ሐረር ተነስቶ የዛሬይቷን ሐረር የሚያስቃኝ ነው፡፡ የሐረርን ታሪክ እንዲሁም ማኅበራዊ መስተጋብሩን ሙዚቃን ከተውኔት ጋር በማዋሐድ ያሳያል፡፡ በቻላቸው ፈረጅ፣ ነብዩ ባዬና ተስፋዬ እሸቱ የተጻፈው ቴአትሩ፣ የተዘጋጀው በቻላቸውና ተስፋዬ ሲሆን፣ ከ150 በላይ ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡

ቻላቸው ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ለአሥራ አንደኛው የብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል የተዘጋጀው ሙዚቃዊ ቴአትሩ ሐረር የተቆረቆረችበትን ታሪካዊ ዳራ በማስቃኘት ይጀምራል፡፡ ለቴአትሩ መነሻ የተደረጉት በአገር ውስጥና በውጭ ጸሐፍት የተዘጋጁ የታሪክ መጻሕፍትን ሲሆኑ፣ ሐረር አሁን ከምትገኝበት አስተዳደር ሥርዓት በፊት የነበረውን የአሚሮች አስተዳደር የሚያንፀባረቅ ክፍል በቴአትሩ ይገኛል፡፡

ወደ አንድ ሰዓት ከሠላሳ ደቂቃ ገደማ የሚወስደው ‹‹ሐረር ኢትዮጵያ››፣ ሐረርን ካስተዳደሯት 72 አሚሮች መካከል 42ኛው አስተዳዳሪ የነበሩትን አሚር ኑር እንደ አንድ ገፀ ባሕሪ ወስዷል፡፡

ቻላቸው እንደሚናገረው፣ ስለ ሐረር ሲነሳ ከማይዘነጉት አንዱ የሐረር ጀጎል ግንብ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) መዝገብ እንዲሠፍር ለማስቻል ያደረጉትን ጥረት መነሻ በማድረግ የአሚር ኑር ገፀ ባሕሪ ጎልቷል፡፡ ‹‹የጁገል ግንብ ባለፈው የሐረር ታሪክ፣ በአሁኑ ነባራዊ ሁኔታና ለወደፊት በሚመጣው ትውልድም ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ቅርሶች አንዱ ነው፤›› የሚለው ጸሐፊና አዘጋጁ በቴአትሩ ይኼ እውነታ መንፀባረቁን ያስረዳል፡፡  

በሙዚቃዊ ቴአትሩ የሐረር እንዲሁም የአጎራባች ከተሞቿ የንግድ ልውውጥም ቦታ ተሰጥቶታል፡፡ ሐረር የየትኛውም አካባቢ ተወላጅ ተቀባይነት አግኝቶ የሚኖርባት ከተማ መሆኗም ቴአትሩ ከሚያጠነጥንባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ውስጥ ይገኝበታል፡፡ ‹‹ሐረር ውስጥ ከየት መጣችሁ? ብሔራችሁ ምንድነው? የሚል ጥያቄ የለም፡፡ ሁሉም ሰው በፍቅር ተቻችሎ የሚኖርባት ከተማ መሆኗን በቴአትሩ አሳይተናል፤›› ሲል ቻላቸው ይገልጻል፡፡ ይኼንንም ከመጻሕፍትና ከታሪካዊ ሰነዶች ባለፈ በሐረር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ማስተዋላቸው የዓይን እማኝ እንዳደረጋቸውም ያክላል፡፡

ሐረር የረዥም ዓመታት ታሪክ ያላት ከተማ እንደመሆኗ ሁሉንም ነገር በአንድ ቴአትር ማካተት ባይቻልም፣ የከተማዋን አንኳር እውነታዎች ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ሐረር በዓለም ካሉት አራት እስላማዊ መንግሥታት አንዷ ከመሆኗ አስቀድሞ ከነበረው ታሪክ ጀምሮ፣ እስከ ዛሬዋ ሐረር ለመዳሰስም ጥረት ተደርጓል፡፡

‹‹ሐረር ከተማ ለአዲስ አበባ መቆርቆርም እንደ መነሻ ትሆናለች፡፡ ከንግድ እንቅስቃሴ ባሻገር በሃይማኖትና በብሔር የተለያዩ ማኅበረሰቦችን አቅፎ በመያዝ ያላትን ታሪክ ወደ ሌሎች የኢትዮጵያ ከተማዎችም ለማምጣት ቴአትሩ ያግዛል፤›› ይላል ቻላቸው፡፡ በሃይማኖት መቻቻል ረገድ እንደ ምሳሌ ከሚጠቅሳቸው አንዱ ከተማዋ ውስጥ መስጊድ፣ የካቶሊክ ቤተክርስቲያንና የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በቅርብ ርቀት ተገንብተው ማየቱን ነው፡፡

ስለ ሐረር ታሪክ መረጃ ያላቸው ግለሰቦች ሙዚቃዊ ቴአትሩ የበለጠ ትርጉም ሊሰጣቸውም ቢችልም ስለ ሐረር የማያውቁ ሰዎችም አንዳች መልዕክት ሊቀስሙ እንደሚችሉ ያምናል፡፡፡ ተዋንያኑ ከሐረር ከተማ አማተር የቴአትር ክበቦችና የባህል ቡድኖች የተውጣጡ ሲሆኑ፣ የከተማዋን ባህል ለማንፀባረቅ በተደረገው ጥረት አበርክቶ ነበራቸው፡፡ ቴአትሩ ለመድረክ ከመብቃቱ ከ17 ቀናት በፊት ልምምድ ጀምረው ለብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል አድርሰውታል፡፡

ሙዚቃዊ ቴአትሩን ልዩ ገፅታ ካላበሱት ተሳታፊዎች መካከል ድምፃውያኑ ንዋይ ደበበ፣ ኢሳን አብዱልሰላምና ተስፋዬ ታዬ ይጠቀሳሉ፡፡ የቴአትሩ ደራስያንና አዘጋጆች በሐረር ዙሪያ ያቀነቀኑ የሐረር ተወላጅ የሆኑና ያልሆኑም ድምፃውያን አሳትፈዋል፡፡ ኢሳን አብዱልሰላም የጁገል ግንብ በዩኔስኮ ሲመዘገብ የለቀቀው ዘፈን ‹‹ሐረር ሰላም›› ይገኝበታል፡፡ በሐረሪና የኦሮምኛ ሙዚቃዎቹ የሚታወቀው መሐመድ ጠይልና በሐረሪ የአዘፋፈን ዘዬ እየታወቁ የመጡት ወጣቶቹ የ‹‹አዲስ ቃና›› ቡድን አባላትም ይጠቀሳሉ፡፡ ሙዚቃዊ ቴአትሩ የሐረረን ባህልና ታሪክ ከማንጸባረቅ ጎን ለጎን ብሔር ብሔረሰቦችን ያማከለ እንዲሆን፣ በተለያዩ የብሔር ብሔረሰቦች ዘፈኖቹ የሚታወቀውን የተስፋዬ ታዬ ሙዚቃ አካቷል፡፡

ቻላቸው እንደሚገልጻው፣ የብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል እንደመሆኑ ሐረርን ከሌሎች አካባቢዎች ጋር ለማጣመር ተሞክሯል፡፡ ‹‹ቴአትሩ የሚጠናቀቀው ሐረር ስትሞሸርና የብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች እንኳን አደረሰሽ ሲሏት ነው፡፡ አጨራረሱ ተምሳሌታዊ ሲሆን በገፀ ባሕሪዎቹ በሐረር የነገሠው ሰብአዊነትና ፍቅር ይንፀባረቃል፤›› ሲል ያስረዳል፡፡

በቴአትሩ ዝግጅት ወቅት ታሳቢ ከተደረጉ እውነታዎች አንዱ የሐረርን ሕዝብ አኗኗር በመላው ኢትዮጵያም የማስፋፋት ጉዳይ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ‹‹ሐረር ኢትዮጵያ ከሚለው የሙዚቃው ቴአትሩ ርዕስ ጀምሮ ቴአትሩ በሐረር ያለው የአብሮነት ኑሮ አኗኗር በሌሎች ከተሞችም እንዲሰራጭ የታሰበበት ነው፤›› ይላል፡፡ ሙዚቃዊ ቴአትሩ ሲጠናቀቅ ከታዳሚዎቹ በጎ ምላሽ እንደተገኘም ያክላል፡፡ ሐረርን በማስተዋወቅ እንዲሁም ታሪክና ባህሏን በማንፀባረቅ ረገድ ግባቸውን እንደመቱም እምነቱ ነው፡፡ ቴአትሩ ለዕይታ በበቃበት ስታዲየም የነበሩ ተመልካች ሞቅ ያለ ድጋፍ አሰምተዋል፡፡ በአንፃሩ በቴአትሩ ከሐረር በተጨማሪ የሌሎች አካባቢዎች ነባራዊ ሁኔታም ቢታከል ሲሉ አስተያየት የሰጡም አሉ፡፡

እንደ ብሔር ብሔረሰቦች ክብረ በዓል ሁሉ ለበርካታ መርሐ ግብሮች የሚዘጋጁ ቴአትሮች ከአንድ ቀን በዘለለ ለተመልካች ሲቀርቡ አይስተዋልም፡፡ ቴአትሮቹን ለማዘጋጀት ከሚውለው ጊዜና ገንዘብ አንፃር ከአንድ ቀን ፍጆታ በላይ አለመሆናቸውም ይተቻል፡፡ ቻላቸው እንደሚለው፣ ከአንድ መርሐ ግብር ባለፈ ለኅብረተሰቡ መቅረብ የነበረባቸው ብዙ ሥራዎች ችላ ተብለው ቀርተዋል፡፡ የቴአትሮቹ አዘጋጆችም ከዝግጅቶቹ በኋላ ቴአትሮቹ የሚታዩበት መድረክ ሲያመቻቹ አይስተዋልም፡፡ ‹‹በብዙ አዘጋጆች ዘንድ ቴአትሮች አንዴ ከቀረቡ በኋላ ቸል የማለት ነገር አለ፤›› ይላል፡፡

የ‹‹ሐረር ኢትዮጵያ›› ሙዚቃዊ ቴአትርን በተመለከተ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ቴአትሩን ቀርጾ በሲዲ የማሠራጨት ዕቅድ አለው፡፡ ቴአትሩን በተለያዩ አካባቢዎች በመድረክ የማቅረብና ሰኔ 24 ቀን 2009 ዓ.ም. በሐረር በሚከበረው የዳያስፖራ በዓል ዕለት ቴአትሩን የማሳየት ዕቅድም አለ፡፡  

በታምራት ጌታቸውና በምሕረተሥላሴ መኰንን

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...