Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምአሜሪካና ሩሲያን ሊያፋጥጥ ይችላል የተባለው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጠለፋ

አሜሪካና ሩሲያን ሊያፋጥጥ ይችላል የተባለው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ጠለፋ

ቀን:

አገሮች ወይም ግለሰቦች የሌሎችን የኮምፒዩተር ግንኙነት መረብ ሰብረው መግባትና መረጃ መጥለፍ ከጀመሩ ከ40 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ የአሜሪካ ጦር ኃይል ኃላፊዎችም በወቅቱ ጥቂት ለነበሩት የኮምፒዩተር ሳይንቲስቶች ማንኛውንም ዓይነት መረጃ በቀጥታ ሊገኙ ከሚችሉ ኔትወርኮች ላይ እንዳያስቀምጡ ማስጠንቀቂያ የሰጡት እ.ኤ.አ. በ1967 ነበር፡፡ የኮምፒዩተር (ሳይበር) ግንኙነት ደኅንነትን ከሽብርተኞች፣ ከውጭ የስለላ ተቋማትና ከወንጀለኞች ለመከላከል ያስችላል የተባለውን መመርያም፣ የወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን የፈረሙትም እ.ኤ.አ. በ1984 ነው፡፡

ይህንን መመርያ ያዘጋጁት አብዛኞቹ የፔንታጎንና የናሳ ተመራማሪዎች፣ የአገሮችንና የግለሰቦችን የኮምፒዩተር ግንኙነት መጥለፍ ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ፣ በየአገሮች የኮምፒዩተር ግንኙነቶች ሰርገው እየገቡ ስላዩት ይህ በአሜሪካ ላይ ቢሆን ምን ሊከሰት ይችላል? የሚለውን ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ በመሆኑም የአሜሪካ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ግንኙነት በሌሎች እንዳይደፈር የአሜሪካ ሳይንቲስቶች ለዓመታት ሲባዝኑ ከርመዋል፡፡ በዚሁ ልክ ደግሞ ወዳጅ አገር የሚሏቸውን ጭምር ኔትወርክ ሰብረው በመግባት የየአገሮችን ሚስጥር መዝብረዋል፣ የወዳጆቻቸውን ገመና ለአደባባይ አብቅተዋል፡፡

እ.አ.አ. የ2016 የአሜሪካ ምርጫ በማይበገር የሳይበር ቴክኖሎጂ ተደራጅቻለሁ፣ የሳይበር ሠራዊት አለኝ የምትለዋን አሜሪካ የፈተነ ሆኗል፡፡ የቀዝቃዛው ጦርነት ካከተመ ወዲህ በሶሪያና በአፍጋኒስታን በግልጽና በህቡዕ ጦራቸውን በጽንፍ እያሠለፉ የሚገዳደሩት አሜሪካና ሩሲያ፣ የአንድ አገር መሪን መምረጥ ድረስ ጣልቃ መግባት ድረስ ተዳርሰው መወዛገቡን ይዘዋል፡፡ የአሜሪካን ምርጫ ያሸነፈው የሕዝቡ ድምፅ መሆኑ ቀርቶ፣ የሩሲያ ወይስ የሲአይኤ ካርድ እስከመባልም ደርሷል፡፡

አሜሪካ ከሩሲያ ቀድማ የአገሮችን የኢንተርኔት ግንኙነት በመበርበር መረጃዎችን ስታካብትና በዚህም መሠረት በዓለም ኃያልነቷን አስጠብቃ ለመቆየት ፖሊሲዎቿን ስታደራጅ የከረመች ቢሆንም፣ አሁን ደግሞ ሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ እስከመግባት ያደረሳትን የኮምፒዩተር ግንኙነት ጠለፋ አካሂዳለች ተብሏል፡፡ ሲአይኤ ዶናልድ ትራምፕ እ.ኤ.አ. የ2016 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እንዲያልፉና ሒላሪ ክሊንተን እንዲሸነፉ ሩሲያ የምርጫ ሲስተሞችንና የዴሞክራቶችን የምርጫ ዘመቻ በመጥለፍ ተባብራለች ሲል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡

ተመራጩ ትራምፕም ሆኑ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሲአይኤን ድምዳሜ ቢያጣጥሉትም፣ የመገናኛ ብዙኃኑም ሆነ የፖለቲከኞቹ አጀንዳ በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሩሲያ ጣልቃ ገብነት የአሜሪካ ምርጫ ከማንም በላይ እንዳልሆነ ለማሳየት፣ አሊያም ዶናልድ ትራምፕ እንዲያሸንፉ ለመርዳት በሚለው ላይ ያጠነጠነ ሆኗል፡፡ ሩሲያ ከአሜሪካ ዘግይታ የኮምፒዩተር ግንኙነት መረቦችን መጥለፍና መበርበር የጀመረችው እ.ኤ.አ. በ1997 ሲሆን፣ የአሜሪካ የመከላከያ መረጃ መረቦችም በተለያዩ ጊዜዎች ተበርብረው እንደነበር የታወቀው በዚሁ ጊዜ ነው፡፡ በዚሁ ዓመት የፈረንሣይ መከላከያ ዲፓርትመንት ኔትወርክ ተጠልፎና ተበርብሮ እንደነበር ታውቋል፡፡ ቻይና የመከላከያ የመሣሪያ አምራቾችን፣ የማንኛውንም ዓይነት ንግድ፣ የመንግሥታዊ ተቋማትንና የትልልቅ መሠረተ ልማቶች ግንኙነቶችን እ.ኤ.አ. በ2001 ትጠልፍ እንደነበርም መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2008 ሩሲያ የአሜሪካን መከላከያ ማዕከላዊ መምርያ መጥለፏና መረጃዎችን ማግኘቷ መረጋጋቱ በሳይበር ቴክኖሎጂው ዘርፍ አንድ ዕርምጃ ወደፊት ለመራመድ ምክንያት ነበር፡፡ ጉዳዩ ኢራን፣ ሶሪያና ሰሜን ኮሪያን ጨምሮ ከ20 በላይ አገሮች ለመጠቃቃት ዝግጁ እንዲሆኑና የየራሳቸው የሳይበር ወታደሮች እንዲኖራቸውም ምክንያት ሆኗል፡፡ አሜሪካና ሩሲያ ከእነዚህ ውስጥ የሚመደቡ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2016 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የታየው ደግሞ አሜሪካ ወይም ምዕራባውያን ምሥራቁን (የቀድሞዋን ሶቪየት ኅብረት) ለመበታተን ለሠሩት ሸፍጥ የሩሲያ የብቀላ ዱላ ነው የሚሉ አስተያየቶችም ይሰነዘራሉ፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም የነበሩ የመረጃ መረብ ጠለፋዎች መረጃ ከማግኘት የዘለሉ አልነበሩም፡፡ የሳይበር ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ የአንድ አገር ምርጫ ውስጥ ሲገባም የመጀመሪያው ነው፡፡  

‹‹ዳርክ ቴሪቴሪ ዘ ሴክሪት ሂስትሪ ኦፍ ሳይበር ዋር›› የሚለው መጽሐፍ ጸሐፊ ፍሬድ ካፕላን እንደሚሉት፣ ከዚህ ቀደም በነበሩ የአሜሪካ ምርጫዎች ከምርጫው ጋር የተያያዙ የኮምፒዩተር ግንኙነቶች ይጠለፉ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን የታየው ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየና እንዲሁ ስለምርጫው ለማወቅና መረጃ ከማግኘት የዘለለም ነው፡፡ ‹‹ሩሲያ መረጃ ብቻ ለማግኘት ጠለፋ አታካሂድም፡፡ የምታገኘውን መረጃ የጦር መሣሪያ ታደርገዋለች፡፡ የአሜሪካን ፖለቲካ ለማወቅ በማለት ብቻም የመረጃ መረብ አትበረብርም፡፡ በመረጃው መሠረት ስትራቴጂ በመቀየስ የአሜሪካን ፖለቲካ በምትፈልገው መንገድ ትቃኘዋለች፤›› ሲሉም ካፕላን አትተዋል፡፡

የሲአይኤ ባለሥልጣናት ለአሜሪካ ሴናተሮች ሩሲያ በማያጠራጥር ሁኔታ ዶናልድ ትራምፕ እንዲመረጡ ዓላማ ስለነበራት ይህንንም የመረጃ መረቦችን በመጥለፍ አድርጋዋለች ብለው ቢያቀርቡም፣ በኤፍቢአይ ምርመራ የተደረገባቸውና የትራምፕ የቀድሞ የውጭ ግንኙነት አማካሪና ቡድኑ ውስጥ የሚገኙት ጆን ቦልተን የሲአይኤ ድምዳሜ ብዙ ጥርጣሬዎችን የሚያጭርና ምናልባትም የውሸት ጩኸት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሲአይኤ የሸፍጥ ንድፈ ሐሳብ እየተከተለ ነው፤›› ሲሉም ሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ገብታለች፣ የትራምፕን የዋይት ሐውስ ጉዞ መርታለች መባሉን አጣጥለውታል፡፡

ተመራጩ ፕሬዚዳንት ትራምፕም፣ ‹‹የምርጫው ውጤት አሁን ካለው በተቃራኒ ቢሆን ኖሮ የሩሲያና የሲአይኤ ካርድ እያልን እንጫወት ነበር? ይህ የሸፍጥ ንድፈ ሐሳብ ይባላል፤›› ሲሉ ምርጫው የሕዝብ ድምፅ ቢሆንም፣ በሲአይኤና በሩሲያ መሀል እንዲንሸራሸር መደረጉን አጣጥለው በትዊተር ገጻቸው ማስፈራቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡

ሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ የመግባቷ ጉዳይ ከምርጫው ቀድሞ ሲነገር የከረመ ቢሆንም፣ ሲአይኤ ከድምዳሜ ላይ የደረሰው ከምርጫው በኋላ ነው፡፡ የቀድሞው የሲአይኤ ዳይሬክተር ማይክል ሃይደን ከወር በፊት ከሲኤንኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ ሲአይኤን ደግፈው ትራምፕን ማጣጣላቸው ይታወሳል፡፡ ‹‹ትራምፕ የሩሲያን ጣልቃ ገብነት ማውገዝ ሲገባው፣ ሩሲያ እጇ የለበትም ማለቱና ዊኪሊክስ ጠፉ የተባሉ የሒላሪ ክሊንተን ኢሜይሎችን መልቀቁን ማመስገኑ አግባብ አይደለም፤›› ሲሉም ከአገር ደኅንነትና ከሳይበር ጥቃት ግንዛቤ ጋር አያይዘው ተናግረው ነበር፡፡

የሲአይኤ የቀድሞ ተጠባባቢ ዳይሬክተር ማይክል ሞሬል፣ ‹‹የሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ መግባት በፖለቲካው መነፅር ከ9/11 ጋር አቻ ነው፤›› ይሉታል፡፡ ሲአይኤን እ.ኤ.አ. ከ2011 እስከ 2013 በተጠባባቂ ዳይሬክተርነት ያገለገሉት የምርመራ ተንታኙ ሞሬስ፣ የሩሲያን በምርጫ ጣልቃ መግባት፣ በአሜሪካ ዴሞክራሲ ላይ የተቃጣ ጥቃት ነው ብለዋል፡፡

‹‹የውጭ መንግሥት በአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ መግባት ለአሜሪካ መኖር ሥጋት ነው፤›› የሚሉት ሞሬል፣ ሩሲያ የተጠቀመችውን የመረጃ መረብ ብርበራ ቴክኖሎጂ ማወቅና ይህንን መልሰው እንዳያደርጉ የሚያስችል ቴክኖሎጂ በመጠቀም መረጃዎችን መጠበቅ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ተሰናባቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሩሲያ በዴሞክራቶች ላይ የሠራችው ወንጀል ተጣርቶ ሙሉ ሪፖርቱ ሥልጣን ከማስረከባቸው በፊት እንዲቀርብላቸው ሲጠይቁ፣ ሴኔቱ ደግሞ ሩሲያ በአሁኑ የአሜሪካ ምርጫ ጣልቃ ስለመግባቷ ምርመራ እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡ ‹‹ተመራጩ ፕሬዚዳንት ወደዱትም አልወደዱት ምርመራው ይደረጋል፡፡ በኮንግረሱም በዶናልድ ትራምፕና በሪፐብሊካኑ የመጀመሪያው መወያያ አጀንዳ ይሆናል፤›› ሲል ሴኔቱ አስታውቋል፡፡

የሳይበር ምኅዳር በቀላሉ የሚታወቅ አይደለም፡፡ በአብዛኛው የሳይበር ጥቃት የሚፈጽሙም ሆነ የሚፈጸምባቸው ጉዳዩን ሚስጥር አድርገው መቆየትን ይመርጣሉ፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ የሳይበር ብርበራዎችም መረጃ ከማግኘት የዘለሉ አልነበሩም፡፡ ብዙ ጊዜም በመሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ፡፡ ሩሲያ የሒላሪ ክሊንተን ዘመቻ ግንኙነቶችን በሙሉ መጥለፏ ግን አንድ አገር በሌላ አገር የምርጫ ሒደት ውስጥ በኢንተርኔት ቴክኖሎጂው ተጠቅሞ ሲገባ የመጀመሪያው መሆኑ ብዙ ተብሎበታል፡፡ ይህም ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እናደርጋለን ለሚሉ አገሮች ሌላ ፈተና፣ ሩሲያንና የአሜሪካን ፖለቲካ ደግሞ የሚፈታተን ነው እየተባለ ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ ሲአይኤ ሩሲያ በአሜሪካ ምርጫ ውስጥ እጇን አስገብታለች የሚለውን ሪፖርት ቢያቀርብም፣ የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አጣጥለውታል፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ከሚወራው ወሬ ውጪ በዝርዝርና በተብራራ ሁኔታ የቀረበ መረጃ አለመኖሩ ደግሞ ከውዥንብር በላይ ምንም ማሳየት አልተቻለም፡፡ የአሜሪካም ሆነ የምዕራቡ ሚዲያዎች ከግምት ያላለፉ ትንተናዎችን ከማቅረብ ውጪ በተጨባጭ የሩሲያን ድርጊት ማጋለጥ አልቻሉም፡፡

 

      

    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...