Wednesday, February 28, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የሪፖርቶች ተዓማኒነት የሚረጋገጠው ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲኖር ብቻ ነው!

በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በዘፈቀደ የሚወጡ ዕቅዶችና አፈጻጸሞቻቸው ላይ የሚታዩ ችግሮች በአገሪቱ ላይ በስፋት ችግር ሲፈጥሩ  ይታያሉ፡፡ ከዕቅድ አወጣጥ እስከ አፈጻጸም ባለው ሒደትና በሪፖርት አቀራረብ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማስወገድ፣ አዲስ አሠራር ተግባራዊ እንደሚደረግ ሰሞኑን ተሰምቷል፡፡ በተለይ በተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት የሚቀርቡ ሪፖርቶችን ትክክለኛነት ለማረጋገጥና አስፈላጊውን ዕርምጃ ለመውሰድ ትኩረት እንደሚሰጥበትም ተመልክቷል፡፡ እርግጥ ነው መያዣ መጨበጫ በሌላቸው የተለጠጡ ዕቅዶችና ክትትልና ግምገማ በማይደረግባቸው አፈጻጸሞች ሳቢያ የሚደርሰውን ጉዳት ለመደበቅ በሚደረግ ጥረት፣ በሐሰተኛ ሪፖርቶች እየተቀባቡ የሚወጡ ማደናገሪያዎች በብዛት ታይተዋል፡፡ አሁንም በስፋት ይታያሉ፡፡ የተሰጣቸውን በጀት በአግባቡ የማይጠቀሙና ክንዋኔያቸውም እዚህ ግባ የማይባሉ የተለያዩ መንግሥታዊ ተቋማት በብዛት እንዳሉ በተደጋጋሚ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ ይህ ሁሉ ጥፋት የሚፈጸመው ግን ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚባለው መርህ በመጣሱ ነው፡፡

ግልጽነትና ተጠያቂነት በሌለበት የሚወጡት ዕቅዶች ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር ስለመጣጣማቸው አይታወቅም፡፡ ዕቅዶቹን ተግባራዊ በማድረግ ሒደት ውስጥ የአፈጻጸሞች የጊዜ ሰሌዳና የቁጥጥር ሥርዓት በዘፈቀደ ይከናወናል፡፡ በዚህ መንገድ የሚመራ ፕሮጀክት ወይም ሥራ ውጤቱ ከተጠበቀው በታች ስለሚሆን መዋሸትና መደባበቅ ውስጥ ይገባል፡፡ ለዚህም በሐሰት የተለወሱ ሪፖርቶች ይቀርባሉ፡፡ ሪፖርቶቹ ምንን መነሻና መሠረት አድርገው ተሠሩ? ብሎ አጥብቆ ጠያቂ ስለማይኖር መዋሸትና ማድበስበስ የአገር በሽታ ሆኗል፡፡ ይህ ሁሉ አሳዛኝ ድርጊት የሚፈጸመው የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዳለበት በሕገ መንግሥት በተደነገገበት አገር ውስጥ ነው፡፡ የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነው ሕገ መንግሥት የመንግሥት አሠራርና ተጠያቂነትን በአንቀጽ 12 ላይ ደንግጎታል፡፡

የአገሪቱ ሕግ አውጪና ትልቁ የሥልጣን አካል የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባሩ ከሚሸፍናቸው መካከል፣ በአንቀጽ 55 ንዑስ አንቀጽ 17 እና 18 የተጠቀሱት ይገኙበታል፡፡ በንዑስ አንቀጾቹ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ሌሎች የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናትን ለጥያቄ የመጥራትና የሕግ አስፈጻሚውን አካል የመመርመር ሥልጣን  አለው፡፡ እንዲሁም ለሕግ አስፈጻሚው አካል በተሰጠ ማንኛውም ሥልጣን ላይ የምክር ቤቱ አባላት በአንድ ሦስተኛ ድምፅ ሲጠይቁ ምክር ቤቱ ይወያያል፡፡ ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ የመመካከርና አስፈላጊ መስሎ የታየውን ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አለው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሕግ የማስከበር ሥልጣን ያለው አሠራር ተግባራዊ በሚሆንበት አገር፣ እገሌ ከእገሌ ሳይባል አሠራሩ ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት ይሆናል ማለት ነው፡፡ ሐሰተኛ ሪፖርቶችም ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡

የመንግሥት አሠራር ለሕዝቡ ይበልጥ ግልጽ ሲሆንና ተጠያቂነት ሲኖርበት ሥራዎች በአግባቡ ይከናወናሉ፡፡ ብልሹ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ በመጀመርያ የተቋማት የአቅም ግንባታ ጉዳይ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በዘልማዳዊ አሠራር እጅና እግራቸው የታሠሩ ተቋማት መቼም ቢሆን ለለውጥ ዝግጁ አይሆኑም፡፡ የአቅም ግንባታ ጉዳይ ሲነሳ የመንግሥት ተቋማት በበጀት፣ በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በቁሳቁስ ሊጠናከሩ ይገባል፡፡ ከማቋቋሚያ አዋጃቸው ጀምሮ ደንቦቻቸውና መመርያዎቻቸው ለዘመናዊ ተቋም የሚመጥኑ ሆነው ሊዘጋጁ ይገባል፡፡ በሰው ኃይል ረገድ ለእያንዳንዱ ሙያ የሚመጥኑ ሠራተኞችና ኃላፊዎች መመደብ ሲኖርባቸው፣ መለኪያውም ብቃት ብቻ መሆን አለበት፡፡ ተቋማቱ የአገር አቅም በፈቀደ መጠን በበጀት እየታገዙ አስፈላጊውን ቴክኖሎጂና ቁሳቁስ ማግኘት አለባቸው፡፡ በዚህ መንገድ ሥራና ባለሙያ በአግባቡ እየተገናኙ ብቃት ባላቸው አመራሮች ሲታገዙ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት የበላይነት ይይዛሉ፡፡ የተጭበረበሩና የተድበሰበሱ ድርጊቶች ሥፍራ አይኖራቸውም፡፡

መንግሥት ከሚጠበቁበት የለውጥ ተግባራት መካከል አንደኛው ከዚህ ቀደም የነበሩ ብልሹ ድርጊቶችን ማስወገድ ነው፡፡ ብልሹ ድርጊቶች ሲወገዱ መሠረታዊ የሆኑ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡ የተዘጋጋው የፖለቲካ ምኅዳር ይከፈታል፡፡ ብቁና ንቁ የሆኑ አገር ወዳድ ዜጎች ለአመራርነት ይታጫሉ፡፡ ልማዳዊ አሠራሮች ተወግደው ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር የሚራመዱ አሠራሮች ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የአገር ወግና ልማድ ይሆናሉ፡፡ ለሙስና መስፋፋት ምክንያት የሚሆኑ አልባሌ ድርጊቶች ቦታ ያጣሉ፡፡ በኔትወርክ እየተደራጁ አገር መዝረፍና ሕዝብ ማስለቀስ ያበቃላቸዋል፡፡ ለሁከትና ለብጥብጥ የሚዳርጉ አጓጉል ድርጊቶች ይወገዳሉ፡፡ ሐሰተኛ ሪፖርቶች አሳፋሪና የማይረቡ ሰነዶች ተብለው ይጣላሉ፡፡

ለግልጽነትና ለተጠያቂነት መዳበር ዋናው ጉዳይ የሕዝብ ተሳትፎን ያለገደብ ማጠናከር ነው፡፡ ሕዝብ የሐሰተኛ ዕቅዶች፣ አፈጻጸሞችና ሪፖርቶች ቀጥተኛ ተጎጂ በመሆኑ ከታች ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በትክክለኛ መንገድ ተሳትፎ ሊኖረው ይገባል፡፡ ዴሞክራሲ ሥርዓት ሆኖ በተግባር መረጋገጥ የሚችለው የሕዝብ ተሳትፎ ሳይገደብ በአገሪቱ ሁሉም ጉዳዮች ዋነኛ ተዋናይ መሆን ሲቻል ነው፡፡ መንግሥት በተሃድሶም ሆነ በለውጥ እንቅስቃሴው አሸጋግሮ ማየት ያለበት ዛሬን ብቻ ሳይሆን ነገን ጭምር ነው፡፡ ለአዲሱ ትውልድ የምትመጠን አገር የምትፈጠረው አሁን በሚታየው ሁኔታ ሳይሆን፣ በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው የሪፖርቶች ተዓማኒነት የሚረጋገጠው ግልጽነትና ተጠያቂነት ሲኖር ብቻ ነው የሚባለው! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...