Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ረዥሙ የትንፋሽ መሣሪያ 11ኛው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሐረር ሲከበር አጃቢ ነበር

ትኩስ ፅሁፎች

የሚሉት ያጡ

            አሯሩጠው ሳያደክሙኝ፤

ወይ ላይጥሉ ሲጎትቱኝ፤

ተከላክለው ላያስጥሉኝ፤

ከወጠንኩት ላያስቀሩኝ፤

ከፊት ቀድመው ተገትረው፤

ከመንገዴ ተደንቅረው፤

ሊያዳክሙኝ ተማምለው፤

ደግሞ አስወሩ ሰነፍ ብለው፡፡

ሰውነቴን ተጠራጥረው፤

ሙሉነቴን አውቀው ንቀው፤

በኔነቴ ቢሳለቁ፤

ቢናገሩኝ ቃል አስከፊ፤

እንዳልሰማ ባቀረቅር፤

ብለው አሉኝ አንገት ደፊ፡፡

በራሴ ዓለም ተወስኜ፤

ደግሞ ብኖር ለብቻዬ፤

ብለው እርፍ ይሄ አውሬ፡፡

ፍስሃ ተክሉ ‹‹የግዞት ዓለም›› (1996)

**************

ልብሳቸውን ሲቀይሩ የነበሩ 49 ሴቶችን ፎቶ ያነሳው እንግሊዛዊ ታሰረ

በአውስትራሊያ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ሴቶች ልብስ መቀየሪያ ክፍል ውስጥ በሚስጥር ፎቶ ያነሳ እንግሊዛዊ ታሰረ፡፡ የ28 ዓመቱ ወጣት የታሰረው ከዋና ስፖርት በኋላ በመልበሻ ክፍል ልብሳቸውን ሲቀይሩ የነበሩ 49 ሴቶችን ፎቶ በሚስጥር ካነሳ በኋላ ነው፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው፣ የአውስትራሊያ ፖሊስ ከወጣቱ የእጅ ስልክ የሰውን መብት የሚጋፉ ተንቀሳቃሽ ምስሎችና ከ100 በላይ ራቁታቸውን የነበሩ ሴቶች ፎቶግራፎች አግኝቷል፡፡ ብዙዎቹ ፎቶዎችም በግል የፌስቡክ ገፅ ላይ የተጫኑ መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

በአውስትራሊያ በሥራ ቪዛ የሚንቀሳቀሰው ወጣት፣ የግለሰቦችን መብት በመጋፋት በ54 ጉዳዮች ክስ ተመሥርቶበታል፡፡

***************

ቬንዙዌላ ከአምራቾች የወረሰችውን አራት ሚሊዮን የክሪስማስ አሻንጉሊቶች ለደሃ ልታድል ነው

የቬንዙዌላ ባለሥልጣናት ከሁለት የአሻንጉሊት አምራች ኩባንያዎች የወረሱትን አራት ሚሊዮን የክሪስማስ አሻንጉሊቶችና የሕፃናት መጫወቻዎች ለደሃ እንደሚያከፋፍሉ አስታወቁ፡፡ ከኩባንያዎቹ አሻንጉሊቶችና የተለያዩ የሕፃናት መጫወቻዎች የተወረሱትም የገናን በዓል አስመልክቶ ኩባንያዎቹ የዋጋ ንረት ስለፈጠሩ ነው፡፡ ባለፈው ሳምንት መንግሥት ማንኛውም ቸርቻሪ በተለያዩ ሸቀጦች ላይ 30 በመቶ ቅናሽ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ አስተላልፎ የነበረ ቢሆንም፣ የሕፃናት መጫወቻዎችና አሻንጉሊቶችን የሚያከፋፍሉ ነጋዴዎች ዕቃዎቹን በመጋዘን እያከማቹና ወቅት እየጠበቁ ከ50 በመቶ በላይ ትርፍ ሲሸጡ መያዛቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል፡፡

*********

‹‹ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን››

ከጥንት ጀምሮ በቃል ሲነገር የሚኖረውን የአባቶቻችንን ተረት ብንመለከተው ብዙ የሚጠቅም ምክር እናገኝበታለን፡፡

‹‹ደባ ራሱን ስለት ድጉሱን›› እንደሚያመለክተው ክፉ ሥራ መሥራት ጉዳቱ ለሠሪው ነው፡፡ ንብ ሌላውን አጠቃሁ ስትል በመርዟ ትነድፋለች፡፡ እሷም ይህን ክፋተ ከሠራች በኋላ አንድ ደቂቃ ሳትቆይ ትሞታለች፡፡ የእሳት ራትም እንዲሁ መብራቱን ለማጥፋት ስትሞክር ተቃጥላ ራሷ ትጠፋለች፡፡ ትንኝ ሰው ዓይን ለማወክ ትገባና ሕይወቷን አጥታ ተጎትታ ትወጣለች፡፡ እንክርዳድን የዘራ እንክርዳድን ያመርታል ክፉ የሠራም ሰው በክፋቱ ይጠፋል፡፡ በሰው የሚድነው በምነቱና በቅንነቱ ብቻ ነው፡፡

አያሌው ተሰማ ዘብሔረ ጎጃም (የካቲት 20 ቀን 1935 ዓ.ም.)

****

‹‹የሚበሉ ነፍሳት ፈጽሞ የማንረሳው ምግብ››

የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው በባንጊ የሚኖሩ ወዳጆቻችን እኔንና ባለቤቴን ቤታቸው ጋብዘውናል።

እንደደረስን ‹‹ግቡ! ግቡ! መቼም ርቧችሁ መሆን አለበት›› አሉን። ገና ወደ ውስጥ ሳንገባ የቀይና የነጭ ሽንኩርት እንዲሁም የተለያዩ ቅመሞች ሽታ አወደን፤ የወዳጆቻችን ሞቅ ያለ ጨዋታም ከደጅ ይሰማል። ጋባዣችን ኤላም ስለሚቀርብልን ምግብ ታጫውተን ጀመር።

ኤላ ‹‹በማዕከላዊ አፍሪካ ለሚኖሩ ብዙ ሰዎች፣ ነፍሳት ዋነኛ የፕሮቲን ምንጭ ናቸው›› አለችን። ‹‹ነፍሳትን የምንበላው ግን ጠቃሚ እንደሆኑ ስለሚሰማን ሳይሆን በጣም ስለሚጣፍጡ ነው።›› አክላም ‹‹ዛሬ ማኮንጎ ማለትም አባጨጓሬ እንበላለን›› አለችን።

ይህ የሚያስገርም አይደለም። ነፍሳት ገበታ ላይ መቅረባቸው ለአንዳንዶች የሚያጓጓ ባይሆንም አንዳንድ ነፍሳት ከመቶ በሚበልጡ አገሮች ተወዳጅ ምግብ ናቸው።

‹‹ንቁ!›› (2012)

************

በገና አባት ዕቅፍ ሆኖ የሞተው ሕፃን

ባደረበት ሕመም በሕክምና ሲረዳ የቆየው የአምስት ዓመት ታዳጊ ልጅ በገና አባት እቅፍ ውስጥ ሆኖ ይሕወቱ ማለፉን ያሆ ኒውስ አስነብቧል፡፡ አጋጣሚ የብዙዎችን ልብ በሐዘን የሰበረ ነበር፡፡ የገና አባት ሆኖ 80 ፕሮግራሞችን የሠራው ኤሪክ ሺማትዚን የተባለው ግለሰብ ከጥቂት ሣምንታት በፊት ሕፃኑን እንዲጎበኘው ጥያቄ በቀረበለት መሠረት ሕፃኑ ያለበት ቦታ ሄዶ እንዳየው ተናግሯል፡፡ አጋጣሚው የተፈጠረበትን ሁኔታም እንዲህ አስታውሷል፡፡ ሕፃኑ የተኛበት ክፍል ገብቶ ያነጋግረው ጀመር፡፡ አሻንጉሊትም ሰጠው፡፡ ሕፃኑም ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ወደሚሄድበት ዓለም ሲደርስ ምን ማለት እንዳለበት የገና አባትን ጠየቀ፡፡ ሳንታም ‹‹አንደኛ የሣንታ ክለሙስ አገልጋይ ነኝ ብለህ ንገራቸው፡፡ ከዚያም ወደ ውስጥ ያስገቡኃል፤›› ሲሉ መለሱለት፡፡ ልጁም የገና አባትን ለማቀፍ እጁን ዘረጋ፡፡ መድረስ አልቻለም ነበርና ‹‹ሣንታ ትረዳኛለህ›› ሲል ጠየቀ፡፡ የገና አባትም ወደ ልጁ ተጠግቶ አቀፈው፡፡ የልጁ ሕይወትም ወዲያው አለፈ፡፡ አጋጣሚው የገና አባትን ጨምሮ በአካባቢው የነበሩ ልጆችን በእንባ ያራጨ ነበር፡፡ አጋጣሚውም የተፈጠረው በዚህ ሳምንት ቴንስ በተባለች የአሜሪካ ግዛት ውስጥ ነው፡፡  

**********

የዳግማዊ ምኒልክ 103ኛ ዓመት

በዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ታላቅ ሥፍራ ከሚሰጣቸው ነገሥታት በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ዳግማዊ ምኒልክ፣ ካረፉ ታኅሣሥ 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ላይ 103 ዓመት ሞላቸው፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ የሸዋው ንጉሥ ኃይለ መለኮት ልጅ ሲሆኑ፣ የተወለዱት ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም. በአንጎለላ (ሰሜን ሸዋ) ነበር፡፡ አፄ ዮሐንስ አራተኛ መጋቢት 2 ቀን 1881 ዓ.ም. መተማ ላይ ከተሰዉ ከሁለት ሳምንት በኋላ ምኒልክ ዘውዱን የተቀዳጁ ሲሆን፣ ጥቅምት 25 ቀን 1882 ዓ.ም. በእንጦጦ መንበረ ፀሐይ ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ሥርዓተ ንግሥ መፈጸማቸው ይታወቃል፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ዘመናዊ የአስተዳደር መዋቅር በመመሥረት የመጀመሪያውን የሚኒስትሮች ካቢኔ ያዋቀሩ፣ ከዓድዋ ድል በኋላ (1888 ዓ.ም.) ከውጭ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ባቡር፣ ባንክ፣ ሆስፒታል፣ ስልክ፣ ፖስታ የመሳሰሉት ማስገባታቸው ይታወቃል፡፡ 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች