ክፍል አንድ
በደጀኔ አሰፋ ዳምጠው
‹እንኳን ደስ አላችሁ› ለማለት የክልል ወይም የሆነ ርዕሰ መስተዳድር መሆንን የማይጠይቅ ከሆነ ከሁሉ አስቀድሜ የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ በመመዝገቡ ‹እንኳን ደስ አላችሁ እንኳን ደስ አለን› ለማለት እወዳለሁ:: ካልሆነ ግን ደስታዬን ለብቻዬ አጣጥመዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ገዳ ማለት ለኔ የማይዳሰስ ቅርስ ሳይሆን የሚነካ፣ የሚጨበጥ፣ አስተማሪና አሳታፊ የሆነ ዴሞክራቲክ ትውፊት ነውና፡፡ አሳታፊነቱ ደግሞ ሁሉንም ነው፡፡ ሕፃናትንና ወጣቶችን ጭምር በተወሰነ ዕድሜያቸው ደረጃ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ መሪነትን በሚመለከት በምርጫ ያከናውናል፡፡ ለዚያውም በተወሰነ የጊዜ ገደብ ታዲያ ‹ቢራ መጠጣትን› እንደ ባህላዊ ትውፊት አድርጋ ለማስመዝገብ እንደታገለቸው ቤልጅየምም ሆነ ‹ቂጣ ጋግሮ ከጎረቤት ጋር መካፈልን› ከማይዳሰሱ ቅርሶች ተራ ማስመዝገብ እንደቻለችው አዘርባይጃን ሳይሆን ገዳ ማለት ከቂጣ የዘለለ፣ አገራዊ ብቻ ሳይሆን አኅጉራዊ ፋይዳና በተለይም ለአፍሪካ ፖለቲካ ብዙ ምልከታና ትርጉም ያለው፣ የሚዳሰስና የሚነካ ባህል ነው፡፡ የሚማርበት ከተገኘ!
ስለዚህ የገዳ ሥርዓት አሁን በመመዝገቡ ድቤ ከመደለቅና የተለየ ሥራ ተሠርቶ እንደመጣ ከመለፈፍ ይልቅ፣ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ቀደም ብሎ ለምን አላስመዘገብነውም በማለት ልንቆጭና ለወደፊቱ ሌሎች የአገራችንን ቅርሶች ለማስመዝገብ በሚደረገው ሒደት ትምህርት መውሰድ ነው የሚገባን፡፡ በተረፈ የገዳ ሥርዓት መመዝገቡ ለራሱ ለዩኔስኮም ነው የሚጠቅመው፡፡ ካልሆነማ ቂጣ ጋገራን እየዞረ ይመዝግባ! አለቀ! ብቻ በኢሬቻ በዓል ስለተከሰተው ነገር ምንም ሲሉ ያልሰማኋቸውና የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ መመዝገቡን ተከትሎ በቴሌቪዥን መስኮትም ሆነ በቴክስት ሜሴጅ ‹‹እንኳን ደስ አለህ›› የሚሉኝን ተሿዋሚዎችን ‹‹እንኳን አብሮ ደስ አለን›› ለማለት እፈልጋለሁ፡፡ ከትዝብት ጋር! እዚህ ላይ ግን የክልል መስተዳድርም ባልሆን አሜሪካ 41ኛውን ሳይሆን 45ኛውን ፕሬዚዳንቷን እንደመረጠች አልስተውም፡፡ ገዳ በመመዝገቡም እየዘለሉ የነበሩ አባ ገዳዎች የደስ ደስ ወተት ቢጋብዙንም፣ ላሞቹ ከፊንፊኔ ውጪ ደጅ ላይ በመሆናቸው መጠጣት አልቻልንም፡፡ ምነው “ቴሌ ፓቲ” እንደሚባለው “ቴሌ ሚልኬ” ቢኖር አያስብልም? መልካም ንባብ!፡፡
እንደሚታወቀው በአገራችን ከሚከበሩ ዓመታዊ ክብረ በዓላት መካከል በዋናነት በኦሮሞ ማኅበረሰብ የገዳ ሥርዓት አካል የሆነው የኢሬቻ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓል አንዱ ነው፡፡ ይሁን እንጅ በዕለተ ሰንበት መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ሆራ አርሰዴ ሐይቅ በደማቅ ሁኔታ ሊከበር ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው የኢሬቻ በዓል ከወትሮው የተለየ ሁኔታን አስተናግዶ አልፏል፡፡ በታዳሚውና በመንግሥት መካከል በተፈጠሩ አለመግባባቶች ነገሮች መልካቸው በመቀየሩ የዜጎችን ሕይወት የቀጠፈ ክስተት ሆነ፡፡ በመሆኑም በዓሉ የምሥጋና በዓል (Thanks Giving Day) መሆኑ ቀርቶ የሦስት ቀናት ብሔራዊ ሐዘንን የጠራ እጅግ አሳዛኝ ክስተት ለመሆን በቃ፡፡ ክስተቱ ካለፈ እነሆ ድፍን ሁለት ወራትን አስቆጠረ፡፡ “ተጠያቂው ማን ነው?” የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ክስተቱ ግን አስደንጋጭ ከመሆኑ ባሻገር፣ የአብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ልብ የሰበረና የህሊና ጉዳትን የፈጠረ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ ክስተትም ዙሪያ ብዙ ተብሏል፡፡ ሁሉም እንደገባው መጠን ትንታኔ ሰጥቷል፡፡ ተናጋሪው ከሚናገርበት ጎራ አንፃር ለሚፈልገው ዓላማ ለማዋል ሞክሯል፡፡ ገሚሱም በልቡ የሆነ ነገር ብሎ ይሆናል፡፡
ጽሑፉም በሚከተሉት ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኩራል፡፡ በኢሬቻ በዓል መስተጓጎልና የዜጎች ሕይወት መጥፋትን በሚመለከት ሲቀርቡ የነበሩ ወቅታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፤ የተላለፉ የሐዘን መግለጫዎችና በአጠቃላይ የታዩ መስተጋብሮችን በወፍ በረር ይቃኛል፡፡ በአንፃሩ ክስተቱ ካለፈ ከሁለት ወራት በኋላ የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ በመመዝገቡ የተላለፉ የደስታ መግለጫዎችን ይዳስሳል፡፡ በየመሀሉም ተያያዥ ጉዳዮችን በወግ መልክ በመጠረቅ የመስከረም 22ቱ ‹‹ክስተት እንደ ችግር ብቻ ወይስ ትምህርት ሊወሰድበት የሚችል አጋጣሚ?›› የሚል መሠረታዊ ጥያቄን ለውይይት ያቀርባል፡፡ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ባላቸው ጉዳዮች ላይ ደግሞ በተለያዩ የጽሑፉ ክፍሎች ዕይታውን ያካፍላል፡፡ የግል ዕይታዬን እነሆ!፡፡
የኢሬቻ ክስተትን ተከትሎ ኢቢሲ 1 ያቀረባቸው ፕሮግራሞች ምን ይዘት ነበራቸው? የሚለውን በጨረፍታ ለመዳሰስና ይኼንኑ የበለጠ ለማሳየት አንድ ምናባዊ ሰው ልሳል፡፡ ይኼ ምናባዊ ሰው የኢሬቻን አሳዛኝ ክስተት ያልሰማ ወይም በወቅቱ እዚህ ያልነበረ ነው እንበል . . . ቢሆንም ግን ከዚያ በኋላ በወቅቱ ይተላለፉ የነበሩ የሐዘን መግለጫዎችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን የመከታተል አጋጣሚ ነበረው ብንልና ከእነዚህ ፕሮግራሞች ምን ሊረዳ ይችላል? የሚለውን ልገምት፡፡ እንደኔ ዕይታ ከሆነ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ ሲያይና በሚያሳዝን ክላሲካል የታጀቡ በግራፊክስ የተቀረፁ እጥር እጥር ያሉ ሻማዋች እየበሩ ሲመለከት ይህ ሰው አገሪቱ ውስጥ ሐዘን እንዳለ በትክክል ይገነዘባል፡፡ ነገር ግን ይኼ ሐዘን በምን ምክንያት ነው የተፈጠረው? የሚለውን ጥያቄ ኢሬቻ በዮኔስኮ ባለመመዝገቡ እንደሆነ እንጂ ሕይወታቸውን ባጡ ዜጎች ነው ብሎ ለማሰብ የሚከብደው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በቴሌቪዥን የቀረቡት አስተያየት ሰጪዎችም ሆኑ ዜናዎች በሙሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ ሲገልጹ የነበሩት ኢሬቻ በዮኔስኮ እንዳይመዘገብ በመደናቀፉ እጅጉን እንዳዘኑ፣ ይህም አገርን በጥልቅ የጎዳ አሳዛኝ ክስተት እንደሆነና የአገርን ገጽታ እንደሚያበላሽ፣ ቱሪዝምን እንደሚጎዳና እንዲህ ያደረጉትን አካላት መንግሥት ተጠያቂ እንዲያደርጋቸው በሲቃ እየተማፀኑ ነበር ማይኩን ተራ በተራ ሲቀባበሉ የነበሩት፡፡
ለነገሩ ከተለያዩ ክልሎች የቀረቡት አስተያየት ሰጪዎች ተመሳሳይ ነገር ከመናገራቸው የተነሳ አንድ ወዳጄ “ሁሉም የሚናገሩትን ተጽፎ ነው እንዴ የተሰጣቸው?” አለኝ፡፡ እኔም ‹‹ይኼንን አላቅም፡፡ ሆኖም ግን ከደቡብ ክልል አስተያየት የሰጠውን ሰው በድሬዳዋው ፕሮግራም ያየሁት መስሎኛል፡፡ ይኼም ቢሆን ግን የኤዲቲንግ ችግር እንጂ ሌላ አይሆንም?” ብዬ ሳልጨርስ እንዲህ አለኝ፡፡ ‹‹ይኼንንማ ድሮም ለምደነዋል፡፡ እንዲያውም ካስታወስክ በአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የፌስቡክና የትዊተር ገጽ የሌላ አገርን የባቡር መስመር ከወልዲያ እስከ ናምን እየተገነባ ያለው ሐዲድ ብሎ ለጥፎ ነበር፡፡ በተመሳሳይም የሌላ አገርን ግድብ በኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው ምን የሚባል ግድብ ብሎ ለጥፎ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ኧረ ይኼ የሌላ አገር ሐዲድና የሌላ አገር ግድብ ነው ብለው ሰዎች በመነዝነዛቸው ይቅርታ ጠይቋል?” አለኝ፡፡ ከዚያም ንግግሩን ዘለግ አድርጎ፣ ‹‹ይቅርታ አጠያየቁ ግን ትንሽ አስቂኝ ነበር፤›› አለ፡፡ ‹‹መሥሪያ ቤቱ ምንም እንኳን የሚሠራቸው ዜናዎች ትክክል ሊሆኑ ቢችሉም የፎቶ ክምችት እጥረት ስለነበረበት ደስ ደስ የሚሉ ማራኪ ፎቶዎችን ከሌላ ቦታ ኢምፖርት በማድረጉ ነው፤›› አለኝና በግርምት ተለያየየን፡፡
ከተለያየን በኋላ ግን ከኢሬቻ ክስተት ወዲህ በሕይወቴ ውስጥ አንድ ጥያቄ ተፈጠረብኝና መልስ ሳላገኝለት ይኼው አዕምሮዬን እንደጨመደደኝ ከእኔው ጋር ይኖራል፡፡ ይኼም በዮኔስኮ ከመመዝገብ ወይም አለመመዝገብና ከዜጎች ሕይወት የትኛው ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል? የትኛውስ ነው የበለጠ አሳዛኝ ሊሆን የሚገባው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ እንኳን ኢሬቻ ‹‹ገና ዘንቦ ተባርቆ›› እንደሚባለው ማለትም ኢሬቻ (ገዳ) ገና ተመዝግቦ፣ ለዓለም ሕዝብ ተዋውቆ፣ ሰው መምጣት ቢጀምርና የቱሪዝም ፍሰትን በተወሰነ ደረጃ ሊያሳድግ ቢችል፣ ከዚያም ለአገሪቱ ተጨማሪ ገቢን ወይም ሌሎች ጥቅሞችን ማስገኘት ቢችል . . . ወዘተ፣ እንደማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ መነሳት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ አይደለም ኢሬቻ (ገዳ) ሥርዓት ብዙ ያልተሠሩ የቤት ሥራዎች ያሉበትና በዓመት አንድ ቀን ብቻ የሚከበር በዓል ቀርቶ በአገሪቱ የሚገኙ የተመዘገቡም ያልተመዘገቡም ቋሚና የማይዳሰሱ ወካይ የዓለም ቅርሶችና መስህቦችን በሙሉ ጨምሮ፣ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሚገኘው አጠቃላይ ገቢ ለብሔራዊ ጠቅላላ ምርት (GDP) የሚያበረክተው ድርሻ እዚህ ግባ የማይባል ነው፡፡ ይኼንን ስናነሳ ጎረቤታችን ኬንያ ባትሰማን ደስ ይለኛል! ግን ኧረ ለመሆኑ ከዘመናት በፊት በዩኔስኮ በተመዘገቡት እነ ቅዱስ ላሊበላ፣ አክሱም ጽዮን፣ ጎንደር ፋሲለደስ፣ ሶፍ ኦማር ዋሻና ሌሎች ቋሚ ከሆኑ የቱሪዝም መስህቦቻችን በሚገኝ ትሩፋት ሙሉ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርና ቅርሶቹ በሚገኙበት አካባቢ የሚኖረውን ማኅበረሰብ እንኳን በቀን ሦስት ጊዜ እንዲበላ ካላደረጉት፣ የኢሬቻ (ገዳ) በዮኔስኮ አለመመዝገብ (እንዲያውም የመመዝገብ ዕድሉ በዚያ ጊዜ ሙሉ ለሙሉ ተሟጦ ሳያልቅ ለዚያውም አሁን ተመዘገበ እሰይ! ምን ይውጣቸው?!) እንዲያ ከወገኖቻችን ሞት በላይ አሳዛኝ ሆኖ መቅረቡ ሌላ ሕመምን ይፈጥራል፡፡
እዚህ ላይ የኮንሶ ቴሬሲንግን ያልጠቀስኩት በቅርብ ከተመዘገቡት ቅርሶች ስለሚመደብ እንጂ በሌላ አይደለም፡፡ ብቻ የዜጎች ሕይወት ዋጋው ስንት ነው? በፈጣሪ መልክና አምሳል የተፈጠረው የሰው ልጅ ተመኑስ ስንት ነው? የሚለው ነጥብ ስለሚያንገበግበኝ እንጂ . . . መቼም ትረዱኛላችሁ ቱሪዝም ማደግ የለበትም ወይም የኢሬቻ (ገዳ) ሥርዓት በዩኔስኮ መመዝገብ ጠቀሜታ የለውም እያልኩ እንዳለሆነ፡፡ ምክንያቱም አገሬ በየትኛውም መስክ መበልፀጓን በቅን ልብ ከሚሹና የበኩላቸውን ጥረት ከሚያደርጉ ወገኖች መካከል ልመደብ የምችል ዓይነት ሰው ነኝ፡፡ በነገራችን ላይ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለ ዕዳ አይቀበለውም” እንዲሉ የዜጎችን ዋጋ የሚተምነው መንግሥት በመሆኑ፣ ሌሎች አገሮች ዜጎቻችንን የሚያስተናግዱበትም ሁኔታ በዚሁ በወጣው ተመን ልክ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ‹‹አሞሌነት ብቻውን አያስከብርም፡፡ አሞሌ ነህ መባልንና በባለቤቱ መከበርን ይሻል›› ካልሆነ ግን ዜጎቼን እንዲህ አደረጋችሁብኝ ብሎ ለመወቃቀስ አያመችም፡፡ ወይም “ለሕይወትህ ዋጋ ስጥ” የሚለው መሪ ቃል ‹‹የስንት›› የሚልን ጥያቄ ማስነሳቱ አይቀርም፡፡ ብቻ ከዋጋ ጋር በተያያዘ ‹‹የአንድ ኢትዮጵያዊ ዋጋ ከአፄ ሚኒልክ እስከ ኢሕአዴግ›› በሚል ርዕስ አጭር መጣጥፍ በቅርብ ጊዜ (Coming Soon) ለፊልም ብቻ ያለው ማነው?፡፡
ወደ ዋና ጉዳዬ ልመለስ፡፡ ከላይ እንደተጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎች የሚመስሉ ሌሎች ደግሞ ወረፋቸውን ጠብቀው የቀረቡ ነበሩ፡፡ እነዚህኞቹ ግን ሲታዩ እንደ አስተያየት ሰጪ የሚያደርጋቸው ሆነው “አዋቂ ተቺ”ነትም የሚነካካቸው ሦስት ብሎገሮች (ጦማሪያን) ነበሩ፡፡ በእኔ ግምት ከሦስት ብሔሮች የተወጣጡ ይመስሉኛል፡፡ ይሁን እንጂ በወቅቱ የቀረበው ዝግጅት የብሔር ብሔረሰቦች ፕሮግራም ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ እንዲህ የሚል ጥያቄ ፈጠረብኝ፡፡ በአገሪቱ ካሉ ጦማሪያን መካከል (ለዚያውም ጦማሪያን በሚነቀፉበት ወቅት) እነዚህ ሦስት ጦማሪያ በምን መሥፈርት ተመርጠው በመንግሥት ሚዲያ እንደቀረቡና ሌሎች ጦማሪያንን የመዝለፍም ሆነ የመተቸት መብትን እንዴት ሊጎናፀፉ ቻሉ? የሚለው ግልጽ አለመሆኑ መገመት ግን ይቻላል፡፡ “መደገፍ” ሳይሆን አይቀርም የሚሉ ወገኖች አይጠፉም፡፡ “መደገፍ” ማለት “መድገም” ማለት ከሆነ ግን መቃወም በስንት ጣዕሙ! ያስብል ይሆን? እኔ እንጃ . . . ብቻ የሰነዘዋቸውን ዋና ዋና ሐሳቦች በጥቂቱ ላካፍላችሁና ትዝብቴን ልቀጥል፡፡
አንደኛው እንዲህ አለ፣ “እነ ጃዋርና መሰሎቹ የውጭ ተልዕኮን ለማስፈጸም ነው እንዲህ የሚረባረቡት፡፡ ይኼ ደግሞ ሕዝብን እንደ መናቅ ነው?” ብሎ እርፍ፡፡ እንደ እኔ ዕይታ ከሆነ ግን የውጭ ተልዕኮን ለማስፈጸም ነው በማለት የቀረበው ትችት በማን ተመዝኖ? በየትኛው ወገን ታይቶ? የሚል ጥያቄን ያስነሳል፡፡ የፍሬ ጉዳዩን ትክክለኝነት ወይም ስህተት እንደታየበት መነፅር (ጎራ) ሊወሰን የሚችልበት አጋጣሚ ስላለ ማለት ነው፡፡ ከዚያ በላይ ግን “ይኼ ደግሞ ሕዝብን መናቅ ነው” ያለው ሐሳብ የተገላቢጦሽ ሆኖ ይታየኛል፡፡ ምክንያቱም ለአኔ ሕዝብን መናቅ ብዬ የማስበው ሕዝቡ የራሱ ጥያቄ የለውም? ይልቅ በጃዋርና መሰሎቹ ነው የሚነዳው? የሚለው ሐሳብ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ብሎ መደምደም ደግሞ ምንም እንኳን ሊጫወት የሚችለው የራሱ ሚና ቢኖርም፣ ሕዝቡ የራሱ የሆነ ሕጋዊና ፍትሐዊ ጥያቄ የለውም ወደሚል ስለሚያዘነብል አግባብነት ላይኖረው ይችላል፡፡ ምክንያቱም ይኼኛው አካሄድ በሌሎች ወገኖች ዘንድ የሚሰጠው ትርጉም ሌላ ሊሆን ስለሚችል፡፡ ይኼም ወደ መንግሥት እየመጡ ያሉ የሕዝብ ጥያቄዎችን በመልክ በመልክ ሰድሮ ለሕዝቡ የሚሆን እውነተኛና አጥጋቢ መልስ በየደረጃው ለመስጠት ወይ አልተዘጋጀም ወይ አልፈለገም የሚል ይሆናል፡፡ ይኼ ዕይታ ትክክል ይሁንም የተሳሳተ ልብ ማለቱ ግን ለሁሉም ወገን ጠቃሚ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡
ሌላኛዋ ጦማሪ ያነሳችው ሐሳብ ደግሞ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ጃዋር በትዊተር ገጹ ቢቢሲን ተሳደበ፣ ሲኤንኤን ነቀፈ፣ . . . ምናምን ካለች በኋላ ለምን እነዚህን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችን ይሳደባል?›› ብላ በመጠየቅ ለማሳቀቅ የሞከረች ያስመስልባታል፡፡ ይኼም ጦማሪዋ ጦማሪ መሆኗ ቀርቶ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተቆርቋሪ ተቋም በኢትዮጵያ ተወካይ ሊያስብላትም ላያስብላትም ይችላል፡፡ ለእኔ ግን ሌላ ወሳኝ ጉዳይ አንስታ በአመክንዮ ላይ የተመሠረተ ሙግት ብታቀርብ ውኃ የመቋጠር ዕድል ነበራት እላለሁ፡፡ ሦስተኛው ጦማሪ ደግሞ እንዲህ አለ፣ ‹‹እኛ ጃዋርን ነው የምንከተለው፤›› እንዲህ ሲል ትንሽ ደንገጥ ብዬ ነበር፡፡ ምክንያቱም መንግሥት አምኖት ሕዝብ ፊት ያቀረበው ብሎገር እሱን እከተላለሁ ሲል ማለቴ ነው፡፡ በልቤ ግን ምንም አላልኩም! ቀጠለና ‹‹እሱ (ማለትም ጁ . .) የሚጽፈውን ነገር እግር በእግር ስንከተለው ነበር ፕላን “A” ፕላን “B” አለን ሲል ነበር . . . ›› ብሎ ተናገረ፡፡ ይኼኛው አስተያየት ለእኔ የሚያሳየኝ ነገር ቢኖር እነዚህ ጦማሪያን አየር መቃወሚያ የደገኑ ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት ያሰፈሰፉ እንጂ የራሳቸው አውሮፕላን (አጀንዳ) ያላቸው እንዳልሆኑ ነው፡፡
ከሦስቱ ብሎገሮች የተረዳሁት ሌላው ነገር ቢኖር አሸባሪ አሊያም የጥፋት ኃይሎች ተብለው በመንግሥት የተፈረጁ ግለሰቦችን ወይም የሌላ ጎራ አክቲቪስቶችን እንደሚከተሉ ነው፡፡ እዚህ ላይ ማንሳት የፈለግኩት ለምን የእነሱ ተከታዮች ሆኑ የሚለውን አይደለም፡፡ ምክንያቱም የባላጋራውን የሙግት ሐሳብ የማያውቅ የራሱን መከራከሪያ ፍሬ ነገር በሚገባ አጥርቶ አያውቅም የሚል አባባል አለ፡፡ ወይም በእንግሊዝኛ ”Those who do not know the arguments of their opponents, do not know their own effusively” ይባላል፡፡ የእኔ ጥያቄና አትኩሮት ግን እነዚህ በሚዲያ የቀረቡት ጦማሪያን ለተጻፉ ጽሑፎች መልስ ከመስጠት በዘለለ በራሳቸው የተቀረፀ፣ የሚያምኑበትና የሚያራምዱት የራሳቸው የሆነ አጀንዳ የላቸውም ማለት ነው? የሚለው ነጥብ ነው፡፡
ለነገሩ ስለነዚህ ጦማሪያን አነሳሁ እንጂ እንኳንስ እነዚህ በግለሰብ ደረጃ ያሉት ቀርቶ መንግሥትስ ቢሆን አጀንዳ ቀርፆ ሕዝባዊ ንቅናቄን ከመፍጠር አንፃር ምን ያህል ውጤታማ ነበረ? ምን ያህልስ አበክሮ ይሠራል? ብንል የምናገኘው መልስ እምብዛም ነው፡፡ ‹‹ሰፊ ክፍተት አለ›› የሚል ይሆናል፡፡ ተቀዳሚ ሥራው “አጀንዳ መቅረፅ” እና ሕዝባዊ ንቅናቄን መፍጠር ሳይሆን፣ ለሚነሱ ጉዳዮች ምላሽ መስጠት ነው የሚመስለው፡፡ ከዚህ አንፃር አንድ ለእናቱ ለሆነው ሕዝባዊና ብሔራዊ ፕሮጀክታችን የህዳሴው ግድብ እንኳን በተለይ ሁከቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ተገቢውን ሽፋን ሰጥቶ ሲንቀሳቀስ አልነበረም፡፡ ስንት ጊዜ ሆነው በተጀመረበት ግለት ለማስቀጠል፣ የማስተዋወቁን፣ የማስተባበሩንና ሕዝባዊ መነሳሳትን የመፍጠር ቁልፍ ተግባራትን ቸል ካለ፡፡ ብቻ መንግሥት የራሱ አጀንዳ ላይ ቢያተኩር ምንኛ በተሻለ ሥራዎችንም በግብር ይውጣ አሊያም በሰሞንኛ (Campaign Mentality) ከመከወን አባዜ ወጥቶ የነገሮችን “ከ እስከ” ሥልታዊ በሆነ መንገድ ተልሞ አንዳች ሳያስተጓጉል ቢተገብር ምንኛ ውጤታማ በሆነ እላለሁ፡፡
ይኼንን የበለጠ ለመግለጽ በወቅቱ ካዘንኩባቸው ጉዳዮች አንዱን ልጥቀስ፡፡ መንግሥት ሁሌም መንግሥት ነው፡፡ ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ፡፡ ይኼም ሚዲያውን በመጠቀምም ሆነ በመረጠው አደረጃጀት ከሕዝቡ ጋር መገናኘትና መቆራኘት ሲችል (በነገራችን ላይ ኢሕአዴግ 17 ዓመታት በትጥቅ፣ 25 ዓመታት በከተማ፣ በአጠቃላይ 42 ዓመታት የፖለቲካ ታሪክ እንዳለው ልብ ይሏል) ትልቅና ሥልታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ሊያተኩርና በዋናነት የራሱን አጀንዳ ማራመድ ሲገባው እንዲህ ወርዶ፣ ወርዶ፣ ወርዶ . . . ጦማሪያንን ቀምሮ፣ አስተያየት ሰጪዎችን ሰድሮ፣ ጎምቱ የትግል ጓዶችንና ትንታኔ ሰጪ ሊህቃንን ወድሮ፣ ዶክመንታሪ ሽፋን ሰጪ ፊልሞችን ተጠቅሞ ከአንድ በዕድሜው ገና ለጋ ከሆነና የተደራጀ ፓርቲ እንኳን ካልሆነ ግለሰብ ለዚያውም በዚህ አገር ከማይኖር ሰው ጋር የዚህ ዓይነቱን የፕሮፓጋንዳ ጦርነት መክፈቱ ገርሞኛል፣ አሳዝኖኛል፡፡ መንግሥት የሚባለውን ትልቅ ‹‹ጽንሰ ሐሳብም›› የሆነ ‹‹ሰውዬ›› አድርጌ እንድሥለው ከማድረጉ በተጨማሪ ከዚህ በፊት የነበረኝንም ግምት መልሼ እንድጠይቅ አስገድዶኛል፡፡ “ኢት ኢዝ ፒቲ!” እንደሚሉት፡፡
የበለጠ አሳዛኝ ሆኖ ያገኘሁት ደግሞ መንግሥት እነዚህ ሁሉ ሰዎችና መንገዶች እንኳን ተጠቅሞ አገርን ማረጋጋት አለመቻሉ ነው፡፡ በተለመደው የሕግ አግባብም ቀውሱን መቆጣጠር ባለመቻሉም አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንድትተዳደር ዳረጋት፡፡ ከሌሎች ዕርምጃዎችና ክልከላዎች በማይተናነስ ሁኔታ ማኅበራዊ ድረ ገጾችን መዝጋት እንደ ሥልት ተጠቀመ፡፡ ከዚያም “በኢቢሲ ሳሳያችሁ ካልሆነ በቀር . . . እነዚህ አሸባሪ የተባሉ ሰዎችንና ሚዲያዎችን ማየትም ሆነ መስማት፣ የእነሱን ገጽ ላይክ፣ ሼር ወይም ፎሎው ማድረግ ክልክል ነው . . .” ብሎ አወጀ፡፡ በዚህ ደግሞ ጥቂት ትዝብት እንጂ ቅሬታ የለኝም፡፡ ምክንያቱም አገሬ እንድትረጋጋ፣ ለውጦችም በሰከነ መልክ እንዲከወኑ እንጂ የአንድም ኢትዮጵያዊ ደም እንዲፈስ ስለማልፈልግ፡፡ ትዝብቴ ደግሞ ይኼንን እንዳናደርግ መንግሥት ራሱ ከከለከለ ለምን በኢቢሲ ያሳየናል የሚል ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ስለእነሱ መስማትም፣ ማየትም፣ ማወቅም፣ የማይፈልጉ ዜጎችን ነፃነት የተጋፋ ይመስለኛል፡፡ ብቻ መንግሥት እንደሚለው ከሆነ ይኼ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሆነ ጊዜ ላይ መነሳቱ አይቀርም፡፡ መንግሥትም ዳር ዳርታን እያሳየ ነው፡፡ የተነሱም ክልከላዎች አሉ፡፡ አዋጁ ሙሉ በሙሉ በሚነሳበት ወቅት ማኅበራዊ ድረ ገጾች መከፈታቸው አይቀርም፡፡ የተጀመረም ይመስለኛል፡፡ ታዲያ አገሪቱ አልፋበት የነበረቸው አጣብቂኝ የፈተና ጊዜ ተመልሶ እንደማይመጣ መንግሥት ምን ዋስትና አለው? የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ይሆናል፡፡
እንደኔ ዕይታ ከሆነ በዚህ ወቅት መንግሥት ቆም ብሎ ይኼ ጉዳይ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? ከየት መጣ? መንስዔውስ ምንድነው? አባባሽ ምክንያቶችስ ምን ምን ናቸው? የሚሉ ስትራቴጅካዊ ጥያቄዎችን እንደሚገባ መመርመርንና መመለስን እንደ ቁልፍ ተግባሩ በመውሰድ፣ ችግሮችን እንደ መስፈንጠሪያ መልካም አጋጣሚ ሊጠቀምባቸው የሚገባው ይመስለኛል፡፡ ይኼም በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት ዕውን በዚህ በተጠቀሰው ግለሰብ ብቻ የሚመራ ነበርን? ወይስ መንግሥት ከሕዝቡ ጋር የተሸዋወደበት ጉዳይ ይኖር ይሆን? ወይስ ኢሕአዴግ እንደ ፓርቲ በውስጡ ለዓመታት ሲነሱ የነበሩ ነገር ግን በተለያየ መንገድ ሲመለሱ አሊያም ሲዳፈኑ የቆዩ ፓርቲን መሠረት ያደረጉ የኃይል ሚዛን ጥያቄዎችና አለመግባባቶች አብጠው በመፈንዳታቸው ይሆን? ወይስ ናዳው ከፓርቲው ፍጥነት በላይ ሳይገመት በደራሽ መልክ በመምጣቱ? ወይስ በተያያዙና በተቆላለፉ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ሳቢያ የተፈጠሩ? አሊያም የተራገቡ? መልሱ ምንም ይሁን ምን አንድ ነገር ማድረግን የግድ ይላል፡፡ በችግሮቹ ዙሪያ ጥልቅ ፍተሻ እውነተኛ መፍትሔና አፋጣኝ ምላሽ መስጠትን፡፡ ካልሆነ ግን የዚህን ያህል ጊዜና ወጪ ወስዶ እየተከናወነ ያለው ጥልቅ ተሃድሶ ዘለቄታዊ የሆነ አገራዊ ፋይዳ ያመጣል የሚል ግምት የለኝም፡፡
በዚህ በተጠቀሰው ግለሰብም ሆነ ሌሎች አክቲቪስቶች ምክንያት ነው ቀውሱ የመጣው ተብሎ ከታመነ ግን ለምን “መሪ አልባ እንቅስቃሴ” ሲባል ከረመ የሚል ትዝብትን ከመፍጠሩ ባሻገር፣ እንደ አገር ግን የከፋ ዝቅጠት ይመስለኛል፡፡ በተለይም ኢሕአዴግ በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባች ኢትዮጵያን መሥርቻለሁ ብሎ በየምኩራቡ የሰበከውን ስብከት ፉርሽ ስለሚያደርግና በፅኑ መሠረት ላይ ተገነባች የተባለችው አገር የት አለች? የሚል ወሳኝ ተጠይቅን ስለሚያስነሳ ነው፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ወራት የታየችው ኢትዮጵያ በፅኑ መሠረት የተገነባችው ሳይሆን በሁለት መስመር የትዊተር ወይም የፌስቡክ መልዕክት ለመፍረስ የምትንገዳገድ ኢትዮጵያ ነበረች፡፡ ይኼን ያልኩት እኔ ሳልሆን በመንግሥት ዘንድ ያለውን አመለካከትና ዝንባሌ በዚያን ወቅት በራሱ ሚዲያ ከሚቀርቡት ዝግጅቶችና መልዕክቶች በመረዳት ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይኼ አስተሳሰብ አሁንም ካለ በጥልቀት የመታደሱን ሒደት የበለጠ ጥልቅ እንዲሆን፣ የአመራሩን ቁርጠኝነትና ተራማጅነትን የሚጠይቅ ይሆናል፡፡
እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት “ለምን አትተውትም” በማለት ፋና ብሮድካስቲንግ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የሞገተችው ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ ነበረች፡፡ ምኑን መሰላችሁ ወ/ሮ ሰሎሜ ያነሳቸው? ኢቢሲ 1 ከዜና በኋላ እንደ ቋሚ ፕሮግራም ጃዋርንና መሰል አቋም አላቸው የተባሉ ግለሰቦችን በሚመለከት እንደ ተወዳጅ ተከታታይ ድራማ ዓይነት ማቅረቡን ነው፡፡ ምክንያቱም ይቀርቡ የነበሩት የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ይኼ ግለሰብ የት እንደሄደ? ከእነማን ጋር እንደዋለ? ዕቅዱ ምን እንደሆነ? (በነገራችን ላይ ጂቲፒ 2 እንደ አገራዊ የልማት ዕቅድ የጃዋር ዕቅድን ያህል የአየር ሽፋን የተሰጠው አይመስለኝም) የት ስብሰባ እያካሄደ እንደሆነ (እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም የሆነ ልዑክ ቡድን)፣ ከማን ጋር ፎቶ እንደተነሳ? . . . ወዘተ ቀን በቀን ሲቀርብ ማየት ኢቢሲ የህዳሴና የብዝኃነት ድምፅ መሆኑን ዘንግቶ እንደ ፓፓራዚ ሲደክም ነበር የሰነበተው ያስብላል፣ ላስተዋለው፡፡ ነገር ግን “አቢሲ የህዳሴና የብዝኃነት ድምፅ ነበረ እንዴ?” ብላችሁ ከጠየቃችሁኝ መልስ የለኝም፡፡ በሙያው ብዙ ልምድ የለኝምና፡፡
የዚህን ጽሑፍ ተከታይ ክፍል በሚቀጥለው ሳምንት እንዲያነቡ በአክብሮት እጋብዛለሁ፡፡ የሳምንት ሰው ይበለኝ፣ ይበላችሁ፣ አሜን!
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡