Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በጅማሮው ኪሳራ የገጠመው ራያ ቢራ በሁለተኛው ዓመት ​በአትራፊነት መጓዝ እንደጀመረ ገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ዓምና 104 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዝግቧል

ራያ ቢራ አክሲዮን ማኅበር ምርቱን ለገበያ ማቅረብ የጀመረበትን የመጀመሪያ ዓመት በኪሳራ አጠናቅቆ አዲሱን በጀት ዓመት ግን በአትራፊነት ጉዞ መጀመሩን ገለጸ፡፡

አክሲዮን ኩባንያው የ2008 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ለባለአክሲዮኖቹ ቅዳሜ ታኅሳስ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. ባስታወቀበት ሪፖርቱ 104.9 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንዳስመዘገበ ይፋ አድርጓል፡፡

የአክሲዮን ማኅበሩ ቦርድ ሊቀመንበር ሌተና ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሣይ ባቀረቡት ሪፖርት መሠረት በበጀት ዓመቱ በዕቅድ ተይዞ የነበረው የትርፍ መጠን 102.6 ሚሊዮን ብር ነበር፡፡ ሆኖም 104.9 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደተመዘገበ የኩባንያው የሒሳብ መዝገብ እንደሚያሳይ ጠቅሰው፣ በበጀት ዓመቱ ለተመዘገበው ኪሳራ ዋናው ምክንያት የሽያጭ መጠኑ ከታቀደው እጅግ በማሽቆልቆሉና ሥራ ላይ የዋለው የፋብሪካው የማምረት አቅም በ38 ከመቶ ብቻ በመወሰኑ ነው ብለዋል፡፡

የዓመቱ የሽያጭ መጠን ዝቅተኛ በመሆኑና ሥራ ላይ የዋለው የማምረት አቅም ዝቅተኛ መሆን በበጀት ዓመቱ ትርፍ ሊያስገኝ ባለመቻሉ ኩባንያው ለባለአክሲዮኖች የሚያከፋፍለው የትርፍ ድርሻ እንደማይኖር ተነግሯል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ በበጀት ዓመቱ ላጋጠመው ኪሳራ ብሎም በዕቅድ ያስቀመጠውን ግብ ሊያሳካ ካልቻለባቸው ምክንያቶች አንዱ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ በቢራ ጥራት ላይ የተከሰተ መዋዠቅ ትልቁን ድርሻ ይይዛል ተብሏል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም. ይጀምራል ተብሎ የነበረው የድራፍት ምርት ሽያጭ በተለያዩ ቴክኒካዊ ምክንያቶች ዘግይቶ ጥር ላይ መጀመሩ የታቀደው ስላለመሳካቱ ሌላው ምክንያት ነው፡፡ የምርቱ ዋነኛ የገበያ መዳረሻ ይሆናል ከተባለው ከሰሜን ኢትዮጵያ ውጭ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የተደረገው እንቅስቃሴ ውስን መሆንም፣ ፋብሪካው የመጀመሪያውን ዓመት በኪሳራ እንዲያሳልፍ ማስገደዱን ከቀረበው ሪፖርት መረዳት ተችሏል፡፡

በ2008 በጀት ዓመት ኩባንያው 6.1 ሚሊዮን ሳጥን የጠርሙስ ቢራና 219,730 የድራፍት ቢራ ለማምረት አቅዶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ማምረት የቻለው 2.7 ሚሊዮን ሳጥን የጠርሙስ ቢራና 33,010 ድራፍት ቢራ ነበር፡፡ የጠርሙስ ቢራ ምርቱ የዕቅዱን 45 በመቶ፣ የድራፍት ምርቱም የዕቅዱን 15 በመቶ ብቻ ሊሆን ችሏል፡፡ በበጀት ዓመቱ በጠቅላላው ሊመረት ይችላል ከተባለውና በዕቅድ ከተያዘው ውስጥ ማሳካት የተቻለው 41 በመቶ ብቻ እንደሆነ ሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡

600 ሺሕ ሔክቶ ሊትር የማምረት አቅም ያለው የራያ ቢራ ፋብሪካ፣ በ2008 በጀት ዓመት ያመረተው 229,38 ሔክቶ ሊትር ብቻ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ይህም ኩባንያው በበጀት ዓመቱ አከናውናለሁ ብሎ በዕቅድ ይዞት የነበረው የ1.08 ቢሊዮን ብር ሽያጭ እንዳያሳካ አድርጎታል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከሽያጭ ያገኘው ገቢ 449.7 ሚሊዮን ብር ወይም የዕቅዱን 41.5 በመቶ ብቻ ሊሆን ችሏል፡፡ ከዚህ ባሻገር በአክሲዮን ማኅበሩ የዓምናው የሒሳብ ሪፖርት ላይ ኪሳራ ሊመዘገብ ከቻለባቸው ሌሎች ምክንያቶች ውስጥ በበጀት ዓመቱ ኩባንያው ያወጣው ከፍተኛ ወጪ ነው፡፡

የባንክ ዕዳና ወለድ፣ የማኅበራዊ ልማት ድጋፎች፣ የፕሮሞሽን ወጪዎች፣ ለሲቪል ሥራ ተከፋይ ለሆኑ ሒሳቦች በከፊል ለቢራ ሳጥንና ለጠርሙስ መግዣ የዋለው ገንዘብ እነዚህ ከኦፕሬሽን የተገኘ መሆኑን ባለአክሲዮኖቹ እንዲገነዘቡ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡ ከፍተኛ ወጪዎች በኩባንያው ለተመዘገበው ትርፍና ኪሳራ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የነበራቸው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደነበር ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡ ሆኖም በወደፊት የኩባንያው ሥራ መቃናት ላይ የሚኖራቸው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ኩባንያው አትራፊ አልነበረም ሊባል እንደማይችል የሚጠቁም ነው ተብሏል፡፡ እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በኩባንያው ላይ በ2008 በጀት ዓመት ከፍተኛ ወጪ ካስከተሉት መካከል ለባንክ ወለድ የተከፈለ 90.6 ሚሊዮን ብር፣ ለማኅበራዊ ልማት ድጋፍ ጨምሮ ለተለያዩ የምርት ማስተዋወቂያ ወጪዎች 28.3 ሚሊዮን ብር፣ ለአዲስና ነባር የሲቪል ሥራዎች ተከፋይ የሆነ 22.9 ሚሊዮን ብር፣ ለቢራ ጠርሙስ፣ ለካሳና ለመሳሰሉት የዋለው 56.7 ሚሊዮን ብር ወጪ ለአብነት ተጠቅሰዋል፡፡

ኩባንያው ገና በመጀመሪያ ዓመቱ ያወጣው ከፍተኛ ወጪ በሚያገኘው የሽያጭ ገቢ መሸፈን መቻሉ፣ የኩባንያው የወደፊት ተስፋ ብሩህነት የሚያመለክት ነው በማለት በቦርድ ሰብሳቢው የቀረበው ሪፖርት ጠቅሶ፣ ምንጊዜም ቢሆን ለጀማሪ ድርጅት እንዲህ ያሉ ወጪዎች ቀላል እንደማይሆኑ አስፍሯል፡፡ በትርፍና ኪሳራ ላይ ቀላል የማይባል ጫና ሊያሳድር እንደሚችልም ጠቅሰዋል፡፡ ኩባንያው ያስመዘገበው የኪሳራ መጠን ብዙ ጫናዎችን ተቋቁሞ የተመዘገበ በመሆኑና ኩባንያው ለቢራ ገበያው አዲስ ከመሆኑ አንፃርም በገበያው የነበረው የፉክክር ጫና ተዳምረው ከኪሳራው ባሻገር የበጀት ዓመቱ እንቅስቃሴ በጎ ምልክቶች ታይተውበታል ብለውለታል፡፡ የፋብሪካውን አቅም በመጀመሪያው ዓመት 50 በመቶ ለማድረስ በአዋጭነት ጥናቱ የተቀመጠው ከዚህ የመነጨ እንደሆነ የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከዕቅድ በታች ለሆነ አፈጻጸሙ ምክንያት የሆኑትን ክፍተቶች በመሙላት በተለይ ከጥራት አኳያ ለተከሰተው ችግር መፍትሔ ሊበጅ በመቻሉ፣ በ2008 ዓ.ም. የመጨረሻ ወራቶች ምርትና ሽያጩ እየጨመረ ሊመጣ መቻሉን አብራርተዋል፡፡ በ2009 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ኩባንያው አትራፊ መሆን እንደጀመረ ተገልጿል፡፡

የቦርድ ሰብሳቢው ይህን በተመለከተ እንደገለጹት፣ በ2008 በጀት ዓመት በተሠሩ ሥራዎች ምክንያት በዓመቱ የመጨረሻዎቹ ወራትና በ2009 የመጀመሪያዎች አራት ወራት ውስጥ ኩባንያው በትክክለኛ የስኬት ጎዳና ላይ መራመድ ለመጀመሩ አመላካች ውጤቶች እየተገኙ ለመሆኑ አስረጂ ያሏቸውን አኃዛዊ መረጃዎችን አቅርበዋል፡፡

ፋብሪካው ወደ አትራፊነት መሸጋገሩን ያመለክታሉ ከተባሉ አኃዛዊ መረጃዎች ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው የፋብሪካው የማምረት አቅም ደረጃ በደረጃ ዕድገት እያሳየ መጥቶ በ2009 የመጀመሪያዎቹ ወራት ላይ 85 በመቶ መድረሱ አንዱ ነው፡፡ የአራት ወራት ጠቅላላ የሽያጭ መጠን 170.5 ሺሕ ሔክቶ ሊትር መድረሱና የጠቅላላ የሽያጭ መጠን በገንዘብ ሲተመን 338.9 ሚሊዮን ብር ማስመዝገቡ፣ የፋብሪካውን ዕድገት ያሳያል ብለዋል፡፡ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ብቻ የተገኘው የተጣራ ትርፍ 29.47 ሚሊዮን ብር እንደደረሰ የድርጅቱ የሒሳብ መዝገብ ማሳየቱ ትልቅ ተስፋ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ በጥቅምት ወር መጨረሻ የነበረው የጥሬ ገንዘብ መጠን 107 ሚሊዮን ብር እንደሆነ፣ የባንክ ዕዳዎች ዋናውና ወለዱን ጭምር ባወጣው የጊዜ መርሃ ግብር መሠረት እየከፈለ መሆኑ፣ በመቀሌ፣ በሽሬና በማይጭው ከተሞች የሚገኘውን የቢራ ገበያ በአብዛኛው መቆጣጠር መቻሉና፣ የጠርሙስ ቢራ ወደ ውጭ አገር መላክ መጀመሩ ኩባንያው አዲሱን ዓመት በአትራፊነት እንዲጀምር አስችለውታል ተብሏል፡፡ ኩባንያው ምርቱን የላከው በአብዛኛው ወደ እሥራኤል ሲሆን፣ ከዚህ ሽያጭ የተገኘው ገቢ የውጭ ምንዛሪ በመጠኑም ቢሆን የግብዓት አቅርቦቱን ለማሟላት እንዳስቻለው ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

ፋብሪካው በ2008 በጀት ዓመት መጨረሻ ወራት የነበረው አፈጻጸም እየተሻሻለ በመምጣቱ፣ በ2009 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሦስት ወራት የፋብሪካውን 85 በመቶ የማምረት አቅሙን በመጠቀም ምርቱን ለገበያ እያቀረበ በመሆኑ የተመዘገበው ውጤት አበረታች እንደሆነ ተንፀባርቋል፡፡   

ከዚህ ባሻገር የፋብሪካውን ምርት በእጥፍ ለማሳደግ እየተሠራ ያለውን ሥራ በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ ዕቅድ መያዙ ተነግሯል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን ሲያጠናቅቅ ምርቱን በስፋት የመሸጥ አቅሙን ሙሉ ለሙሉ አሟጥጦ ለመጠቀምና ወደ በለጠ ትርፋማነት ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን ደረጃ በደረጃ ለማስፈጸም የሚውለው ገንዘብ ከኦፕሬሽን ከሚገኝ ገቢ መሆኑን የሚጠቁመው ሪፖርቱ፣ የመጀመሪያውን የማስፋፊያ ሥራ ጠቅላላ የፋብሪካውን የማምረት አቅም በ25 በመቶ የማሳደግ ሥራ በተያዘው በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ አቅዷል፡፡ ይህ የማስፋፊያ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የማምረት አቅሙን በ150 ሺሕ ሔክቶ ሊትር አሳድጎ 750 ሺሕ ሔክቶ ሊትር እንደሚያደርሰውና ለማስፋፊያ ፕሮጀክቱም እስከ 30 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደሚያስፈልገው በጥናት መረጋገጡን ራያ ቢራ አስታውቋል፡፡

በ2008 ዓ.ም. የታየውን ኪሳራ በተመለከተ ያነጋገርናቸው የኩባንያው ከፍተኛ ባለአክሲዮኖች የራያ ስኬት ሒደት ነው ብለውታል፡፡ ኩባንያው በበጀት ዓመቱ ያወጣው ከፍተኛ ወጪ በተከታዩ ጊዜ ስለማይኖር መጪው ዓመት ጥሩ ትርፍ እንደሚያስመዘግብ በግለሰብ ደረጃ ከፍተኛ ባለአክሲዮን የሆኑት አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሒሳብ ሪፖርት ስለሆነ ኪሳራ ተብሏል፡፡ ነገር ግን ኪሳራ ሊባል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ብዙ ወጪ አውጥተናል፡፡ የማስፋፊያ ሥራውን ለመጀመር ተጨማሪ መሣሪያዎች እያስገባን ነው፡፡ ስለዚህ ሀብታችንን ለማሳደግ የወጣው ወጪ በመብዛቱ የተከሰተ ነው፡፡ አሁን ግን አትራፊ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡ ፋብሪካው በተከፈተ በ15 ወራት ውስጥ ለመንግሥት ከፍተኛ ገቢ አስገብቷል፡፡ ይህ ትልቅ ነገር ነው በማለት አቶ ዳዊት የራያ ቢራ ተስፋን ገልጸዋል፡፡

የፋብሪካው መቋቋም ያስገኘው ጥቅም መታየት አለበት የሚሉት አቶ ዳዊት፣ ‹‹በ15 ወራት ብቻ በተለያዩ የግብር ዓይነቶች ለትግራይ ክልል ከ251 ሚሊዮን ብር በላይ ማስገባት መቻሉ ለእኔ ትልቅ ትርጉም አለው፤›› ይላሉ፡፡

ራያ ቢራ ከ2400 በላይ ባለአክሲዮኖችን አቅፎ ተቋቋመ ሲሆን፣ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ ካፒታል ከባለአክሲዮኖች አሰባስቦ ቀሪውን ከባንክ ብድር በመሸፈን ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በታሪካዊቷ የማይጨው ከተማ ፋብሪካ ገንብቷል፡፡ ከአክሲዮን ኩባንያው ባለድርሻዎች መካከል 42 በመቶውን ቢጂአይ ኢትዮጵያ፣ 25 በመቶውን ደግሞ አቶ ዳዊት ገብረ እግዚአብሔር ይዘውታል፡፡ ከጠቅላላ ጉባዔው ጎን ለጎን በተደረገው ምርጫ እስካሁን ያለው ቦርድ በኃላፊነቱ እንዲቀጥል ተመርጧል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች