Wednesday, May 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያ በአሥር ዓመት ውስጥ ወደ መካከለኛ ገቢ ተርታ እንደማትገባ ተመድ ይፋ አደረገ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የንግድና የልማት ጉባዔ (ዩናይትድ ኔሽንስ ኮንፈረንስ ኦን ትሬድ ኤንድ ዲቨሎፕመንት- አንክታድ) በዝቅተኛ ደረጃ ያደረጉ አገሮች ላይ ያወጣው የዘንድሮ ሪፖርቱ፣ እ.ኤ.አ. ከ2017 ጀምሮ እስከ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ መካከለኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ወይም ከዝቅተኛ የዕድገት ደረጃ ይወጣሉ ብሎ ካስቀመጣቸው 16 አገሮች ውስጥ ኢትዮጵያ ሳትካተት ቀርታለች፡፡

የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ሪፖርት በአዲስ አበባ ይፋ በተደረገበት ወቅት በኢትዮጵያ የሚገኘው የተቋሙ የአፍሪካ ቀጣና ጽሕፈት ቤት ኃላፊዋ ዶ/ር ጆይ ካቲጌክዋ እንደገለጹት፣ በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ያላደጉ ተብለው ከተፈረጁ 48 የዓለም አገሮች ውስጥ ሦስቱ ማለትም አንጎላ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እንዲሁም የፓስፊካዊቷ አገር  ቫናቱ ካላደጉ አገሮች ተርታ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ይሰለፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ቀሪዎቹ 13 አገሮች እ.ኤ.አ. ከ2021 እስከ 2024 ባሉት ዓመታት ውስጥ ከዝቅተኛ ደረጃ ወይም ካላደጉ አገሮች ተርታ በመውጣት መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡

በተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ ትንበያ መሠረት እ.ኤ.አ. ከ2021 እስከ 2024 ባለው ጊዜ ውስጥ ካላደጉት አገሮች ተርታ ይወጣሉ ተብለው የሚጠበቁት አፍጋኒስታን፣ ባንግላዴሽ፣ ቡታን፣ ጂቡቲ፣ ኪሪባቲ፣ የላዖስ ሕዝቦች ዴሞክሲያዊ ሪፐብሊክ፣ ማይናማር (በርማ) ፣ ኔፓል፣ ሳዖተ ቶሜና ፕሪንቺፕ፣ የሰሎሞን ደሴቶች፣ ቲሞር፣ ቱቫሉ እንዲሁም የመን ተካተዋል፡፡ 

እነዚህ አገሮች ከታችኛው ድልድል ወደ መካከለኛው እንደሚሸጋገሩ የሚጠበቁት የተመድ ንግድና ልማት ጉባዔ ከ46 ዓመታት በፊት ባወጣቸው ሦስት መስፈርቶች ቢያንስ ሁለቱን ሲያሟሉ ነው፡፡ ከመሥፈርቶቹ አንደኛው የነፍስ ወከፍ የካፒታል ገቢ ይገኝበታል፡፡

በዚህ መሥፈርት መሠረት በሦስት ዓመታት አማካይ ገቢ ስሌት የአገሮች ግምታዊ አጠቃላይ ብሔራዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ 1035 ዶላር ማስመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ከዝቅተኛ ታዳጊ አገሮች ተርታ ለመውጣት 1242 ዶላር ብሔራዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ማሳመዝገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንን መሥፈርት ኢትዮጵያ ማሟላቷ አጠራጣሪ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ዶ/ር ጆይ እንዳብራሩትም ኢትዮጵያ ይህንን መሥፈርት አታሟላም፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጠው የሰው ሀብት መሥፈርት ነው፡፡ የሰው ሀብት ጠቋሚ መለኪያዎች ተብለው ለዚህ መሥፈርት ከተቀመጡት መካከል የተመጣጠነ ሥነ ምግብ ይገኝበታል፡፡ ከጠቅላላው የሕዝብ ቁጥር ውስጥ ምን ያህሉ የተመጣጠነ ምግብ ያገኛል የሚል ንዑስ መጠይቅ ሲኖረው፣ ጤና በተለይም የሕፃናት ሞት ቁጥር በትምህርት ቤት የሚገኙ ተማሪዎች ቁጥር ማለትም የተማሪዎች ጥመርታ ሬሾ እንዲሁም የተማረው ሕዝብ ብዛት (የተማሩ አዋቂዎች ቁጥር) አንፃር የአገሮች የሰው ሀብት መጠን በሚለካበት መሥፈርትም ኢትዮጵያ የለችበትም ተብሏል፡፡

በሦስተኛነት የሰፈረው የኢኮኖሚ ተጋላጭነት የሚለካበት መሥፈርት ነው፡፡ በዚህ መሥፈርት ውስጥ መለኪያ ሆነው የቀረቡት ጠቋሚ ነጥቦች የተፈጥሮ አደጋ (በአደጋው ወቅት የግብርና ዘርፍ የተረጋጋ ምርታማነትና በአደጋው ተጋላጭ የሆነው ሕዝብ ብዛት ይመዘናሉ)፣ ከንግድ ጋር ተያያዥ የሆኑ አሉታዊ ክስተቶች (ማለትም የዕቃዎችና የአገልግሎቶች የተረጋጋ ኤክስፖርት አፈጻጸም ጠቃሚ አኃዞች) የመሳሰሉት ይካተታሉ፡፡ በዚህ መስክ የተቀመጡትን የመስፈርቱን መለኪያዎች በማሟላት ኢትዮጵያ ከሌሎች አገሮች ብትካተትም፣ በተመድ ሪፖርት መሠረት ግን ከ16 አገሮች ተርታ በመሰለፍ ከዝቅተኛው የድሃ አገሮች ተርታ ለመውጣት ተስፋ ከሚደረጉ አገሮች ዝርዝር ውስጥ መግባት ግን አልቻለችም፡፡ 

አገሮችን ያደጉና ያላደጉ ወይም በዝቅተኛ ደረጃ ያደጉ በሚል መሥፈርት ለሁለት የሚከፍለው የተመድ የንግድና የልማት ጉባዔ መሥፈርት ከወጣ 45 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ ግን ካላደጉ 48 አገሮች ተርታ መውጣት የቻሉት አራት ብቻ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ወደ ላይኛው ዕርከን ያድጋሉ ተብለው ከሚጠበቁት አገሮች መካከል እንደ አንጎላ ያሉት ባስመዘገቡት ብሔራዊ የነፍስ ወከፍ ገቢ ተመዝነው እንደሆነ ያብራሩት ዶ/ር ጆይ ይሁንና በነዳጅና በሌሎች ሸቀጦች ላይ የተመሠረተ ገቢ ያላቸው አገሮች ግን በዓለም የነዳጅ ገበያ ላይ በታየው ዝቅተኛ ዋጋ ምክንያት ውሳኔያቸውን ለማጤንና ካላደጉ አገሮች ተርታ የመውጣት ውሳኔያቸውን ለማዘግየት እያስገደዳቸው ይገኛል፡፡

አንጎላ በነዳጅ ገቢ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ገንብታለች፡፡ ይሁንና ላለፉት ሁለት ዓመታት በታየው ዓለም አቀፍ መቀዛቀዝ ምክንያት ክፉኛ ከተጎዱ አገሮች መካከል ጎልታ የምትጠቀስ ሆናለች፡፡ በአንፃሩ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ከዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ወደ መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ተርታ ለመግባት እየተሰናዳች አንደምትገኝ መንግሥት እያስታወቀ በሚገኝበት ወቅት፣ ተመድ ግን ይህ ቢያንስ በመጪው አሥር ዓመት ውስጥ ሊሆን እንደማይችል ይፋ አድርጓል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች