Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየአክሱም የማይዳሰሱ ቅርሶች ትኩረት የሚያገኙት መቼ ነው?

የአክሱም የማይዳሰሱ ቅርሶች ትኩረት የሚያገኙት መቼ ነው?

ቀን:

ኢትዮጵያ የዩኔስኮን ረቂቅ ባህላዊ ቅርስ በመዲናዋ አዲስ አበባ አስተናግዳ ሦስተኛውን የማይዳሰስ ቅርሷን የገዳ ሥርዓት ኅዳር 21 ቀን ስታስመዘግብ፣ በዕለቱ የጥንቷ መዲና አክሱም የኅዳር ጽዮን በዓልን በአደባባይ እያከበረች ነበር፡፡ በአገሪቱ በአደባባይ ደምቀው ከሚከበሩ ባህላዊና ሃይማኖተዊ በዓላት አንዱ ለሆነው የጽዮን በዓልና ቅርሶችን አስመልክቶ የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ሲምፖዚየም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚሁ መድረክ ላይ እንደ መስቀልና ፊቼ ጫምበላላ ክብረ በዓላት ሁሉ በአክሱም በተለይ በአደባባይ የሚከበሩት የኅዳር ጽዮንና የሆሣዕና ክብረ በዓላት ከአገር ውስጥ አልፎ የባሕር ማዶ ሰዎችን የሚስቡ ለዓለም የሰው ዘር ወካይ ቅርስነት ሊመዘገቡ የሚያስችላቸውን መደላድል መፍጠር እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

በመድረኩ ‹‹የአክሱም የማይዳሰሱ ቅርሶችና ለዘላቂነት የልማት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ›› በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት የመቀለ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶ/ር አየለ በከሬ ናቸው፡፡

ጥንታዊ መዲናና መንግሥት የነበረችው አክሱም፣ ተመራማሪዎች እንደሚገልጿት የኃያል መንግሥት ዋና ከተማ፣ ቀጥሎም የሃይማኖት ማዕከል ብሎም የጥንት ሃይማኖታዊ መንግሥት በአፍሪካ ውስጥ የመሠረተች አሁንም በርካታ ምዕመናን የምታስተናግድ የተቀደሰች ከተማ ነች፡፡

- Advertisement -

በውስጧም እጅግ በጣም የተቀደሰው ጽላትና የክርስትና ሃይማኖት የተለየው መገለጫ ይገኛል፡፡ እንደ ባለታሪኩ ፍራንሲስ አንፍሬ የአክሱም መንግሥትና ከተማ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓለም ከሚገኙት አራት መንግሥታት ከሮም፣ ከፋርስና ከቻይና ቀጥሎ አራተኛው ኃያል መንግሥት ነበረች፡፡ ለኃያልነቷ ምስክር ግዙፍ ሐውልት፣ ግዙፍ የድንጋይ፣ ጠረጴዛ፣ ግዙፍ የዘውድ መሠረታዊ ድንጋይ የተሰባበሩ ትላልቅ ዐምዶች፣ የነገሥታት መቃብር ከተለያዩ የማይዳሰሱ አፈ ታሪኮችና ባህሎች ጋር ከመገኘታቸውም በላይ ጎብኚን የጥንቱ ታሪክ ምን ያህል ታላቅ እንደነበር ያሳያል፡፡

እንደ ዶ/ር አየለ አገላለጽ፣ አክሱም በርከት ያሉ የማይዳሰሱ ቅርሶች አሏት የንግሥተ ሳባ አፈ ታሪክ፣ ቀዳማዊ ምኒልክ ያመጣው ጽላትና የቅዱስ ያሬድ ዜማ ከዋና ዋናዎቹ ውስጥ ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ቅርሶች የማንነትና የእምነት መገለጫ ብቻ ሳይሆኑ የብሔራዊ ታሪካችን ገንቢ ከሆኑት እምነቶች መካከል ከዘመናት ዘመናት ለረዥም ጊዜ ተላልፈው አሁንም በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ያላቸው በመሆኑ የሕዝቡ ገላጭ ናቸው፡፡

አፈ ታሪክ

የጥንት አፈ ታሪክን በሚመለከት ምናልባት እጅግ በጣም ዝነኛው አፈ ታሪክ የንግሥተ ሳባ አፈ ታሪክ ነው፡፡ አፈ ታሪኩ ለጥበብ ፍለጋ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረጋቸውን ታላቅ ጉዞ ይተርካል፡፡ የንጉሥ ሰለሞንን ጥበባዊነት ለመፈተሽ የተለያዩ ስጦታዎች አስጭና ተጉዛለች፡፡ ይህ አፈ ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም የሃይማኖትና የመንግሥት ታሪክ ውስጥ በዋናነት ይገኛል፡፡ በኢየሩሳሌም ጉዞዋ ምክንያት ቀዳማዊ ምኒልክ ተወለደ ሲያድግም አባቱን ጎብኝቶ ሲመለስ ጽላት ይዞ ወደ አገሩ ተመልሷል፡፡ ጽላቱን ይዞ አክሱም የገባበት ዕለት ኅዳር 21 ቀን በየዓመቱ ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት ይከበራል፡፡ ዘንድሮም የሆነው ይኸው ነው፡፡ በተለይ በዋዜማው በአክሱም ዋና ዋና ጎዳዎች በፈረስ በሚጎተት ሠረገላ ላይ ንግሥተ ሳባና ቀዳማዊ ምኒልክን የሚወክሉ ሁለት ወጣቶች ተቀምጠው የታቦተ ጽዮን መምጣት የሚያበስር ትርዒት በምዕመናን ዝማሬ ታጅበት ሲያሳዩ ነበር፡፡

ንግሥተ ሳባ በተለያዩ አገሮችም በተለያየ ስያሜ እንደምትታወቅ ዶ/ር አየለ በጥናታቸው ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ንግሥተ ሳባን ሮማኖች ኒኮል ይሏታል፤ የመኖች ቢልኪስ ይሏታል፤ ኢትዮጵያውያን ማክዳ ይሏታል፡፡ አዲስ ኪዳንም የደቡቧ ንግሥት (ንግሥተ አዜብ) ብሎ ሲጠራት፣ ኦሪት ንግሥተ ሳባ ይላታል፡፡ ስለሆነም ብዙዎች የኛ ናት የሚሏት የሚያደንቋት ንግሥት ነበረች፡፡››

‹‹ከቀይ ባሕር ባሻገር በስተ ምሥራቅ የምትገኘው የመን፣ ‹‹ንግሥተ ሳባን የኛ ናት›› ቢሉም የየመኖች አፈ ታሪክ ግን ከኢትዮጵያ ይለያል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያን የመኖችም ወደ ኢየሩሳሌም ንጉሥ ሰለሞንን ለመጎብኘት ሄደች ይላሉ፡፡ የየመኖች አፈ ታሪክ መጨረሻው ቢልኪስና ሰሎሞን አብረው መተኛታቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ አፈ ታሪክ የቀዳማዊ ምኒልክን መፀነስና መወለድን ይጨምራል፡፡ ይኽም አፈ ታሪክ ክብረ ነገሥት በሚባለው ታዋቂ መጽሐፍ ውስጥ ተጨምሮ ወጥቷል፤›› ሲሉም ያብራራሉ፡፡

ንግሥተ ሳባ ምናልባትም በቅድመ አክሱማዊት ዘመን አንዳንዶች ደአማት ብለው በሚጠሩበት ዘመን ኢትዮጵያን (አክሱምን) ገዝታ ሊሆን እንደሚችል የጠቆሙት ዶ/ር አየለ፣ በውቅሮ ከተማ በሥነ ቅርስ ተመራማሪዎች የተገኙ ቅርሶች እስከ 2000 ዓመተ ዓለም ዘመን ግምት መሰጠቱን ሳያወሱ አላለፉም፡፡

አፈ ታሪኩ ለሥነ ጥበብ ባለሙያዎች ማነቃቂያ መሆኑም አልቀረም፡፡ ለዚህም ማሳያ የኢትዮጵያ ሠዓሊዎች አፈ ታሪኩን ሥዕሎች በመቀየር ልክ እንደ ፊልም የንግሥተ ሳባን የኢየሩሳሌም ጉዞ ምንም ሳያስቀሩ በባህላዊ መልክ መሣላቸው  ነው፡፡ በውጭና አገር በውስጥ ጎብኝዎች ተወዳጅ በመሆኑም የጥንት ቅርስ ንግድ ላይ የተሰማሩ በብዛት ከሚሸጧቸው የቅርስ ቁሳቁሶች ውስጥ ይኸው የንግሥተ ሳባ የኢየሩሳሌም ጉዞ አፈ ታሪክ መገኘቱ ሌላው ቢቀር አፈ ታሪኩ ሥራ ፈጣሪ መሆኑን ሥዕሎቹ ማረጋገጫ መሆናቸው ያሳያል ብለዋል፡፡

ታቦተ ጽዮን

እንደ ዶ/ር አየለ ማብራሪያ ሁለተኛው የማይዳሰስ የአክሱም ቅርስ ያልጠፋው ጽላት ነው፡፡ በሁሉም እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መገለጫ ጽላት ነው፡፡ ይህ ጽላት ከኦሪት ጀምሮ በአዲስ ኪዳን የቀጠለ ነው፡፡ እንደ ዶ/ር ሥርግው ሀብለ ሥላሴ የጥናት ግኝት አቡ ሳሊ የሚባል አርመናዊ ተጓዥና ጸሐፊ የሙሴ ጽላት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው በማለት በመጻፍ የመጀመርያው የውጭ ጸሐፊ ሆኗል፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን የሃይማኖታቸው መለያ ዓርማ ጽላቱ ነው፡፡ ሌላው ዓለም ‹የጠፋው ጽላት› በማለት ስለመጥፋቱ የተለያዩ ትንተና ሲሰጥ፣ ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ግን አለመጥፋቱን ለማሳየት በዓመት አንዴ በኅዳር ወር ወደ አክሱም በመምጣት የጽላቱን በዓል ያከብራሉ፤››

እንደ ግራሃም ሃንኮክና እንደ ጀምስ ብሩስ የመሳሰሉት ጸሐፊዎች፣ ጽላቱን ፍለጋ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣታቸውም በላይ ያልጠፋውን ጽላት ለማግኘት ያደረጉትን የፍለጋ ጥረት በመጻሕፍት መልክ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ተባባሪ ፕሮፌሰር አየለ፤ ጽላቱ በኢትዮጵያ አመለካከት የባህልና የቀጣይነት ምንጭ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹በመሠረታዊ ሥርዓተ ሃይማኖት እየተመሩ አማኞች ከፈጣሪያቸው ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት ይፈጥራሉ፤ ወደ አክሱምና አክሱም የመሳሰሉት የተቀደሱ ሥፍራዎች በበዓል ወቅታቸው መንፈሳዊ ጉዞ በማድረግ የሃይማኖታቸውን ሕይወታዊነት ያረጋግጣሉ፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

ምንም እንኳ ጽላቱ ያለመጥፋቱን ላለመቀበል ተሟጋቾች ቢኖሩም በታላቅ ድምቀት በአክሱም በኅዳር የሚከበረው ሥርዓተ በዓል የዓለም ሕዝቦች በኢትዮጵያ ላይ እንዲያተኩሩ ብሎም እንዲጎበኙ ዘላቂ መንገድ መክፈቱንም ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡

የአክሱም የማይዳሰሱ ቅርሶችን ለማስተዋወቅ ምን ይደረግ?

እኒህን ዘመን ጠገብ የማይዳሰሱ ቅርሶች እንደ ሀብት ምንጭ በመቁጠር የቱሪስት ብሎም የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ፣ የቅርሶቹን ታሪክና ባህል በተለያየ ቋንቋና መንገድ ለሕዝብ እንዲደርስ መሥራት እንደሚያስፈልግ እንዳመለከቱት ዶ/ር አየለ አገላለጽ፣ ቅርሶቹን በቅርብ ለማወቅና ለመረዳት የሚፈልጉ ቱሪስቶችን ለመሳብ የሶሻል ሚዲያ (የኅብረተሰብ የኤሌክትሮኒክ መገናኛ ዘዴዎችን) መጠቀም ይገባል፡፡

የማይዳሰሱ ቅርሶችና በዓለ ሥርዓታቸውን በፌስቡክና በትዊተር ከማሰራጨትም በላይ ታላቁን የኅዳር ጽዮን ዓመታዊ በዓል መዝግቦ በቀጥታ በተመሳሳይ ጊዜ የዓለም ሕዝብ የበዓሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግም፣ ቅርሶቹ ከኢትዮጵያ አልፈው በመላው ዓለም ዕውቅና ሲያገኙ ወደ አክሱም የውስጥና የውጭ አገር ጎብኝዎችን ይስባሉ፡፡ ቅርስን በዘላቂነት መንገድ የሥራ ፈጣሪ ለማድረግ መደረግ ከሚገባቸው ተግባራት አንዱ በአክሱም የሚገኙትን የማይዳሰሱ ቅርሶች ታሪክ መመርመር፣ መጻፍ፣ ማሳየት፣ ማሰራጨትና ማስተዋወቅ ነው፡፡

የማይዳሰሱ የአክሱም ቅርሶች ኢትዮጵያዊ አመለካከት ይዘው ማንኛውም ሕዝብ ሊገባው በሚችለው ቋንቋ ቢገለጹ፣ ቢተረጐሙ የበለጠ ለማወቅ የሚፈልግ ግን ቅርሶቹ በቦታቸው ለማየትና ጥልቅ ዕውቀት የሚፈልገውን መሳባቸው አይቀርም፡፡

አክሱምና ሐውልቶች በግዙፍ ቅርስነት በዓለም ቅርስነት እንደተመዘገበላት ሁሉ

የአክሱም የኅዳር ጽዮን ሆነ የሆሣዕና በዓል አከባበርን ዘርፈ ብዙ ገጽታ በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ሰፊ ሥራ እንደሚጠብቅ የተናገሩ አንድ ተሳታፊ በ2001 ዓ.ም. ዩኔስኮ የክሮሺያን የቅዱስ ብሌይዝ ክብረ በዓለን እንደመዘገብ ሁሉ አክሱምም ዕድሉ ሊኖራት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...