Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የገበያ አማራጭ በመሆን ችግር እንዳይፈጠር እናረጋጋለን እንጂ ገበያውን በሞኖፖል የመቆጣጠር ሐሳብ የለንም››

አቶ አስፋወሰን አለነ፣ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

አቶ አስፋወሰን አለነ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት ልማት ድርጅት (ኢግልድ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲሆኑ፣ ግዙፉን መንግሥታዊ የልማት ድርጅት ካለፈው ዓመት ጀምሮ እየመሩ ይገኛሉ፡፡ ላለፉት 70 ዓመታት የቆየው አንጋፋው የጅምላ ንግድ አከፋፋይና አስመጪ ድርጅት (ጅንአድ) ከ2006 ዓ.ም ለሁለት በመከፈሉ ምክንያት፣ ኢግልድ በአገሪቱ ያለውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለበትን የግብዓት አቅርቦት ችግር ለማገዝ በሚል ዓላማ ነበር የተመሠረተው፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪውን ከመደገፍ ጎን ለጎን ለኅብረተሰቡ ፍጆታ የሚሆኑ መሠረታዊ ሸቀጦችን በጅምላ እያከፋፈለ ይገኛል፡፡ ይህ ግዙፍ ድርጅት በአሁኑ ወቅት እያከናወናቸው ባሉት ተግባራትና ከራሱ ጋር በሚያያዙ ጉዳዮች ጥያቄዎች ይነሱበታል፡፡ በአጠቃላይ በድርጅቱ ወቅታዊ አቋምና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚነሱበትን በርካታ ጉዳዮች በተመለከተ  ዮናስ ዓብይ ከዋና ሥራ አስፈጻሚው ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢግልድ ኢንዱስትሪው ያለበትን የግብዓት እጥረት በመቅረፍ እገዛ እንዲያደረግ ነው በመንግሥት ውሳኔ መሠረት የተቋቋመው፡፡ ድርጅቱ በአዋጅ እንደ አዲስ ቢቋቋምም ቀድሞ የጅምላ ንግድና አስመጪ ድርጅት (ጅንአድ) የተባለውን ድርጅት ሥራ እየሠራ ነው፡፡ በእርግጥ ሌላውም አዲስ ሊባል የሚችለው አለ በጅምላ በተመሳሳይ ሥራ ላይ ይገኛል፡፡ እስኪ ከአለ በጅምላ ጋር የምትጋሩት ካለ ቢገልጹልን?

አቶ አስፋወሰን፡- ከአለ በጅምላ ጋር ያለን ግንኙነት በእርግጥ እኔ ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት በነበረው አመራር የተደረገ አደረጃጀት ስለሆነ ብዙ ወደኋላ በመሄድ ባልዘረዝር ይሻላል፡፡ ኢግልድን በተመለከተ መግለጽ የሚቻለው በ2007 ዓ.ም. በአዋጅ መቋቋሙ ነው፡፡ በእርግጥ አለ በጅምላ ሲቋቋም የመቋቋሚያ ገንዘብና መጋዘኖች ያስፈልገው ስለነበር ከእኛ የተወሰነ ገንዘብና ጥቂት መጋዘኖች ተሰጥቶቷል፡፡ ነገር ግን ከነበረንና አሁን ካለን አጠቃላይ ሀብት አንፃር  ለአለ በጅምላ የተሰጠው ያን ያህል ብዙ የሚባል አይደለም፡፡ በዝርዝርም የሚታወቅ ሲሆን ለአብነት ያህል ድሬዳዋ፣ ሻሸመኔ፣ ባህር ዳርና የመሳሰሉት አካባቢዎች የነበሩንን መጋዘኖች መጥቀስ ይቻላል፡፡ በጥያቄው እንደተነሳው የአሁኑ ኢግልድ ቀድሞ በነበረው ጅንአድ ሲቀየር በስም ብቻ አይደለም፡፡ አጠቃላይ ተግባሩም ሆነ ተልዕኮው ነው የተቀየረው፡፡ ቀደም ብሎ በጅምላ ንግድ ላይ ብቻ ነበር ያተኮረው፡፡ የአሁኑ ኢግልድ የተቋቋመበት ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት የማንፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት በማቅረብ እንዲጠናከሩ ሲሆን፣ በተለይ ትልልቅ ኢንዲስትሪዎች ሲቸገሩ የነበሩት ከግብዓት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ነበር፡፡ ይህ ችግር መፈታት የነበረበት በመሆኑ፣ በምን ዓይነት መንገድ ሊፈታ ይገባል በማለት መንግሥት መመለስ ስለነበረበት ነው ኢግልድ የተቋቋመው፡፡ በዚህ ሁኔታ  በጨርቃ ጨርቅ፣ በአልባሳት፣ በቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ እንዲሁም በግብርና ማቀነባበር ያሉ ዘርፎች የሚፈልጉዋቸውን ግብዓቶች ሊያቀርብ የሚችል ድርጅት መቋቋም እንዳለበት ታስቦ ነበር የተቋቋመው፡፡

ሪፖርተር፡– ለኢንዱስትሪው ከምታቀርቡት በተጨማሪ አሁንም ለኅብረተሰቡ  ግብዓት እያቀረባችሁ ነው፡፡ ምናልባት የተወሰኑ መጋዘኖችና የአቅርቦት ሥራዎች ለአለ በጅምላ የተሰጡ ቢሆንም፣ የቀድሞውን ጅንአድ ሥራ እየሠራችሁ ከሆነ ምን ላይ ነው ልዩነታችሁ?

አቶ አስፋወሰን፡- እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ነገር ግን የዚህ ድርጅት ማቋቋሚያ አዋጅን ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ አዋጅ ቁጥር 328/2006 የድርጅቱን መሸጋገሪያ ድንጋጌ ያስቀመጠ፣ የመሸጋገሪያ ጊዜውን አስመልክቶ አንቀጽ 9 ‹‹የዚህ ደንብ አንቀፅ 9 ድንጋጌ ቢኖርም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር የተቋቋመው የኢትዮጵያ ንግድ ድርጅት (አለ በጅምላ) ዓላማውን በአግባቡ ተግባራዊ እስከሚደረግ ድረስ፣ በሸቀጦች ጅምላ ንግድና አስመጪ ድርጅት ዓላማ ሥር የተቀመጡ ተግባራትን ድርጅቱ (ኢግልድ) እያከናወነ ይቆያል፤›› ይላል፡፡ ምክንያቱም አለ በጅምላ ተብሎ የሚጠራው ወይም የንግድ ሥራ ኮርፖሬሽኑ በሁለት እግሩ እስከሚቆም ድረስ ባሉት ጊዜያት ለኅብረተሰቡ መሠረታዊ ዕቃዎችንና ፍጆታዎችን አቅርቦት ማቆም ስለማይገባ፣ ጅንአድ ቀደም ብሎ ሲሠራው የነበረውን ኢግልድ ይዞ ያቆያል ነው የሚለው ማቋቋሚያ አዋጁ፡፡

በዚህ በተሰጠን ድንጋጌ መሠረት እኛም በዚህ ደረጃ ጅንአድ ሲሠራው የቆየውን ከሞላ ጎደል ጎን ለጎን እያስኬድን ነው፡፡ በተለይ ትኩረት የምንሰጠው ደግሞ መሠረታዊ ሸቀጦች ማለትም እንደ ስኳርና ሌሎች ግብዓቶችን በማቅረብ ነው፡፡ በእርግጥ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የዘይት አቅርቦት የነበረ ቢሆንም አሁን ዘይት አንሸጥም፡፡ ለሌሎች አካላት ዘይትን የማከፋፈሉ ኃላፊነት የተሰጠ በመሆኑ፣ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ግን በማከፋፈል ላይ ነን፡፡ ይህን ስናደርግ ሁለት ዓላማዎች አሉ፡፡ አንደኛው ኢንዱስትሪውን መደገፍ ሲሆን ሁለተኛው ለኅብረተሰቡ በተለይም አነስተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች መሠረታዊ ሸቀጦችን ማቅረብ ነው፡፡ ይህንን ዓይነት ሥራ ለማከናወን በመጋዘን መጠንም ሆነ በቁጥር እንደ ኢግልድ ያለ የተጠናከረ ተቋም በአገሪቱ ውስጥ የለም፡፡ አለ በጅምላም ቢሆን ገና እየተጠናከረ ያለ ተቋም ስለሆነ ሥራው በእኛ እየተከናወነ እንዲቆይ ተፈልጓል፡፡ ሌላው ዋና ጉዳይ ደግሞ ኢንዱስትሪዎችን ስንደግፍ የገበያ እጥረት እንዳይፈጠር እገዛ እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- የፍጆታ ዕቃዎችን የማከፋፈል ሥራ ወደ ሌላ አካል ሊዛወር ይችላል የሚሉ መረጃዎች ነበሩ፡፡ በዚህ ላይ ያለው እውነታ ምንድነው?

አቶ አስፋወሰን፡- የፍጆታ ዕቃዎች ከእኛ እንዲወጡ ነበር የታሰበው፡፡ ነገር ግን ይኼንን ኃላፊነት የሚወጣ የተጠናከረ ድርጅት ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በየክልሉ እንደ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና ዩኒየን ዓይነት የተደራጁ ማኅበራት አሉ:: እነዚህ ድርጅቶች ይህን ጉዳይ በቅርበት እያጤኑት ነው፡፡ በቀጣይ እነሱ አቅም መፍጠር ሲችሉና የሚፈለገውን ያህል ደረጃ መድረስ ሲችሉ የማከፋፈል ተግባሩን ለእነሱ ማስረከብ ነው የሚታሰበው፡፡ አለ በጅምላም ሆነ ሌሎቹ አብዛኛዎቹን መሠረታዊ ሸቀጦች በማከፋፈል ሥራ እንዲሳተፉ የመንግሥት ፍላጎት ነው፡፡ እዚህ ደረጃ ለመድረስ ዩኒዮኖች ወይም የኀብረት ሥራ ማኅበራቱ ጊዜ ሊወስድባቸው እንደሚችል ይታሰባል፡፡ ይህ ድርጅት የሰባ ዓመት ልምድ ያለውና በአግባቡ የተደራጀ ከመሆኑ አንፃር፣ በዚህ ደረጃ ሌሎች ለመምጣት ሊያስቸግራቸው እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ የመንግሥት ፍላጎትም ቢሆን እኛን ከዚህ ሥራ በማስወጣት ኢንዱስትሪው ላይ ብቻ ትኩረታችንን እንድናደርግ ብቻ ሳይሆን፣ ሌሎች ድርጅቶች በቅድሚያ የሚፈለገው ደረጃ መድረሳቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ለምሳሌ የስኳር ማከፋፈል ሥራ ከእናንተ ይወጣል የሚል መረጃ ነበር፡፡ ያ ማለት የማከፋፈሉ ተግባር አሁን ከተገለጹትና ወደ ሌሎች አካላት ለማዘዋወር እየታሰበ ካለው ዕቅድ ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል?

አቶ አስፋወሰን፡- የዚህ ዓይነቱ መረጃ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ስኳርን ወደ ሌሎች ማዘዋወርን በተመለከተ መንግሥት በጥልቀት ሲያስብበት ቀላል ሆኖ አልተገኘም፡፡ ሁኔታው ካለው እውነታ አንፃር ሲታይ የዩኒየኖችና የኅብረት ሥራ ማኅበራት አቅም ገና ሆኖ በመገኘቱ እኛ ቀጥሉበት ተብለናል፡፡ በዚህም የተነሳ ትናንት [ማክሰኞ ኅዳር 20 ቀን 2009 ዓ.ም.] ስኳር ለማጓጓዝ ጨረታ ነበረን፡፡ አገር ውስጥ ያሉ የስኳር ፋብሪካዎች በክረምቱ ወቅት ምርት አቋርጠው ስለነበር፣ በገበያው ውስጥ እጥረት እንዳይፈጠር ቀደም ብለን ከውጭ አስገብተን ነበር፡፡ ካለፉት ወራት ጀምሮ ፋብሪካዎቻችን ወደ ማምረት በመመለሳቸው አሁን በቂ የስኳር ምርት አለን፡፡ እስካሁን የተመረቱትንም ከየፋብሪካዎቻችን በማንሳት በመላው አገሪቱ ወዳሉ መጋዘኖች ለማጓጓዝ ነበር በጨረታው 34 የሚሆኑ የትራንስፖርት ድርጅቶች ያሸነፉት፡፡ አሁን የማጓጓዝ ሥራው እየተካሄደ ነው፡፡ በመላው አገሪቱ ለስኳር ብቻ ከ70 ያላነሱ ዝግጁ የሆኑ መጋዘኖች አሉን፡፡ ነገር ግን ዩኒየኖች በመጋዘንም ሆነ በትራንስፖርት የመሳሰሉ ጉዳዮች ተደራጅተውና አቅሙን አዳብረው ሲገኙ ሥራውን ልናስረክብ እንችላለን፡፡ እስከዚያው ግን ኢግልድ እያስኬደ ይቆያል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  በኢንዱስትሪ አቅርቦት አሁን ያላችሁበት ደረጃ እንዴት ይለካል?

አቶ አስፋወሰን፡- ኢንዱስትሪዎችን በተመለከተ ስናያቸው ሰፊና ብዙ ናቸው፡፡ እንደ መንግሥት ፍላጎት ስናየው አሁን ባለንበት ደረጃ ለሁሉም ተደራሽ ለመሆን አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ቅደም ተከተል አስቀምጠን ነው ባለን አቅም መሠረት የተወሰኑትን ለማገዝ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ነው እንቅስቃሴ የጀመርነው፡፡ ለጊዜው በሦስቱ እንቅስቃሴ በጀመርንባቸው ንዑሳን ዘርፎች እየተጓዝን ነው፡፡ እነዚህም የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ፋብሪካዎች፣ የቆዳና የቆዳ ውጤት ፋብሪካዎች፣ የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡ በተለይ ቀደም ብለን በጀመርነው የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ዘርፍ ዋናው ግብዓት የጥጥ አቅርቦት ነው፡፡ ሌሎች ተጨማሪ እንደ መለዋወጫና ተዛማጅ ግብዓቶች ቢኖሩትም ትልቁ የጥጥ ግብዓት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጥጥ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ እያስገባን ነው የምናግዛቸው፡፡ ከውጭ የምናስገባላቸው አገር ውስጥ እንደሌለ ሲታወቅ ብቻ ነው፡፡ ወይም አገር ውስጥ የማይገኝ የተፈጥሮ ጥጥ ሲኖር ነው፡፡ ይህም የተፈጥሮ ጥጥ ፋብሪካዎች ከደንበኞቻቸው ይቅረብልን የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው ነው ከውጭ የምናስገባው፡፡ ዋናው መርሐችን የአገር ውስጥ የጥጥ ምርትን ማንሳት ነው፡፡ ይህንን ስናደርግ ደግሞ የአገር ውስጥ አምራቾችን ማገዝ እንችላለን፡፡ በተመሳሳይ ጊዜም ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን ወጪም ሆነ ጊዜ መቀነስ እንችላለን ማለት ነው፡፡

በአጭር ጊዜም ለፋብሪካዎች እንዲቀርብላቸው እንደርጋለን፡፡ ይህ በሚደረግበት ጊዜም የጥራት ጉዳይ ሊነሳ ይችላል፡፡ ለጊዜው ጥራትን በተመለከተ የፍተሻ ሙከራ ማድረግም ሆነ ደረጃ የማውጣቱ ደረጃ ላይ ግን ገና አልደረስንም፡፡ ተሞክሮም የሌለን ሲሆን ገና እየተዋወቅን ነው የምንገኘው፡፡ ለጊዜው የጥራት ደረጃን እያከናወነልን የሚገኘው የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ነው፡፡ ኢንስቲትዩቱም ደረጃውን የጠበቀና ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ያለው ነው፡፡ የኢንስቲትዩቱ ባለሟሎች የጥጥ ጥራትና ደረጃ አረጋግጠው ከላኩልን በኋላ እንደ የደረጃው ለአቅራቢዎች ክፍያ እንፈጽማለን፡፡ ስለዚህ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፉን በግብዓት ስንደግፍ ከአነስተኛ አምራቾች ጀምሮ እስከ ትልልቅ ፋብሪካዎች ያሉትን ሁሉንም እንደግፋለን፡፡ ለምሳሌ እንደ አይካ አዲስ ዓይነት ደረጃ ላይ ያሉ ግዙፍ አምራቾችና  ለውጭ ገበያ ላኪዎች የሚፈልጉትን ግብዓት በጅምላ እናቀርባለን፡፡ በጥቃቅንና በአነስተኛ ደረጃ የሽመና አልባሳት የሚሠሩትንም በተሻለ ሁኔታ ለማገዝ እያሰብን ነው፡፡ እነዚህ ጥጥ ባይፈልጉ እንኳ እንደ ክር ያሉ ሌሎች ለአልባሳት ሥራ የሚውሉ ግብዓቶችን ከፋብሪካዎቹ እየገዛንም ሆነ ከውጭ እያስገባን እንደግፋቸዋለን፡፡ ምናልባት የፋይናንስና የአቅም ውሱንነት ሊኖራቸው ስለሚችል እኛ በጅምላ እየገዛን በፈለጉት ጊዜና መጠን ከእኛ እየገዙ፣ የአልባሳት ሥራውን እንዳያቋርጡ የበኩላችንን እናደርጋለን፡፡ ከጨርቃ ጨርቅና ከአልባሳት ባሻገር በሌሎቹም ዘርፎች እንዲሁ ተመሳሳይ እገዛችንን እንቀጥላለን፡፡

ሪፖርተር፡-  የጥጥ አቅርቦትን  በተመለከተ እስከ ታች በመውረድ አቅራቢዎችንስ በማገዝ ረገድ?

አቶ አስፋወሰን፡- እዚህ የጥጥ ምርት ላይ ብዙ ተዋናዮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ተመርቶ ፋብሪካ እስከሚደርስ ድረስ ብዙ እጅ ይገባበታል፡፡ የእኛ ድርሻ በተወሰነ ደረጃ ላይ ብቻ ያተኮረ ነው፡፡ በቀጣይ አቅም እያደራጀን ስንሄድ ወደ እርሻው ገብተንም ቢሆን እዚያው ድረስ በመሄድ ያለውን ችግር ከመፍታት አኳያ ተሳትፎ ሊኖረን ይገባል፡፡ ምክንያቱም የመጨረሻ ተልዕኮው ጥራት ያለው ጥጥ ኤክስፖርት ለሚያደርገው የጨርቃ ጨርቅ  ኢንዱስትሪ ማቅረብ ስለሆነ፡፡ ለጊዜው ግን እርሻው አካባቢ ተሳትፎ የለንም፡፡ ለዚህ ደግሞ በቂ አቅምና ክህሎቱ ያላቸው የጨርቃ ጨርቅ ኢንስቲትዩትና የግብርና ሚኒስቴር እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ትኩረታችሁ በገበያው ውስጥ የተገደበ ነው ተብሎ መደምደም ይቻላል?

አቶ አስፋወሰን፡- ዋናው ትኩረታችን የጥጥ አቅርቦትም ሆነ  የገበያ እጥረት እንዳይፈጠር ማድረግ ነው፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት ገበሬዎቹ ጥጡን አምርተው ገበያ አጣን የሚል ቅሬታ ያቀርቡ ነበር፡፡ አሁን እንዲህ ዓይነት ችግሮችን መፍታት ችለናል፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት 14 ሺሕ ኩንታል የሚሆን ጥጥ መጋዘናችን ውስጥ አለን፡፡ ዓመቱን ሙሉ የጥጥ እጥረትን የተመለከተ ችግር እንዳይፈጠር በማድረግ ላይ ነን፡፡ በኮምቦልቻ፣ በመልካ ሰዲና በቃሊቲ ባሉን መጋዘኖች በቂ ክምችት አለን፡፡

ሪፖርተር፡- በጥጥ አምራቾች  የሚነሱ ሁለት ቅሬታዎች አሉ፡፡ አንደኛው ያመረቱትን ጥጥ ወደ እናንተ መጋዘን ካስገቡ በኋላ ጥራትና ደረጃውን መርምሮ ውጤት ለማሳወቅ ብዙ ጊዜ ስለሚወስድ፣ ላስገቡት ምርት በፍጥነት እየተከፈላቸው አለመሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው ቅሬታ የጥራት ደረጃ ምዘናን በተመለከተ ወጥነት ያለውና ራሱን የቻለ ተቋም አለመኖሩ ይነሳል፡፡ በዚህ ጉዳይ የድርጅታችሁ ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል?

አቶ አስፋወሰን፡- ይህ ጉዳይ በተወሰነ ደረጃ እውነትነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ሁሉም በተፈለገው መንገድና በፍጥነት ላይሄድለት ይችላል፡፡ ይህ ዓይነቱ የጥራት ምዘና ጉዳይ ሌላ አካል ስለያዘው ብቻ የሚነሳ ሳይሆን፣ እኛም ዘንድ የሚቀርብ ቅሬታ ነው፡፡ ጥጥ አቅራቢው አካል ለቀረበው ጥጥ ቶሎ ገንዘብ ተከፍሎት እንዲሄድ ነው የሚፈልገው፡፡ መሆን እንዳለበትም የሚጠብቀው ይኼንን ነው፡፡ የጥጥ ዋጋን በተመለከተ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ዋጋ ብቻ አይደለም የሚወሰነው፡፡ ጥጥ ከአብዛኞቹ የሸቀጥ ዓይነቶች በተለየ ሁኔታ ዓለም አቀፍ ባህሪ ያለው ነው፡፡ ስለዚህ የሽያጭ ዋጋውም የሚወሰነው የዓለም አቀፍ ዋጋን መሠረት አድርጎ ነው፡፡  ከፍም ዝቅም ሊል ይችላል፡፡  ገበያውን የሚያጤነው የጨርቃ ጨርቅ ኢንስቲትዩት ካለፉት ስድስት ወራትና ከሚቀጥሉት ስድስት ወራት ዋጋ ትንበያ ጋር በማገናዘብ፣ እንዲሁም የዓለም ዋጋን አይቶ ነው የሚወስነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ የጥጥ ዋጋ እንደ ሌሎች የሸቀጥ ዓይነቶች ዋጋው በፍጥነት አይዋዥቅም፡፡ ምናልባት በየወሩ ወይም በየቀኑ ተመሳሳይ ላይሆን ግን ይችላል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አጥንቶ ነው የሚተምነው፡፡ ልክ እንደ ቡና ሁሉ ዓለም አቀፍ ገበያውን ተንተርሶ ነው ዋጋው የሚተመነው ማለት ይቻላል፡፡ የጥራት ምዘናውን በተመለከተ ከተገልጋዩ ቅሬታዎች ሊነሱ ይችሉ ይሆናል፡፡ የላብራቶሪውን አቅምና ደረጃ በተመለከተ በአገር ውስጥም በውጭም ብቃቱ የተመሠከረለት መሆኑ ነው የሚታወቀው፡፡

ሪፖርተር፡- መመዘኛዎችንስ በተመለከተ?

አቶ አስፋወሰን፡- አንድ ጥጥ የራሱ የሆኑ ዝርዝር መመዘኛዎች አሉት፡፡ በእነዚህ መመዘኛዎች መሠረት ከ ‘A’ እስከ ‘C’ ባሉ ሦስት ደረጃዎች ይለያል፡፡ ዋጋውም በዚህ መሠረት ነው የሚወጣው፡፡ ዋጋ ከዓለም ዓቀፍ ገበያ አንፃር ሲጨምር እኛም ማስተካከያ እናደርጋለን፡፡ ከዚህ በፊት ‘A’ ደረጃ ለሚባለው ጥጥ በኪሎ ግራም 33 ብር ነበር፣ ለ ‘B’ ደረጃ 31 ብር፣ ለ’C’ ደረጃ 30 ብር ነበር፡፡ በቅርቡ ግን ዋጋ በመጨመሩ ለ ‘A’ ወደ 35 ብር፣ ለ’B’ ወደ 33 ብር፣ እንዲሁም ለ ‘C’ 32 ብር ከፍ አድርገን እየገዛን ነው፡፡ ይህ የዋጋ ጭማሪ አቅራቢው ጨምሩልኝ ስላለ ወይም ስላላለ ሳይሆን፣ የገበያው ሁኔታ ነው ማስተካከያ እንዲደረግ ምክንያት የሆነው፡፡ ሌላው የተነሳው ጉዳይ አቅራቢው እኛ መጋዘን ካስገባ በኋላ ነው ተመዝኖ ደረጃ የሚወጣለት የሚለው ነው፡፡ የቀረበው ምርት ከምዘና በኋላ ከሦስቱ ደረጃዎች ውጪ ሆኖ ከተገኘ ተቀባይነት አይኖረውም፡፡ በእርግጥ አንድ ያልፈታነው እውነታ ቢኖር ከሩቅ አጓጉዘን መጋዘን ካስገባን በኋላ፣ ከደረጃ በታች ነው ተብሎ መመለሱ ለወጪ ዳርጎናል የሚለው ሊሆን ይችላል፡፡ ልናደርገው ይገባል ብለን እያሰብን ያለነው ጉዳይ አለ፡፡ ያሉን መጋዘኖች ለአብነትም በኮምቦልቻ፣ በመልካ ሰዲና በቃሊቲ ያሉንን ዓይነቶች ሰፋ የማድረግና ጥጥ የሚመረትባቸው እርሻዎች አካባቢ ቀረብ ብለን ማስፋፋት ነው፡፡ በአብዛኛው የሚታወቁት ጋምቤላ፣ አፋር፣ መተማ፣ አርባ ምንጭ አካባቢ ነው የሚገኙት፡፡ እነዚህን ተከትለን ሁሉም ቦታ መጋዘን ባንከፍትም ተጨማሪ እናዘጋጃለን፡፡ ቢያንስ አቅራቢው ከሩቅ ቦታ በሚያጓጉዝበት ጊዜ የሚያወጣውን ወጪ እንዲቀንስ ማድረግ እንችላለን፡፡ ከጋምቤላ አዲስ አበባ የመጣው ጥጥ ደረጃው ሲለካ ከ ‘C’ በታች ከሆነ ይዘህ ሂድ ማለቱ አስቸጋሪ ነው፡፡ ለዚህም ነው ወደ ሚያመርቱበት ጠጋ ብለን የምንከፍትበትን መንገድ እያሰብን ያለነው፡፡ በቀጣይ ደግሞ ወደ አምራቹ ከተጠጋን ወደ ማዳመጥ እንገባለን፡፡ እነዚህን ካደረግን  በአቅራቢያቸው የጥራት ምዘናና የደረጃ ምደባውን እናከናውናለን ማለት ነው፡፡ ለእነዚህ ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት፣ ራሳችንን ለማደራጀትና አቅም ለመገንባት ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ሌላው ከአቅራቢዎች የሚነሳው ከገንዘብ ክፍያ ጋር በተያያዘ ሲሆን፣ እናንተ ለተረከባችሁት ግብዓት ባለፋብሪካዎች ምርታቸው በውጭ ገበያ ተሸጦ እስከሚመጣ ድረስ ክፍያ ይዘገይብናል የሚል ነው፡፡ መንግሥትም ቢሆን ትኩረቱ በዋነኝነት በአምራቾች ነው ይባላል፡፡ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

አቶ አስፋወሰን፡- ፋብሪካዎች ውጭ ገበያ አቅርበው እስከሚያመጡ ድረስ የፋይናንስ አቅማቸው ያነሰ በመሆኑ ክፍያ ይዘገያል የሚለው እውነት የለውም፡፡ ፋብሪካዎችም ቢሆኑ ለአቅራቢዎች የሚከፍሉበት ሁኔታ የለም፡፡ የእዚህን ዓይነት ችግር እንዳይፈጠርም ነው እኛ በመሀል የገባነው፡፡ ለአቅራቢዎች እኛ ነን የምንከፍለው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ከመዘግየቱ ጋር በተያያዘ መወቀስ ያለባችሁ እናንተ ናችሁ ማለት ነው?

አቶ አስፋወሰን፡- ችግሩ ከእኛ ሊሆን ይችላል፡፡ የመዘግየት ጥያቄው ከተነሳ አጠቃላይ ሒደቱም መታየት አለበት፡፡ የጥጥ ምርቱ ከማሳ ተሰብስቦ ወጥቶ፣ተዳምጦ፣ የጥራት ፍተሻና ምዘና ተካሂዶ፣ ከዚያም አልፎ ውጤቱ እስኪመጣ ድረስ ሊዘገይ ይችላል፡፡ የጥራት ምዘና በአንድ ቀን ተከናውኖ ሊጠናቀቅ አይችልም፡፡ አንድ አምራች ምናልባት ምርቱን ካስረከበበት ቀን ጀምሮ ሊቆጥር ይችላል፡፡ ነገር ግን ማለፍ ባለበት ሒደቶች ሁሉ ሄዶ የመጨረሻው የጥራት ደረጃ እስኪረጋገጥና እኛም እስከምንከፍለው ድረስ ያለው ጊዜ ዘገየ ሊያስብል ይችላል፡፡ ይህንንም ለመቅረፍ ታዲያ አዲስ ደረጃ ወይም የዜጎች ቻርተር እያዘጋጀን ነው፡፡ እኛም እንደፈለግነው መቆየት ስለሌለብን ይኼ ስታንዳርድ እየተዘጋጀ ነው፡፡ በተረፈ ከመዘግየት ጋር የተነሳው ውኃ የሚቋጥር አይደለም፡፡ ይልቁንም ፋብሪካዎች ሸጠው ክፍያ ለእኛ እስከሚያከናውኑ ድረስ ጫናው እኛ ላይ ነው፡፡ በእነሱ በኩልም የተነሳውን ዓይነት ችግር ለመቅረፍ ነው ወደ አንድ ቢሊዮን ብር በጅተን ወደ ገበያው የገባነው፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት ጉዳይ ቢኖር መንግሥት ድጋፍ ማድረግ አለባችሁ ብሎ ወደዚህ ሥራ ሲያስገባን ፋብሪካዎችን ብቻ ለማገዝ አይደለም፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ጭምር እንጂ፡፡ ለዚህም ነው አቅራቢዎች ምርት ወደ መጋዘን ሲያስገቡ ቢያንስ የትራንስፖርትና የሌሎች ወጪያቸውን ለማገዝ በማለት ቅድመ ክፍያ አሥር በመቶ ያህል የምንከፍላቸው፡፡ በተጨማሪ ለሚመረተው ምርት የገበያ ችግር እንዳይገጥማቸው በማለት ነው እኛ ራሳችን ምርታቸውን በቀጥታ የምንገዛቸው፡፡ ስለዚህ የገበያ ጭንቀት እንደማይፈጠርባቸው ሊታይ ይገባዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ስንመለከት በዚህ በኩል ደግሞ የጨው አቅርቦት ይነሳል፡፡ በቅርቡ የእዚህ ዘርፍ ተዋናዮች በጨው ግብዓት እጥረት ምክንያት ቆዳ እየተበላሸባቸው እንደሆነ የሚያነሱት ጥያቄ በድርጅታችሁ እንዴት ይታያል?

አቶ አስፋወሰን፡- በዚህ ዘርፍ አካሄድ ያለውም ተመሳሳይ ነው፡፡ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች ዘርፍ ያሉበት ችግሮች እንደ ጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ ነው የሚታየው፡፡ የጨው ግብዓት ጉዳይም በጨርቃ ጨርቅ ካለው የጥጥ ችግር ዓይነት ጋር ይመሳሰላል፡፡ ስለዚህ በጨው እጥረት የሚነሳው ችግር እውነት ነበረው፡፡ በዚህ ምክንያት ካለፈው ወር ጀምሮ ኢግልድ ወደ ጨው ገበያም ገብቷል፡፡ ለምሳሌ አሥር ሺሕ ኩንታል ያህል የጨው ግዢ ባለፈው ወር ፈጽመናል፡፡ ጦር ኃይሎች አካባቢ በሚገኘው መጋዘናችን አስገብተናል፡፡ ፋብሪካዎችን በመጡበት ጊዜ ለማስተናገድ ዝግጁ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ሁኔታ ኢግልድ ወደፊት የሚኖረው የገበያ ድርሻ እንዴት ይታያል? ምናልባትም ለኢንዱስትሪው ግብዓት የማቅረብ ሥራውን ሙሉ ለሙሉ ወደ መውሰድ ሊያዘነብል የሚችል ሥጋት ሊኖር አይችልም?

አቶ አስፋወሰን፡- እኛ የገበያ አማራጭ በመሆን ችግር እንዳይፈጠር እናረጋጋለን እንጂ ገበያውን በሞኖፖል የመቆጣጠር ሐሳብ የለንም፡፡ አቅምም ሊኖረን አይችልም፡፡ ከምንም በላይ የማረጋጋት ሚና ብቻ ነው የሚኖረን፡፡ ፍላጎቱ እንኳ ቢኖር ብቃት ሊኖረን አይችልም፡፡ እጥረት ባለባቸው መሠረታዊ ሸቀጦችን በመሳሰሉ ግብዓቶች ላይ ብቻ ነው የምንቀሳቀሰው፡፡

ሪፖርተር፡- አቅርቦት ሲባል ለኢንዱስትሪው ፍላጎት ከሟሟላት በተጨማሪ፣ ግብዓት ከውጭ ማስገባትን በመቀነስ አገር ውስጥ እንዲመረት የምታደርጉት ጥረትስ አለ?

አቶ አሰፋወሰን፡- በመርህ ደረጃ ይህ ጉዳይ ትክክል ነው፡፡ አንድ ፋብሪካ ትልቅ የሚባለውን የምርት ዓይነት እዚሁ ማምረት ከቻለ ጥቃቅን የሚባሉ የግብዓት ዓይነቶች ከውጭ እንዲገቡ ማድረግ ትርጉም የለውም፡፡ ሁሉንም ግብዓቶች ደግሞ ከውጭ አስገብቶ አይዘለቅም፡፡ ራስን መቻል ማለት በተቻለ መጠን አገር ውስጥ ያሉትን ኢንዱስትሪዎች ማስፋፋት ሲቻል ነው፡፡ አንድ ጫማ ወይም የልብስ ዓይነት ተመርቶ ለውጭ ገበያ የሚላከው ብዙ ነገሮችን አካትቶ ነው፡፡ ከቁልፍ እስከ ዚፕ የመሳሰሉትን ይዞ ነው፡፡ አቅራቢ ብንሆንም ይህንን ለማበረታት ከውጭ የሚመጣውን በአገር ውስጥ ምርት መተካት የሚቻልበትን አማራጭ ሁሉ ልንደግፍ ይገባል፡፡ በእርግጥ ይህንን ሥራ በዋነኝነት የሚያበረታታው ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  ድርጅቱ ገና ከሁለት ዓመት ያልዘለለ ዕድሜ ቢኖረውም የእስካሁኑን አፈጻጸም እንዴት ይገመግማል? በገበያው ያላችሁ ድርሻስ ምን ያህል ደርሷል?

አቶ አስፋወሰን፡- መንግሥት በሚጠብቀው ደረጃ ስናይ ገና ብዙ ይቀረናል፡፡ ቀደም ብሎ እንደገለጽኩት ሥራችንን የጀመርነው በውስን ዘርፎች ነው፡፡ በተለይ ከዚህ ቀደም ብሎ ከግብይት አቅርቦት ጋር በተያያዘ በርከት ያሉ ችግሮች የነበሩባቸው ዘርፎች አሉ፡፡ አምራች ኢንዱስትሪው ደግሞ በጣም በርካታና ሰፊ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ተደራሽ ለመሆን አቅሙም ልምዱም ስለሚያስፈልግ፣ በቅደም ተከተል መርጠን ነው  በሦስቱ  የጀመርነው፡፡ የአገሪቱ የኢንዱስትሪ ፍላጎትም ቢሆን ሰፊ በመሆኑ መንግሥት ከሚፈልገው አንፃር ብዙ ርቀት ይጠብቀናል፡፡ ነገር ግን የግብዓት እጥረትን በተመለከተ አንገብጋቢ የነበሩ ነገሮችን ከማስተካከልና ችግሮችን ከመቅረፍ አኳያ ስኬታማ ሆነናል፡፡ በተለይ የጥጥ እጥረትን ከመቅረፍና በዓላትን ተከትሎ የሚገኘውን የቆዳ ግብዓት ከመበላሸት በማዳን ረገድ በተሻለ ስኬታማ ነን፡፡ ኢግልድ ከመምጣቱ በፊት በአቅራቢዎች በኩል ከገበያ እጥረት ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች ይሰሙ ነበር፡፡ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም ድረስ በመሄድ አገር ውስጥ እኛ አምርተን ከውጭ ዕቃ እየገባ በመሆኑ ገበያ አጣን ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጹም ነበር፡፡ አሁን የዚህ ዓይነት ጥያቄ ከሞላ ጎደል ጠፍቷል፡፡ ቆዳና ሌጦም ቢሆን በገበያ ዕጦት እንዳይጣሉ አድርገናል፡፡ የገበያ ድርሻችንን በተመለከተ በአሁኑ ጊዜ አንድ ቢሊዮን ብር የሚደርስ ፋይናንስ እናንቀሳቅሳለን፡፡ ከዚህም ውስጥ 500 ሚሊዮን ብር ለጥጥ ግዢ የዋለ ሲሆን፣ የፋይናንስ ምንጩም ከልማት ባንክ በተገኘ ብድር ነው፡፡ 300 ሚሊየን ብር ደግሞ ለቆዳና ሌጦ ግብይት በሥራ ላይ ውሏል፡፡ ይህ ገንዘብ በብድር ከልማት ባንክ የተገኘ ነው፡፡  ቀሪውን 140 ሚሊዮን ብር ከራሳችን ካዝና የተጠቀምን ሲሆን፣ በዋነኝነት ለስኳርና ለሌሎች መሠረታዊ ሸቀጦች ግብይት የዋለ ነው፡፡        

    

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...

‹‹በሁለት ጦር መካከል ተቀስፎ ያለ ተቋም ቢኖር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው›› አቶ ዘገየ አስፋው፣ የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር

በኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍል የተነሳው ግጭት በተጋጋለበት ወቅት በ2014 ዓ.ም. በአገሪቱ መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ወሳኝ ምክንያቶችን በጥናትና በሕዝባዊ ውይይቶች በመሰብሰብ፣ በተለዩ...

‹‹ዘላቂ ጥቅም ያመጣል ብዬ ያሰብኩትን ሥራ ለመተግበር እንደ መሪ መጀመሪያ ቃሌን ማመን አለብኝ›› እመቤት መለሰ (ዶ/ር)፣ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ለመቀላቀል የሚያስችለውን ፈቃድ ካገኘ 25ኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ ለበርካታ ዓመታት ጉዞው በውጤታማነት ሲራመድ የነበረ ባንክ ቢሆንም፣ ከጥቂት ዓመታት...