Sunday, March 26, 2023

በዓባይ ጉዳይ የሚሠሩ ፖሊሲ አውጪዎች ከተመራማሪዎች ጋር በቅርበት እንዲሠሩ ተጠየቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሱዳን ዋድ መዳኒ ከተማ ከኅዳር 24 እስከ ኅዳር 26 ቀን 2009 ዓ.ም. የተካሄደው የውኃና መሬት ኢንቨስትመንት ዓውደ ጥናት ተሳታፊዎች፣ በዓባይ ጉዳይ የሚሠሩ ፖሊሲ አውጪዎች ከተመራማሪዎች ጋር በቅርበት እንዲሠሩ ጠየቁ፡፡

የስቶኮልም ዓለም አቀፍ የውኃ ኢንስቲትዩት (ሲዊ)፣ የዓለም አቀፍ የውኃ ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት (ኢውሚ) እና የሱዳን ኃይድሮሊክ ምርምር ማዕከል (ኤችአርሲ) በመተባበር ባዘጋጁት ዓውደ ጥናት የተገኙ ተመራማሪዎች፣ ምሁራን፣ ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የግል ዘርፉና የሚዲያ ተወካዮች ይህን የጠየቁት በዓውደ ጥናቱ የቀረቡት ጥናቶች በምሥራቃዊ የዓባይ ተፋሰስ የሚከናወኑ የመሬት፣ የውኃና ኢነርጂ ኢንቨስትመንቶች የወደፊት ዕጣ ፈንታን በተመለከተ መሠረታዊ የዕውቀት ክፍተት እንዳለ ከደመደሙ በኋላ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ፣ ከግብፅ፣ ከሱዳንና ከደቡብ ሱዳን የተገኙትን ጨምሮ የዓውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በባለስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫቸው በአንድ ድምፅ እንደገለጹት፣ የምሥራቃዊ ዓባይ ተፋሰስ ሀብቶችን በጋራ ለመጠቀም የሚደረጉ ትብብሮች በአካባቢው የሚከናወኑ የመሬት፣ የውኃና ኢነርጂ ኢንቨስትመንቶች የወደፊት ዕጣ ፈንታን በተመለከተ ባሉ ዕውቀቶች ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ተሳታፊዎቹ እንዳመለከቱት የአየር ንብረት ለውጥና የሕዝብ ቁጥር ዕድገት በምሥራቃዊ ተፋሰስ በተለየ ሁኔታ ተግዳሮት እየፈጠሩ ከመሆኑ አንፃር ለጠንካራ ውሳኔ ድጋፍ ሰጪ የሆኑ ማዕቀፎችን በመቅረፅ፣ የተሻሉ ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት ውጤታማ የሆነ የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር ሥርዓት በማበጀት ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ፖሊሲዎችና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ተፈላጊውን ውጤት እንዲያስገኙና ዘላቂ የልማት ውጤት እንዲያስመዘግቡ ከማድረግ አኳያ፣ በአካባቢው ያለው መሠረታዊ የዕውቀት ክፍተት መሟላት እንዳለበት አስምረውበታል፡፡

ቀጣይነት ያለው ውይይትና ምክክርን በሁሉም እርከኖች ላይ ማዳበር የተሻለ ዕውቀት፣ ጠንካራ ማስረጃና ጠንካራና ጤናማ አቅም ለመገንባት፣ ይህንኑ መሠረት አድርጎም የተፋሰሱ አገሮች ሕዝቦች ፍላጎትና የተፋሰሱን ሥነ ምኅዳር ግምት ውስጥ ያስገባ ውሳኔ ለማሳለፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ተሳታፊዎቹ አመልክተዋል፡፡

በተለይ የመሬት፣ ውኃና ኢነርጂ ኢንቨስትመንቶች ላይ የሚደረግ ውይይትና ምክክር ቀጣይነት ኖሮት ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ መደረግ እንዳልበትም ገልጸዋል፡፡ ይህ መሰል መድረኮች ከመንግሥትና ከምሁራን በተጨማሪ ሲቪል ማኅበራትንና ሚዲያን ሊያሳትፉ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ አንፃር መሰል ዓውደ ጥናቶችን ለማድረግ ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን፣ ቀጣዩን ዓውደ ጥናት በግብፅ እ.ኤ.አ. በ2017 ለማድረግ ዕቅዱ ቶሎ መጀመር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ላይ የቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች በአካባቢው የተከናወኑና ለማከናወን የታቀዱ የውኃና መሬት ኢንቨስትመንቶች ስለሚኖራቸው ተፅዕኖና ዘላቂነት ባለው ሁኔታ ለማካሄድ፣ መደረግ ስላለባቸው ዕርምጃዎች ዝርዝር መረጃዎችን አቅርበዋል፡፡

ይህ የዋድ መዳኒ ዓውደ ጥናት እ.ኤ.አ. ከ2013 ጀምሮ ‹‹Water Politics in the Nile Basin – Emerging Land Acquisition and the Hydro Political Landscape›› በሚል ርዕስ የተመሪማሪዎች ቡድን ሲያካሂድ ከቆየው ፕሮጀክት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በስዊድን ምርምር ማዕከል የገንዘብ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ የሚፈጸመው ደግሞ በሲዊ፣ በኖርዲክ አፍሪካ ኢንስቲትዩትና በስዊድን የግብርና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡

በተጨማሪም ሲዊና ኢውሚ በተመሳሳይ አጀንዳ ላይ የተለያዩ አውደ ጥናቶችን ያዘጋጁ ሲሆን፣ በዚህም ሳይንሳዊ ዕውቀትን ለማሠራጨትና በተመራማሪዎችና በውሳኔ ሰጪ/ፖሊሲ አውጪዎች መካከል መቀራረብ ለመፍጠር ጥረዋል፡፡ ሁለቱ ተቋማት በጋራ ካዘጋጇቸው ዓውደ ጥናቶች መካከል በግንቦት ወር 2008 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የተዘጋጀው ተጠቃሽ ነው፡፡

በዓውደ ጥናቱ የተሳተፉ ኤክስፐርቶች በአካባቢው የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ዘላቂ እንዲሆኑ፣ የፕሮጀክት ዕቅድና አፈጻጸም ላይ ሊወሰዱ ይገባል ያሏቸው ዝርዝር አካሄዶች ላይ ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በተለይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሏቸውን አሳሳቢ ጉዳዮችንም አብራርተዋል፡፡ ሰፋፊ የእርሻ ሥራዎችና የውኃ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ስለሚፈጥሩት ተፅዕኖ፣ ተፅዕኖውን ለመቀነስና ለመቆጣጠር ስለሚወሰዱ ዕርምጃዎችም ዝርዝር ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ የቀረቡት ማብራሪያዎች ላይ ስምምነት መኖሩ ባያጠያይቅም በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ግን ሰፊ ውይይትና ክርክር መደረጉ አልቀረም፡፡

ውይይትና ክርክሩ በምሁራንና በኤክስፐርቶች ብቻ የተገደበ አልነበረም፡፡ ምሁራኑ ከመንግሥት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ከተወከሉ ፖሊሲ አውጪዎችና ውሳኔ ሰጪዎች ጋርም ውይይትና ክርክር አድርገዋል፡፡

በመካሄድ ላይ ያሉና ሊካሄዱ የታቀዱ መጠነ ሰፊ ኢንቨስትመንቶች በተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር፣ በሕጋዊ ግንኙነቶችና ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ላይ የሚኖራቸው አገራዊና ክልላዊ ተፅዕኖም ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ ባለፉት አራት ዓመታት የተለያዩ ተመራማሪዎች በኢትዮጵያ፣ በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በዩጋንዳና በግብፅ የመስክ ጉብኝት በማድረግ ጭምር ጥናት እንዲያደርጉ አስችሏል፡፡ ከፕሮጀክቱ ውጤቶች መካከል አንዱ ‹‹Land and Hydro Politics in the Nile River Basin – Challenges and New Investments›› የሚል ርዕስ ያለውና ሳንድስትሮም፣ ጃገርስኮግና ኦስቲጋርድ አጋታኢ የሆኑበት መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉ የዓውደ ጥናቱ አጀንዳ ጋር የተያያዙ በርካታ የምርምር ሥራዎችን አካቷል፡፡ መጽሐፉ እ.ኤ.አ. በሚያዚያ 2016 የተመረቀ ቢሆንም በዋድ መዳኒ በድጋሚ ተመርቋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ ከተሳተፉት ኢትዮጵያዊያን መካከል በኖርዲክ አፍሪካ ኢንስቲትዩት ከፍተኛ ተመራማሪ ዶ/ር አትክልት በየነና በሉንድ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲ ተማሪና ተመራማሪ አቶ ወንድወሰን ሚቻጎ ሰይድ በመጽሐፉ ኢትዮጵያን በተመለከተ የጻፏቸው ጥናቶች ተካተዋል፡፡

በተጨማሪም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመሬትና ውኃ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ጌጤ ዘለቀና በኢውሚ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ የሚሠሩት ልኬ ንጉሤ ጥናት አቅርበዋል፡፡ የኢንትሮ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ፣ አቶ ተፈራ በየነና አቶ ተሾመ አጥናፌ ከውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም አቶ ዘሪሁን አበበ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዓውደ ጥናቱ ተሳትፈዋል፡፡              

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -