Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ የሚፈጠረው በጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ነው!

  ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርዓት ተግባራዊ ካደረገች ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል፡፡ በአገሪቱ ፌዴራላዊ ሥርዓት ይበልጥ ተግባራዊ የሆነው ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቃል ኪዳን ያደረጉበት ሕገ መንግሥት ተግባራዊ ከሆነ በኋላ ነው፡፡ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት እንዲፋጠን፣ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት በመጠቀም በነፃ ፍላጎት፣ በሕግ የበላይነትና በራስ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ስምምነት ላይ ከተደረሰ 22 ዓመታት ነጉደዋል፡፡ ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ ደግሞ የግለሰብና የቡድን መሠረታዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ የፆታ እኩልነት እንዲረጋገጥ፣ ባህሎችና ሃይማኖቶች ያላንዳች ልዩነት እንዲራመዱ ፅኑ እምነት መያዙ በሕገ መንግሥቱ ተወስቷል፡፡

  በተጨማሪም በአገሪቷ የሚኖሩ የተለያዩ ሕዝቦች የራሳቸው አኩሪ ባህል ያላቸው፣ የራሳቸው መልክዓ ምድር አሰፋፈር የነበራቸውና ያላቸው፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስረው አብረው የኖሩባትና የሚኖሩባት አገር በመሆንዋ፣ ያፈሩት የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለው ስለሚያምኑ፣ መጪው የጋራ ዕድላቸውም መመሥረት ያለበት ከታሪካቸው የወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸውን በማሳደግ ላይ መሆኑን መቀበላቸውን አረጋግጠዋል፡፡ እንዲሁም ጥቅማቸውን፣ መብታቸውንና ነፃነታቸውን በጋራና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባት አስፈላጊነት በማመን፣ በትግላቸውና በከፈሉት መስዋዕትነት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሰላም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ ሕገ መንግሥቱን በተወካዮቻቸው አማካይነት ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. ማፅደቃቸውን አስታውቀዋል፡፡ ይህ ፅኑ የሆነ የአንድነት መንፈስ የተላበሰ ፍላጎት ከወረቀት ጌጥነት ተላቆ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ብዙ መሠራት አለበት፡፡ ለጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት አስፈላጊው መስዋዕትነት ሊከፈል ይገባል፡፡  

  የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ጫፍ ድረስ የጋራ ጥቅሙና መብቱ በሕግ የበላይነት ሥር ቢከበርለት ከልዩነቱ ይልቅ አንድነቱ እጅግ በጣም ሰፊና ጥልቅ ነው፡፡ በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ ጎልቶ ሊታይና ሊደመጥ የሚገባው ይህ ኩሩ ሕዝብ ያላንዳች ልዩነት ቋንቋዎቹ፣ ባህሎቹ፣ ሃይማኖቶቹ፣ አመለካከቶቹና የመሳሰሉት መብቶቹና ነፃነቶቹ ሊከበሩለት ይገባል፡፡ ከዚህ ቀደም በነበሩ የተዛቡ አመለካከቶች ምክንያት የተፈጠሩ ቅሬታዎች ብቻ እየተቀነቀኑ ልዩነቶችን መለጠጥ ኪሳራው ለአገር ነው፡፡ ሕዝባችን በዘወትር ግንኙነቱ እርስ በርሱ እየተከባበረና ዕውቅና እየተሰጣጠ መኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያ አልፎ ተርፎ በጋብቻ ተሳስሮ በመዋለድ ተምሳሌትነትን ማሳየት የቻለ ነው፡፡ የተዛቡ ግንኙነቶች እየታረሙ ለጠንካራ አንድነት ከመሥራት ይልቅ ልዩነትን ማቀንቀን ጥፋት መደገስ ነው፡፡ በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ ከዚህ ቀደም ዜጎችን እንደ ባዕድ ውጡልን እየተባለ የተፈጸመው አስከፊ ድርጊት ሊያበቃ ይገባል፡፡ አገር አፍራሽ ድርጊት ነው፡፡

  በሕገ መንግሥቱ መሠረት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በመረጠው የአገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት፣ እንዲሁም ሀብት የማፍራት መብት አለው፡፡ ይህ በሕገ መንግሥቱ ዋስትና ያገኘ መብት በፍፁም ሊጣስ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ ነውና፡፡ የግለሰብ ወይም የቡድን መብቶችም በእኩልነት እንዲከበሩ ሕገ መንግሥቱ ዋስትና ሰጥቷል፡፡ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲኖርና መብቶችም በዝርዝርና በጥልቀት ዋስትና ያገኙት በሕገ መንግሥቱ ነው፡፡ ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲ ሊኖር የሚችለውም የፌዴራል ሥርዓቱ የጀርባ አጥንት የሆነው ሕገ መንግሥት በተግባር ሥራ ላይ ሲውል ነው፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሞላ ጎደል በጋራ ጥቅሞቹና ዕድሎቹ ላይ በሕግ የበላይነትና በራሱ ፈቃድ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ላይ የሚደርሰውና አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ የሚፈጥረው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ሕዝብ በእኩልነት የሚስተናገድበት ፌዴራላዊ ሥርዓት ካገኘ አንዲት ጠንካራ አገር ለመፍጠር ይችላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕግ የበላይነት ወሳኝ ነው፡፡ በፌዴራል ሥርዓቱም ሆነ በሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ቢኖሩ እንኳ፣ እያንዳንዱ አካሄድ የተጠናና ሕግን የተከተለ ሊሆን ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ በአጠቃላይ ሕዝቡን የሚያግባቡ የጋራ አጀንዳዎች መኖር አለባቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ልዩነትን የሚያቀነቅኑ ጠባብ አስተሳሰቦችን ማረም፣ በጠንካራ አንድነት ላይ የተመሠረተች የጋራ አገር እንድትገነባ ትውልዱን ማስተማር፣ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ምኅዳር መፍጠር፣ መብቶችንና ነፃነቶችን የሚጋፉ ኢዴሞክራሲያዊ አሠራሮችን ማስወገድ፣ ከዘመኑ አስተሳሰብ ጋር የሚመጥኑና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረቱ ግንኙነቶችን ማዳበር፣ የሕዝብ ተሳትፎን በላቀ መንገድ ማሳደግ፣ ወዘተ. ጠቃሚ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የማንነት ጥያቄዎችም ሆኑ የመብት ጥያቄዎች ሲነሱ ሒደቱ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆንና የሠለጠነ ምላሽ እንዲኖር መድረኩን ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ በዚህ መንገድ አገሪቷ እንድትጓዝ ሲደረግ በእርግጥም ኅብረ ብሔራዊ አንድነቱ ጠንካራ ከመሆኑም በላይ፣ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ተገንብቷል ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር ይቻላል፡፡

  በመፈቃቀርና በመግባባት ላይ የሚመሠረት ፌዴራላዊ ሥርዓት ልዩነትን አይሰብክም፡፡ በማንነት ስም የሚቀነቀን ጠባብነትንም ሆነ ትምክህትን አያስተናግድም፡፡ ይልቁንም ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ልዩ ጥበቃ በማድረግ፣ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡ በሕግ የበላይነት ሥር የምትተዳደር ሉዓላዊት አገር እንድትኖር ይረዳል፡፡ ለኅብረ ብሔራዊ አንድነት ጠንካራ መሠረት በማበጀት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ያገለግላል፡፡ ኢፍትሐዊና ሕገወጥ ድርጊቶችን ያስወግዳል፡፡ ለምግባረ ብልሹዎችና ለአምባገነኖች ቦታ አይኖረውም፡፡ የፌዴራል ሥርዓቱ ያሉበትን እንከኖች አስወግዶ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መጓዝ ከቻለ፣ በእርግጥም የኢትዮጵያ ህዳሴ በተግባር ይረጋገጣል፡፡ መላውን የአገሪቱ ሕዝብ በእኩልነትና በፍትሐዊ መንገድ የሚያስተናግድ ፌዴራላዊ ሥርዓት በጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት ታላቁን የኢትዮጵያዊነት ምሥል ማስቀደም ተገቢ ነው፡፡ ለአገር ዘላቂ ሰላም፣ ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ ይበጃል፡፡ አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥርዓት የሚፈጠረው በጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ላይ ነውና!   

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...

  ኢትዮጵያ በብድርና ዕርዳታ የምታገኘው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ፓርላማው አሳሰበ

  በብድር የተገኘ ገንዘብ በሥልጠናና ውሎ አበል መልክ እንዳይባክን ተጠየቀ የሕዝብ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...