የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዘመናዊ የሶፍት ዌር ቴክኖሎጂ በመጠቀም አሠራሩን ለማዘመን የሚያግዘውን ቴክኖሎጂ በ24 ሚሊዮን ብር በመግዛት የፕሮጀክት ትግበራውን አጠናቆ ሥራ ማስጀመሩን አስታወቀ፡፡
ፕሮጀክቱ የድርጅቱን ተወዳዳሪነት ከሚያሳድጉ ሌሎች ሥራዎች ባሻገር እንደተከናወነ ድርጅቱ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
24 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ቴክሎጂ የድርጅቱን አሠራር ዘመናዊ የማድረግ (የኦቶሜሽን ፕሮጀክት) ሒደት አካል ሲሆን፣ Enterprise Resource Planning (ERP) በመባል የሚታወቅ ሲሆን፣ በትላልቅ ተቋማት ተመራጭ ቴክኖሎጂ እየሆነ የመጣ ነው።
የኦቶሜሽን ሥራው ለባለድርሻ አካላትና ለደንበኞች ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋ የኤርፖርት አገልግሎት እንዲኖር የሚያግዝ እንደሆነ ያስታወቀው ኤርፖርቶች ድርጅት፣ በድርጅቱ ውስጥ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲኖር ከማስቻል ባለፈ ሁሉንም አገልግሎቶች በማዘመን ለተጠቃሚው ለማቅረብ የሚያስችል ነው ብሏል። የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ሥራውን እንዲያከናውን ለኧርነስት ኤንድ ያንግ ኩባንያ በሰጠው ሥራ መሠረት ፕሮጀክቱ ተጠናቆ በይፋ መተግበር መጀመሩን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቴዎድሮስ ዳዊት፣ ቀደምት የአቪዬሽን ታሪክ ያላት ኢትዮጵያን በኤርፖርት አገልግሎት ዘርፍ መሪ ለመሆን እንድትችል ከሚከናወኑ ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል ተጠቃሽ እንደሆነ ገልጸዋል። ኢንዱስትሪውን ይበልጥ ለማሳደግና ዓለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ገብቶ ለመወዳደር እንዲቻል በማሰብ የተተገበረ አዲስ አሠራር መሆኑን አመልክተዋል። ይህም በአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ሌላ ታሪክ ለመሥራት በር የከፈተ ሒደት ነው ብለዋል። ከአመራሮችና ከመላው ሠራተኛ የሚታይ ለውጥ ማምጣት እንደሚጠበቅ አሳስበዋል።
የኧርነስት ኤንድ ያንግ ማኔጂንግ ፓርትነር አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለውን ዘመናዊ አሠራር መከተሉ ድርጅቱ በአየር ትራንስፖርት ዘርፍ ያለውን ድርሻው በማስፋት የበለጠ ተወዳዳሪና ብቃት ያለው እንዲሆን የሚያስችለውና ወደፊት ሊደርስበት የሰነቀውን ዓላማ ዕውን ለማድረግ መሠረት የሚጥል ሥራ ነው ብለዋል። ድርጅቱ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦም ከፍ የሚያደርግለት መሆኑንም ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መጠናቀቅ መቻሉ የመጀመሪያ ትልቅ ሥራ መሆኑ፣ የሠራተኞችን ተነሳሽነት የሚያሳይና የሚያኮራ ሥራ እንደሆነም አቶ ዘመዴነህ ተናግረዋል።
የፕሮጀክቱ ትግበራ የድርጅቱን ዋና መሥሪያ ቤትን ጨምሮ የአዲስ አበባ ቦሌ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት፣ የድሬዳዋ፣ የባህር ዳር፣ የግንቦት ሃያና የመቀሌ አሉላ አባ ነጋ ዓለም አቀፍ ኤርፖርቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በተደገፈ ሥርዓት በመረጃ መረብ በማስተሳሰር ሥራቸውን ለማከናወን የሚያስችል እንደሚሆን ይጠበቃል።