ሪፖርተር ጋዜጣ ኅዳር 25 ቀን 2009 ዓ.ም. በወጣው ዕትሙ ጥራቱን ያልጠበቀ የጨው ምርት ገበያውን ማጥለቅለቁ ጥያቄ አስነስቷል በማለት በፊት ገጹ ያወጣው ዜና፣ ድርጅታችን በአገሪቱ ከአንድ ወር ተኩል በፊት አጋጥሞ የነበረውን የጨው ዕጥረትና የዋጋ ንረት መንግሥት በሰጠው አቅጣጫ በመፍታቱ ሆን ተብሎ ስሙን ለማጥቆርና አምራቹ ሳይጠቀም የራሳቸውን ጥቅም ለማጋመስ ከኋላ ሆነው የአምራቾቹን ስም ለማጥፋት የፈለጉ ኃይሎችን ፍላጎት የያዘ ጽሑፍ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ የአምራች አክሲዮን ማኅበሩ ስለጉዳዩ ምንም ሳይጠየቅ፣ በጋዜጣው ኤዲቶሪያል ፖሊሲ የተቀመጠውን የሁሉንም ወገኖች ሐሳብ ማካተት የሚለው መርኅ በመጣስ ያወጣችሁት ጽሑፍ ትክክል ባለመሆኑን ለተደረገብን ስም ማጥፋት ዘመቻ እንደሚከተለው ምላሳችንን አቅርበናል፡፡
እኛ የአፍዴራ ጨው አምራቾች፣ መንግሥታችን ባደረገልን ጥሪ መሠረት አገራችንን ከውጭ ከሚገባ ጨው ጥገኝነት ለማላቀቅ ብዙ ለፍተናል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ውጊያ በከፈተበት ማግሥት ሳይቀር በውጊያ ቀጣና ውስጥ ሆነንም የሕዝባችንን ፍላጎት በማሟላት ረገድ የዜግነት ግዴታችንን የተወጣን የአገሪቱ የቁርጥ ቀን ዜጎች ነን፡፡
በዚሁ ጊዜ ሁሉንም ችግሮች ተጋፍጠን ገንዘባችንን፣ ንብረታችንንና ሕይወታችንን ሳይቀር በመስጠት የከፈልነው ዋጋ ነገ የተሻለ ቀን ለማምጣት፣ ለሕዝባችንና ለአገራችንም የተሻለ ነገር ለማበርከት በመሆኑ፣ አገራችንን ከውጭ የጨው ጥገኝነት ብናላቅቅም እኛ አምራቾች ግን እስከ አሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል ሀብትና ጥሪት አላገኘንበትም፡፡ ይልቁንም ብዙዎቻችን ገና ለገና የተሻለ ሥራ እንደሚኖር እያሰብን በኪሳራ የምንንቀሳቀስ ዜጎች ነን፡፡
በነዚህ አሥር ዓመታት በተለይም መሠረተ ልማት ባልነበራቸው ጊዜያትም ቢሆን በአገሪቱ የጨው ዕጥረት እንዳያጋጥም በቂ ምርት በማምረትና በማከፋፈል የዓመታት ተሞክሮ አካብተናል፡፡
ይህንን አካሄዳችንና ልፋታችንን በመገንዘብ ንግድ ሚኒስቴርና የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በጋራ በመሆን በአክሲዮን እንድንደራጅና አክሲዮን ማኅበር እንድናቋቁም በሰጡን አቅጣጫና የሥራ መመርያ መሠረት የተሻለ ተጠቃሚ ለመሆን እየጣርን እንገኛለን፡፡ ይሁንና በአገሪቱ የተረጋጋ የጨው ግብይት እንዲኖር የበኩላችንን እንድናበረክት በቀረበው ሐሳብና አምራቹም የራሱን አክሲዮን ለማቋቋም የሚያደርገውን ጥረት ጥቅማቸው የሚነካባቸው የመሰላቸውና በአምራቹ ላብና ጥረት መጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች ከፍተኛ መሰናክልና እንቅፋት ፈጥረዋል፡፡ በአምራቹ ጥንካሬ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ተደጋጋሚ ድጋፍ ካዳባ ጨው አቅራቢ አክሲዮን ማኅበር በ350 አምራቾች የቀድሞው ንግድ ሚኒስትር አቶ ከበደ ጫኔ በሰጡት የሥራ መመርያ በታኅሳስ ወር 2006 ዓ.ም. በሰመራ ከተማ ማኅበሩን አቋቁመናል፡፡
ሆኖም አክሲዮን ማኅበራችን ከተቋቋመ በኋላ በቀጥታ ወደ ሥራ እንዳይገባ እልህ አስጨራሽ ውጣ ውረዶች አጋጥመውት የነበረ ቢሆንም፣ ችግሮቹን በመንግሥታችን እገዛ በማለፍና በ2007 ዓ.ም. ሥራ በመጀመር ለሁለት ዓመታት ያክል የተረጋጋ የጨው ግብይት እንዲኖር አስችሏል፡፡ በነሐሴ ወር 2008 ዓ.ም. በሰመራ ከተማ ለተቋቋመው ፋብሪካ ምርታችሁን አስረክቡ በተባልነው መሠረት ለፋብሪካው ብናስረክብም፣ እኛ ማከፋፈል ባቋረጥንበት አንድ ወር ውስጥ ግን በአፍዴራ ከዘጠኝ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ጨው ክምችት ቢኖርም በአገሪቱ ከፍተኛ ጨው ዕጥረት እንዲያጋጥም ተደርጎ ነበር፡፡ በችርቻሮ አንድ ኪሎ ጨው በአራት ብር ይሸጥበት የነበረውን ዋጋ ወደ አሥራ ስድስት ብር ከፍ በማድረግና ከነአካቴው ከገበያ እንዲጠፋ መደረጉ ሕዝባችንና አምራቾቻችንን ክፉኛ ያሳዘነ ተግባር ተፈፅሞ ነበር፡፡
ይህ ተግባር ከአምራቾቻችን ባሻገር መንግሥታችንንም በማስቆጣቱ፣ የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ያዕቆብ ያላ ከሚኒስቴር ዴታዎቻቸው ጋር በመሆን ለአክሲዮን ማኅበራችን አመራርና ለፋብሪካው ባለቤቶች ያቀረቡትን ጠንካራ የሥራ ትዕዛዝና ያስቀመጡትን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውን አቋም እንደሚከተለው እንዘረዝረዋለን፡-
- በዚህ ሁለት ዓመታት ካዳባ ጨው አቅራቢ አክሲዮን ማኅበር (ከ600 በላይ ከፍተኛና መካከለኛ ጨው አምራጮች ያቀፈ) ጨውን ማከፋፈል ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በዋጋ አቅርቦት ይህ ነው የሚባል ችግር ባለማጋጠሙ የንግድ ሚኒስቴር ዕረፍት አግኝቶ እንደነበርና በዘርፉ ላይ ትኩረቱን ቀንሶ እንደነበረ፤
- ካዳባ ጨው የማከፋፈሉን ሥራ ካቋረጠ ጊዜ ጀምሮ ግን (ከሐምሌ 2008 ዓ.ም.) በአንድ ወር ውስጥ ከፍተኛ የጨው ዕጥረት እንዳጋጠመና የአንድ ኪሎ ጨው ዋጋም ከአራት ብር ወደ አሥራ ስድስት ብር መናሩ፣ በአብዛኛው የአገሪቱ ክልሎችም ከነአካቴው ጨው እንደጠፋና መንግሥት ሆን ብሎ ሕዝብን በጨው እየቀጣው ነው እየተባለ በኅብረተሰቡ ዘንድ ለከፍተኛ እሮሮና ለአመፅ የሚጋብዝ ሁኔታ እንደተከሰተና የጨው ጉዳይ ከንግድ በላይ ፖለቲካዊ መሆን እንደጀመረ፤
- በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ሕዝቡ ላነሳነው ጥያቄ ፀረ ሰላም ኃይሎች የመብት ጥያቄ ስላነሳህ መንግሥት ሆን ብሎ ምግብ እንዳትበሉና ጨውም እንዳታገኙ ክልከላ በማለት ሕዝብና መንግሥትን የማቃቃር ሥራ እየተሠራ መሆኑን፤
- በዚሁ መሠረት ለምን ዕጥረት እንደተፈጠረ በሒደት ተጣርቶ አስፈላጊውን እርምጃ እንደሚወሰድ ሆኖም ካዳባ የአገሪቱን ኮታ ጠቅልሎ ለፋብሪካ መስጠት እንዳልነበረበት አዮዲን ከተከለከለም ሪፖርት ማድረግ እንደነበረበት፤
- በተግባር እንደታየውም ፋብሪካው አገሪቱን በሙሉ የማዳረስ አቅም እንደሌለውና ያሟላል ቢባልም እንኳ በንግድ ዘርፍ ውስጥ ያለውን የተመሰቃቀለ አሠራር ትተን ፋብሪካው በሚያጋጥመው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና የቴክኒክ ብልሽት ምክንያት 100 ሚሊዮን የሚጠጋው የአገሪቱ ሕዝብ ለአደጋ ስለሚያጋልጠው ያለ ተጨማሪ አማራጭ በአንድ ፋብሪካ ብቻ ጥገኛ መሆንን እንደማይቀበሉት፤
- በአገሪቱ ሕግ መሠረት መሠረታዊ ሸቀጥን በሞኖፓሊ ለአንድ ፋብሪካ እንዲያቀርብ መፍቀድ፣ አገሪቱን በግለሰቦች ቁጥጥር ሥር በማስገባት ሚዛኑን ያልጠበቀ ግብይት እንዲኖርና አገሪቱን ለአደጋ የማጋለጥ ተግባር በመሆኑ ተግባሩን እንደሚኮንኑት፤
- ያጋጠመውን ከፍተኛ የጨው ዕጥረት ካዳባ በአስቸኳይ ሌት ተቀን ብሎ ገበያውንና ሥርጭቱን እንዲያስተካክል በቀጣይም የሚኖር ሥርጭት በሞኖፖሊ ለአንድ ፋብሪካ እንደማይሰጥና ካዳባ ማኅበር የራሱን ፋብሪካ እስኪያቋቁም ድረስም አሁን ካለው ፋብሪካ ጋር ገበያውን ተከፋፍለው እንዲያቀርቡ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ለአንድ ኪሎ ጨው በአራት ብር መግዛት የሚፈልግና በአሥራ ስድስት ብር ገዝቶ ለመጠቀም ለሚፈልገው የኅብረተሰብ ክፍል እንደየሁኔታው ሊያስተናግድ በሚችል መልኩ መመርያ እንደሚዘጋጅ የሥራ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ ትዕዛዙን ከተቀበልንበት ሳምንት ጀምረን በሙሉ አቅማችን በመሥራት የዋጋ ንረቱን በመቆጣጠር የመንግሥታችንን ዕቅድ ተግባሪዎች መሆናችንን በድጋሚ አረጋግጠናል፡፡
ከቀን ወደ ቀን የጨው አመራረት ሥርዓታችንና የአዮዲን አጠቃቀም ሒደታችን እየተሻሻለ በሄደበት ወቅት፣ የአገራችን የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣንና የሕዝብ ግንኙነት ዳሬክተር አቶ ሰለሞን አብርሃም፣ ከስድስት መቶ በላይ አምራቾች ባለቤት የሆንበት አክሲዮን ማኅበራችን በሪፖርተር ጋዜጣ በኩል በማጥላላት ከሥሮ ከገበያ እንዲወጣና በጥቂት ግለሰብ ባለሀብቶች ቁጥጥር ሥር እንዲገባ የሚገፋፉ ገለጻ ሰጥተዋል፡፡ መንግሥትና ሕዝብ የጣለብንን አደራ እንዳንወጣ በሪፖርተር ጋዜጣም እምነት እንድናጣ በሚያደርግ አኳኋን ተንቀሳቅሰዋል፡፡ አቶ ሰለሞን ከጋዜጣው ጋር ባደረጉት ውይይት መሠረት ቅሬታ ያሳደሩብን ነጥቦችን እንጠቅሳለን፡፡
የአፍዴራ ጨው በኢትዮጵያ ከሚመረተው ጨው ሁሉ በጥራቱ ቀዳሚ መሆኑ እየታወቀ እሳቸው ግን የአፍዴራን ጨው ለይተውና በስም ጠቅሰው ችግር እንዳለበት ማስቀመጣቸው ያሉብንን የአቅም ክፍተቶችን የመሙላትና የማገዝ ተግባር ሳይሆን፣ አክሲዮናችንን ነጥሎ በመምታት በገበያ ተወዳዳሪ እንዳንሆንና ማኅበራችንን ለማፍረስ የተደረገ ተግባር እንደሆነ ቆጥረነዋል፡፡
መቶ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት አገር ከመሠረታዊ ሸቀጦች አንዱ የሆነውን ጨው በክምችትነት መያዝ ያለባት የስንት ወር ፍጆታ ነው? ኃላፊው እንደሚሉት ከእርሻ ወደ ጉርሻ ነው ወይስ በ2007 ዓ.ም. የንግድ ሚኒስቴር እንደገለጸልን ለሁለት ወር የሚሆን ጨው በመጠባበቅያነት መያዝ ነው? እንደ መንግሥት ማሰብ የነበረባቸው ቢያንስ የሁለትና የሦስት ወር ፍጆታ ማከማቸት እንደሚገባ ነበር፡፡ በተለይ አሁን በአየር ንብረት መዛባት ምክንያት የጎርፍ አደጋ ሊኖር ይችላል በተባለበት ወቅትና በአፍዴራ ዝናብ እየዘነበ ባለበት ሁኔታ ችግር ቢያጋጥም፣ አገሪቱን ለአደጋ የሚያጋልጥ አጋጣሚ ስለሚፈጠር ይህን ታሳቢ ማድረግ ነበረባቸው፡፡ በአገራችን ታሪክ ሰመራ ውስጥ የተቋቋመው ፋብሪካ ከመምጣቱ በፊት ጨው አብዝታችሁ አመረታችሁ የሚል ወቀሳ ቀርቦ አያውቅም፡፡ ከሦስት ወራት በፊት ላጋጠመው ችግር መንስዔ ግን ይኼው ኃላፊው በጠቀሱት አስተሳሰብ ምክንያት ተጠባባቂ ጨው ባለመያዙ ነው፡፡
በአፍዴራ የሚገኙ የጨው አምራች ማኅበራት የአመራረት ጥራት ብቃት ላይ የሚነሳው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከነአካቴው አዮዲን ያልተቀላቀለበት የጨው ምርት በስፋት ወደ ገበያ እየገባ እንደሆነ ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል በማለት ሪፖርተር የዘገበው፣ ከአፍዴራ ጨው አምራቾች የአመራረት ስልት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል ጋር የሚቃረን ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ የመድኃኒትና ቁጥጥር ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊም ቁጥጥር እንደሚደረግ ለጋዜጣው ገልጸው ሳለ፣ ጥራት የሌለውና ከነአካቴው አዮዲን ያልተቀላቀለበት ጨው ወደ ገበያ እየገባ እንደሆነ የተገለጸው ግን ከእውነት የራቀ ነው፡፡ በጋዜጣው እንደቀረበው፣ ለፋብሪካዎች ጥሬ ዕቃነት ካልሆነ በስተቀር ከነአካቴው አዮዲን የሌለው ጨው ለምግብነት እንደማይሸጥ የመድኃኒትና ምግብ ቁጥጥር ባለሥልጣንና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የሚታወቁት ሃቅ ሆኖ እያለ፣ እንደዚህ ዓይነት የማጥላላት ዘመቻ መደረጉ ተቀባይነት የለውም፡፡
አቶ ሰለሞን ምንም ዓይነት አዮዲን የሌለው ነገር ግን ለፋብሪካ ጥሬ ዕቃነት የሚቀርብ በማስመሰል ለምግብነት ፍጆታ የሚውል ጨው (አዮዲን የሌለው) ለገበያ ለማቅረብ ጥረት ሲደረግ እየተያዘ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ጨው አምራቹና አክሲዮን ማኅበሩ በተቻለው አቅም፣ በመንግሥትና በአጋር ድርጅቶች ድጋፍ አዮዲን እያቀላቀለ ለገበያ እንደሚያቀርብና ከጊዜ ወደ ጊዜ ጥሩ መሻሻሎችም እንዳሉ፣ የመድኃኒት የምግብና ቁጥጥር ባለሥልጣንም ጥሩ መሻሻል እየመጣ መሆኑን እየገለጸ በቆየበት ወቅት፣ አዮዲን ከነአካቴው የሌለበትና ለፋብሪካ ጥሬ ዕቃነት የተፈቀደ ጨው ለምግብ ፍጆታነት ሊውል ሲል ተብሎ የተሰጠው መግለጫ አምራቾችና አክሲዮን ማኅበራችን እንደዚህ ዓይነት ወንጀል እንደማይሠሩ፣ ለፋብሪካ ጥሬ ዕቃነት የወጣውን ጥሬ ጨው ለምግብ ፍጆታነት ያቀረበ አካል በግልጽ ወጥቶ በሕግ እንዲጠየቅ እንፈልጋለን፡፡ ሆኖም ይህ አባባል ሆን ተብሎ ግለሰቦች የአምራቹን ተጠቃሚነት ለመቀማትና የራሳቸውን ጥቅም ለማጋበስ ሆን ተብሎ የተሸረበ ሴራ እንዳይሆን ከፍተኛ ሥጋት አለን፡፡
የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ የጠቀሱት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ በባህላዊ የጨው አምራቾች ከአዮዲን ጋር የሚደባለቅበት ሁኔታ (መንገድ) ነው ብለው የገለጹት ነው፡፡ አምራቹ ለመላው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጨው የሚያቀርብና መንግሥት የሚያወጣውን የውጭ ምንዛሪ እያስቀረ ያለ፣ በአመራረቱም መንግሥትም ሆነ አጋር አካላት የተለየ ሥልጠናና ድጋፍ በማድረግ የጨው አመራረቱና አዮዲን አደራረጉ እየተሻሻለ የመጣ መሆኑ ባለሥልጣኑም የሚያምንበት ሆኖ ሳለ፣ መሻሻሎችን ሳይገልጹ ሥጋቱን ብቻ ማስቀመጣቸው ሆን ተብሎ አምራቹን ተስፋ ለማስቆረጥና የግለሰቦችን ጥቅም ለማስከበር የተደረገ ጥረት አስመስሎታል፡፡
አምራቹ ከፌዴራል መንግሥትና ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመሆን እንደ አዲስ ባቋቋመው አክሲዮን ማኅበር ከአገር በቀል ባለሀብት ሦስት መቶ ሚሊዮን ብር ዘመናዊ የጨው ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለማቋቋም እንቅስቃሴ እያደረገና መሬት ተረክቦ ፋብሪካውን በስድስት ወር ለማጠናቀቅ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረግን ይገኛል፡፡ የሚነሱት የጥራት ችግሮች ተፈትነው ሙሉ ለሙሉ ጥራቱንና ደረጃውን የጠበቀ ጨው ለሕዝብ በአግባቡ ለማድረስ አቅዶ ወደ ተግባር ሥራ ገብቷል፡፡
በአጠቃላይ አቶ ሰለሞን የሰጡት መግለጫ እርስ በርሱ የሚጣረስና በአንድ በኩል ከአምራረቱ ጀምረው ቁጥጥር እንደሚደረግ ለአምራቹ የአቅም ግንባታ እንደሚደረግለት፣ ለፋብሪካ ጥሬ ዕቃነት የሚወጣ ጨው በመንግሥት ፈቃድ እንዲወጣ እንደሚደረግ እየተገለጸ በሌላ በኩል ግን አምራቹና የአምራቹ አክሲዮን ማኅበር በግለሰቦች ተፈጥሮ የነበረውን ሰው ሠራሽ የጨው እጥረትና የዋጋ ንረት በመንግሥት መመርያ መሠረት ተንቀሳቅሰው ችግሩን ስለፈቱ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ የአፍዴራ አምራች የጨው ጥራት እየተሻሻለ ቢሆንም፣ የጥራት ችግር እንዳለ አስመስለው በማስረጃ ያልተደገፈና የራሳቸው ተቋም አጣርቶ የለቀቃቸውን ከ65 በላይ መኪኖች ጥራትና ከነአካቴው የአዮዲን ጨው የሌለው አስመስለው ማቅረባቸው የሕዝብ ጥቅምንና የመንግሥት ሕግን ለማስከበር ከቆመ የመንግሥት አካል የማይጠበቅ፣ አምራቹና የአምራቹ አክሲዮን ማኅበርንም ከገበያ ለማውጣት የተደረገ ሊሆን እንደሚችል የተሰማንን እንገልጻለን፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣም የሁለት ወገንን ሐሳብ ያላካተተ ዘገባ ማቅረቡ የኤዲቶሪያል ፖሊሲውን የሚጻረርና ያለውን ክብርና ዝና ትዝብት ውስጥ የሚከት መሆኑን እንዲገነዘበው እናሳስባለን፡፡
(የካዳባ ጨው አቅራቢዎች አክሲዮን ማኅበር)