Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትያልተሻገርናቸው አስቸጋሪዎቹ የፖለቲካ ሰርጦች

ያልተሻገርናቸው አስቸጋሪዎቹ የፖለቲካ ሰርጦች

ቀን:

በያሲን ባህሩ

ፖለቲካ አስቸጋሪው የማኅበራዊ ዘርፍ ዕይታ ነው፡፡ በቀዳሚነት በፖለቲካ ውስጥ በአብዛኛው እውነት አለመኖሩ ነው፡፡ የትም ይሁን የት በሠለጠነው አገርም ሆነ በደቀቀው የሚነገረውን ያህል የማይተገበርበት መስክ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በፖለቲካ ውስጥ ዘለዓለማዊ ጠላት ወይም ወዳጅ አይኖርም፡፡ ምንም እንኳን አገሮች፣ ፓርቲዎች፣ ግለሰቦች፣ . . . ስትራቴጂካዊ አጋርነት ወይም ባላንጣነት ሊኖራቸው ቢችልም በጊዜና በሁኔታ ሊቀያየር የሚችል ክስተት ነው፡፡ ሦስተኛው ፖለቲካን አስቸጋሪ የሚያደርገው የሰው ፍጥረት ሁሉ ፍላጎት ያለበት በመሆኑ እንደሆነ የመስኩ ምሁራን ያትታሉ፡፡

ፍልስፍናውን ትቼ ‹‹ኳስ በመሬት›› ላድርገው መሰለኝ፡፡ በዚችው መከረኛ ኢትዮጵያችንም ፖለቲካ አስቸጋሪው ዕጣ ፈንታችን ነው፡ አገራችን ከነበረችበት ከፍ ያለ የሥልጣኔና የታሪክ ደረጃ ተሸቀንጥራ የኋሊት የወደቀችው በሰከነና በሰላ የፖለቲካ ሕይወት ዕጦት ነው፡፡ አንዱ ሌላውን ወንድሙን ለማስገበር፣ ሌላው አንድ ሆኖ እንደ አገር ከመቆም ይልቅ በየጎጡ በተናጠል ለመቆም በተፈጸመ ፍልሚያ ብዙ ሕይወት አልፏል፡፡ የአገር ንብረትና ሀብት ውድሟል፡፡ አገሪቱም ለድህነትና ለኋላቀርነት ተዳርጋ ቆይታለች፡፡

- Advertisement -

በዚሁ መዳከማችን መዘዝ አገራችን ያላትን የፖለቲካ መልክዓ ምድር ጠቀሜታ የተረዱ የውጭ ኃይሎች በተከታታይ ዘምተውብናል፡፡ ከአውሮፓ (ቱርክ፣ ፖርቹጋል፣ እንግሊዝ፣ ጣሊያን) ከሰሜን አፍሪካ (በተለይ ግብፅ) ከጀርባ ሆነው በሚያግዟት በርካታ የዓረብ አገሮች ወግተውናል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ግን ደሃና ኋላቀር ቢሆኑም፣ በጀግንነታቸውና በአገር ፍቅር ወኔያቸው የመጣውን ጠላት ሁሉ በመመለስ አገሪቱን አቆይተውልናል፡፡ ይኼም ያለፈው ፖለቲካችን ውጤት ነው፡፡

ወደ ግማሽ ምዕተ ዓመት እየተጠጋ ያለው የአገራችን ዘመናዊ ፖለቲካ ውጥንቅጥ ክስተት የታየበት ነው፡፡ በአንድ በኩል ዘውዳዊውን ሥርዓት ገፍትሮ የጣለ ትውልድ ሕዝባዊ ማዕበል የፈጠረበት፣ በፍልስፍና ላይ የተመሠረተ የአዲስ ምዕራፍ ጉዞ የቀረፀበት ጥረት አለ፡፡ በሌላ ጥግ ደግሞ ፀረ ዴሞክራሲያዊና የጠመንጃ ትውልድ አቆጥቁጦ የፖለቲካ የኃይል ሚዛኑን በነፍጥ ለመቀየር ተረባርቧል፡፡ እነዚህ ኃይሎች የንጉሡን ሥርዓት በመጣልም ሆነ አንዱ ሌላውን በመጣል የተሳካላቸው ቢሆንም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግን ከችግር አልወጣም፡፡

ይኼንን ለማለት የሚያስደፍረው ደግሞ ከአራትና ከአምስት አሥርት ዓመታት በኋላ እንኳን ደረት የሚያስነፋ የዴሞክራሲ ፍንጭ አለመታየቱ ነው፡፡ አሁንም ፖለቲካችን በአብዛኛው ፅንፈኝነት የተጠናወተው ነው፡፡ አሁንም የፖለቲካ ተገዳዳሪነት በጠላትነት የሚያስፈርጅ ነው፡፡ አሁንም ተቀራርቦ ከመሥራትና ከመደራደር ይልቅ ማሸነፍ (መሸነፍ) ይቀናናል፡፡

በአገሪቱ ‹‹ሥር ነቀል የፖለቲካ ለውጥ ተደርጓል›› በተባለባቸው ያለፉት 25 ዓመታት ውስጥ እንኳን ብሔራዊ ዕርቅና መግባባት አልተፈጠረም፡፡ አሁንም በፖለቲካ ዕምነታቸው ብቻ የስደት ኑሮ ላይ የወደቁ፣ በዚያውም አሁን ባለው አገዛዝ መጥፋት ላይ የሚባዝኑ ዜጎቻችን ቁጥር አልቀነሰም፡፡ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ዕውን በሆነው ሕገ መንግሥት የዴሞክራሲ እሴቶች በወረቀት ደረጃ ቢኖሩም ጠንካራ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ‹‹ነፃ›› የሚባል ምርጫ . . . ገና አልተፈጠሩም፡፡ የሐሳብ ነፃነትም ቢሆን እንቅፋት አላጣውም፡፡

በዚህ ምክንያት አሁን ባለችው ኢትዮጵያም ቢሆን ‹‹ሥልጣን በሰላማዊና ሕጋዊ  መንገድ ይሸጋገራል›› ከሚለው ምኞት ይልቅ፣ መፍትሔው ‹‹ኃይል ነው›› የሚል አስተሳሰብ ገንኖ ይታያል፡፡ ለዚህ አባባል ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በውጭ ያለው ፅንፈኛ ተቃዋሚ ኃይል ባለችው ውስን የትጥቅ ኃይልም ይሁን በሕዝባዊ ማዕበል ገዢውን ፓርቲ ከሥልጣን ለመገፍተር ሲሯሯጥ ታይቷል፡፡ ያለው መንግሥትም ቢሆን የተነሳውን ሕዝባዊ እንቢተኝነትም ይባል ቀውስ ለመግታት የሞከረው በኃይል ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከፖለቲካው በስተቀር በሁሉም መስኮች መሻሻል እያሳየች ነው ማለት ስህተት የለውም፡፡ እርግጥ ‹‹ፖለቲካ›› ከኢኮኖሚ፣ ከማኅበራዊ፣ ከባህላዊ ወይም ከዲፕሎማሲያዊ እሳቤዎች ተነጥሎ ብቻውን አይቆምም፡፡ ያም ሆነ በፖለቲካ መስተጋብር ውስጥ ቀዳሚው ከሚጠቀሱ ጭብጦች አንፃር በሚመዘዙ ዕውነታዎች መለኪያነት ያልተሻገርናቸውን ሰርጦች መጠቃቀስ ይቻላል፡፡ በዚህ ጽሑፍም መፍትሔው ምን ይሁን? በሚል ሙግት የግል ዕይታዬን ለመሰንዘር እወዳለሁ፡፡
የተዘጋው የኢሕአዴግ በር ጉዳይ

ኢሕአዴግ መራሹ የአገሪቱ መንግሥት ያሳለፍናቸውን ወራት ያህል ጠንከር ያለ ሕዝባዊ ተቃውሞ ገጥሞት አያውቅም፡፡ በአንድ በኩል የገጠርና የከተማ ሕዝብ ሳይባል፣ በክልል ሳይገደብ ቁጣ የታየበት ነው፡፡ በሌላ በኩል የሕዝቡ እንቢተኝነት፣ ቁጣና ጥፋት የተቀላቀለበት ስለነበር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕይወት አልፏል፡፡ የንብረት ውድመት ደርሷል፡፡ ይኼንን ለማስቆም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መተግበሩም ሆነ ኢሕአዴግ ዋናው ችግር ‹‹የእኔ ነው›› ብሎ ‹‹ተሃድሶ›› መጀመሩ ከፋት አልነበረውም፡፡

ችግሩ ግን እየተነገረ ያለው ተሃድሶ አንደኛ በኢሕአዴግ ማዕቀፍ ብቻ እንዲተገበር የሚታሰብ ነው፡፡ ሁለተኛ በራሱም ውስጥ ቢሆን ዙሪያ መለስ ችግሮችን ፈትሾ በቁርጠኝነት ሊያራግፍ የሚችል አይደለም፡፡ አሁን በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ደረጃ ‹‹ተሃድሶው እየተጠናቀቀ ነው›› በሚባልበት ወቅት እዚህ ግባ የሚባል የተወሰደ  ዕርምጃ አልታየም (ከሹም ሽር ወይም ሰው መቀያየር ባለፈ ማለት ነው)፡፡

ሕዝቡ ግን አደባባይ የወጣበት አልፎ ተርፎ ወደ ሁከትና ተስፋ መቁረጥ የገባበት (ምንም እንኳን የውጭ ኃይሎች ቢቀሰቅሱትም) ምክንያቶች ነበሩት፡፡ ለአብነት ያህል የበዛው ወጣት ሥራ አጥነት፣ የዴሞክራሲ ምኅዳር መጥበብ፣ የማንነት ጥያቄ አለመፈታት፣ የክልሎች ወሰን ጉዳይ አጀንዳ መሆን፣ የፍትሐዊ ሀብት ክፍፍል ጥያቄ (ሥርዓቱ የእነ እገሌ ነው የሚለው ሀተታ) የከፋ የሙስና ችግርና የመልካም አስተዳደር ዕጦት፣ በመልሶ ማልማትና በፕላን ስም ይዞታን የማጣት ሥጋት፣ በተለይ በከተሞች የኑሮ ውድነት፣ በሕገ መንግሥት አፈጻጸም ላይ የሚታይ የየመስኩ ጉድለት፣ ወዘተ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡

ታዲያ እነዚህና ሌሎች በየቦታው የሚነሱ ጉዳዮች እንዴት ሆነው በገዢው ፓርቲ ‹‹ተሃድሶ›› ብቻ ሊፈቱ ይችላሉ? እርሱም ይሁን ቢባል እንኳን በተመሳሳይ ፖሊሲና አቅጣጫ ያውም በዚያው ዓይነት አደረጃጀትና ግብዓት አመራሩን ብቻ በመቀየር እንዴት ሕዝቡን ሊያረካ ይችላል? የፖለቲካና የዴሞክራሲ ጉዞውንስ ምን ያህል ያሳድገውና ይቀይረው ይሆን? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ሆናል፡፡

በዚያ ላይ በአሥር ቢሊዮን ብር የወጣቶች ፈንድ መርሐ ግብር ይፈጠራል የተባለው የሥራ ዕድል፣ ወይም ይሻሻል የተባለው የምርጫ ሕግ ምን ዓይነት ጊዜና ፈጻሚ ተቀመጠለት? ይመለሳሉ የተባሉ የማንነት ጥያቄዎችና የክልልል ወሰን ጉዳዮች መቼና እንዴት ሊተገበሩ ይሆን? ከሁሉ በላይ ሕዝቡን ካስመረሩና በሥልጣን ከበለፀጉ ሰዎች መካከል እነማን ተጠየቁ? ምን ዓይነት የእርምት ዕርምጃ ተወሰደ? ከፖለቲካ ኃይሎች ጋር ይደረጋል የተባለውን ንግግርስ ከእነማን ጋር? ለምን ዓላማ ሊካሄድ ታሰበ? ፀረ ዴሞክራሲያዊነትን ያነገሡ አሠራሮችና ሕጎች ጉዳይስ . . . ? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት መፍትሔውን ያቀርባል፡፡

ባሳለፍናቸው በርካታ ወራት ኢሕአዴግ ውስጥ ቆይተው የወጡ ቱባ ፖለቲከኞች፣ የተቃዋሚ መሪዎችና በተለይ በውጭ ያሉ ምሁራን ሁሉ የሚሰነዝሯቸው ተመሳሳይ አስተያየቶች ነበሩ፡፡ ኢሕአዴግ የፖሊሲ ለውጥ ካላደረገ፣ አሁን የመጣውን ትውልድ የሚመጥን ሥርዓት ካላበጀ፣ የሰከነ ፖለቲካ ማራመድ ይቸግራል የሚል፡፡ በተለይ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች አለማነጋገርና ዴሞክራሲያዊ ባህልን በተሻለ ምዕራፍ አለመገንባት አገርንም ለውድቀት እንደሚዳርግ በአጽንኦት በመጠቆም፣ እየታየ እንዳለው ግን የኢሕአዴግ በር አሁንም የተዘጋ ነው፡፡

እንዲያውም በማያላውስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ በፍጥነት ፖለቲካን የማስረፅ፣ መታሰር ያለበትን የመያዝ፣ የነፍስ ወከፍ መሣሪያ ሳይቀር ማስፈታት፣ ‹‹ሐሳብን በነፃ መግለጽም ቢሆን መገደብ›› (በማኅበራዊ ድረ ገጽ፣ በስብሰባና በሚዲያ ንግግር ጭምር መጠየቅ) ላይ አተኩሯል፡፡ አንዳንድ አባላቱም ይኼንን በማድረግ ቢያንስ ለአሥር ዓመታት ያህል መተንፈስ ይቻላል እያሉ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ እሳቤ ግን ለማንም የማይጠቅምና የበለጠ ትርምስ እንዲፈጠር በር የሚከፍት ነው፡፡

ፅንፍ የረገጠው የዳያስፖራ ፖለቲካ ጉዳይ

እምብዛም በሌላው አገር የማይታይና የኢትዮጵያ ልዩ ገጽታ የሆነ በርካታ የዳያስፖራ ተቃዋሚ አለ፡፡ በተለይ በአሜሪካና በአውሮፓ የአገሪቱ ሉዓላዊነት መገለጫ የሆኑ ኤምባሲዎችን የሚወሩ፣ ክቡር የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ የሚያቃጥሉና የሚረግጡ በየጎዳናው ነበሩ፡፡ በአስተናጋጁ አገር እስኪቸገር ድረስ ነጋ ጠባ የተቃውሞ ሠልፍ የሚያደርጉ ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡

በእርግጥ ለዚህ ችግር አንዱ መንስዔ ያለፈው ታሪካችን የፈጠረው የፖለቲካ መበላሸት ነው፡፡ ከዚያም ወዲህ ከመቀራረብ ይልቅ የጥላቻ ፖለቲካን ማሳደድ ከላያችን ባለመውለቁ እንዲህ ሆነን ቀርተናል፡፡ የዳያስፖራ ፖለቲካውን የሚያሾሩ አንዳንድ ግለሰቦች ከፖለቲካ ፍላጎትም በላይ ‹‹የገቢ ማግኛ ዘዴ›› ስለሆናቸው ለችግሩ መባባስ ተጠቃሽ ምክንያት ነው፡፡

ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ አሁን ባለችው ዓለምም ሆነ በአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ፣ ‹‹የትጥቅ ትግል››፣ ሕዝባዊ ማዕበልና ነውጥ እንዲቀሰቀስ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ የውጭ ጠላቶች አሉ፡፡ እነዚህ አገሮችም ፅንፈኛ ፖለቲካ እየተጠናከረ እንዲሄድ ከማድረግ ባሻገር፣ አገሪቱ የለየለት ቀውስ ውስጥ እንድትገባ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡

እንግዲህ በዚህ ማዕበል የሚነዳው በውጭ የሚኖሩ መገኛችን ትንሿን ነገር ትልቅ አድርጎ ማየቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን፣ መሬት ላይ ካለው እውነት የበለጠ ሐሰተኛውን ውዥንብር ሲቀበል ኖሯል፡፡ በአብዛኛው በጥላቻና በዘር ፍረጃ አረንቋ ውስጥ ሰጥሟል፡፡ ባለፉት ወራት በግልጽ እንደታየውም በአንድ በኩል ሥርዓቱንና ደጋፊዎቹን በማባረር ከምኅዳሩ የማስወገድ ጉም የጨበጡ ወገኖች ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ ኢሕአዴግም ፅንፈኛ ዳያስፖራው ሊያጠፋህ ነው ሲል አባሉን ቀስቅሶበታል፡፡ በሌላ በኩል እኔ ለአገሬ ምን ሠራሁ? ከሚልም ባይሆን በተራዬ ‹‹የሥልጣኑ ኮርቻ ይድረሰኝ›› የሚል ስሜት ያለው ‹‹አገራችን ልንገባ ነው›› ተዘምሯል፡፡ እነዚህ ሁሉ የነገር ፍላፃዎች ግን ለአገሪቱም ሆነ ለሕዝቡ የሚፈይዱት ነገር አልነበረም፣ የለምም፡፡

ያልተሻገርናቸው ሰርጦችን በምን እንለፋቸው?

ለዘመናት ከገባንበት ድህነትና ኋላቀርነት ቀና እያልን ነው፡፡ ለዚህ የኢሕአዴግ ፖሊሲና ጥረት ብቻ ሳይሆን፣ የዓለም ተጨባጭ ሁኔታና የሕዝቡም ጥረት ረድተውናል፡፡ አለፍ ብለን ‹‹በልበ ብርሃንነት›› ፈጣሪም እንደረዳን አስበን ብናመሰግን ክፋት የለውም፡፡

የፖለቲካ ዳገቱንና ሰርጡን ለመሻገር ግን አሁን መነሳት እንዳለብን ጥርጥር የለውም፡፡ በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት በአገሪቱም ሆነ በውጭ በሚኖረው ኢትዮጵያዊ ስሜት ውስጥ እንደታየው መቀራረብና መደማመጥ ግድ ይለናል፡፡ ለዚህም በቀዳሚነት ጥላቻና ቁርሾን ትተን በብሔራዊ መግባባት መንፈስ መሳሳብ ያስፈልጋል፡፡ ይኼንን ለማድረግ ደግሞ መንግሥትና ፅንፈኛ ፖለቲከኞች ሊቀራረቡ ግድ ነው፡፡

በመሠረቱ መንግሥት ያለበት ኃላፊነት ከፖለቲከኞች ጋር በመቀራረብ ብቻ አይደለም፡፡ ከሕዝቡም ጋር ቢሆን ከአሸናፊነት ስሜት ወጥቶ የመሪነትና የአባትነት ሚና መጫወት ይጠበቅበታል፡፡ ግንቦት 20፣ የብሔራዊ ድርጅቶች በዓላት፣ የሰንደቅ ዓላማ ቀን የብሔር ብሔረሰብ ቀን፣ . . . ሲከበር ‹‹የቀድሞ ሥርዓት አሸንፈን›› የሚል ፕሮፓጋንዳ ከአሸናፊና ከተሸናፊ ፖለቲካ የተላቀቀ አይደለም፡፡ ‹‹የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ግንባታ›› አስተሳሰብም የቀድሞውን ሙሉ በሙሉ እያፈረሰ ድንገት የተፈጠረ ‹‹ታሪክ›› የሚቀርፅ የሚያስመስል የጠባብ አተያይ ውጤት ነው፡፡ በመሆኑም የሁሉንም አስተሳሰብ አቅፎ በአዲስ የለውጥ ማዕቀፍ ለመምራት አያስችልም፡፡

ከዚህ አንፃር ያልተሻገርናቸው አስቸጋሪ የፖለቲካ ሰርጦች በማለት መውሰድ ያለብን የኢትዮጵያ ብሔርተኛነትን መንከባከብና አገራዊ ስሜትን ማጠናከር ያስፈልጋል የሚለው ቀዳሚ ነው፡፡ የብሔር ብሔረሰብ መብቶችም ይሁን የግለሰብ መብቶች እኩል እንዲከበሩ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ የክልሎች ሰንደቅ ዓላማ ከፌዴራሉ በላይ መሆን እንደሌለበት ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ ኢሕአዴግና መንግሥቱ ይኼንን ልክፍት መሻገር ካልቻሉ ከውድቀት አይድኑም፡፡ ‹‹አንተ ከመንደሬ ውጣ! ከ25 ዓመታቱ ‹‹ፌዴራሊዝም›› ወዲህ የተቀነቀነ በሽታ ስለሆነ እርምት ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩል ‹‹ተሃድሶ ወይም ህዳሴ›› ይባል ‹‹ሥር ነቀል ለውጥ›› ኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊ ባህልን እየገነባ በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ አገር ካልመራ ሕዝብን ማርካት አይችልም፡፡ ገና ምርጫ በመጣ ቁጥር እንደ ዛር ዶሮ ተንደፋድፈው ፀጥ የሚሉ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲዎችን›› ለማሟሟቂያ ይዞ ሕግን መተግባር የሚቻለው አይሆንም፡፡ ስለዚህ የመደራጀትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን በተግባር አረጋግጦ፤ የዜጎችን መደራጀት ሊያከብርና ጥበቃ ሊያደርግም ይገባዋል፡፡ ካለ ዴሞክራሲ ዳቦ እንካችሁ ከሚለው የቻይና ልክፍት መውጣት አለበት፡፡

በፖለቲካ ኃይሎች ደረጃም ከፅንፈኛና ከጥላቻ መንገድ መውጣት ሕዝቡን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ማንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ዴሞክራሲያዊ ተልዕኮ የሚከፍለውን መስዋዕትነት ሁሉ መክፈል ደግሞ የትውልዱ ኃላፊነት መሆን አለበት፡፡ በጥቅሉ እንደ አገር ያልተሻገርናቸው አስቸጋሪ የፖለቲካ ሰርጦች ለይተን ገደልም ሳንገባ፣ ባለንበትም ቁጭ ብለን ሳንቀር በብልጠት ለመሻገር እንትጋ ለማለት እወዳለሁ፡፡   

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...